ችግኞችን በመትከል ወቅቱ የሚጠይቀውን ታሪክ እንሥራ!

17

 እየደጋገመ የሚመታንን ድርቅና ረሀብን የመከላከያው አንዱና ዋነኛው መንገድ የደን ሀብታችንን ማልማትና መጠበቅ ነው። ደን ህይወት ካላቸው ነገሮች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው የዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ባለቤት ነው። ጋራ ሸንተረሩ፣ የምንኖርበት ከተማና መንደር አረንጓዴ ሲለብስ ንጹህ አየር እንተነፍሳለን።

ደን የኢኮኖሚ ሀብትም ነው። ከቱሪዝም ለሚገኘው ሀብት የገቢ ምንጭ ይሆናል። የሥራ ዕድል ፈጠራን ያሰፋል። ከዚህም ሌላ ከውጭ በከፍተኛ ምንዛሬ ወደ ሀገራችን የምናስገባውን የጣውላ እና ሌሎች የእንጨት ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት የውጭ ምንዛሬ ወጪን ያድናል። የደን መኖር የውሃ አካላትም ውጤታማ ሆነው እንዲቀጥሉ ያስችላል። የመስኖና የመጠጥ ውሃ ግድቦች በሙሉ ውሃ የሚያገኙት በደን አማካይነት መሆኑ ለአንዴም ቢሆን መዘንጋት አይኖርበትም።

የኃይል አቅርቦት ማነስና መቆራረጥ አንዱ ምክንያት ከደን መመናመን ጋር ተያይዞ የሚፈጠር የአፈር መሸርሸርና የግድቦች በደለል መሙላት ነው። ይህም በእርሻ እና በተፈጥሮ ሀብቶቻችን ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል። እነዚህና ሌሎችም ያልነካካናቸው በርካታ ነገሮች ከሰው ልጆች ህልውና ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ግንኙነት ያላቸው ወሳኝ ጉዳዮች ናቸው።

ለሰዎች ልጆች ወሳኝ የሆነውን ደን ከማልማት ይልቅ ስንመነጥር፣ ችግኝ ከመትከል ይልቅ የተተከለውን ስንቆርጥ እና ለዕለት ፍጆታ ስናውለው ኖረናል። በዚህም ምክንያት በአጼ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግሥት 40 ከመቶ የነበረው ሀገራዊ የደን ሽፋን አስደንጋጭ በሆነ መልኩ ወደ ሦስት በመቶ አሽቆልቁሎ ነበር። ሆኖም በተሠራው ሥራ እና በተሰጠው መጠነኛ ትኩረት ከነበረበት አስፈሪ ደረጃ ዛሬ ወደ 15 ነጥብ ስድስት ከመቶ መድረስ ችሏል። ይሄም ቢሆን ግን ዛሬም የደን ሽፋን አሳሳቢ ደረጃ ላይ መሆኑን ያሳያል።

በዓለም ላይ የአየር ንብረት ለውጥ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል። በአየር ንብረት ለውጥ ተጠቂ ይሆናሉ ከሚባሉት እና በስጋት ከሚታዩት የአፍሪካ ሀገራት መካከልም ኢትዮጵያ አንዷ ናት።

 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሀገራዊና ዓለምአቀፋዊ የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂን ከግብ ለማድረስና በሰው ልጆች ህልውና ላይ የተጋረጠውን የድርቅና የረሀብ ስጋት ለመቋቋም ችግኝ መትከል ወሳኝ መሆኑን በማስገንዘብ ለስኬታማነቱ ሁሉም ህብረተሰብ እንዲሳተፍ ጥሪ አድርገዋል። በዚሁ መሰረት በዘንድሮው ዓመት ብቻ አራት ቢሊየን ችግኞችን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመትከል እቅድ ተይዞ ወደ ተግባር ተገብቷል።

የችግኝ ተከላው በከተማና በገጠር እያንዳንዱን ህብረተሰብ በማስተባበር እና በማሳተፍ በተሠራው ሥራ እስከአሁን ድረስ ሁለት ነጥብ ስድስት ቢሊየን ችግኝ ለመትከል ተችሏል። ይሄ ትልቅ ለራሳችን ራሳችን የምናመሰግንበት የሥራ ውጤት ነው። ሊበረታታም ይገባል። በቀጣይም ሀምሌ 22 ቀን በአንድ ጀምበር 200 ሚሊየን ችግኞችን በመላ ሀገሪቱ ለመትከል ቀጠሮ ተይዟል።

በዚህ የአረንጓዴ ልማት አሻራን የማሳረፍ ቀን ሁላችንም ልንረባረብ ይገባል። ዛሬ የምናሳርፈው አሻራ የነገዋን ኢትዮጵያን አረንጓዴ፣ ለመኖሪያ ምቹ ፣ ከድርቅና ረሀብ ያመለጠች ሀገር ያደርጋታል። በቀጣይነት ለምናስረክባቸው ልጆቻችን ታሪካዊ ቅርስ ማቆየት መሆኑ መዘንጋት አይኖርበትም።

ኢትዮጵያውያን የምንታወቀው በጦር ጀግንነት ነው። ጀግንነት ግን በጦርነት ብቻ አይደለም። ጀግንነት ወቅቱ የሚጠይቀውን ዋነኛ ጉዳይ ማሸነፍና ለውጤት ማብቃት ነው። ጀግና ራሱን ከድንቁርና፣ ከረሀብና ከበሽታ ነፃ ያወጣ ነው። የሰለጠነችና ለዜጎቿ የምትመች ሀገርን ማውረስ እና ይህንኑ መልካም ነገር ማስቀጠል ነው፡፡ በመሆኑም ሁላችንም አካባቢያችንን ፅዱ እና አረንጓዴ አድርገን ማልማት ፤ በችግኝ ተከላ መሳተፍ እና ከተከላውም በኋላ ጸድቆ ለውጤት እንዲበቃ ስንረባረብ ጀግኖች እንሆናለን።

ከፍተኛ ገንዘብ ፣ጉልበት እና ጊዜ ወጥቶበት በሚካሄደው የሀምሌ 22 የችግኝ ተከላ ዕለት ሁሉም ሰው በየአካባቢው እንዲሁም በሚሠራበት የሥራ ቦታ በነቂስ በመውጣት 200 ሚሊየን ችግኞችን በመትከል የታሪክ አሻራውን ማኖር ይጠበቅበታል። የዚህ ዘመን ጀግና ጊዜው የሚጠይቀውን ሠርቶ ታሪክን ማስቀጠል የቻለ ነውና።

አዲስ ዘመን ሐምሌ 14/2011