“የኦሮሞን ህዝብ እሴቶች ሊሸረሽሩ የሚችሉ ተግባራትንና አመለካከቶችን ከህብረተሰቡ ውስጥ ማውጣትና የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ላይ ሰፊ ስራ ተሰርቷል” – አቶ አድማሱ ዳምጠው፣ የኦሮሚያ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ

26

እንደ አገር በተመዘገበው ለውጥ ውስጥ ስሙ ጎልቶ ይነሳል፤ ከለውጡ በኋላም ቢሆን በበርካታ ፈተናዎች ውስጥ አልፏል፤ የኦሮሚያ ክልልና ህዝብ። አሁንም ቢሆን የክልሉንና ህዝቡን የሰላም፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ከመመለስ አኳያ በርካታ ተግባራት መከናወን እንዳለባቸው ሲነገር፤ የክልሉ መንግስትም ይሄን ለማከናወን ያግዙኛል ያላቸውን እርምጃዎች እየወሰደ ስለመሆኑ ሲገልጽ ይደመጣል።

ከዚህ አኳያ በክልሉ ምን ተሰርቷል፤ ምንስ ውጤት ተገኝቷል፤ በቀጣይስ ምን ታስቧል፤ በሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ አቶ አድማሱ ዳምጠው ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ ይዘን ቀርበናል።

አዲስ ዘመን፡የክልሉ ምክር ቤት (ጨፌ ኦሮሚያ) በቅርቡ ባካሄደው ጉባኤ ትኩረት ሰጥቶ የተመለከታቸው ጉዳዮች፣ ያሳለፋቸው ውሳኔዎችና ያስቀመጣቸው አቅጣጫዎች ምንድን ነበሩ?

አቶ አድማሱ፡ጨፌ ኦሮሚያ ዓመታዊ አስረኛ መደበኛ ጉባኤውን ሲያካሂድ የትኩረት ነጥቦቹ በክልሉ የአንድ ዓመት ሂደት ውስጥ የለውጥ ጉዞውን መሰረት ያደረጉ በኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች የተሰሩ አንኳር ስራዎችን መገምገምና ለ2012 በጀት ዓመት የተያዘውን ዕቅድ በሃሳብ በማዳበር ማጽደቅ፤ ብሎም የክልሉን በጀት ማጽደቅ ነበር።

ከእነዚህ ባለፈም የፍትህ አሰጣጥ ሥርዓቱን ማዘመንና የህዝቡን የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ የተሰሩ ስራዎችን ሪፖርት በማዳመጥ፤ የተለያዩ አዋጆች ላይ ተወያይቶ የማዳበሪያ ሃሳብ መስጠት፤ እንዲሁም የተለያዩ ሹመቶችን ማጽደቅ ነበር። ከእነዚህ ውስጥ በተለየ ሁኔታ የሚታየው ግን የኦሮሚያ የዜግነት አገልግሎት አዋጅ ሲሆን፤ የዚህን አገልግሎት አስፈላጊነት፣ ዓላማዎችና መርሆዎች ምን እንደሆኑ ጨፌው በሰፊው ከተወያየበት በኋላ ወደስራ እንዲገባ አቅጣጫ አስቀምጧል።

አዲስ ዘመን፡በክልሉ በስፋት ሲነሳ የነበረው በኋላም ለመጣው አገራዊ ለውጥ ትልቅ ድርሻ የነበረውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ተረድቶ ከመስራትና ከመመለስ አኳያ ከለውጡ ማግስት በተለይም 2012 በጀት ዓመት ምን ተሰራ? ምንስ ውጤት ተገኘ?

አቶ አድማሱ፡በክልሉ ለውጡ እንዲመጣ ሰፊ ትግል ሲካሄድ ነበረ። ለውጡ ከመጣ በኋላ ደግሞ ለውጡን በስኬት የማስቀጠል ጉዳይ፤ የህዝቡንም የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ከመሰረቱ የመፍታት ጉዳይ ልዩ ትኩረት የተሰጠው ነው። በዚህ ረገድ አንዱ ስራ በክልሉ ሰላምና የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ነበረ። በዚህም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንደ ክልልም ሆነ እንደ አገር በመሳሪያ አፈሙዝ መብትን የመጠየቅና የራስን ፍላጎት የማራመድ ሂደቶች እንዲዘጉ ተደርጎ በሰላማዊ መንገድ ብቻ በሃሳብ የበላይነት የመንቀሳቀስ አዲስ ምዕራፍ የተከፈተበት ነው።

