ተግባራዊ እንክብካቤ ለችግኞች ልምላሜ

13


በኦሮሚያ ልዩ ዞን አቃቂ ወረዳ ወደ ቢል ቢሎ ቀበሌ የሚወስደው ጥርጊያ መንገድ ቀይ አሸዋ ፈሶበታል።መንገዱ ነባር ቢሆንም በቅርቡ መጠነኛ ማስተካከያ እንደተደረገበት ያስታውቃል።በመንገዱ ላይ ብዛት ያላቸው አውቶብሶችና አነስተኛ ተሸከርካሪዎች በሰልፍ ቆመዋል።ተሽከርካሪዎቹ መንገዱን ይዘው ቢል ቢሎ ተራራ ጋር ሲደርሱ ተሳፋሪዎቻቸውን ማውረድ ጀመሩ።

ከተሽከርካሪዎቹ የወረደው ለቁጥር የሚታክት ህዝብ በእጆቹ ችግኞችን በመያዝ ወደ ቢልቢሎ ተራራ ይተማል።ከፊት ለፊት ጎልቶ የሚታየው የቢልቢሎ ተራራ አልፎ አልፎ ከሚታዩ ቁጥቋጦዎችና ግቻ ሳር በስተቀር በላዩ ላይ አንድም የእፅዋት ዝርያ አይታይበትም።ከተራራው ሥር የሚታየውና አረንጓዴ ምንጣፍ የመሰለው የስንዴ ማሳ በተራራው መራቆት የሚያሾፍ ይመስላል።

ከግብርና ሚኒስቴር፣ ቤቶችና ከተማ ልማት ሚኒስቴር እና ከብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን የተወጣጡ ሠራተኞች ወደተራራው በመውጣት ችግኞችን ለመትከል ያላቸው ወኔና የሞራል ተነሳሽነት በእጅጉ ያስደንቃል።የቢልቢሎ ተራራ በተጠጉት ቁጥር እስቲ ድረሱብኝ እያለ ወደኋላ በመሸሽ ተስፋ ለማስቆረጥ ይሞክራል።ተራራው ከሩቅ ሲታይ በቀላሉ ከጫፉ ላይ የሚወጣበት ቢመስልም በቀረቡት ልክ ግን ይበልጥ ፈታኝና ለጉዞ አስቸጋሪ ይሆናል።

አቶ ፀጋዬ ጫላ በግብርና ምርምር ኢንስቲ ትዩት የሕግ ባለሞያ ሲሆኑ በችግኝ ተከላ መርሐግብሩ ከተሳተፉ ሰዎች መካከል አንዱ ናቸው።የዘንድሮው የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር በህዝቡ ሙሉ ተነሳሽነትና ፍላጎት እየተከናወነ በመሆኑ የተለየ እንደሚያደርገው ይናገራሉ።

በተራቆቱና አስቸጋሪ በሆኑ ቦታዎች ላይ ችግኞችን መትከል ከዚህ በፊት ያልተለመደና ህዝቡ ችግኞችን በየትኛዎቹም አካባቢዎች ላይ ለመትከል ያለውን ዝግጁነት እንደሚያሳይም ይገልፃሉ።የችግኝ አተካከል ሁኔታውም ጥንቃቄ የተሞላበትና ሥርዓቱን የጠበቀ እንደሆነ ያስረዳሉ።

እንደ አቶ ፀጋዬ ገለፃ፤ ችግኞችን ለመትከል ህዝቡ ያሳየው ተነሳሽነት የሚደነቅ በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።ከዚህ በኋላም በዘላቂነት የችግኝ ተከላ መርሐ ግብሮችን ማካሄድ ያስፈልጋል።ከሁሉም በላይ ደግሞ ችግኞች እንዲፀድቁ ቃል ከመግባት በዘለለ በአካል በመገኘት ተግባራዊ እንክብካቤ ማድረግ ይጠበቃል።

ሁሉም ሰው የተከለውን ችግኝ በየጊዜው እየመጣ ክትትል የማድረግ ሃላፊነት ይጠበቅበታል የሚሉት አቶ ፀጋዬ፤ ይህ የማይሆን ከሆነ ችግኞቹ በተተከሉባቸው አካባዎች ላይ ያሉ ወጣቶችን በማደራጀትና አስፈላጊውን ሁኔታ በማሟላት ክትትል መደረግ ይኖርበታል ይላሉ።በዘንድሮው የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ለችግኞቹ መተከያ የተዘጋጁ ጉድጓዶች ከተሳታፊው ቁጥር ያነሱ በመሆመናቸውም በቀጣይ ይህ ሊስተካከል ይገ ባል ብለዋል።

