ብድር ሳይገኝ የማይጀመሩ ፕሮጀክቶችና አማራጮቻቸው

20

 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በተያዘው በጀት ዓመት ብድርን ተማምኖ የሚጀመሩ ምንም ዓይነት ፕሮጀክቶች እንደማይኖሩ ገልፀዋል። ምሁራኑ ደግሞ ይህ እገዳ ሲቀመጥ ብድርን ሊተኩ የሚችሉ ሌሎች ሁኔታዎች መስፋት እንደሚኖርባቸው ይናገራሉ።

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለፃ፤ በተያዘው በጀት ዓመት ምንም ዓይነት ብድርን ተማምኖ የሚጀመሩ ፕሮጀክቶች አይኖሩም። ምክንያቱም ከዚህ ቀደም ፕሮጀክቶች በደንብ ሳይጠኑ ብድር ተወስዶ ገንዘቡ እጅ ላይ ሲደርስ ፕሮጀክቶቹ ባለመጀመራቸው አገሪቱ ዋጋ ከፍላለችና። አገሪቱ በብድር የተጀመሩ ፕሮጀክቶችንም ለማጠናቀቅ ለሚውል ዕዳ ክፍያ በ2012 ዓ.ም ሦስተኛው ትልቁ በጀትን እንድትይዝ ተገዳለች። ስለሆነም ይህ ሁኔታ ሳይስተካከል ብድር ይመጣል ተብሎ የሚሰሩ ፕሮጀክቶች አይኖሩም።

እስከ ዛሬ በጀት ሲያዝ የነበረው ከጃፓንና ከአፍሪካ ልማት ባንክ መጥቶ ይሠራል በሚል እሳቤ ነበር የሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በብድርና በዕርዳታ ላይ ተማምኖ ፕሮጀክቶችን በዕቅድ መያዝ እስካልተተወ ድረስ ፕሮጀክቶች ውጤታማ ሊሆኑ አይችሉም። ስለሆነም ከዚህ በኋላ ፕሮጀክቶች ሲታቀዱ መቶ በመቶ እርግጠኛ በሆንባቸው ሀብቶች ላይ ብቻ ተንተርሶ መሆን ይኖርበታል ብለዋል።

በየዓመቱ ክለሳ እየተደረገ የኮንትራት ዋጋቸውም እየጨመረ የሄደበት ሁኔታ በመኖሩ ፕሮጀክቶቹን ጨርሶ ወደ ሥራ በማስገባት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ሲባል የበጀት ድጋፍ ተደርጓል። ይህ አሠራር ከዚህ በኋላ አይቀጥልም ያሉት ዶክተር አብይ፤ የፕሮጀክቶች መዘግየት የወጪ መጨመርን ስለሚያስከትል በበጀት ላይ ጫና እንዳያሳድሩ፣ ተጠቃሚነትን በፍጥነት ከማረጋገጥ አንፃር የራሱ ተጽዕኖ እንዳይኖረው ብድር ይገኛል ተብሎ በዕቅድ የሚያዝ ፕሮጀክት እንዳይኖር መደረጉን ያስረዳሉ።

ፕሮጀክቶች ሁልጊዜም መሠራት የሚችሉት በካፒታል በጀት ነው። ይህ ደግሞ ከውጭ ብድር ካልተገኘ በስተቀር በአገር አቅም ለመሸፈን እንደሚያዳግት የሚናገሩት ደግሞ የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያው ዶክተር ኢዮብ ተስፋዬ

 ናቸው። እንደእርሳቸው ማብራሪያ፤ አገሪቱ ትልልቅ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ጀምራለች፤ አዳዲስ ያሰበቻቸውም ፕሮጀክቶች ይኖራሉ። ሆኖም በብድር ሊሸፈን አይችልም መባሉ ብዙም የሚያራምድ አይደለም። የታቀደና በሌላ መልኩ የሚያሠራት አቅም ከተመቻቸ ይቻል ይሆናል። ለአብነትም ቅድሚያ ለግል ባለሀብቱ ሰጥታ ብድርን ለእነርሱ ማመቻቸት ከቻለች ይህንን የምታደርግበት ሁኔታ ይሰፋል። አገሪቱ አሁን ባለችበት ሁኔታ ግን አይደለም ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ትንንሾቹን የፕሮጀክት ሥራዎች ማጠናቀቅ ይከብዳታል።

