የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁነኛ ፈተና

22

 ብሪታኒያ እእአ በ2016 በህዝበ ውሳኔ ከአውሮፓ ህብረት ጋር ለመፋታት ከወሰነች ማግስት አንስቶ ባለፉት ሦስት ዓመታት ሶስት ጠቅላይ ሚኒስትሮችን ለመቀያየር ተገዳለች። ‹‹ከአንድነት ይልቅ ልዩነቱ ይበጀኛል›› በሚል የመረጠችው የብሬግዚት ጣጣ ዴቪድ ካሜሩንን አሰናብታ ተሬሳ ሜይን እንድትተካ አስገድዷታል።፡

በታሪክ ሁለተኛዋን ሴት ጠቅላይ ሚኒስትር ስትመርጥም ፍላጎቷ እውን እንደሚሆን ጥርጥር አልነበራትም። እያደር የሆነው ግን የተቃራኒ ነበር። ሜይም አገራቸውን ከህብረቱ ማፋታቱን እንዳቀለሉት አልቀለላቸውም። በጉዳዩ ላይ ከፓርላማ አባላት ጋር ከስምምነት መድረስ ተስኗቸው በገዛ ፈቃዳቸው ስልጣናቸውን ለመልቀቅ ተገደዋል።

በመጡበት መንገድ የተመለሱትን ሜይ ለመተካትና በመንበረ ስልጣኑ ለመቀመጥ ከተመረጡት እጩዎች መካከል በተለይም ጀርሚ ሀንትና ቦሪስ ጆንስን ብርቱ ፉክክር አድርገዋል። በመጨረሻም የሃምሳ አምስት አመቱ ቦሪስ ጆንሰን 66 በመቶ ድምጽ በማግኘት የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

የብሬግዚት አቀንቃኙ የቀድሞ የለንደን ከተማ ከንቲባና የብሪታንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰንም ከቀናት በፊት በቤኪኒንጋሀም ፓላስ በተደረገ ስነስርዓት ኃላፊነቱን ከሜይ ተረክበው፣ ሹመታቸውን ከንግስት ኤልሳቤት ሁለተኛ ተቀብለዋል።

ከህዝበ ውሳኔው በኋላ ሶስተኛው የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት ጆንሰን፣ መንበረ ስልጣኑን በተረከቡ ማግስት ለንደን በሚገኘው የንግስት ኤልሳቤጥ ማዕከል ተገኝተው ‹‹የህዝቡን ስሜት አነቃቃለሁ፣በራስ የመተማመን መንፈሳችንን እንደገና እንመልሰዋለን›› ብለዋል። የብሬግዚትን አጀንዳ እንደሚያሳኩና የሃገሪቷን አንድነት እንደሚያስጠብቁም አረጋግጠዋል።

ጊዜ ሳያባክኑ አዲስ ካቤኔያቸውን በማዋቀር ቀደም ሲል 29 የነበረውን የአባላት ቁጥር ወደ 31 ከፍ አድርገዋል። ከነባር አባላቶች ግማሽ ያህሉን እንዳባረሩም፣ አንዳናዶቹም በገዛ ፈቃዳቸው ስራቸውን እንደለቀቁም ታውቋል።

አዲሱ ካቢኔም እንደ ጆንሰን ሁሉ አገሪቱን በተቻለ አቅም ከአውሮፓ ህብረት ማስወጣት ምርጫቸው ያደረጉ ግለሰቦች ስብስብ ሲሆን፣ የስብስቡ አባላት እእአ በ2016 በተካሄደው ሕዝበ ውሳኔ የእንገንጠል አቋም አቀናቃኞች ብሎም በቀድሞዋ ጠቅላይ ሚኒስትር ዘመነ ስልጣን አንድም የተገፉ አሊያም በራሳቸው ፈቃድ ስራቸውን የለቀቁ ሰለመሆናቸውም መረዳት ተችሏል።፡

በተለይ አገሪቱን ከአውሮፓ ህብረት መነጠልን የሚያቀነቅኑትና በጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲሱ ካቢኔ የአገር ውስጥ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው የተሾሞት ፐሪቱ ፓተል እና ዶሞኒካ ራብ እንዲሁም የብሬግዚት ዋና ፀሃፊዉ እስቲቪ ባርከሌይም ብሪታኒያን ከሕብረቱ የማፋታት አጀንዳን ዳር ለማድረስ ዋነኞቹ ተዋናዮች ሰለመሆናቸው ተጠቁሟል።

በካቢኔ አባላቱ ውቅር የተነሳም የብሪታኒያው ትራምፕ በሚል ቅፅል መጠራት የጀመሩት ጆነስን፣ የብሬግዚትን አጀንዳ ዳር ለማድረስ መቁረጣቸው በቂ ማስረጃ ሆኖ በመቅረብ የአንዳንዶችን አድናቆት አስገኝቶላቸዋል። ከዚህ በተቃራኒው አውሮፓዊነትን በሚያቀነቁኑት ዘንድ ቅቡልነትን አግኝቷል።

