እናቱን የገደለ ምላስ ታሰረ

17

 ባሳለፍነው ሳምንት ነበር “የስክንድስ ዝምታ” የሚለው መጽሐፍ የተመረቀው። መፅሐፉ በደራሲ መጋቢ አዲስ አማኑኤል መንግስተ አብ የተጻፈ ሲሆን በአንድ መቶ ስልሳ አራት ገጾች የአንድ መቶ ብር የመሸጫ ዋጋ ተቆርጦለት ለአንባቢያን ቀርቧል።

በኢትዮጵያ ቅርስ እና ጥበቃ ባለስልጣን አዳራሽ በተካሄደው የመጽሐፉ ምርቃት መርሃ ግብሩ በበገና ድርደራ ቀጥሎም በወጣት እና አንጋፋ ገጣሚያን የግጥም ስራ ተከፈተ። በመቀጠል ወደ መድረኩ የወጣው ደራሲ መጋቢ አዲስ አማኑኤል መንግስትአብ ነበር። የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክቱን ካስተላለፈ በኋላ የመፅሐፉን ጠቅላላ ሃሳብ እና ጭብጥ በዳሰሳ መልክ በተለያዩ ምሁራን ቀርቧል፤ እኛም የመጽሐፉን አንኳር ሃሳብ አሳጥረን አቀርበናል።

መጋቤ ጥበብ ምናሴ ወልደ ሃና ከመጽሐፉ ካነሱት ሃሳቦች መካካል በጥበበኛው ስክንድስ እድገቱንና ትምህርቱ በፍልስፍና ትምህርት ቤት ውስጥ የተጠየቁ ጥያቄዎችን በተግባር ማየቱ በአቴንስና በዋሪጦስ ትምህርት ቤት መምህራኖቹና መጽሕፍቶቹ ከክርስትና ወጣ ባለ መልኩ ሴቶች ሁሉ አመንዝራ ናቸው የሚል እምነት ነበራቸው∷ ጠቢቡም ለጊዜው ቢቃወመውም ዳሩ ግን የተነገረውን ለማረጋገጥ ከ24 ዓመታት በኋላ ወደ ሃገሩ ተመልሶ እናቱን በዝሙት ፈትኗት እናቱም በፈተናው ስትወድቅ ታንቃ መሞትዋን ይናገራል። በዚህም ምክንያትም “አንደበት ሆይ እናትህን ገድለሃልና አርምሞ ይገባሃል” በማለት አርምሞ ወይም ዝምታ መረጠ።

በዘመኑ ነግሶ በነበረው እንድርያኖስን ለብዙ ፈተና እንደተዳረገ እና ፈተናውን ባለመናገር ማለፉን ይነግረናል። ንጉስ እንድርያኖስ ከጠቢቡ ስክንድስ ብዙ እንደተማረና እንዳከበረውም ያሳያል። ጠቅለል ባለ መልከ ብዙ ሰምተን የተወሰኑ ፍሬ ነገር መናገር እንዳለብን አበክሮ ይመክራል።

በሌላ ዘርፍ የስነ ጽሑፍ ይዘት የድርሰት አወቃቀር የፍልስፍና ሕይወት በዓላማ እስከ ሞት ድረስ መጽናት እንዳለብን ያስረዳል። በ“ዜና ስክንድስ ጠቢቡ” 15 ክፍሎች ያሉትና የግሪኩ ንግሱ እንድሪያኖስና ሌሎች ሰዎች የጠየቁት 150 ጥያቄዎችን ጠቢቡ በጽሑፍ የመለሰላቸውን አካቶ የያዘ መጽሐፍ ነው። መጽሐፉ ከደብረ ቢዘን፣ ከገዳም አቡነ እንድሪያስ ኤርትራ ፤አምባ ማሪያምና ጉንዳጉንዲት ማሪያም… ይገኛሉም ብለዋል።

በቅድስት ስላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህርና የኮሌጁ ዲን የሆኑት ቀሲስ ዶክተር መዝገቡ ካሳ አጭር ሂስ አቅርበዋል። ዶክተሩ ስለመጽሐፉ ሲናገሩ ሁለት ነገር ቀልባቸውን እንደያዘው ጠቅሰው

