የ‹‹አረንጓዴ አሻራ›› ችግኞች-የደን ሀብቱ ግብዓቶች

40

የደን ሽፋናቸውን ማሳደግ አጀንዳቸው ያደረጉ አገሮች ሕዝባቸውን አስተባብረው በዘመቻ ችግኝ መትከልን ተያይዘውታል። በአንድ ቀን ውስጥ ብዙ ዛፎችን በመትከል ህንድ ቀዳሚውን ቦታ የያዘች ሲሆን፤ እ.ኤ.አ. በ2017 አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን በጎ ፈቃደኛ ዜጎቿን አስተባብራ 66 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል በድንቃድንቅ መዝገብ ላይ ስሟ እንዲሰፍር አድርጋለች፡፡

በዚህ ዓመት ደግሞ በአንድ ቀን ብዙ ችግኞችን የመትከል ሪከርድ ለመንጠቅ የኢትዮጵያ መንግሥት ዝግጅቱን አጠናቅቋል። በዛሬው ዕለት ‹‹አረንጓዴ አሻራ›› በሚል መሪ ቃል የሚተከሉት 200 ሚሊዮን ችግኞች ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ ያላትን ተጋላጭነት ይቀንሳሉ ተብሎ ተስፋ ተጥሎባቸዋል፡፡

ኢትዮጵያ የተራቆተ መሬትዋን እ.አ.አ እስከ 2025 ድረስ በደን ለመሸፈን የያዘችውን ዕቅድ ይፋ ማድረጓ ይታወሳል። በአገሪቱ በአሁኑ ወቅት የደን መመናመን እየበዛ በመምጣቱ በየዓመቱ የችግኝ መርሃ ግብር እየተካሄደ ይገኛል፡፡ ከዚህ ውስጥ ደግሞ ዛሬ የሚካሄደው ‹‹አረንጓዴ አሻራ›› ችግኝ ተከላ አንዱ ነው፡፡ የአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የደን ልማት ዳይሬክተር ከአቶ ቢተው ሽባባው ጋር በደን ሀብቱና ችግኝ ተከላው ላይ ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

የደን ሀብቱና የመመናመኑ ምክንያቶች

ከስልሳ ዓመት በፊት የነበረው የአገሪቱ የደን ሽፋን 40 በመቶ እንደነበር ይታወሳል። በተለያዩ ምክንያቶች የደን ሀብቱ እየወደመ በመምጣት አሁን ያለበት ደረጃ 15 ነጥብ አምስት በመቶ ብቻ ሆኗል፡፡ ለዚህ የሚቀመጡ ምክንያቶች የመጀመሪያው ከህዝብ ቁጥር ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የህዝብ ቁጥሩ በየጊዜው እየጨመረ መጥቷል፡፡ በዚህም ፍላጎቶች እያደጉ ስለሚመጡ ለማገዶነትንና ለቤት መስሪያነት ደን ይጨፈጨፋሉ። ለሌሎች ግልጋሎቶችም የደን ውጤቶችን መጠቀም በየጊዜው እየጨመረ መጥቷል፡፡

በተጨማሪም የእርሻ መሬቶች መስፋፋት ለደን ሀብቱ መመናመን ተጠቃሽ ሆኗል። የህዝብ ቁጥር እየጨመረ ሲመጣ የመሬት ምርታማት እየቀነሰ ስለሚመጣ ወደ ደን መሬቶች በማተኮር ደኖች እየተጨፈጨፉ ይገኛሉ፡፡ በተለይ በቆላማ አካባቢ የደን መሬቶች ለእርሻ መሬት የዋሉበት ሁኔታ ይስተዋላል፡፡ በሌላ በኩል አማራጭ የሀይል ምንጮች አለመስፋፋት ለደን መውደም ዋነኛ ችግር ሲሆኑ፤ አብዛኛው የአገሪቱ ህዝብ በተለይ የገጠሪቱ ክፍል ነዋሪ ለማገዶነት የሚጠቀመው የእንጨት ውጤቶች ብቻ እንዲሆን አድርጓል። አማራጭ የሀይል ምንጭ ቢኖር ኖሮ በደን ላይ ያለው ጫና ይቀንስ ነበር፡፡

