ለዜጎች በውጭ ሀገራት የሥራ እድል የመፈለጉ ሥራ በትኩረት ይሰራበት!

18

 ኢትዮጵያ ከ11 ሚሊየን በላይ ዜጎቿ ሥራ አጦች ናቸው፡፡ በዘህ አሀዝ ላይ በየዓመቱ ሁለት ሚለየን አዳዲስ ሥራ አጦች ይታከሉበታል፡፡ ይህን ችግር ታሳቢ በማድረግም ሀገሪቱ በተያዘው በጀት ዓመት ለሦስት ሚሊየን ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር አቅዳለች፡፡ ይህ የሥራ እድል የሚፈጠረው በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በውጭ ሀገሮችም ጭምር ነው፡፡

እንደሚታወቀው ብዙ ዜጎች በቤት ሠራተኛነት ወደ መካከለኛው ምስራቅ ይሄዳሉ፡፡ በሳኡዲ ዓረቢያ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በቤት ሠራተኛነት ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡ በሌሎች መካካለኛው ምስራቅ ሀገሮችም እንዲሁ። በርካታ ኢትዮጵያውያን በቤት ሠራተኛነት ተሰማርተዋል፡፡ በሌሎች የሥራ ዘርፎች የተሰማሩም አሉ፡፡

ዜጎች በእነዚህ ሀገሮች የሚገኙት ግን በአብዛኛው በህገ ወጥ መንገድ በመግባት ሲሆን፣ የሚሄዱትም ምንም አይነት ስልጠና ሳይከታተሉ ነው፡፡ በእዚህ የተነሳም ሰብዓዊ መብታቸው ሲጣስ ቆይቷል፡፡ ዝቅተኛ ደመወዝ ተከፋይ ሆነውም ነው የኖሩት፡፡ ህገወጥ ተብለው በየዓመቱ ከሳኡዲ ዓረቢያ የሚባረሩት ኢትዮጵያን ቁጥርም ከፍተኛ ነው፡፡

ከዚህ መሰረታዊ ችግር በመነሳትም መንግሥት ዜጎች በህጋዊ መንገድ ወደ እነዚህ ሀገሮች እንዲሄዱ እና ሰብዓዊ መብታቸው ተጠብቆ እንዲሠሩ የሚያስችሉ ተግባሮችን አከናውኗል፡፡ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት አዋጅ በማውጣትም ከሀገራቱ ጋር ድርድር ሲያደርግም ቆይቷል፡፡ ወደ እነዚህ ሀገሮች የሚሄዱ ኢትዮጵያውያን ከስራቸው ጋር የሚዛመድ ስልጠና እንዲከታተሉም ማድረግ ተጀምሯል፡፡

መንግሥት ወደ መካከለኛው ምስራቅ ሀገሮች በመሄድ በቤት ሠራተኛነት የሚሰማሩ ዜጎችን የሥራ ሁኔታ የተሻለ ለማድረግ የወሰደው እርምጃ በተያዘው በጀት ዓመት በውጭ ሀገር ለዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር ለተያዘው እቅድ ስኬት ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን በእነዚህ ሀገሮች ሲሠሩ ከሌሎች ሀገሮች አንጻር ሲታይ ይከፈላቸው የነበረው ክፍያ እንዲሻሻል ያስችላል፡፡ ሰብዓዊ መብታቸው ተጠብቆ እንዲሰሩ የሚያስችል በመሆኑም በዜጎቹ ላይ ይደርስ የነበረውን በደልና ግፍም እንደሚያስቀር ይታመናል፡፡

ዜጎች ስልጠና ተሰጥቷቸው የሚሰማሩ እንዲሆኑ የሚያስችል በመሆኑም ከስልጠና አለመኖር ጋር ተያይዞ ከአሠሪዎች ጋር የሚኖረው አለመግባባት ይወገዳል፡፡ የሚያግኙት ክፍያ የተሻለ እንዲሆንም ይጠቅማል፡፡

በዚህ አይነት መንገድ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ወደ ተባበሩት ኤሜሬት መሄድ የሚችሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ከሳኡዲ ዓረቢያ ጋር በርካታ ውይይቶች ከተደረጉ በኋላ ሰሞኑን ኢትዮጵያውያን በህጋዊ መንገድ ወደ ሀገሪቱ የሚገቡበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ሀገሪቱ ለኢትዮጵያውን ሠራተኞች ቪዛ መምታትም በይፋ ጀምራለች፡፡

