“ የጀጎል ግንብ ከዓለም ቅርስነት የሚያሰርዝ አደጋ ውስጥ ወድቋል”የሐረሪ ክልል ባህል፣ ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ

59

“ከተጋረጠበት አደጋ ለማውጣት እየተሠራ ነው”

የቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን

 ሐረር፡የጀጎል ግንብ እየደረሰበት ባለው ጉዳት ከዓለም ቅርስነት ሊሰርዝ ይችላል የሚል ሥጋት ማሳደሩን የሐረሪ ክልል ባህል፣ ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ ገለፀ። ካጋጠው ጉዳት እንዲያገግም እየሠራ መሆኑን የቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን አስታውቋል።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ እዮብ አብዱላሂ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳሉት ቅርሶቹ በተፈጥሮ የሚደርስባቸውን አደጋ ለመከላከል እና ለመጠበቅ ተብሎ ዩኔስኮ በሚልከው በጀት ይጠገናሉ፡፡ ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት ህገወጥ ቡድኖች በቅርሱ ዙሪያ እና ውስጥ ወረራ በማድረግ በቅርሱ ውስጥ ሊሠሩ የማይገባቸውን ግንባታ እየገነቡ ነው።

 ከዚህ ቀደም በጀጎል ግንብ ውስጥም ሆነ ውጭ ማንኛውም ግንባታ ሲካሄድ በአካባቢው ያለው ቀበሌ ለባህል ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ ደብዳቤ ጽፎ ይሁንታ ሲያገኝ ግንባታ ይካሄድ እንደነበር አቶ እዮብ አስታውሰው አሁን ግን ወረራ ሊባል በሚችል መልኩ ቤቶች መገንባታቸውን ገልፀዋል፡፡

እንደ ቢሮ ኃላፊው ገለፃ ወረራው በጣም በተደራጁ ሕገ ወጥ በሆኑ ሃይሎች የተከናወነ ሲሆን ከጀጎል ግንብ ባሻገር በዩኔስኮ የተመዘገቡ የሃይማኖት ስፈራዎች ሳይቀር በእነዚሁ የሕገ ወጥ ቡድኖች መዘረፋቸውን ጠቅሰዋል፡፡በቅርስ ውስጥ የሚገኘው እና የሐረሪ ክልል መለያ የሆኑ አገር በቀል ፍራፍሬዎች የሚተከልበት ጥብቅ ስፍራ ሳይቀር ቤቶች የተገነቡበት ሲሆን የተቀረው መሬት ደግሞ እየታራሰ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አቶ እዮብ እንደሚሉት ቅርሱን ለማዳን በፌዴራል የቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ተደጋጋሚ ደብዳቤ ጽፈናል፡፡ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱም ጉዳዩ ለሚመለከተው አካል ደብዳቤ ጽፏ ል። ሆኖም ግን የተጻፈውን ደብዳቤ ተከትሎ ተግባራዊ የሚያደርግ አካል አለመገኘቱን ገልፀዋል፡ ፡ ጀጎል ማለት የሐረሪ ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያውያን ቅርስ ነው ያሉት አቶ እዮብ ስለዚህም ማንኛውም ይመለከተኛል የሚል አካል ይህን ቅርስ ከመጥፋት እንዲታደገው ሲሉ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

የቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን በበኩሉ ከክልሉ ባህል ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ የተነገረውን ችግርና የጀጎል ግንብ ላይ ያለውን ሥጋት እንደሚያውቀው እና ችግሩንም ለመቅረፍ እየሠራ መሆኑን አስታውቋል፡፡

የባለሥልጣን መሥሪያቤቱ የመካነ ቅርሶች ልማት እና አስተዳደር ዳይሬክተር ወይዘሮ ፀሐይ እሸቴ እንደተናገሩት ቅርሱ የመሰረዝ ደረጃ ላይ የደረሰ ባይሆንም እየደረሰበት ባለው ወረራ ሥጋት ላይ እንደሚገኝ አምነዋል፡፡ ሆኖም የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የጀጎል ግንብን ከሰው ሠራሽ አደጋ ለመከላከል የአስር ዓመት ስልታዊ ዕቅድ ነድፎ ወደ ተግባር ለመግባት በዝግጅት ላይ ነው፡፡ ቅርሱን ከየትኛውም ሰው ሰራሽ አደጋ ለመከላከል ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ይሠራል ብለዋል ፡፡

አዲስ ዘመን ሐምሌ 14/2011

 አብርሃም ተወልደ