በችግኝ ተከላ የሰበርነውን ሪከርድ የሀገራችንን ሰላም በማስከበር እንድገመው!

24

ኢትዮያውያን በአንድነት ከተነሳን ምንም የሚያዳግተን ነገር አለመኖሩን ከዚህ ቀደምም የሀገርን ሉአላዊነት ለማስጠበቅ በአንድነት እንደተነሳነው ሁሉ ዘንድሮም ለአረንጓዴ ልማት በአንድነት በመነሳት ታሪክ መሥራት ችለናል። ታሪክ መሥራት እንደምንችልም ዳግም ለዓለም ህዝቦች አሳይተናል። ያሳለፍነው ሳምንት ኢትዮጵያውያን በዓለም መገናኛ ብዙሃን የተደነቅንበት፤ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ከሚያውቁን በተለየ መልኩ ስማችንን በአረንጓዴ ልማት ከፍ አድርገው ያነሱበት ጊዜ ነበር።

ዓለምን ብሎም ሀገራችንን እያሳሰበና እያስጨነቀ የመጣውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመቋቋም አንዱና ዋነኛው አማራጭ አረንጓዴ ልማት መሆኑን በመገንዘብ መንግሥት በያዘው ዕቅድና ጠንካራ እንቅስቃሴ ህብረተሰቡ የሃይማኖት፣ የብሔር እና የፖለቲካ ሌሎች ልዩነት ሳይበግሩት አረንጓዴ አሻራውን አሳርፏል፡፡ እንደ ሀገር አንድ በሚያደርጉን ጉዳይ ላይ በጋራ በመዝመትም ለሀገራዊ ጥሪው በሰጠነው ምላሽ በአንድ ቀን ከ353 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል ተችሏል። ይህም በህንድ ተይዞ የነበረውን በአንድ ቀን የተተከለውን 66 ሚሊዮን ችግኝ ተከላ ሪከርድ መስበር አስችሎናል።

ይሄ የሚያሳየው ኢትዮጵያውያን ቆርጠን ከተነሳን ምንም የሚያዳግተንና የሚያደናቅፈን ነገር አለመኖሩን ነው። ካለፉት ሦስት አስር ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ለልማት ስንነሳና የአንድነታችን መገለጫ የሆኑ ታሪኮችን ስንሠራ ይሄ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። የመጀመሪያው ኢትዮጵያውያን ካለ ልዩነት አንድ ሆነን የተንቀሳቀስነው ለታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ነው። የኢኮኖሚ አቅም ያለው የሌለው፣ ወንድ ሴት፤ የተማረ ያልተማረ፤ ህፃን አዋቂ፣ ሠራተኛ ገበሬ፣ … ሳንል ቦንድ ገዝተን፣ የገንዘብና የሞራል ድጋፍ አድርገን ለሀገራዊ ልማቱ አንድነት ጉልበት መሆኑን አሳይተናል። የታሪክ አሻራችንን አሳርፈናል። ይሄ መቼም ቢሆን የማይረሳ የዚህ ዘመን ትውልድ ታሪክ እና መኩሪያ፣ እያንዳንዳችንም በስማችን ሀውልት የተከልንበት ነው። ይሄ ተነሳሽነታችን አሁንም ተጠናክሮ የህዳሴው ግድብ ዳር ደርሶ ውጤቱን እስክናጣጥም ድረስ ልንቀጥልበት ይገባል።

ሁለተኛው ኢትዮጵያውያን የማንነጣጠል በአንድ ገመድ የተጋመድን ህዝቦች መሆናችንን ለዓለም ህዝቦች ያሳየንበት ወቅት ደግሞ አሁን ነው። በአንድ ክረምት ብቻ አራት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ዕቅድ ከወረደበት ጊዜ ጀምሮ ሁሉም በየአካባቢው፣ በየመሥሪያ ቤቱ፣ በየክልሉ እና በሌሎችም ቦታዎች ሦስት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ችግኞችን መትከል ተችሏል። ከዚህም መካከል ሐምሌ 22 በአንድ ጀምበር ሁለት መቶ ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ሲታሰብ ያለ ልዩነት በነቂስ በመውጣት ከዕቅድ በላይ 353 ነጥብ 6 ሚሊዮን ችግኞች በመትከል ዳግም የአንድነት ታሪክ መሥራት እንደምንችል ያሳየንበት ነበር። ይሄ በጣም የሚያስደስት ለዓለምም የሚያስደንቅና ኢትዮጵያውያን ምንም የሚያግዳቸው ነገር እንደማይኖር ማሳያና ምስክር ነው።

