ተመራቂዎች የቀሰሙትን እውቀት ለሀገር ልማትና ብልጽግና ሊያውሉት ይገባል

15

«የፈተና ኩረጃን ለማስቀረት

 የተለያዩ ተቋማት ተማሪዎቻቸውን አስመርቀዋል

 ባህርዳር፡ተመራቂዎች በዩንቨርሲቲ ቆይታቸው የቀሰሙትን እውቀትና ልምድ ተጠቅመው ለሀገር ልማትና ብልጽግና ሊተጉ እንደሚገባ የሱማሌ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት ገለፁ፡፡

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያ፣ በሁለተኛና በሦስተኛ ዲግሪ ዘጠኝ ሺ 750 ተማሪዎችን አስመርቋል፡፡ በምርቃት መርሐ ግብሩ በክብር እንግድነት ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሙስጠፌ ሞሐመድ እንደተናገሩት፤ ምሩቃን የቀሰሙትን እውቀትና ልምድ በመጠቀም ትክክል ያልሆኑ አካሄዶችን በማረም ለሀገር ልማትና ብልጽግና እንዲተጉ ጠይቀዋል፡፡

 “ኢትዮጵያ የቀደምት ስልጣኔ ባለቤትና የሰው ልጅ መገኛ፣ የነፃነት ፈርጥ፣ የጥበበኛ ህዝቦች ሀገር ብትሆንም፤ በሂደት ከሥልጣኔ ማማ በመውረድ የዓለም ሥልጣኔ ጭራ እንድንሆን ካደረጉ መነሻ ምክንቶች አንዱ በትምህርት መዳከማችን ነው” ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ አሁን ካለንበት ውርደት መላቀቂያ ብቸኛው መንገድ ትምህርት መሆኑን ገልፀዋል፡፡

አሁን ካለንበት ሁኔታ ለመውጣት ትምህርት ሁነኛ መሣሪያ መሆኑን በመገንዘብ መንግሥት ለትምህርትና ስልጠና ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ርብርብ በማድረጉ መልካም ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ተናግረዋል። ሆኖም በትምህርትና ስልጠና ዘርፍ ላይ በርካታ ችግሮች መኖራቸውንም አንስተዋል፡፡

 እንደ አቶ ሙስጠፌ ማብራሪያ፤ በትምህርት ዘርፍ ተሳታፊ የሆኑ አካላት የመቻቻል፣ የመከባበር፣ የመደማመጥና የመፈቃቀር ኢትዮጵያዊ ባህል እየተሸረሸረ መጥቶ በተለያዩ ጉዳዮች ዩንቨርሲቲዎች የመማር ማስተማር ጊዜ ሲስተጓጎል እንደነበር አስታውሰው በዚህም በርካታ ንብረቶችም ወድመዋል፡፡ እነዚህ ጊዜ ሊሰጣቸው የማይገቡና መስተካከል ያለባቸው ናቸው ብለዋል፡፡

“ኢትዮጵያዊያን ከሚለያዩን ጉዳዮች በላይ የሚያግባቡ በርካታ የጋራ እሴቶችና ታሪክ አለን፡ ፡ ሆኖም ባለፈው ታሪክ እየተነታረክን ጊዜ እያቃጠልን ነው፡፡ ባለፈ ታሪክ መነታረክን ትተን በጋራ የምንጋፈጠውን ነገን እንዴት እንሻገር ብለን ማሰብ አለብን፡፡ የነገን ዕጣ ፋንታ ለመወሰን ደግሞ ትምህርት ጥሩ ስንቅ ነው” ብለዋል፡፡

እንደ አቶ ሙስጠፌ ማብራሪያ፤ የመማር ትርጉም ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ጋር መላመድ ብቻ ሳይሆን ሰብዓዊነት፣ ምክንያታዊነት፣ ሀገራዊ ፍቅር፣ በመተባበርና በመቻቻል ታላቅ ሀገር የመገንባት የጋራ ፕሮጀክት የጋራ ሃላፊነት መውሰድ ያስፈልጋል፡፡

የታሪክ ተመራማሪና የሥነ ጽሑፍ ሰው ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ለተመራቂዎቹ ባስተላለፉት መልዕክት ተመራቂዎቹ የሚያለያዩ ጉዳዮችን ወደ ጎን በመተው ኢትዮጵያዊነት ላይ እንዲያተኩሩ እንዲሁም በሄዱበት እና በተሰማሩበት ሙያ ሁሉ ከሙስና የፀዳ አገልግሎት በመስጠት ሀገራቸውን እንዲያገለግሉ አሳስበዋል፡፡