ሌላው ደግሞ ያልተጠና የህዝብ አሰፋፈር በደን ይዞታዎች ላይ የሚካሄድበት ሁኔታ እየበዛ መጥቷል። በጥናት ላይ የተመሰረተ አሰፋፈር ጥሩ ቢሆንም አልፎ አልፎ ደኖች ውስጥ እንዲሰፍሩ የሚደረግበት ሁኔታዎች ይከሰታሉ፡፡ ደኖች ውስጥ የሰፈሩት ሰዎች ደግሞ በደኖች ላይ ጉዳት እያደረሱ ናቸው፡፡ በተጨማሪም በቆላማ አካባቢዎች የሚታየው የሰደድ እሳት ደኖችን እያጠፋ ይገኛል፡፡

ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ እንስሳት ቁጥር ካላቸው አገራት ተርታ ትመደባለች። የእንስሳት ቁጥር ሲበዛ ደግሞ በሚተከሉ ችግኞች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ በማሳደር በደኖች ውስጥ የሚበቅሉ ችግኞችን የሚበሉበት ሁኔታ እንዲፈጠር አድርጓል፡፡ ልቅ ግጦሽ በከፍተኛ ሁኔታ በደን ሀብቱ ላይ ችግር እየፈጠረ ነው፡፡ የመሰረተ ልማት መስፋፋት በተለይ የመንገድ ግንባታ ሲከናወን ዛፎች እንዲቆረጡ ያደርጋል።

ከማዕድን ቁፋሮ ጋር በተገናኘ በአንዳንድ አካባቢዎች ወርቅ ለማውጣት የደን ሀብቶች እንዲቃጠሉ የማድረግ፣ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ የሚመጣው ተፈጥሯዊ ችግር እና ከመሬት አጠቃቀም ጋር የተያያዘ እቅድ አለመኖር ለደን መመናመን አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ በተጨማሪም የህብረተሰቡ የገቢ ምንጭ እያነሰ በሚሄድበት ጊዜ ወደ ደን ሀብቱ የመሄድ ሁኔታዎች ያሉ ሲሆን፤ በተለይ ደግሞ በመንግስት ደኖችና በማህበራት ደኖች ላይ የመሰማራትና የማውደም ነገር አለ፡፡ ከላይ በተዘረዘሩት ምክንያቶች የደን ሀብቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲመናመን አድርጓል፡፡

በየዓመቱ የሚተከሉ ችግኞች አስተዋፅኦ

በየዓመቱ በርካታ ችግኞች ይተከላሉ፡፡ የሚተከሉት ችግኞች ሁሉ ይፀደድቃሉ ማለት አይደለም፡፡ በየዓመቱ የችግኝ መፅደቅ መጠን ቢታይ ከ65 እስከ 70 በመቶ ብቻ ነው። ይሁን እንጂ የሚተከሉት ችግኞች ባይኖሩ አሁን ያለው የተፈጥሮ ደኖች አይኖሩም ነበር። የሰው ፍላጎት እየጨመረ በሄደ ቁጥር ሰው ሰራሽ ደኖች ባይስፋፉ ኖሮ የተፈጥሮ ደኖች ይጠፉ ነበር፡፡ አሁን ላለው የደን ሀብት ሰው ሰራሽ ደን አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው፡፡ ስለዚህ ችግኝ ተከላው ለተፈጥሮ ደን ሀብት መጎልበት አንዱ ግብዓት ነው፡፡ በየዓመቱ ባይተከል ኖሮ አሁን ካለበት እየቀነሰ ይመጣ ነበር፡፡ የችግኝ ተከላው የሚፈለገውን ያክል ባይሆንም ተከላው መካሄዱ ጥሩ ውጤት አለው፡፡ በተለይ በግለሰብ ደረጃ የሚተከለው ችግኝ መቀጠል አለበት። አብዛኛው ህብረተሰብ የሚጠቀመው የደን ውጤት ማገዶ በመሆኑ ለዚህ ደግሞ ህብረተሰቡ ምትክ እንዲተክል ካልተደረገ በተፈጥሮ ደኖች ላይ ጫና መፍጠሩ አይቀርም፡፡