ይሄ ለውጥ ግን በሁለት ምክንያት እንዳይቀጥል ችግሮች የተፈጠሩበት አጋጣሚም ነበር። አንደኛው፣ ለውጡ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ጥቅማቸውን የሚነካባቸው አካላት ለውጡን ለማደናቀፍ የተለያዩ ሴራ በመሸረባቸው ችግሮች ተከስተው ነበር።

በዚህም ህዝብን ከህዝብ የማጋጨት፣ የማፈናቀል፣ የህዝቡን አብሮ የመኖር እሴቶችን የሚሸረሽሩ ድርጊቶች ሲከናወኑ ነበረ። ሁለተኛው ደግሞ፣ ከነበረው አስተሳሰብ ወደ አዲስ አስተሳሰብ ለመቀየር በሚደረግ ጥረት ውስጥ ለውጡን በውል ካለመረዳት የተፈጠሩ ችግሮች ነበሩ።

በመሆኑም እነኚህን ችግሮች ከመሰረቱ የመፍታትና በክልሉ ሰላምና የሕግ የበላይነትን የማረጋገጡ ጉዳይ የሞት የሽረት ጉዳይ ተደርጎ የክልሉ ከፍተኛ አመራር የመጀመሪያ ስራ ያደረገው ህዝብን ያሳተፉ ኮንፍረንሶች ከክልል እስከ ቀበሌ ተካሂደዋል። ከህዝቡ ጋር በተደረሰው መግባባትም አጥፊዎችን አሳልፎ ለመስጠትና ለሕግ ለማቅረብም በገባው ቃል መሰረት በተግባር ማሳየት የቻለበትን የተሳካ ስራ ማከናወን ተችሏል።

የኦሮሞ ህዝብ ደግሞ ችግሮች ሲከሰቱ ችግር የሚፈታበት የገዳ ሥርዓት ያለው፤ እንኳን ሊያፈናቅል የራሱ ያልሆነውን ዜጋ ጉዲፈቻና ሌሎችም ስያሜዎች በመስጠት የራሱ ወገን አድርጎ ቀድሞ የሚሞትና ለወንድሙ ብሎ ቀድሞ ራሱን አሳልፎ የሚሰጥ ህዝብ እንደመሆኑ የተፈጸመው ተግባርም የህዝቡ ዓላማና ፍላጎት እንዳልሆነ፤ ህዝቡ በመፈቃቀር፣ በመከባበርና በመቻቻል አብሮ ሲኖር እንደነበረ መረዳት ተችሏል።

ይሄንንም በውል በማስረዳት እርቀ ሰላም ወርዶ በሁሉም አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎች ወደቄያቸው እንዲመለሱ፤ አብሮ የመኖር እሴቶቻቸውም ዳብረው እንዲቀጥሉ ተደርጓል። በዚህ ሂደት ውስጥም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እጃቸው ያለ አካላት ለሕግ በማቅረቡ በኩል በህዝቡ ጥቆማና በጸጥታ ሃይሎች ቅንጅት ሰፊ ስራ በመሰራቱ አሁን በክልሉ አስተማማኝ ሰላም ማረጋገጥ ተችሏል።

እንደ ሰላሙ ሁሉ በኢኮኖሚው መስክ በተሰራው ስራም ውጤት ማግኘት ተችሏል። በተለይም በክልሉ ያለን የተፈጥሮ ሀብት ወደ ኢኮኖሚ ምንጭነት በመቀየር፤ ግብርናን በማዘመን፣ ለወጣቶች የስራ እድሎችን በመፍጠር ተጠቃሚ ከማድረግ፣ የገበያ ትስስርን ከማጠናከርና የኢንቨስትመንት ችግሮችን ከመሰረቱ ከመፍታት አንጻር ከለውጡ በፊት የነበሩ የህዝብ ቅሬታዎች በሙሉ አንድ ሁለት ተብለው ተለቅመው ወደ ውጤት እንዲለወጡ ታቅዶበት ተሰርቷል።

