የከተማ አስተዳደሩ በጎ ስራዎች በሁሉም ዘርፍ ይጠናከሩ

19

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማዋ የሚገኙ ዘርፈ ብዙ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ ይገኛል። ከነዚህ ውስጥ አንዱ በትምህርት ዘርፉ ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት እያከናወናቸው የሚገኙ ስራዎች ተጠቃሽ ናቸው።

አስተዳደሩ በ2012 የትምህርት ዘመን ከ600 ሺህ ለሚበልጡ የመንግስት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ዩኒፎርምና የተለያዩ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ለማድረግ እየሰራ ይገኛል። ከዚህም ጎን ለጎን የመማር ማስተማሩን ሂደት ስኬታማ ለማድረግ የትምህርት ቤቶች እድሳት እያከናወነ ሲሆን፣ የተማሪዎች የምገባ ስራንም በተጠናከረ መልኩ ለማከናወን እየሰራ ይገኛል። ይህ ተግባር ደግሞ በከተማዋ አቅም ለሌላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ትልቅ ድጋፍ ሲሆን አጠቃላይ የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትንም ለማሳካት የሚኖረው አስተዋፅኦ የላቀ ነው።

እንደሚታወቀው በከተማዋ ከድህነት ወለል በታች የሚገኙ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች ይገኛሉ። እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ደግሞ ልጆቻቸውን በስርዓቱ ለማስተማር በቂ አቅም የላቸውም። በአንጻሩ በዚህ ችግር ውስጥ የሚገኙ ተማሪዎችም ወደ ትምህርት ቤት ሲሄዱ ትምህርታቸውን በስርዓት ለመከታተል የተለያዩ ተግዳሮቶች ያጋጥማቸዋል። ይህ ደግሞ በትምህርታቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ይፈጥራል።

በተለይ አሁን ባለው ሁኔታ የትምህርት ቁሳቁስ ዋጋ መናር ለወላጆች ትልቅ ፈተና ሲሆን ለተማሪዎችም ከትምህርት ገበታ ላይ መቅረት አንዱ ምክንያት እየሆነ ይገኛል። በሌላ በኩል በየአመቱ ለልጆቻቸው ዩኒፎርም ማሰፋት የሚያቅታቸውና በዚህም የተነሳ ከትምህርት ገበታ ላይ የሚስተጓጉሉ ወይም ጥራት ያለው ዩኒፎርም በማጣት በበታችነት ስሜት ወደ ትምህርት ቤት የሚሄዱ ተማሪዎች ቁጥር ቀላል አይደለም።

በተለያዩ የትምህርት ደረጃዎችና ትምህርት ቤቶች በነበረው የዩኒፎርም ቀለምና ጥራት መለያየት የተነሳም በትምህርት ቤቶች መካከል ትልቅ ልዩነት የሚንፀባረቅበት ሁኔታ እንደነበር የሚታወቅ ነው። ይህ ደግሞ በተማሪዎች መካከል ልዩነትን ከመፍጠሩም ባሻገር ተማሪዎችን በቀላሉ ለመከታተልና ለመቆጣጠርም አላስቻለም።

በከተማዋ በድህነት ምክንያት የምግብ እጥረት የሚያጋጥማቸው ተማሪዎች ቁጥርም ቀላል አይደለም። ባዶ ሆዳቸውን ወደትምህርት ቤት የሚሄዱና ትምህርታቸውን በአግባቡ መከታተል ያቃታቸው ተማሪዎች ከመኖራቸውም ባሻገር በትምህርት ላይ እያሉ ራሳቸውን ስተው የሚወድቁ ተማሪዎችም እንደነበሩ ይታወሳል። ይህ ደግሞ ትምህርትን ለመከታተል ቀርቶ ትምህርት ቤት ውሎ ለመግባትም የሚያስችል አይደለም።

ከዚህም በተጨማሪ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ትምህርት የሚሰጡባቸው ቁሳቁስ ለትምህርት አሰጣጡ ምቹ ካለመሆናቸውም ባሻገር ለእይታም ማራኪ አልነበሩም። ለምሳሌ አብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች የሚያስምሩባቸው ጥቁር ሰሌዳዎች የተቀዳዱና የወላለቁ ናቸው። ወንበሮቻቸውም ቢሆኑ ለመቀመጥ ምቹ አይደሉም። ህንጻቹም ለተለያዩ ችግሮች የተጋለጡ ሲሆን የመምህራን ማረፊያና የተማሪዎች መመገቢያ ስፍራም ምቹ አልነበሩም። አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ደግሞ መማርያ ክፍሎቻቸው አቧራ በመሆኑና ሲሚንቶውም የተቆፋፈረ በመሆኑ ለተማሪዎችና ለመምህራን ጭምር የበሽታ ምንጭ ነው።

በአጠቃላይ በነዚህና መሰል ችግሮች የተነሳ በከተማዋ ከትምህርት ጋር የተያያዙ ዘርፈ ብዙ ችግሮች መኖራቸው ይታወቃል። እነዚህን ችግሮች ለመፍታትም የከተማ አስተዳደሩ ቁርጠኛ አቋም ይዞ እየሰራ ይገኛል። በዚህም መሰረት በቀጣዩ የትምህርት ዘመን እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የጀመራቸው ስራዎች ለሌሎች ክልሎችና ድርጅቶች አርአያ የሚሆን ነው።

በተለይ በትምህርት ዘርፉ ላይ የሚሰሩ ስራዎች የትምህርት ጥራትን ለማሻሻልና በሂደትም አገር ገንቢ ትውልድ ለማፍራት የሚደረገውን ራዕይ የሚያግዝ በመሆኑ የአስተዳደሩ ተግባር በእጅጉ ሊመሰገን የሚገባው ነው።

ከዚህም ባሻገር ተግባሩ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ያሉት ነው። ከነዚህም ውስጥ አንዱና ዋነኛው የከተማዋን ነዋሪዎች ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መፍታት ሲሆን ተማሪዎች ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉና መምህራንም ተገቢውን ትምህርት እንዲሰጡ ትልቅ የሞራል መነሳሳትን ይፈጥራል። አስተዳደሩ ይህንን ችግር ለመፍታት የወሰደው ጠንካራ አቋም የሚበረታታ በመሆኑ ቁርጠኝነቱም በሁሉም ዘርፎች ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።

አዲስ ዘመን ሀምሌ 29/2011