ሁሉን አቀፍ ትምህርትና ስልጠና-በሰላም መንደር

14

የትምህርትና ስልጠና ጉዳይ፣ በየትኛውም ደረጃ ይሁን እርከን፣ ከዚህ በመለስ የሚባል አይደለም። ከተሳታፊና ተጠቃሚነት አኳያም የእነ እከሌ ነው/አይደለም ብሎ ነገር አይሰራም። ሁሉም ሰው፤ ሁሉም ዜጋ እኩል ተጠቃሚ ነው። ይህን መሰረታዊ ጥቅም ከሚያስፋፉት አካላት መካከል ደግሞ መንግስታዊ ያልሆኑና ለትርፍ ያልተቋቋሙ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ተጠቃሽ ሲሆኑ፤ ከመንግስት ያልተናነሰ ድርሻን ሲጫወቱም ይስተዋላል። ከነዚህ መካከል ደግሞ “ሰላም የህፃናት መንደር” አንዱ ነው።

ከ32 አመት በፊት በአንዲት ኢትዮጵያዊት ግለሰብ የተመሰረተው “ሰላም የህፃናት መንደር”፤ ዛሬ ላይ ይዞት ከተነሳው ወላጅ አልባ ህፃናትን የመታደግ ሰብአዊ ተግባር ገዝፎና ሰፍቶ የከፍተኛ ትምህርት ምሩቃንን ወደማፍራት ተሸጋግሯል። በዚህም አገሪቱ ለምታደርገው የኢኮኖሚ ሽግግር ስራ ውስጥ የበኩሉን እገዛ እያደረገና ከፍተኛ ድርሻ እያበረከተ ይገኛል።

እአአ ጃንዋሪ 16/1986 በወይዘሮ ፀሀይ ሮሽሊ መሰረቱ የተጣለው የሰለም መንደር፤ ከሚሰጣቸው መደበኛና የማታ ትምህርት ፕሮግራሞች፤ አጫጭር ስልጠናዎች ባለፈ እርዳታው ለሚያስፈልጋቸው የምገባ ፕሮግራም፣ የመጠለያ ግንባታ፣ የአልባሳት አቅርቦት፣ የትምህርትና የጤና አገልግሎቶችን ለዜጎች በመስጠት ላይ ይገኛል።

ለዚህም የተለያዩ ለጋሽ አገራትን፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችንና ተባባሪዎችን ከጎኑ ማሰለፍና አጋዥ ማድረግ ችሏል። አቅሙንና ተደራሽነቱን በማስፋፋትም ዛሬ በተቋሙ ውስጥ ሌሎች በርካታ ተቋማትን ፈጥሯል። ከእነዚህ መካከል አንዱና በ1989 ዓ.ም የተቋቋመው “ሰላም ዲቪድ ሮሽሊ ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጅ” ደግሞ መንደሩ ስለደረሰበት ከፍታ ማሳያ ነው።

ይህ ኮሌጅ ባለፈው ቅዳሜ (ሀምሌ 12 ቀን 2011 ዓ.ም) ለ25ኛ ጊዜ በተለያዩ የሙያና ቴክኒክ የጥናት ዘርፎች፤ በቀንና በማታው መርሀ ግብር ያሰለጠናቸውን 1ሺ 258 ተማሪዎች አስመርቋል። ከተመራቂዎች ውስጥም 601 ያህሉ ሴቶች መሆናቸውን እና በዚህም አገሪቱ የምትፈልገውን ብቁና የሰለጠነ የሰው ሀይል በማፍራት ላይ መሆኑም ተነግሯል።

በምረቃ ስነ-ሥርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የፌደራል ቴክኒክና ሙያ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ነጋሽ እንደተናገሩት፤ በኢትዮጵያ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና መስፋፋት የምርጫ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የችግሮች መፍቻ አብይ ቁልፍ (ማስተር ኪይ) ነው። በመሆኑም በሰላም የህፃናት መንደር “የሰላም ዲቪድ ሮሽሊ ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጅ” በዚህ ዘርፍ ባለሙያዎችን ማፍራቱ የሚያስመሰግነው ሲሆን፤ ሌሎችም የዚህን ተቋም አርአያነት ሊከተሉና ኢትዮጵያ እያደረገች ላለው ፈጥኖ የማደግ እንቅስቃሴ የራሳቸውን አስተዋፅኦ ሊያበረክቱ ይገባል።