ለምሳሌ፣ ግብርናውን በማዘመን በግብዓት አቅርቦት፣ በቴክኖሎጂ አጠቃቀምም አርሶ አደሩ ተጠቃሚ እንዲሆን፤ በተለይም በጋ ከክረምት የሚፈሱ ወንዞችን ወደልማት በመቀየር ትላልቅና መለስተኛ መስኖዎች የመገንባት እቅድ ተይዞ በበርካታ አካባቢዎች በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ህዝቦችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶች ስራ ተጀምሮ እየተሰራ ነው።

በተመሳሳይ የጤና ፕሮጀክቶችና ሆስፒታሎች በአጭር ጊዜ ተጠናቅቀው ወደ ስራ እንዲገቡ ተደርጓል። በአካባቢ ጽዳትም ከተሞቻችን ለኑሮም ምቹ እንዲሆኑ የአመለካከትና የድርጊት ንጽህናን መሰረት ያደረጉ የጽዳት ዘመቻዎች ተከናውነዋል። በዕውቀት፣ በክህሎትና ስነምግባር የዳበረ ትውልድ መቅረጽን መሰረት ያደረጉ ሰፊ የትምህርት ተግባራት ተከናውነዋል።

የስራ ባህል ለውጥ ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ተሰርቷል። የስራ ባህልን መለወጥ ስንል ደግሞ ሁሉም ዜጋ ባለው እውቀት፣ ገንዘብና ሀብት ለአካባቢው፣ ለአገሩ፣ ለቤተሰቡ ጉልህ ሚና የሚጫወትበት ሥርዓት መዘርጋት ነው። ከዚህ አኳያ ለመጀመሪያ ጊዜ የዜግነት አገልግሎት አዋጅ ወጥቶ ወደስራ እየተገባ ይገኛል። በአረንጓዴ ልማቱ የችግኝ ተከላም ትልቅ አፈጻጸም ታይቷል።

ከዚህ በተጓዳኝ በተግባርም በአመለካከትም መስራት የሚችልና የአገልጋይነት ስሜትን ያዳበረ አመራር በመፍጠር በኩልም ከ20ሺ በላይ አመራሮችን ከክልል እስከ ወረዳ ድረስ አሰልጥነው ወደ ተግባር ገብተዋል። ይሄ ውጤትም የተገኘው በዚሁ አመራር ነው። አሁንም በክልሉ ከ57ሺ በላይ በቀበሌ ደረጃ ላሉ አመራሮችም ስልጠና እየተሰጠ ነው። በጥቅሉ በዓመቱ በክልሉ በኢኮኖሚው፣ በማህበራዊውም ሆነ በፖለቲካው መስኮች የኦሮሚያን ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ለማረጋገጥ ሰፊ ስራዎች ተሰርተዋል፤ ውጤቶችም መመዝገብ ጀምረዋል።

አዲስ ዘመን፡በክልሉ በነበረው የሰላም ችግር ከክልሉም ሆነ ከአጎራባች ክልሎች የተፈናቀሉ ዜጎችን ህዝቡን ባሳተፈ መልኩ በዘላቂነት ለማቋቋም፤ ብሎም አጥፊዎችን ተጠያቂ ለማድረግ ምን ተጨባጭ ስራ ተሰርቷል?

አቶ አድማሱ፡- እነዚህ ዜጎች ከቄያቸው ለቀው ሲወጡ በሶስት ምክንያት ነው። አንደኛው፣ የራሳቸውን የፖለቲካ ፍላጎት ለማሟላት ህዝብን ከህዝብ በማጋጨትና ዜጎች እንዲፈናቀሉ ግፊት በማድረግ የፖለቲካ ሴራ ነው። ሁለተኛው፣ በስጋት ሲሆን፤ ሶስተኛው፣ በተለያዩ አሻጥሮች (በተለይ ጉጂና ጌዲኦ የተሰራው አካባቢ እርዳታ ታገኛላችሁ በሚል ህዝብን ከቀዬው ማፈናቀል) ነው።

እነዚህ ዜጎችም ወደቄያቸው እንዲመለሱ ሲደረግም እነዚህን በማጤን ሲሆን፤ በዚህ ውስጥ በተለይም የፖለቲካ አሻጥር በመፍጠር ህዝብን በማፈናቀል ውስጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እጃቸው ያለበት ሰዎችን በርካቶች በህግ ቁጥጥር ስር ውለው የፍርድ ሂደታቸውን በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ።

