የታካሚውን ትከሻ ያጎበጠው የጤና አገልግሎት

20

ሞት ቀድሟቸው ሬሳቸው በሳጥን ታሽጎ እንዳይጓዝ ማልደው የተነሱ ታካሚዎች የሽንትና የደም ናሙና በመስጠት የላቦራቶሪውን ክፍል ከበዋል፡፡ ድንገት መብራት ጠፋ፡፡ ወረፋ ሲጠባበቁ የነበሩ ተገልጋዮች ደነገጡ፤ በሸቁ፡፡ አንደኛው ድምፁን ከፍ አድርጎ፤ ባለሙያዎችን የሚያጥላላ ንግግር ተናገረ፡፡ በዚህ የተቆጣው የላቦራቶሪው ባለሙያ ወረፋ ወደሚጠብቁት ሰዎች ዞሮ መቆጣት ጀመረ፡፡ “ማነው አሁን ኃይለ ቃል የተናገረው እኔ ምን ላድረግ” እያለ ተመልሶ ወደ ክፍሉ አመራ፡፡ ይህ የሆነው በአዲስ አበባ በሚገኝ አንድ የመንግሥት ጤና ጣቢያ ውስጥ ነው፡፡

መንግሥት የጤናውን ዘርፍ ለማጠናከር በጤና ጣቢያ ደረጃ ትኩረት ቢሰጥም ዛሬም ድረስ ሳንካዎች አልተለዩትም፡፡ ታዲያ ችግሩን ላለመጋፈጥ የሚሹ አቅሙ ያላቸው ታካሚዎች ከመንግሥት ጤና ተቋም ይልቅ የግሉን ሲመርጡ፤ በኢኮኖሚ ምክንያት ደግሞ ምንም ገቢ የሌላቸው ከነችግሩም ቢሆን የመንግሥትን ጤና ተቋም የሙጥኝ ይላሉ፡፡ ችግሩ ባስ ሲልባቸውና ተበድረው ተበድረውም ይሁን ለምነው በግል ለመታከም ሲሹ ደግሞ ዋጋው ሰማይ የነካ ይሆንባቸዋል፡፡

የአልጋ ቁራኛ ከሆኑ ወራት ያስቆጠሩት ወይዘሮ አያልነሽ ገላዬነው፤ ምንም እንኳን ራሳቸውን ለማስተዳደር በቂ ገንዘብ ባይኖራቸውም፤ በመንግሥት ጤና ተቋማት የሚሰጠው አገል ግሎት ለወረፋ ስለሚዳርግ ህይወታቸውን ከሞት ለመታደግ ሲሉ የግል የጤና ተቋም መር ጠዋል፡፡ “ሁለት ወዶ አይሆንም” ይሉትን ብሂል በውስጣቸው ቢያሰላስሉም የአገልግሎቱ ቅልጥፍና ከመንግሥት የጤና ተቋማት አንጻር ሲታይ የተሻለ ሆኖ ቢያገኙትም ዋጋው ግን የማይቀመስ ሆኖባቸዋል፡፡ እርሳቸውም “ከመሞት መሰንበት” በማለት ከካርድ ክፍያ እስከላብራቶሪ ምርመራ ድረስ ከፍተኛ ወጪ አውጥተው ህይወታቸውን መታደግ ችለዋል። ነገር ግን እዳው አልቀረላቸውም፡፡ መንግሥት የግል የጤና ተቋማት የሚያደርጉትን ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ሊቆጣጠረው እንደሚገባም ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል፡፡

በዘርፉ ችግር ፈቺ የተባለ ጥናት አጥንተው የነበሩት የኦሮሚያ ፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሀብት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ እንደሚሉት፤ መሠረታዊ አገልግሎት የሚባሉት በተለይ በባህሪያቸው ከድህነት ቅነሳ ጋር ግንኙነት ያላቸውና የአገልግሎትን ፍትሐዊነት ለማረጋገጥ አስተዋጽኦ ያላቸው፤ እንደትምህርትና ጤና ያሉ ሙሉ በሙሉ በግል ሴክተርም ሆነ በመንግሥትም ሲሰጡ የገበያ ውድቀት ማጋጠሙ አይቀርም፡፡