ከአዲስ ዘመን ጋር ቆይታ ያደረጉት የኮሌጁ ምክትል ዲን አቶ ጥበቡ ለታ እንደሚሉት፤ ኮሌጁ 70 በመቶ ተግባር ተኮር፤ 30 በመቶ ንድፈ ሀሳብ ላይ የተመሰረተ ስልጠናን ስለሚሰጥ በሰለጠኑበት ሙያ ብቃት እና በገበያ ላይ ሰፊ ተፈላጊነት ያላቸውን ባለሙያዎች ማፍራት ተችሏል። ከ95 በመቶ በላይ የሚሆኑት ተመራቂዎች ብቃታቸውን በተቋሙ ውስጥ እና በአገር አቀፍ የሙያ ብቃትና ምዘና ማረጋገጫ ማእከል በኩል በየደረጃው ተመዝነው ብቁ ሆነዋል፤ በተባባሪ ድርጅቶች ውስጥ የተግባር ልምምድ በማድረግ ልምዳቸውን አዳብረዋል። እነዚህም በስነ-ምግባራቸው የተመሰገኑ ሙያተኞች ናቸው።

ከአገር ውስጥና አለም አቀፍ ግብረ-ሰናይ ተቋማት ጋር በመተባበርና መደጋገፍ እየሰራ የሚገኘው ሰላም የህፃናት መንደር፤ ስደትን በመከላከል፣ እናቶችና ህፃናትን በመታደግ፣ ዘርፈ ብዙ የስራ እድሎችን በመፍጠር፤ እና መሰል ተግባራት በኩል የድርሻውን እየተወጣ ይገኛል። ከወርድ ኤን ዳድ / Woord en Daad/ ጋርም የሚሰራው “ኢምፕሎዬብል ዩዝ ኢን ኢትዮጵያ” (EYE) ፕሮግራም በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ነው።

የወርድ ኤንድ ዳድ ሲኒየር ፕሮግራም ማናጀር አቶ ኤፍሬም ሺፈራው እንደሚሉት ደግሞ፤ የ“ኢምፕሎዬብል ዩዝ

ኢን ኢትዮጵያ”ን ፕሮግራም የወጣቶችን የትምህርት፣ የስራ እድልና ፈጠራን በማበረታታትና በማመቻቸት ወጣቶችን ለስደት በሚያጋልጡ ምክንያቶች ላይ ልዩ ትኩረት በማድረግ ስደትን እንደ አማራጭ ሳይቆጥሩ አገራቸው ላይ ያሉ አማራጮችን በመፈተሽ እና ምቹ የስራ እድል በመፍጠር የነገይቱን ኢትዮጵያ እና የወጣቶቹን ተስፋ በአገር ውስጥ ለመገንባት የሚሰራ ነው። በዚሁ መሰረትም በአዲስ አበባ የተመረጡ የአካባቢው ክፍለ-ከተሞች ተግባራዊ ተደርጎ ውጤት ማምጣት ተችሏል።

እንደ አቶ ጥበቡ ገለፃ፤ ሰላም የቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ከመደበኛው እና ከማታው መርሀ ግብር ጎን ለጎን መቀመጫውን ስዊዘርላንድ ካደረገው ወርድ ኤን ዳድ አለም አቀፍ ግብረ-ሰናይ ድርጅት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በየካና ቦሌ ክፍለ ከተሞች ስራ የሌላቸውንና ለህገ ወጥ ስደት ተጋላጭ የሆኑ ወጣቶችን በመመልመል ገበያ ተኮር እና በፍጥነት የስራ እድል ሊፈጥሩ በሚችሉ ሙያች ስልጠና በመስጠት በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች በሀገራቸው ሰርተው የተሻለ ኑሮ መኖር እንዲችሉ የራሱን ድርሻ በማበርከት ላይ ይገኛል። በአዲስ አበባ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን በሌሎች ክልሎችም እየተስፋፋና ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል።

አቶ ኤፍሬም እንደሚሉት፤ ፕሮግራሙ በቦረና፣ በሀዋሳ፣ በአርባ ምንጭ፣ በወላይታ እና በአዲስ አበባ ልዩ ትኩረት በማድረግ ሙሉ ደቡባዊ ኢትጵያን የሚሸፍን ነው። ይህ 80 በመቶ ወጪው በኔዘርላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚሸፈነው ፕሮግራም ሰላም የህፃናት መንደርን ጨምሮ በሶስት አለም አቀፍ እና በሰባት አገር በቀል ድርጅቶች አማካኝነት የሚተገበር የአምስት አመት ፕሮግራም ነው። ለ27ሺህ ለስደት ተጋላጭ ለሆኑ ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር ታሰቦ የተቀረፀም ነው።