ብድር በየትኛውም መልኩ ያስፈልጋል የሚሉት ዶክተር ኢዮብ፤ መንግሥት ይህንን ሲል ምክንያቱ አሳማኝነት ሊኖረው እንደሚችል ይናገራሉ። ማለትም በግዴታም ቢሆን ወደ ብድር የሚገባበትን ሁኔታ ከደፈነና መቶ በመቶ እርግጠኛ የሆነባቸውን ብድሮች ከተገኙ ችግሩ የመከሰቱ ሁኔታ ይቀንሳል። ግዙፎቹ ፕሮጀክቶችም የመጠናቀቅም ሆነ በአዲስ መልኩ የመጀመራቸው ሁኔታ አጠያያቂ እንደማይሆን ይገልፃሉ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህሩ ዶክተር አጥላው አለሙ በበኩላቸው፤ መንግሥት በራሱ ብድር መበደር የለበትም፤ በግሉ ሁሉንም ፕሮጀክቶች በብድር ለመሥራት መሞከርም ኪሳራ ነው ይላሉ። ስለዚህ መቶ በመቶ እርግጠኛ ሳልሆን በብድር መሥራት የለብኝም ማለቱ ተገቢነት አለው። ብድር ያልገባበት አሠራር በየትኛውም መልኩ መከናወን ባይችልም ከብድር ራስን ማራቅ ግን ይቻላል። በመሆኑም መንግሥት ማድረግ ያለበት ብድሩን ከራሱ አርቆ በአገር ውስጥ ቁጠባ ወይም ብድሮች ለባለሀብቶች እንዲሰጥ በማመቻቸት ሥራዎችን ማከናወን ይኖርበታል ብለዋል።

ዶክተር አጥላው፤ መንግሥት አሁንም ቢሆን መቶ በመቶ እርግጠኛ በሆነበት ብድርም ብዙም ራሱን ማስገባት የለበትም። መጀመሪያ መሥራት ያለበት አሠራርን ማስተካከል ላይ ነው። ምክንያቱም እርግጠኛ የሆነበትን ብድር ቢያመጣም ከፋዩ ራሱ ከሆነ መዘናጋት ይከሰትና ሥራዎች በአግባቡ ባለመሠራታቸው ዋጋ ያስከፍለዋል ይላሉ። ለእስካሁኑ እየገጠመ ያለው የፕሮጀክቶች ውጤታማነት የብድር እርግጠኝነት ብቻ ሳይሆን የማኔጅመንት ችግር ነውና እዚህ ላይ ከብድሩ በላይ ትኩረት ሰጥቶ ካልሠራ በቀር ችግሩን ማቃለል እንደማይችል ይገልፃሉ።

ችግሩን ለመፍታት ምርታማነትን ማሳደግ፣ ወደ ውጭ የምንልከውን ምርት በቁጥርም ሆነ በጥራት ከፍ ማድረግ፤ ዕዳ የመክፈል አቅምን ማሳደግና አጋሮቻችን እንዲተማመኑብን ማድረግ ያስፈልጋል የሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፤ ግዙፍ የሆኑትንና ያልቻልናቸውን ከእጃችን አውጥተን ለግል ባለሀብቱ በመስጠት ሥራዎች በፍጥነት እንዲሠሩ ይደረጋል። በግል አዋጭ የሆኑ ሥራዎችም ለመሥራት ዕድል ይመቻቻል ብለዋል። በቀጣይ ከዲዛይንና ቅድመ ዝግጅት ጀምሮ ትኩረት ሰጥቶ ለመተግበር መታሰቡንም ተናግረዋል።

ብድር መበደሩ ችግር እንደሌለው የሚያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አገሪቱ የውጭ ብድር 31 በመቶ ብቻ ያለባት ሲሆን፤ ይህ ደግሞ በጣም አደጉ ከሚባሉት ያነሰ ነው። ስለዚህም ብድሩ ሳይሆን ኪሳራውን የሚያመጣው ፕሮጀክቶቹ በአምስት ዓመት ውስጥ ተጠናቀው ወደ ገበያ መግባት አለመቻላቸው ነውና ፕሮጀክቶቹ በራስ አቅም እየተሠሩ በራሱ የሚሸፍንበትን መንገድ ለመቀየስ ይሰራል ብለዋል። ሳይጠና ብድር ይወሰድና የእኛ ገንዘብ መስሎን መዘናጋቱም እንዳይቀጥል በየጊዜው መከታተል ላይ ትኩረት ይደረጋል ሲሉም አስረድተዋል።