በግብርና ሚኒስቴር ጠቅላላ አገልግሎት ዘርፍ ባለሙያ ወይዘሮ ሰናይት በሪሁ በችግኝ ተከላ መርሐ ግበሮች በየጊዜው ይሳተፉ እንደበር ያስታውሳሉ።የዘንድሮው የችግኝ መርሐ ግብርም በነቂስ እየተካሄደ በመሆኑ ጠቀሜታው ከራስ አልፎ ለሚቀጥለውም ትውልድ የሚጠቅም መሆኑን ይገልፃሉ።በተለይም ችግኞችን ከተከሉ በኋላ በየጊዜው ተግባራዊ ክትትል የሚደረግ ከሆነ ጠቀሜታው ከዚህም በላይ የጎላ እንደሚሆን ያስረዳሉ።

የዘንድሮው የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ሁሉ ንም የህብረተሰበ ክፍል በስፋት ያሳተፈ፣ በአግባቡ የተከናወነና በቀጣይም እንክብካቤ ለማድረግ ሃላፊነት የተወሰደበት መሆኑን በመጥቀስም ከበፊቱ እንደሚለይም ወይዘሮ ሰናይት ይናገራሉ።

ችግኞች ከተተከሉ በኋላ እንክብካቤ ስለማ ይደረግላቸው ብዙዎቹ ስለማይፀድቁ በርብርብ ከመትከል በዘለለ ችግኞችን መንከባከብ የሁሉም ሃላፊነት ሊሆን እንደሚገባም ያሳስባሉ።በዋናነትም ችግኞች በተቋም ደረጃ የተተከሉ እንደመሆናቸው መጠን እያንዳንዱ ተቋም በሃላፊነት ችግኞችን መንከባከብ እንደሚጠበቅበትም ያስገነዝባሉ።

ይህም ካልተቻለ ተቋማት አስፈላጊውን ወጪ በመመደብ የአካባቢው ነዋሪዎች ችግኞችን እንዲ ንከባከቡ የማድረግ ሃላፊነት አለባቸውም ይላሉ።

በብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን የሰው ሀብት ዳይሬክተሩ አቶ ተስፋ እንዳለው በበኩላቸው እንደሚገልፁት፤ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ የትውልድ ቅርስና አሁን ላለው ትውልድም የተፈጥሮ እርካታን የሚሰጥ በመሆኑ ጥቅሙ ዘርፈ ብዙ ነው።

የችግኝ ተከላው በሚገባ ታቅዶበት እየተከ ናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤በተለይም በሀገር አቀፍ ደረጃ ምን ያህል ችግኞች እንደሚተከሉና በየትኞቹ አካባቢዎች እንደሚተከሉ ቅንጅታዊ ሥራ የተሠራበት መሆኑን ይጠቅሳሉ።ይህም የበለጠ ልዩ ያደርገዋል ይላሉ።

‹‹ችግኞችን መትከል አንድ ነገር ሆኖ ሳለ ከሁሉ ባላይ ትኩረት መደረግ ያለበት በችግኝ እንክብካቤ ላይ ነው›› የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ በመንግሥት በኩል መርሐ ግብር ተይዞለት እንክብካቤው ሊደረግ ይገባል።ከዚህ ባለፈም እያንዳንዱ ዜጋ ችግኞቹ እንዲፀድቁ መንከባከብ ይጠበቅበታል።በተለይም የአካባቢው ማህበረሰብ ችግኞቹ እስኪፀድቁ ድረስ ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ ነፃ ማድረግ ይኖርበታል ብለዋል።

ችግኝ መትከል ብቻውን ግብዓት ስለማይ ሆንም ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ በችግኝ ተከላ መርሐ ግብር እንደተሳተፈ ሁሉ በእንከብካቤውም በተ ግባር መሳተፍ ይጠበቅበታል ሲሉ ያስገነዝባሉ።


አዲስ ዘመን ሀምሌ 23/2011


አስናቀ ፀጋዬ