ከሁሉም በላይ ግን በመጪው የፈረንጆቹ ጥቅምት መጨረሻ አገራቸውን ከአውሮፓ ህብረት ለማፋታት የቆረጡትና ‹‹ይሕን በማድረግም አገሪቱን ወደ ቀደመ ሃያልነቷ እንመልሳታልን›› ሲሉ የተደምጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ካለስምምነት ከህብረቱ መፋታትን አዋጭ አድርገው መመልከ ታቸውንም በርካቶች መጪው ጊዚ ለብሪታኒያ ከባድ ስለመሆኑ እንዲገምቱና እንዲሰጉ አድርጓቸዋል።

ይሕን እሳቤ የሚጋሩ መገናኛ ብዙሃን፣የፖለቲካ ጠቢባንና በርካታ የሌበር ፓርቲ አመራሮች ‹ካለስምምነት ብሪታንያን በተቀመጠላት የጊዜ ቀጠሮ ከአውሮፓ ህብረት ማስወጣት ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚያቀሉት ቀላል አይደለም›› በሚል ጠንካራ አስተያየትና አቋማቸውን በማንፀባረቅ ተጠምደዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ አቋም በአንዳንዶች ቢደገፍም ነቃፊዎቹም በርክተዋል። ይህን ዋቢ የሚያደርጉት የፖለቲካና ኢኮኖሚ ምሁራን፣ይሕ ሰፊ ልዩነት ምናልባትም ታሪክ ራሱን ደግሞ የብሪኤግዚት ጉዳይ ስልጣናቸውን የነጠቃቸው ሶስተኛው ጠቅላይ ሚኒስትር ሊያደርጋቸው እንደሚችል ስጋታቸውን አስቀምጠዋል።

በእርግጥም በአሁኑ ወቅት የአገሬ ሕዝብ ለብሬግዚት ጉዳይ በተለያየ አቅጣጫ ቆሞል። የጆንሰን አሸናፊነት በተነገረበት የለንደኑ ጉባኤ ማእከል ፊት ለፊት የፍቺው ደጋፊና ተቃዋሚዎች መፈክርና ሰንደቅ አላማ ይዘው መታየታቸውም ልዩነቱን በገሃድ አስመስክሯል።

መሰል ልዩነቶችንና ብሪታንያን ከአውሮፓ ህብረት የማስወጣት የፍቺ አጀንዳ ውስብስበነትን ዋቢ የሚያደርጉት ጸኃፍትም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀጣይ ፈተና የብሪኤግዚት አጀንዳ ሰለመሆኑ አስምረውበታል። ይሕን እሳቤ የሚጋሩት እንደ ስቴፈን ካስትልና ቤንጃሚን ሙለር አይነት የኒውዮርክ ታይምስ ፀኃፍቶችም፣ጆንሰን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገሪቱ በጥልቅ ቀውስ ውስጥ ባለችበት በዚህ ወቅት ከባድ ኃላፊነት መረከባቸውን አትተዋል።

የአሶሺየትድ ፕሬሱ ጅሊ ሎውለስና ዴኒሺያ ኪርካ በበኩላቸው ‹‹ብሪታንያ ከአውሮፓ ህብረት ጋር የፍቺ ስምምነት ላይ ባትደርስም በተቀመጠላት የጊዜ ሰሌዳ ትለያያለች›› የሚል አቋም ያላቸው የብሬግዚት አቀንቃኙ ሰው፣ በፍቺው ሂደት በእጅጉ እንደሚፈተኑ አትተዋል።

የብሬግዚት አጀንዳን የሚቃወሙ በርካታ የወግ አጥባቂ ፓርቲና የካቢኔ አባላትም ስራቸውን በራሳቸው ፍቃድ እንደሚለቁ እስከመግለጽ የደረሱትና አገሪቱም በፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ውስጥ መሆኗን ያመላከቱት ፀሃፍቶቹ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፍቺውን በተቀመጠላት የጊዜ ሰሌዳ ለማስፈፀም የሚቀራቸው የሶስት ወራት እድሜ ብቻ መሆኑን ያመለክታሉ።

የለንደንን ከህብረቱ የመፋታት ውጥን የሚደግፉት ሳይቀር ያለምንም ስምምነት ፍቺውን መፈፀም አደጋ ከባድ ነው፤ይህን ለማስቀረትም አማራጮችን መቃኘት ያስፈልጋል የሚል አቋም አንፀባርቀዋል። ስኮትላንድም ከዚህ እሳቤ አራማጆች መካከል ግንባር ቀደም ሆኖ ተቀምጣለች።

ያለምንም ስምምነት ፍቺውን መፈፀም በተለይም በአለም ኢኮኖሚ እድገት አምስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠችውን አገር ኢኮኖሚ በእጅጉ እንደሚጎዳ የሚያሳስቡም አልጠፉም። አንዳንድ ኢኮኖሚስቶች፣ ካለስምምነት ከህብረቱ መፋታት ንግድን በማዛባት አገሪቱን ለኪሳራ የሚጥል መሆኑን አስምረውበታል። ገና ከወዲሁ ፓውንድ አቅም መዳከምንም ለዋቢነት አንስተዋል። የአገሪቱ ታላላቅ ኩባንዎችም በፍቺው ጣጣ ስጋት ተደቅኖባቸወ መተማመኛ ሰለማጣታቸው ሲገልፁ ተደምጠዋል።