 አንደኛው በመጽሐፉ የተዘረዘሩ ዝርዝር የመጽሐፍት እንዴት ፈልጎ እንዳገኛቸው እና ለተመራማሪዎችም ሆነ ለኮሌጁ እንዴት ግብዓት ማድረግ አለብን የሚለውን ሃሳብ እንዲጫርባቸው ማድረጉን ገልጸዋል።

በሁለተኛ ደረጃ ያነሱት ሃሳብ ደራሲ መጋቢ አዲስ አማኑኤል መንግስትአብ የስክንድስን ህይወት እና ዝምታ ያየበትን እይታ መልካም እንደሆነ ገልጸው እርሳቸው ጉዳዩን ወደ አገር ብናመጣው የሚል ሂስ አቅርበዋል። ከማይገባን ነገር ጋር ስንጋባ ከማይመቹ ሃሳቦች ጋር ስንስማማ እና ሀገራችንን በዚያ እውቀት ስንፈትን ሀገራችንን እንገላለን̥፤ አላስፈላጊ ትችትና ውዥንብር ውስጥ እነገባለን ስለዚህ በሀገርኛው በኩል ቢቃኝ መልካም ይህን ነበር ሲሉ ሂሰዋል።

የመቀሌ ዩኒቨርስቲ የፍልስፍና መምህር ብሩህ ዓለምነህ ስለ መጽሐፉ እንዳሉት በሀገራችን የምሁራን ታሪክ ውስጥ “የኢትዮጵያ ፍልስፍና” የሚል ፅንሰ ሐሳብ ያመጣው በዜግነት ካናዳዊ፣ በምርጫ ደግሞ ኢትዮጵያዊ የሆነው ክላውድ ሰምነር ነው። ሰምነር “የኢትዮጵያ ፍልስፍና (Ethiopi­an Philosophy – EP) ” ልዩ ባህሪውና ርዕዩ ምንድን ነው? ለሚለው ጥያቄ መልስ ባይሰጥም በኢትዮጵያ ፍልስፍና ውስጥ ምን ዓይነት ፅሁፎች እንደሚካተቱ ግን ያስቀመጠው ነገር አለ።

በዚህም “የኢትዮጵያ ፍልስፍና” ውስጥ በፅሁፍ አምስት መፃህፍት፣ በቃል ደግሞ በየብሔረሰቡ ያሉትን ሥነ ቃሎች እንደሚያካትት ፅፏል። ሰምነር በፅሁፍ የሚገኙ “የኢትዮጵያ ፍልስፍና” ምንጮች በማለት የዘረዘራቸው አምስቱ መፃህፍት እነዚህ ናቸው፣ ፊሶሎጎስ (EP Vol-5) የስክንድስ የህይወት መርሆዎች (EP Vol-4) ፣አንጋረ ፈላስፋ (The Book of the wise philosophers) (EP Vol-1) የዘርዓያዕቆብና የወልደ ሕይወት ሐተታዎች ናቸው።

ከእነዚህ አምስት መፃህፍት ውስጥ የመጀመሪያዎቹ ሦስቱ የግሪኮች ሥራዎች ሲሆኑ በአረብኛ በኩል (ከፊሶሎጎስ በስተቀር) ወደ ግዕዝ የተተረጎሙ ናቸው። ምናልባት እዚህ ጋ “ከውጭ የተተረጎሙ የፍልስፍና ሥራዎች እንዴት የኢትዮጵያ ተደርገው ሊቆጠሩ ይችላሉ?” የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል።

እነዚህ የትርጉም ሥራዎችም በተለያዩ ገዳማት ውስጥ ተገኝተዋል። ሆኖም ግን መፃህፍቱ በቤተ ክርስትያኗ ልሂቃን ዘንድ ምን ያህል አገልግሎት ላይ ውለዋል? የሚለው ጥያቄ አጠያያቂ ቢሆንም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን እነዚህ መፃህፍት ከየገዳማቱ እየተፈለጉ በአማርኛ በመተርጎም ላይ ናቸው። ከዚህ በፊት “አንጋረ ፈላስፋ” እና “ፊሶሎጎስ” በተለያዩ ፀሐፊያን በአማርኛ ተተርጉመው የቀረቡ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ “የስክንድስ የህይወት መርሆች” የሚለው መፅሐፍ “የስክንድስ ዝምታ” በሚል ርዕስ