እንደ አቶ ጥበቡ ደግሞ፤ ሰላም የህፃናት መንደር ከመደበኛ ስልጠናዎች በተጨማሪ በአጫጭር የስልጠና መስኮች 10ኛ ክፍልን ላላለፉና የኮሌጅ መግቢያ መመዘኛ ነጥብን ማግኘት ላልቻሉ ወጣቶች የስልጠና እድል እያመቻቸ ሲሆን፤ ለስድስት ወራት በሚሰጥ አጫጭር ስልጠናም ለወጣቶች የስራ እድል መፍጠርና ህገ-ወጥ ስደትን መቀነስ በሚቻልበት ላይ እየሰራ ይገኛል።

ኮሌጁ የራሱ የሆነ የጥናትና ምርምር ማእከል ያለው ሲሆን የአገሪቱን ወቅታዊና ተጨባጭ እውነታዎችን በመፈተሽ፣ በማጥናትና መፍትሄን በማስቀምጥ ወደ ተግባር እየለወጠ መሆኑም ተነግሯል። ለዚህም “በህዝባችን ላይ የተጋረጠውን የህይወትና የንብረት ውድመትን ከመቅረፍ ባሻገር ለወጣቶች የስልጠናና የስራ እድል የሚፈጥር ነው” በማለት ከስዊድን አለም አቀፍ የልማት ድርጅትና ከቮልቮ ግሩፕ ጋር በመተባበር ተቋቁሞ በቅርቡ ስልጠና መስጠት የሚጀምረው፤ በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነው የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ አካዳሚ አንዱ ማሳያ ተደርጎ ይጠቀሳል።

በአሁኑ ሰአት የሰላም ህፃናት መንደር የልማት ስራዎችን ከመንግስት ፖሊሲና አቅጣጫ ጋር በማጣጣም ለመስራት በሽግግር ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ ሽግግሩን ለማሳለጥ የአምስት አመት ስትራተጂክ እቅድ ማዘጋጀቱን የኮሌጁ ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ይናገራሉ። ተቋሙ ስዊዘርላንድ ከሚገኙ የሰላም ስዊዝ ቻሪቲ ረጂዎች፣ ከጀርመን ቻሪቲ፣ ሲዳ፣ ዩኒዶ፣ ቮልቮ፣ ውርድ ኤን ዳድ፤ ሴቭ ዘ ችልድረን፤ እንዲሁም አገር ውስጥ ካሉ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በመተባበርና በመተጋገዝ በርካታ ስራዎችን በመስራት ላይ እንደሚገኝ ይገልጻሉ።

የሴቶችና ወጣቶችን ኑሮ ማሻሻል፣ መደራጀት የሚፈልጉትን ማደራጀት፣ ካፒታል ለሌላቸው ካፒታል ማፈላለግ፣ ብድርና ቁጠባ አገልግሎት እና ሌሎች ተግባራትንም በምሳሌነት ይጠቅሳሉ።

“ሰላም የህፃናት መንደር” ጎልተው ከሚጠቀሱለት ተግባራት መካከል የእናቶችና ህፃናት እንክብካቤ ስራው ነው። የመንደሩ የሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ዘርፍ ሀላፊ ወይዘሮ ብስራት ቸርነት እንሚሉት፤ በአካባቢው ያሉ ስራ እና ህፃን ልጅ ያላቸው እናቶች ጠዋት ወደ ስራ ሲሄዱ ልጆቻቸውን በሰላም ህፃናት መንደር በተዘጋጀው የህፃናት ማቆያ (Day Care) ክፍል ውስጥ አስቀምጠው ይሄዳሉ፤ ለህፃናቱ አስፈላጊው እንክብካቤ ሁሉ ሲደረግላቸው ይውላል፤ ማታ ከስራ ሲመለሱ ልጆቻቸውን ይዘው ወደ ቤታቸው ይሄዳሉ።

አዲስ ዘመን  ሐምሌ 22/2011

 ግርማ መንግሥቴ