ይሁን እንጂ አሁንም በተሠራው ሥራ መኩራራት ብቻ ሳይሆን የጎደለውን የምናይበት፤ ልዩነቶቻችንን የምናጠብበት፣ ለሀገራዊ አንድነት ተጠናክረን ለመሥራት የምንነሳበት መሆን አለበት። ምክንያቱም ምንም ነገር መሥራትና ማልማት ብንችል በሠራነውና ባለማነው መጠቀምና መደሰት፣ ለትውልድ ማቆየት የምንችለው አሁንም አንድነታችን ሳይነጣጠል መቀጠል ስንችል ብቻ ነው። ለዚህ ደግሞ ቀድሞ የሚመጣው የሠላም ጉዳይ ነው። ለማንም ሰው እንደሰው ለመኖር ሠላም ያስፈልጋል። ሠላም ከምንም በላይ ወሳኝ ነው ። ስለዚህ “ይሄ የእኛ ነው” ከዚህ ውጣ ከዚያ ከሚል የተሳሳተ አስተሳሰብ ወጥተን በአንድነት የምንኖርባትን ሀገር እና ክልሎች በጋራ በማልማት በሠላም መኖር ይገባል። በሠላም ለመኖር፣ ወጥቶ ለመግባት፣ ሠርቶ ለመብላት፣ ተረጋግቶ ህይወትን ለመምራት ዋናውና ትልቁ የሠላም ጉዳይ ነውና በሁሉም አካባቢ ሠላምን ለማስከበር ሁሉም መሥራት አለበት። ሁላችንም ለሠላም እኩል ከሠራን እንደ ችግኝ ተከላው ሁሉ ከአቀድነውም በላይ በመሥራት የሠላም ሪከርድ እንሠብራለን። የሀገራቸውንና የህዝባቸውን ሠላም ያረጋገጡ ተብለን ለዓለም የሠላም ምሣሌዎች መሆን እንችላለን። ይሄ የሚሆነው ሁላችንም ለሠላም ስንሠራ፣ ዜጎችን ከማፈናቀል ወጥተን ማቀፍ ስንችል ነው። የእኔ ከሚል ጎደሎ አስተሳሰብ ወጥተን የሁላችን የሚለውን ከፍ ማድረግ ስንችል ነው።

ሠላምን የምናስከብረው በሠላም አስከባሪ ሃይል ብቻ አይደለም። ሠላም የሚከበረው በእያንዳንዳችን ነው። እያንዳንዳችን ለሠላም ከሠራን፣ የሸፍጥ ፖለቲካን ካቆምንና ከ‹‹እኔነት›› አስተሳሰብ መውጣት ከቻልን የሀገራችን ሠላም ካለማንም የፀጥታ አስከባሪ ሃይል እናስከብራለን። ሠላማችንን ስናረጋግጥ እና የተሻለ ነገር መሥራት ስንችል ደግሞ ያሰብንበት ያደጉት አገራት ተርታ እንሰለፋለን። ለዚህ ሁሉ ውጤት ግን ወሳኙ እያንዳንዳችን መሆናችን መዘንጋት አይኖርበትም። በአረንጓዴው አሻራ ቀን በአንድ ጀምበር ከ353 ነጥብ 6 ሚሊዮን ችግኝ በላይ በመትከል የዓለምን ክብረወሰን እንደሰበርነው ሁሉ የሀገራችንን ሠላም በማስከበር የሠላም ባለሪከርዶች ለመሆን ከምንጊዜውም በላይ ልንሠራ ይገባል!

አዲስ ዘመን ሐምሌ 28/2011