 በመጋቤ ሐዲስ አማኑኤል መንግስተአብ ተተርጉሞ ቀርቧል።

ስክንድስ በ2ኛው ክፍለዘመን በግሪክ የነበረ የCynic or NeoPy­thagorean ፍልስፍና ተከታይ የነበረ ፈላስፋ ነው። ስክንድስ ወደ ቤሩት በመሄድ ፍልስፍና እየተማረ ባለበት ወቅት ከአንደኛው የፍልስፋና መፅሐፍ ላይ “ሴቶች ሁሉ ዘማዊ ናቸው” የሚል “ጥቅልና ደፋር የሆነ ድምዳሜ” ያገኛል። ይሄንን ድምዳሜ በተግባር ለማረጋገጥ ከዓመታት በኋላ ወደ ሀገሩ ይመለሳል፣ ራሱንም በመቀየር እናቱን ፈተነ እናቱም ወደቀች። በራሷም እጅግ ታፍርና ራሷን ታጠፋለች። ስክንድስ ለእናቱ ሞት ራሱን ተጠያቂ በማድረግ ራሱን ለመቅጣት ይወስናል። ቅጣቱም የራሱን አንደበት ለዘላለም መዝጋት ነበር። በዚህም ቀሪ ህይወቱን በዝምታ ለማሳለፍ ይምላል።

ይሄንን ታሪክ የሰማው የወቅቱ የሮማ ንጉስ ሐድሪያን ስክንድስን በመጥራት እንዲናገር ቢለምነውም ሆነ ቢያስፈራራው ሊሳካለት አልቻለም። በዚህም የተነሳ በጽሑፍ ብቻ ለመግባባት ይስማማሉ። በዚህም ንጉሱ ስለ ህይወት የነበሩትን ጥያቄዎች (ለምሳሌ፣ ስለ እግዚአብሔር፣ ስለ ዩኒቨርስቲ፣ ስለ ውበት…የነበሩትን ጥያቄዎች) ለስክንድስ በፅሁፍ ያቀረበለት ሲሆን ስክንድስም በጽሑፍ ብቻ ይመልስለት ነበር።

ሌላኛው በቅድስት ስላሴ መንፈሳዊ ዩነቨርሲቲ የታሪክ እና የቀኖና መምህር የሆኑት መኮንን ወርቅነህ የስልጣኔና የዕውቀት ምንጭ የሆነችው ኢትዮጵያን ከዘመነ አበው ኦሪት ወንጌልና ሊቃውንት እስከ አሁን ድረስ ያከማቸችው ዘርፈ ብዙ የሆኑ በብዚ ሺ የሚቆጠሩ መንፈሳዊ እና ማህበራዊ ዕውቀቶችን የያዙ የልሳነ ግዕዝ የብራና መጽሐፍት አሉት። እነዚህ ሁሉ መጽሐፍት ሕዝቡ በሚረዳው ቋንቋ ገና አልተተረጎመም። ክፍተቱን በማሰብ ግን መጋቢ አዲስ አማኑኤል መንግስትአብ “ዜና ስክንድስ ጠቢብ” የተሰኘውን መጽሐፍ ወደ አማርኛ ተርጉመው በፊት እና በኋላውም ሌላ የዕውቀት ምንጮች ሊሆኑ በሚችሉ ስራዎች አጅበው ለአንባቢያን ማቅረባቸውን አመስግነዋል።

እኛም ይህንን የደራሲ መጋቢ ሐዲስ አማኑኤል መንግስት አብ ፍልስፍና ቀመስ የሆነውን መጽሐፍ እንዲያነቡ እንጋብዛለን።መልካም ሰንብት !

አዲስ ዘመን  ሐምሌ 21/2011

አብርሃም ተወልደ