ሁለተኛው ስራ የአካባቢውን ሰላም ማስፈን ሲሆን፤ ህብረተሰቡንና የአካባቢውን ሚሊሻ ባሳተፈ መልኩ ሰፊ ውይይቶች ተደርገው አስተማማኝ ሰላም መፍጠር ተችሏል። በሶስተኛ ደረጃም፣ ተፈናቃዮች ወደቄያቸው ከመምጣታቸው በፊት በህዝቡና በመንግስት ትብብር የወደጡባቸውና የጠፉ ንብረቶችን የመተካት ስራ ተከናውኗል። በጉጂም ሆነ በኦሮሚያ በአባ ገዳዎች፣ በሀገር ሽማግሌዎችና መላው ህብረተሰቡ የፈረሱባቸው ቤቶች መልሶ በመገንባት፤ በገዳና ሽምግልና ሥርዓት ህዝቡን በማቀራረብና በማወያየት፤ ገንዘብ፣ ልብስ፣ የቤት ቁሳቁስና የቤት እንስሳት ጭምር በማዋጣት ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል።

በአራተኝነት፣ ተፈናቃዮችን ወደቄያቸው የመመለስና እርቀ ሰላም የማውረድ ስራ ተሰርቷል። ወደ ቄያቸው ከተመለሱ በኋላ ድጋፍና ክትትል እንዲያገኙ ተደርጓል። በዚህ በኩል በተለይም የዘር ጊዜ ሳያልፍባቸው የግብርና ግብዓትና ቁሳቁስ መግዣ የሚሆን የክልሉ መንግስት ብር መድቦ ለምሳሌ፣ በምስራቅና ምዕራብ ሐረርጌ፣ ባሌ፣ ቦረና፣ ጉጂ፣ ምዕራብ ጉጂ፣ ምስራቅና ምዕራብ ወለጋ ዞኖች ለሚገኙና ከቄያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች ለዘርና ለማዳበሪያ ግዢ የሚውል 627 ሚሊዮን ብር በድጋፍና ብድር እንዲሰጥ ወስኗል፤ (ከዚህ ውስጥ 169 ሚሊዮን 825ሺ 541 ብር በድጋፍ፣ ቀሪው በብድር) ድጋፍ አድርጓል። ራሳቸውን እስኪችሉ ድረስም ክትትልና ድጋፍ እንዲደረግ ስርዓት ተዘርግቷል።

አዲስ ዘመን፡የክልሉን ሰላምና የህዝቦች አብሮነትን ከማጽናት አኳያ የኦሮሚያ ክልል ህዝብ ከአጎራባች ክልሎች ህዝቦች ጋር ወንድማማችነቱ እንዲጎለብት፤ የልማት ትስስርና ተጋሪነቱ እንዲያድግ ምን እየተሰራ፤ ምንስ ውጤት እየታየ ነው?

አቶ አድማሱ፡በዘንድሮ ዓመት ከሴራ ፖለቲካና ዜጎችን ከማፈናቀሉ ጎን ለጎን እንደ እድል ወስደን ከሰራናቸው ስራዎች አንዱ የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ማጠናከር ነው። ይሄም በሁለት መልኩ የተከናወነ ሲሆን፤ አንደኛው፣ የህብረተሰቡን የጋራ እሴቶች ማጎልበት እና እሴቶቹን በመጠበቅ በተለይም በሰላም፣ በልማትና በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ህዝቡ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ማስቻል ላይ ያተኮረ ነው። ሁለተኛው፣ የመደጋገፍና የልማት ትስስሩን የበለጠ የማጠናከር ነው።

በዚህም የኦሮሚያን ህዝብ ከተለያዩ ክልል ህዝቦች ጋር የወንድማማችነት መድረኮችን አካሂደናል። የኦሮሞ ህዝብ በታሪኩም በተፈጥሮውም፣ በገዳ ሥርዓቱም በአቃፊነቱ ነው የሚታወቀው። በክልሉ ውስጥም ሆነ ውጪ በድንበርም ጭምር ያሉ ብሔር ብሔረሰቦች ከኦሮሞ ህዝብ ጋር በደምና በአጥንት የተሳሰሩ ህዝቦች ናቸው።

ለምሳሌ፣ የኦሮሞና የሶማሌን ህዝብ መለየት በሚያስቸግር ደረጃ የተዋሃዱ ናቸው። የአማራና ኦሮሞ ህዝቦችም በተመሳሳይ የሚገለጹ ናቸው። ይህ በሁሉም ደረጃ የሚስተዋል ነው። በመሆኑም በእነዚህ ህዝቦች መካከል ያሉ እሴቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ፤ እነዚህን እሴቶች ሊሸረሽሩ የሚችሉ ተግባራትንና አመለካከቶችን ከህብረተሰቡ ውስጥ ማውጣትና የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ላይ ሰፊ ስራ ተሰርቷል።