በተለይ ባደጉት አገራት ውስጥ አብዛኛው የአገልግሎት ሥራ የሚከናወነው በግል ሴክተር ሙሉ በሙሉ ትርፋማነትን መሠረት አድርጎ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ሰዎች ከማህበራዊ አገልግሎቱ ተደራሽነትና ከተጠ ቃሚነት ባሻገር በአጭር ጊዜ የሚያገኙትን ትርፍ መሠረት አድርገው ስለሚያሰሉና በዘርፉ የሚያደርጉትንም ኢንቨስትመንት በአጭር ጊዜ ለማግኘት ካላቸው ጉጉት የተነሳ፤ እንዲሁም አገልግሎቱ በፍላጎት ላይ የሚያተኩር በመሆኑ፤ በተጨማሪም በአገራችን ተደራሽነቱ በአግባቡ ስላልተረጋገጠና ክፍተት ያለበት በመሆኑ እነዚህን እድሎች ተጠቅመው ተገቢ ያልሆነ ዋጋ ይጭናሉ፡፡

እንደ ዶክተር ቢቂላ ማብራሪያ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ህመምተኞች በገጠር የሚኖሩ፣ ከፍተኛ የድህነት ሁኔታ ውስጥ ያሉና ከኪሳቸው አውጥተው መታከም የማይችሉ በመሆናቸው ከፍተኛ የህክምና አገልግሎት ለማግኘት የኢኮኖሚ አቅማቸው አይፈቅድላቸውም፡፡ የጤና አገልግሎት ውድና ከፍተኛ የሆነ መሰረት ልማት ግንባታ፤ እንዲሁም የአቅርቦት ጥያቄ የሚያስከትል በመሆኑ በሚፈለገው ደረጃ በመንግሥት በኩል አገልግሎቱን ማቅረብ አልተቻለም፡፡ የአገልግሎትን ጥራት ማስጠበቅና ተደራሽነትን ማረጋገጥ መንግሥትን እየተገዳደረ ያለ ችግር ሆኗል፡፡ በመንግሥትም ሆነ በግል የጤና ተቋም ላይ ውስንነቶች አሉ፡፡

ጤና ከፍተኛ መሠረተ ልማት ይጠይቃል የሚሉት ዶክተር ቢቂላ፤ መድኃኒትና ሌሎች የህክምና መገልገያ መሳሪያዎች አቅርቦት ሳይቋረጡ ማቅረብን እንደሚጠይቅ ጠቅሰው፤ ይህ ደግሞ በከፍተኛ ድህነት ውስጥ ለሚኖር ህዝብና መንግሥት ፈታኝ እንደሆነ፤ በርካታ ህዝብ በዚህ ዘርፍ ከመንግሥት አገልግሎት ማግኘት ባለመቻሉ ምክንያት ወደ ግል የጤና ተቋማት እንደሚሄድ፤ በግል የጤና ተቋማት ለመታከም ሲሄዱ ደግሞ ለከፍተኛ ወጪ እንደሚዳረጉ፤ ይህም ማህበረሰቡን ለችግር መዳረጉን ይገልጻሉ፡፡ አክለውም፤ በጤና አገልግሎት ዘርፍ ያሉትን ውስንነቶች ሊቀርፍ የሚችል ሞዴል ማሰብ እንደሚያስፈልግ ጥናታቸውን መነሻ አድርገው ያስገነዝባሉ፡፡