‹‹የአረንጓዴ አሻራ›› ችግኝ ተከላ

በዚህ ዓመት አራት ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል እቅድ ተይዟል፡፡ አራት ቢሊዮን ችግኝ በአንድ ሚሊዮን ሄክታር ላይ የሚተከል ሲሆን ከሚተከለው ችግኝ ከ70 እስከ 75 በመቶ እንዲፀድቅ ቢደረግ ከፍተኛ የሆነ የደን ሽፋን እንዲጨምር ያደርጋል፡፡ የችግኝ ተከላው በደን ሀብቱ ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ አለው፡፡

የመፅደቅ መጠኑን ከፍ ለማድረግ ብዙ ስራዎች መከናወን አለበት፡፡ የመጀመሪያው ስራ ከተከላ በፊት የሚከናወን ሲሆን፤ ከመሬት ዝግጅት፣ ከችግኝ ዝግጅት፣ የተዘጋጀው ችግኝ ለመሬቱ ተስማሚነቱን መለየትና ችግኞቹ የሚጠበቁበትን መንገድ መፍጠር በተለይ ለተተከሉት ችግኞች ኃላፊነት የሚወስድ አካል መኖር አለበት፡፡ ችግኙ ተተክሎ ክትትል ካልተደረገበት ችግኙ እንደተጣለ የሚቆጠር ነው፡፡ ሌላው በተከላ ወቅት ባለሙያዎች በሚመክሩት መንገድ ተከላው መከናወን አለበት፡፡

ተከላው ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በባለሙያዎች ምክር ሲፈፀም ውጤታማ ይሆናል፡፡ ከተከላ በኋላ ጥበቃና ክትትሉ በተጠናከረ መንገድ መከናወን አለበት፡፡ ችግኙ የተተከለው እርጥበት ባለበት አካባቢ ካልሆነ በየጊዜው ውሃ የማጠጣት፣ ማዳበሪያ መጨመር፣ መሬቱ በጣም የደረቀ ከሆነ ደግሞ በተደጋጋሚ ማዳበሪያዎችን መጠቀም ያስፈልጋል፡፡

ይህንን ለማድረግ ደግሞ ህብረተሰቡ በነቃ ሁኔታ መሳተፍ ይጠበቅበታል፡፡ ችግኙን የተከሉት አካላት ለማፅደቅ ርብርብ ማድረግ አለባቸው፡፡ ለመተከል ያልደረሱ ችግኞችን መትከል አስፈላጊ አይደለም፡፡ በቀጣይ ዓመት በሚደረጉ የችግኝ ተከላዎች ካሁኑ ቅድመ ዝግጅቶች መደረግ አለባቸው፡፡ በተለይ አገር በቀል ዝርያዎች ችግኝ ጣቢያ ላይ ረጅም ጊዜ ስለሚቆዩ ከወዲሁ ዝግጅት ማድረግ ይጠይቃል። የአገር በቀል ዝርያዎችን ለመጠቀም ከአሁኑ ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

‹‹የአረንጓዴ አሻራ›› ችግኝ ተከላ ብሄራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ በሰጠው መረጃ፤ ለክረምት ችግኝ ተከላ ዘመቻው ከአራት ነጥብ ሰባት ቢሊየን በላይ ችግኞች ተዘጋጅተዋል። በኦሮሚያ አንድ ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን፣ በአማራ አንድ ነጥብ ሶስት ቢሊዮንና በደቡብ አንድ ነጥብ አራት ቢሊየን ችግኞች ተዘጋጅተዋል። እስካሁንም አንድ ነጥብ ሶስት ቢሊየን ችግኞች የተተከሉ ሲሆን ከነዚህም መካከል በአማራ 280 ሚሊየን፣ በደቡብ 641 ሚሊየን፣ በኦሮሚያ 470 ሚሊየን ችግኞች እንዲተከሉ ተደርጓል፡፡

በተከላው ዕለት በገጠርም ሆነ በከተማ ሁሉም ዜጋ በነቂስ ወጥቶ የሚሳተፍበት ብቻ ሳይሆን የውጭ አገር ዜጎችም በችግኝ ተከላው ተሳታፊ እንደሚሆኑ መረጃው ያመለክታል የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ የመንግስት ኃላፊዎችና የሃይማኖት መሪዎች በተለያዩ ቦታዎች ላይ ችግኝ ይተክላሉ፡፡

አዲስ ዘመን  ሐምሌ 22/2011

መርድ ክፍሉ