ከልማት ትስስርን አኳያም ለምሳሌ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝና ኦሮሚያ ክልሎች ወሰን አካባቢ ያሉ ህዝቦች በገበያ እንዲገናኙ፣ ምርቶቻቸውንም እንዲለዋወጡ ባጠቃላይ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፉ ለማስተሳሰር መንገድ ያስፈልጋል። ለዚህም በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ብር በኦሮሚያ ክልል በጀት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንገድ የመስራት ተግባር እየተከናወነ ይገኛል።

በሶማሌና ኦሮሚያ ክልሎች መካከልም በሚዋሰኑ በርካታ ዞኖችና ወረዳዎች በልማት ማጠናከር ላይ መሰረት ያደረገ ስራ ተጀምሯል። ለምሳሌ፣ በኦሮሚያ፣ ሶማሌና አፋር አዋሳኝ አካባቢ ያሉ ህዝቦች ከብቶቻቸውን እንኳን አንድ ወንዝ ነው የሚያጠጡት። ሆኖም ይህ አካባቢ በአግባቡ ለምቶ በጋራ እንዲጠቀሙ ካልተደረገ ለግጭት መዳረጋቸው አይቀርም። ምክንያቱም በብዙ ቦታዎች የሚታዩ ችግሮች ከፖለቲካ አሻጥሩ ባለፈ ድህነትና የመሰረተ ልማት አውታሮች እጥረትም ትልቅ ድርሻ ነበረው።

ከዚህ በተጓዳኝ የባህልና ቋንቋ ልውውጥ ስራ እየተከናወነ ሲሆን፤ ለምሳሌ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝና ጋምቤላ አፋን ኦሮሞን ለማስተማር ወስነዋል። እነዚህ ተግባራትም ህዝቦችን የበለጠ የሚያቀራርቡና ሴረኞች በህዝቡ መሃል ቦታ እንዲያጡ የሚያደርጉ ናቸው።

አዲስ ዘመን፡በክልሉ የተጀመረው የኢኮኖሚ ሪቮሉሽን በምን ደረጃ ላይ ይገኛል? የወጣቶች የስራ እድል ፈጠራውስ በጀት ከመመደብ ባለፈ ለውጤታማነቱ ምን የተቀመጠ አቅጣጫ አለ?

አቶ አድማሱ፡የኦሮሚያ ኢኮኖሚ ሪቮሉሽን ኢኮኖሚውን የመቀየርና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ዓላማን የያዘ፤ የአንድ ዘርፍን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ዘርፍ የመለወጥ ስራዎችን መሰረት ያደረገ ነው። ይህ ደግሞ ግብርናውን የማዘመን፣ የገበያ ሥርዓቱን ቀልጣፋና ሕጋዊ ማድረግን፣ ለወጣቶች የስራ እድል መፍጠርን፣ የኢንቨስትመንት ፍሰቱ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ባደረገ መልኩ መስራት፣ እንዲሁም ትላልቅ ካምፓኒዎችን በመክፈት ህብረተሰቡ ሼር ሆልደር ሆኖ ተጠቃሚ እንሆንና የስራ እድልም እንዲያገኝ ማድረግን መሰረት ያደረገ ነው።

ለምሳሌ፣ ግብርናውን ከማሳደግ አኳያም ተገቢውን ግብዓት ማቅረብንና ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ ምርታማነትን ማሳደግ፤ የምርቶችን ልውውጥ በመፍጠር በተለይም አርሶ አደርና ኢንዱስትሪውን በማገናኘት የገበያ ትስስርን መፍጠርም ትኩረቱ ነው። የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግም ግንባር ቀደም አርሶ አደሮች ገንዘባቸውን ወደ ሀብት እንዲለውጡ ወጣቶችን በማደራጀት የማሳተፍ ስራ የሚከናወንበትም ነው። በኢንቨስትመንት የዘርንፉ ችግሮች በመፍታትም፤ ዘርፉ ከስራ እድል ፈጠራ፣ ከገበያ ትስስርና ከውጭ ምንዛሬ ግኝት፤ ከህብረተሰቡ ተሳትፎና ተጠቃሚነት አኳያ ያላቸውን ሚና እንዲወጣ ማድረግ ነው።