 ሳኡዲ ዓረቢያ እንዳለችው ለኢትዮጵያውያን የሚሆኑ በርካታ የሥራ እድሎች አሉ፡፡ ኢትዮጵያ ማድረግ ያለባትም ዜጎችን በሚገባ ማሰልጠን ነው፡፡ ዜጎች በመካከለኛው ምስራቅ የሚሰማሩት ባብዛኛው በቤት ሠራተኛነት እንደመሆኑ በእዚህ ላይ በቂ ስልጠና እንዲያገኙ ማድረግ ይገባል፡፡ መሰረታዊ ክህሎት ማላበስ፣ የቤት ውስጥ ቴክኖሎጂዎች አጠቃቀምንና የሚሄዱበትን ሀገር ባህል ማስተዋወቅ እንዲሁም ለመግባባት ያስችላቸው ዘንድ ለስራ የሚሰማሩበትን ሀገር ቋንቋ እንዲማሩ ማድረግም ተገቢ ነው፡፡

ይህን በማድረግ የዜጎችን ተፈላጊነት ማሳደግና ሌሎችም ወደ ሀገራቱ ሄደው የሥራ እድል እንዲያገኙ በማድረግ በውጭ ሀገር ለዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር የተያዘውን እቅድ ማሳካት ያስችላል፡፡

እነዚህ ዜጎች የሚሰማሩበት የሥራ ዘርፍ ልምድ ተቀስሞበት የእውቀት ሽግግር ወደ ሀገር ቤት በመመለስ የእውቀት ሽግግር የሚደረግበት ስላልሆነም ዜጎች የሚያገኙትን ገንዘብ እንዲቆጥቡ ሁኔታ በማመቻቸት ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ ሥራ የሚፈጥሩበትን ሁኔታ ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡

መንግሥት በቀጣይ በትኩረት ሊሰራበት የሚገባው ግን የቤት እና የጉልበት ሠራተኞችን በመላክ ላይ መሆን የለበትም፡፡ የሰለጠነና የተማረ የሰው ሀይል መላክ ላይ ማተኮር ይኖርበታል፡፡ በውጭ ሀገሮች የሥራ እድል የሚፈጠርላቸው ዜጎች የተማሩ በሆኑ ቁጥር የሚመለሱት ገንዘብ ብቻ ይዘው ሳይሆን ከቴክኖሎጂ ተዋውቀው፣ እውቀት ቀስመውና ልምድ አዳብረው ነው፡፡ በመሆኑም ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ የራሳቸውን ሥራ ለመፍጠር ከመቻላቸውም በላይ ለሌሎች ዜጎችም የሥራ እድል ይፈጥራሉ፡፡

በእዚህ አይነቱ ሥራ ለመሰማራት ዜጎች በየግላቸው የሚያደርጉት ጥረት እንዳለ ሆኖ መንግሥት ለተማሩ ዜጎች በውጭ ሀገሮች የሥራ እድል ለመፍጠር የበኩሉን ጥረት ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ሀገራችን በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ መስኮች ወጣቶች ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመርቀው ቁጭ የሚሉባት ሆናለች፡፡ ስለሆነም እነዚህ ዜጎች በውጭ ሀገሮች የሥራ እድል ማግኘት የሚችሉበትን ሁኔታ መንግሥት ሊያስብበት ይገባል፡፡ ለእዚህም ከቻይና እና ከህንድ ተሞክሮ መቅሰም ያስፈልጋል፡፡

ኢትዮጵያውያን የህክምና ባለሙያዎች በአህጉራችንና በተቀረው የአለም ክፍልም ይፈልጋሉ፡፡ ምንም እንኳ ሀገሪቱ የሚያስፈልጋት የሀኪም መጠን ላይ ገና ያልተሠራ ቢሆንም አሁን ተመርቀው በየቤታቸው እየተቀመጡ ካሉት ሀኪሞች አንጻር ሲታይ ለእነዚህ ዜጎች በውጭ ሀገሮች የሥራ እድል መፈልግ አንድ አማራጭ ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል፡፡ በምህንድስና ባለሙያዎች በኩልም ተመሳሳይ ችግር ይስተዋላልና ሊፈታ ይገባዋል፡፡

በአጠቃላይ ከላይ የተጠቀሱት ሁኔታዎች ለተማሩ ዜጎች በውጭ ሀገራት ሥራ የመፈለግን አስፈላጊነት ያስገነዝባል፡፡ ስለሆነም በዚህ ላይ በትኩረት በመስራት ለዜጎች የሥራ እድል የማስገኘቱን ጥረት ማጠናከር ይገባል፡፡

አዲስ ዘመን ሐምሌ 30/2011