“የሌሎችን አገሮች ተሞክሮና ስኬታማ የሆኑ የአገልግሎት አሰጣጥ ሞዴሎችን ካልተከተልን በስተቀር የጤና አገልግሎትን ሙሉ በሙሉ በመንግሥት ብቻ ማዳረስ አይቻልም፡ ፡ በሌላ መልኩ፤ የመንግሥት ተቋማትን ውስንነት በማየት ሰዎች ወደግል ተቋማት በመሄዳቸው አንጡራ ሀብታቸውን ሸጠው እስኪደኸዩ ድረስ ሀብታቸውን አሟጥጠው ለጤና አገልግሎት እያዋሉ ይገኛሉ፡፡ በግሉ ዘርፍ ብቻም የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ አይቻልም፡፡ በተለይ ደግሞ፤ አብዛኛው ህዝብ በድህነት ውስጥ የሚኖር በመሆኑ የግሉ የጤና ዘርፍ ለህዝቡ መልካም የሚባል አማራጭ አይደለም” ይላሉ ዶክተር ቢቂላ መፍትሄው በአንድ አካል ላይ ብቻ የተንጠለጠለ አለመሆኑን ሲያረጋግጡ፡፡

እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ ነጻ ገበያ በእንዲህ ያሉ መሰረታዊ አገልግሎቶች ላይ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ቢደረግ ህዝብ ተጎጂ ይሆናል፡፡ የነጻ ገበያ እሳቤው በምን አይነት እቃዎች ላይ ተግባራዊ መደረግ አለበት በሚል መቃኘት ይኖርበታል፡፡ “ነጻ ገበያ ነው” ተብሎ የመድኃኒት አቅርቦት እንደ መጠጥና ሌሎች ሸቀጣሸቀጦች መታየት የለበትም፡፡

“ነጻ ገበያ የሚባለው አስተሳሰብ ጫፍ የወጣና በየትኛውም አገር የማይተገበር፤ ነገር ግን በንድፈ ሀሳብ ደረጃ ያለ ነው” የሚሉት በአዲስ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚ ምሁሩ ዶክተር ታደለ ፈረደ ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚያብራሩት፤ በተለይ መሠረታዊ አገልግሎቶች ተብለው ከሚታወቁት ውስጥ አንዱ የሆነው የጤና ዘርፍ በነጻ ገበያ እሳቤ ውስጥ መስተናገድ የለበትም፡፡

የኢንቨስትመንትን ቦታ ጨምሮ ከመንግሥት ድጎማ የሚወስዱ የግል የጤና ተቋማት መኖራቸውን የሚገልጹት ዶክተር ታደለ፤ ተቋማቱ ይህንን ተሳቢ የሚያደርግ አገልግሎት ግን መስጠት እንዳልቻሉ ይናገራሉ፡፡ የግል የጤና ተቋማት መኖራቸው ለታካሚዎች አማራጮችን ማስፋት እንደሆነ፤ በዚህም የግሉ ዘርፍ ከጥራት እስከ ዋጋ ውድነት ድረስ ያሉትን ችግሮች ማስተካከል እንደሚጠበቅባቸውና ዋጋ ሲጨመርም በተለምዷዊ አሰራር ሳይሆን በጥናት ላይ መመስረት እንዳለበት ይመክራሉ፡፡

ዶክተር ታደለ መንግሥት በጤናው ዘርፍ ጥራትን መሰረት ያደረገ ሥራ ቢሰራ ኖሮ የግል የጤና ተቋማት አገልግሎትም ዋጋ ይቀንስ እንደነበር በማመላከት፤ በመንግሥት በኩልም ቢሆን ተደራሽነቱ መስፋት አለበት። ህንጻዎች ብቻ እየተገነቡ አገልግሎቱ ውስን እንደሆነ ጠቅሰው፤ የተጀመሩትን ሥራዎች መፈጸም፤ ተጨማሪ ኢንቨስትመንት እንዲኖር ማድረግ ቀጣይ የመንግሥት የቤት ሥራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡ በዚህ ሂደትም የህብረተሰቡን የኢኮኖሚ ሁኔታ ያገናዘበ አገልግሎት መስጠት እንደሚገባ በማንሳት በነጻ ገበያ ሥም የሚደረግ አግባብ ያልሆነ ክፍያ የሚጠይቅ የጤና አገልግሎት መፍትሄ ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ መንግሥት በተለይም በግል የጤና ተቋማት በህክምና ሥነ ምግባር ላይ ያተኮረ ክትትል ማድረግ እንደሚኖርበት አስታውቀዋል፡፡

አዲስ ዘመን ሀምሌ 19/2019

አዲሱ ገረመው