ትልልቅ ካምፓኒዎችን በመክፈት የህብረተሰቡን ድርሻና ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ስራውም በአምስት ካምፓኒዎች ተጀምሯል። ለአብነት፣ ወላቡ ኮንስትራክሽን (አሁን ላይ ባቱ አካባቢ የሚገኝ የኦሮሚያ ኢንዱስትሪ ፓርክን እየገነባ ይገኛል) ወደ ስራ በመግባቱ ብቻ እስከ ሶስት ሺህ ሰው የስራ እድል ፈጥሯል።

በሻሸመኔ ያለው የትራክተር መገጣጠሚያ የሜካናይዜሽን እርሻ መሳሪዎች አቅራቢም በአርሶ አደሮች ሼር ሆልደርነት የተቋቋመ ነው። ቀሪ ሶስቱ ግን በጨረታና በመሬት ርክክብ ሂደት ላይ ይገኛሉ። እነዚህ ኩባንያዎች ህዝቡ በባለቤትነት ስሜት የሚጠብቃቸው፣ ሰፊ የስራ እድል የሚያገኝባቸውና ባለድርሻም ሆኖ ከትርፉ ውጤት የሚያገኝባቸው ናቸው።

የወጣቶች የስራ እድል ፈጠራን በተመለከተም ቀደም ሲል የስራ ቦታ ሳይለይ ብድር ይሰጣል። አሁን ከብድሩ በፊት የስራ ቦታው፣ የስራ ፍላጎቱ፣ የስራ ዘርፉ፣ እንዲሁም የወጣቶች ሙያና ክህሎት ቀድሞ ይለያል፤ የገበያ ፍላጎቱም ተለይቶ የትስስር መስመር ይፈጠራል፤ የአዋጪነት ጥናት ይከናወናል፤ የብድር አቅርቦትና አመላለስ ሂደቱም ሥርዓት ተዘርግቶለታል።

አዲስ ዘመን፡በክልሉ በአዋጅ ተግባራዊ ለማድረግ ከታቀዱ ጉዳዮች አንዱ የኦሮሚያ የዜግነት አገልግሎት ነው። ይህ ማለት ምን ማለት ነው? ኦሮሚያን እንደ አገር ከመመስረት ጋርስ ይያያዝ ይሆን? ሃሳቡንስ ህዝቡ እንዲያውቀው ምን ተሰርቷል?

አቶ አድማሱ፡የዜግነት አገልግሎት ዋናው ጉዳይ ዜጎች በአገራቸው ላይ ባላቸው እውቀት፣ ሀብት፣ ጉልበትና አቅም ሁሉ ተሳትፎ የሚያደርጉበት፤ ቀጣይነት ባለው መልኩም ሁሉም በየደረጃው ሃላፊነቱን እንዲወጣ ማድረግ ነው። አገሩን፣ ቤተሰቡንና ራሱን የሚወድ ሰው ደግሞ፤ ለራሱም፣ ለቤተሰቡም ሆነ ለአገሩ የሚጠቅም ነገር ለማድረግ በገንዘቡም፣ በጉልበቱም ሆነ በእውቀቱ ቀጣይነት ባለው መልኩ ተሳትፎ የበኩሉን ሚና የሚጫወት ነው። የዚህ ዓላማ ደግሞ በተለይም በስነ ምግባር፣ በባህል እሴቱና በክህሎት የታነጸና ብቁ የሆነ ትውልድ በመቅረጽ የትውልድ ቅብብሎሽ ሥርዓቱን ማሳለጥ ነው።

በአገራችን ድህነት ዕጣ ፈንታ ሆኖ አይደለም። ሰፊ ጉልበት አለ፤ ያልተነካ ሰፊ ሀብት አለ። ይሄን ሀብትና ጉልበት ወደ ልማትና ውጤት መቀየር ይገባል። ለዚህ ደግሞ ከተባበርንና ሁሉም የድርሻውን ከተወጣ እና ትውልድ እንዲቀረጽ ካደረገ የለማችና የበለጸገች ኦሮሚያንም ሆነ አገር መገንባት የማንችልበት ምንም ምክንያት የለም። ስለዚህ የዜግነት አገልግሎት አዋጅ ሲወጣ ዜጎች ለአገራቸውና ለህዝባቸው ልማት፣ ሰላምና ዴሞክራሲ ተጠቃሚነት ቀጣይነት ባለው መልኩ የበኩላቸውን ሚና በመወጣት ነገ የተሻለ ዜጋና አገር የመገንባት ዓላማን ያነገበ ነው።