በተያያዘ ዜና በአገሪቱ ያለው የሆቴል ሥራ በተለምዶ የተገባበትና የሚሠራበት በመሆኑ ተመራቂ ተማሪዎች ይህንን በመቀየር በሰለጠኑበት ዘመናዊ አሠራር ዘርፉን ሊታደጉ እንደሚገባ የሆቴልና ቱሪዝም ሥራ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ማሳሰቡን ጠቅሶ የዘገበው ሪፖርተራችን ሞገስ ፀጋዬ ነው።

ኢንስቲትዩት ትናንት በገነት ሆቴል ተማሪዎቹን ባስመረቀበት ወቅት ዋና ዳይሬክተሯ ወይዘሮ አስቴር ዳዊት እንደተናገሩት፤ በሆቴሉ ዘርፍ ዘመናዊ አሠራሮችን ለማምጣት ኢንስቲትዩቱ ስልጠና ለሚያስፈልጋቸው አጫጭር ስልጠና በመስጠትና የምርምርና የማማከር አገልግሎትን በመስጠት የበኩሉን እየተወጣ ነው። ይህ ደግሞ በሆቴሎች ያለውን ተልምዷዊ አሠራር በመቀየር በዘመናዊ መልኩ እንዲተካ በማድረግ በኩል የማይተካ ሚና አለው።

በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ብዙነሽ መሰረት በበኩላቸው፣ ይህ የሙያ ዘርፍ የተለያዩ የሀገር ውስጥና የውጭ አገር እንግዶች የሚቀበልና ባህልን የማስተዋወቅ አቅም ያለው ነው። በዚህም ተመራቂዎቹ ትልቅ ሃላፊነት አለባቸው። ዘመናዊ አሠራርን በሚመደቡበት ቦታ ገብተው ማስተማርና ቀልጣፋ አገልግሎት ማህበረሰቡ እንዲያገኝ መሥራት ለነገ የማይባል ነውና ተመራቂዎች የሆቴሉን ዘርፍ እንዲታደጉት ጥሪ አቅርበዋል።

በሀገራችን አባባል ‹ከፍትፍቱ ፊቱ› እንደሚባለው እንግዳ ተቀባይነት ትልቁ ባህላችን ነውና ይህንን በማዳበር ለሌሎችም በማስተማር እንዲሁም የልምድ አሠራርን በዘመንኛው መንገድ በመቀየር የውጭ ቱሪዝሙን በዘርፉ ማሳደግ እንዳለባቸውም አሳስበዋል። ትምህርቱን በተግባር በመቀየር ወደፊት በምትሰማሩበት የሥራ መስክ የተሻለ አገልግሎትና መስተንግዶ በመስጠት የሆቴን ኢንዱስትሪ ዘርፉን ከፍ ማድረግ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም “የሠላም ዲቪድ ሮሽሊ ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጅ” ለ25ኛ ጊዜ በተለያዩ የሙያና ቴክኒክ ዘርፎች በቀንና በማታው መርሐ ግብር ያሰለጠናቸውን 1 ሺ 258 ተማሪዎች ማስመረቁን ሪፖርተራችን ግርማ መንግሥቴ ዘግቧል።

የኮሌጁ ተጠባባቂ ምክትል ዲን አቶ ጥበቡ ለታ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት ኮሌጁ 70 በመቶ ተግባር ተኮር፤ 30 በመቶ ንድፈ ሀሳብ ላይ የተመሰረተ ስልጠናን ስለሚሰጥ በሰለጠኑበት ሙያ ብቃት እና በገበያ ላይ ሰፊ ተፈላጊነት ያላቸውን ባለሙያዎች ማፍራት ተችሏል።

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የፌደራል ቴክኒክና ሙያ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ነጋሽ እንደተናገሩት በአገራችን የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና መስፋፋት የምርጫ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የችግሮቻችን መፍቻ የሆኑት የቁልፎች ሁሉ ቁልፍ ነው። በመሆኑም በሠላም የህፃናት መንደር “የሠላም ዲቪድ ሮሽሊ ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጅ” በዚህ ዘርፍ ባለሙያዎችን በማፍራቱ ሊመሰገን የሚገባው ሲሆን ሌሎችም የዚህን ተቋም አርአያናት እንዲከተሉና አገራችን እያደረገች ላለው ፈጣን ዕድገት የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ አሳስበዋል።

አዲስ ዘመን ሐምሌ 14/2011

መላኩ ኤሮሴ