መፍትሄው መንግሥት በብድር ፕሮጀክቶችን አልሠራም ማለት ብቻ ሳይሆን፤ ባለሀብቶችና የውጭ አጋሮችን በሥራው ላይ በቀጥታ እንዲሳተፉ ማድረግ እንደሆነ የሚናገሩት ዶክተር ኢዮብ፤ በአጭር ጊዜ ሠርተው አገርን ተጠቃሚ የሚያደርጉበትን መንገድ መዘርጋት ይገባል። እርግጠኛ ተሆኖ ወደ ሥራ እንዲገቡ ማድረግም ተገቢነት አለው። ግን ሌሎች አማራጮች ሳይመቻቹ ሳንበደር ፕሮጀክቶችን እንሠራለን መባሉ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናልና ይህ በሚገባ መታየት አለበት ይላሉ።

ዶክተር አጥላው በበኩላቸው፤ ብድር አለመበደሩ ብቻ መፍትሄ አይሆንም። ይልቁንም በብድር ጫና ምክንያት የሚታጣውን ገንዘብ ለማዳን ሥራዎች ለግል ባለሀብቶች ሊሰጡ ይገባል። የግል ባለሀብቶች በብድር እንዲሠሩ ምቹ ሁኔታ የሚፈጠርላቸው ከሆነ ደግሞ ብድሩን ቶሎ ለመክፈልና ሥራውን ጨርሶ ትርፋማ ለመሆን ሲሉ በመንግሥት በኩል ያለውን መዘናጋት ከማስቀረታቸውም በላይ ምርታማነት በአገሪቱ እንዲጨምር ያደርጋሉ። ስለዚህም ፕሮጀክቶችን በቀላሉ በፍጥነት ወደ ገበያው እንዲቀላቀሉ ለማድረግ ለግል ባለሀብቶች ቅድሚያ መስጠቱ ያዋጣል ይላሉ።

በ2011 ዓ.ም በፌደራል ደረጃ እየተካሄዱ ያሉ ፕሮጀክቶች ከ1ሺ በላይ የሚደርሱ ሲሆን፤ የእነዚህ ፕሮጀክቶች አጠቃላይ የኮንትራት ዋጋም 593 ቢሊየን ብር ነው። ባለፉት 7 ዓመታት በተያዘላቸው ጊዜ ያልተጠናቀቁ ፕሮጅክቶች በመንግሥት ላይ ያስከተሉት ተጨማሪ ወጪ 43 ቢሊዮን ብር ሆኗል። አሁን ላይ ደግሞ አጠቃላይ ወጪያቸውም ወደ 6 መቶ 34 ቢሊየን ብር አሸቅቧል።

እነዚህ ፕሮጅክቶች በቀጣይም ተጨማሪ ወጪ እያስወጡ የሚቀጥሉ ከሆነ በመጀመሪያ ደረጃ የሀገሪቱን በጀት ያናጋሉ። መንግሥት በጀቱን አመጣጥኖ ለተለያዩ ተግባራት ከማዋል ይልቅ ለእነዚህ ፕሮጄክቶች እንዲመድብ ይገደዳል። የሀገሪቱ ሀብት ወደ አንድ ጉዳይ ብቻ እንዲከማች ያደርጋል። በጀቱ በተደጋጋሚ ለእነዚህ ፕሮጅክቶች ከዋለ ደግሞ ሌሎች በወቅቱ ምላሽ ሊሰጣቸው የሚገባቸው ፕሮጀክቶች ሳይሠሩ ይቀራሉ። ይህ ደግሞ ሀገሪቱ የምታገኘውን ገቢ ልማት ላይ ከማዋል ይልቅ በዕዳ መክፈል ላይ እንድታደርግና ዕድገቷ እንዲጓተት ያደርጋል።

አዲስ ዘመን ሐምሌ 14/2011

 ጽጌረዳ ጫንያለው