የ ዜግነት አገልግሎት ዓላማውም የኦሮሙማ እሴት ያልሆኑትን ማፈናቀል፣ መጥላትና መግፋት የመሳሰሉትን የማስወገድ ነው። ምክንያቱም ኦሮሙማ አቃፊነት፣ ፍቅር፣ መተሳሰብና መቻቻል ነው። ስለዚህ የኦሮሙማን እሴቶች እያዳበርን ከሄድን ለዘላቂ ሰላም ወሳኝ ናቸው። አሁን የትግል ምዕራፉ የመሳሪያ ሳይሆን የሃሳብ ልዕልና እንደመሆኑ ኦሮሙማ ሌት ተቀን መትጋት ነው።

ኦሮሙማ በሁሉም ነገር ተወዳዳሪ ሆኖ መገኘት ነው። በእውቀት፣ በቴክኖሎጂ፣ በገበያ፣ በምርታማነትና ጥራት ተወዳዳሪ መሆን ነው። ኦሮሙማ የአመለካከትና የተግባር ንጽህና ነው። የገዳ ሥርዓትን ከሚቃረኑ ሌብነት፣ ውሸት፣ ሰው መግደልና መጥላትን ማስወገድ፤ መፈቃቀር፣ በተባበርና ተቻችሎ መኖርን ብሎም ትብብርበን መሰረት አድርጎ መስራት ነው።

በመሆኑም የኦሮሚያ የዜግነት አገልግሎት ዓላማ ሌላ ዜጋን መፍጠር ሳይሆን ዜጎች በአገርና ትውልድ ግንባታ ውስጥ የድርሻቸውን እንዲወጡ እድል መስጠት ነው። በስነምግባርና እውቀት የታነጸ፤ የአገር ፍቅር ያለውና በአገር ሁለንተናዊ ልማትና እድገት ውስጥ ይመለከተኛል፤ የትውልድ ጉዳይ ያገባኛል የሚል ዜጋን መፍጠር ነው። ይሄን ከማስገንዘብ አኳያም እስከ ቀበሌ ውይይቶች ተካሂደው ምክር ቤቶችም ተቋቁመዋል። በቀጣይ በክልል ደረጃ ምክር ቤት ተቋቁሞ በመደበኛ ፕሮግራም እየተመራ ስራውን የሚያከናውን፤ ሂደቱንም እየገመገመና ስራዎቹን ለህዝብ ይፋ እያደረገ ይሄዳል።

አዲስ ዘመን፡ክልሉን፣ ትውልዱን ብሎም አገርን የማልማትና የማበልጸግ ጉዞውን በአግባቡ ተረድቶ የድርሻን ከመወጣት አኳያ ለአመራሩ፣ ለህዝቡ፣ ለምሑራንና ባለሀብቱ ምን መልዕክት ያስተላልፋሉ?

አቶ አድማሱ፡እስካሁን እየተሰሩ ባሉ ስራዎች በተለይም የአገራችንንና የክልላችንን ለውጥ በማስቀጠሉ በኩል የህዝቡም የአመራሩም ቁርጠኝነትና ተነሳሽነት የሚበረታታ ነው። አንድ ከሆንና ተደማምጠን ከሰራን የማንቀይረው ነገር እንደሌለ፤ ከዚህ በተቃራኒው ያሉ ድርጊቶችም ኢትዮጵያዊነትን የማይወክሉ መሆናቸው ታይቷል።

ይሄንን ለማስቀጠል ከአመራሩ የሚጠበቀው የሕዝብ አመራር ሆኖ መገኘት ብቻ ነው። የህዝብን ፍላጎት መሰረት አድርጎም ለህዝብ መኖር፤ ለህዝብ ራስን መስጠት፤ ያለውን እውቀት፣ ሀብትና ጊዜ በሙሉ ለህዝብ ጥቅም ማዋል ነው። በዚህ በኩል የተጀመሩ አበረታች ጥረቶች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው። ህዝብ የሚፈልገውን ከሰራን፤ የህዝባዊነት ስሜትን ከተላበስን፤ የልብ ትርታውን ካዳመጥን፤ ካሳተፍነውና ውጤቱንም የእርሱ ካደረግን ለውጥ ማምጣት እንችላለን። ይሄ ደግሞ የአዕምሮ ሰላምና ነጻነት በመሆኑ፤ የታሪክ አሻራ አኑረን ለመሄድ መስራት ይገባል።

ህዝቡም አሁን የሚያስፈልገን የሃሳብ ልዕልና መሆኑን ተገንዝቦ መስራት አለበት። ምክንያቱም ኦሮሙማ ውስጥ ችግሮች ሲከሰቱ ስሜታዊነት ሳይሆን በሰከነ መንፈስ በማስተዋል ላይ የተመሰረተ ውይይት አድርጎ መፍታት አለ። እናም ዛሬ ያለንበት የትግል ምዕራፍ በህዝቦች ተጋድሎ የተገኘውን ለውጥና ውጤት ማስቀጠል እንደመሆኑ፤ ህዝባችን አመራሩን እየደገፈ ከጎኑ ሆኖ ሲያጠፋ እያረመና ሲሰራ እያገዘ የላቀ ለውጥ እንዲመጣ መስራት፤ እሴቶቹን ለልማት፣ ለሰላምና ለዴሞክራሲ ማዋል ይኖርበታል።

ምሁራንና ባለሀብቶችም ቢሆኑ፤ አሁን ላይ አገር ትጣራለች፤ ህዝብ ይጣራል፤ እናት ትጣራለች። ጥሪያቸውም እውቀት ያላቸው በእውቀታቸው፤ ሀብት ያላቸው በሀብታቸው፤ ጉልበት ያላቸውም በጉልበታቸው ኦሮሚያን ብሎም አገርን እንድታለሙ ነው። ስለዚህ ባለሀብቶች ሀብታችሁ የህዝብ ሀብት እንዲሆን እየሰራችሁ እንዳላችሁ ሁሉ፤ በቀጣይም የተጀመሩ ለውጦች በላቀ መልኩ እንዲጓዙ፣ የወጣቱ የስራ እድል ፈጠራም የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን፣ የህዝቡ የልማት ችግሮች እንዲፈቱ መንግስት አቅሙ ውስን በሆነበት ቦታ እናንተ እየደገፋችሁ ኦሮሚያን በጋራ እናልማ፤ አገርንም እናሳድግ።

ምሑራንም፣ ከምንም በላይ ዛሬ ዓለምን እየቀየረ ያለው ሀብት እውቀት ነው። በእውቀት የዳበረና የተመራ ህዝብ፣ በእውቀት የታነጸ ትውልድ አገርን መገንባት አያቅተውም። ስለዚህ የአዕምሮ ብሎም የምርምርና ስርጸት ውጤቶቻችሁን ከሼልፍ ባሻገር ለህዝብና አገር ጥቅም እንዲውሉ በማድረግ በሙሉ ልብና አቅም ተሳትፋችሁ የጀመራችሁትን አስተዋጽኦ አጠናክራችሁ በመቀጠል ኦሮሚያንም አገራችንንም እናልማ።

እንደ መንግስትም አሁን ሌት ተቀን የሚታየን የህዝባችን ሰላምና ልማት ተረጋግጦ ማየት ነው። የህዝባችንን ልማት፣ ሰላምና ዴሞክራሲ መረጋገጥ ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ በሰላማዊ መንገድ የህዝብን ፍላጎት ለማሳካት ከሚጥር ማንኛውም አካል ጋር ለመስራትም ሆነ ለመደገፍ ዝግጁ ነን። የትኛውንም የተሻለ ሃሳብ ምንም ይሁን በማንም ይምጣ ኦሮሚያን ለማልማት፣ ህዝብን ተጠቃሚ ለማድረግና ትስስሩን ለማጠናከር፣ አገርን የማሳደግና ለውጥን የማስቀጠል ድርጊትም ሆኑ ተግባራት በሙሉ በኦሮሚያ ክልል ድጋፍ ያገኛሉ። ለዚህም በራችን ክፍት ነው።

አዲስ ዘመን፡ለቃለ ምልልሱ ፈቃደኛ ስለሆኑ አመሰግናለሁ።

አቶ አድማሱ፡እኔም አመሰግናለሁ።

አዲስ ዘመን ሐምሌ 29/2011

ወንድወሰን ሽመልስ