ከዚህ በአንፃሩ ጆንሰን በቀሪ ወራት ውስጥ ከአውሮፓ ህብረት ጋር ከስምምነት በመድረስ ለብሬግዚት መፍትሄ እንደሚሰጡ የሚተማመኑም አልጠፉም። ከእነዚህም አንዱ ተሰናባቿን ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬዛ ሜይን የብሬግዚት አጀንዳ አፈፃፀምና ብቃት በተደጋገሚ ሲተቹ የነበሩት ዶናልድ ትራምፕ ናቸው።

ቦሪስ ጆንሰን ብቃቱም ጥበቡም እንዳላቸው በመመስከር የተሻለ መስራት እንደሚችሉ እምነታቸው መሆኑን የተናገሩት ትራምፕ፣አዲሱ ጠቅላይ ሚኒትር አገሪቱ ከአውሮፓ ህብረት የምትለያይበትን የተሻለ መንገድ ሊቀይሱ ይችላሉ የሚል ተስፋ ጥለውባቸዋል። የነጩ ቤተ መንግስት የኢኮኖሚ አማካሪ ላሪ ኩድሎው የፕሬዚዳንታቸውን ሃሳብ በመጋራት ‹‹ጆንሰን ለብሬግዚት ጉዳይ መቋጫ ይሰጡታል›› ብለዋል።

ምንም እንኳን በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተስፋ የሚጥሉ ባይጠፉም አቅማቸውን የሚጠራጠሩም አሉ። በዚህ ረገድ ከብሬግዚት መታወጅ መልስ ቀውስ ውስጥ የምትገኘው አገር በአሁኑ ወቅት ከፈተናዎቹ የሚገላግላት ሁነኛ ሰው እየናፈቀች ስለመሆኑ ያተተው እስቴፈን ግሎቨርም፣ ጆንሰን ይህ አቅም ይኖረው ይሆን ሲል በተደጋጋሚ ራሴን ጠይቄአለሁ ፣ይሁንና ለጥያቄው ቀላል የሆነ መልስ አላገኘሁም፣ ሆኖም ተስፋ አደርጋለሁ›› ሲል ዴይሊ ሜል ላይ ጽፋል።

ምንም እንኳን አሁን ሁነኛው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፈተና የብሪኤግዚት አጀንዳን ማስፈፀም ቢሆንም፣ መረሳት የሌለባቸው ሌሎች ፈተናዎች መኖራቸውም ተጠቁመዋል። ከእነዚህ መካከልም የአገሪቱን ኢኮኖሚ ማጎልበት፣ በውጭ ግንኙነት ትስስር ደግሞ ብሪታኒያ ከኢራን ጋር የገባችበትን ፍጥጫ ፈር ማስያዝና ከዋሽንግተን ጋር የነበራትን ፍቅር ዳግም ማደስም ዋንኞቹ መሆናቸው ተብራርቷል።

በብሪታኒያ የሚገኑ የአውሮፓ ህብረት አባል አገራት ዜጎች ጉዳይ በፍቺው ሂደት ላይ አንድ መደራደሪያ አጀንዳ መሆኑም ሌላኛው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፈተና መሆኑም ተጠቁሟል። ሰውየው ግን ገና ከወዲሁ በእነዚህና በሌሎችም ስደተኞች ጉዳይ ላይ የተለሳለሰ አቋም አሳይተዋል።

በስደተኞች አቀባበል ላይ ማሻሻያ እንደሚደረግ ከመግለፅ ባለፈ በአገሪቱ ለሚኖሩ ሶስት ነጥብ ሁለት ሚሊየን የአውሮፓ ህብረት አባል አገራት ዜጎችና ከተለያዩ አገራት የፈለሱ ከአምስት መቶ ሺ በላይ ሰነድ አልባ ህገ ወጥ ስደተኞች የመኖሪያ ዋስትና ሰጥተዋል።

ምንም እንኳን በአሁኑ ወቅት ካለ ስምምነት ፍቺውን ማስፈፀም ከባድ መሆኑን የሚያስረዱ በርካታ ቢሆኑም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን ሁሉን አቅልለው ‹‹ለብሪታኒያ ወርቃማ ጊዜ መጥቷል›› እያሉ ናቸው። ጆንሰን ቃል በገቡት መሰረት አገሪቱ ከአውሮፓ ህብረት ከመጪው የፈረንጆቹ ወር መጨረሻ ቀድማ እንድትወጣ ጉዳዩን የሞት ሽረት አድርገው እንደሚገፉበት አያጠራጥርም።

ከሁሉም በላይ ግን ብሪታንያን ካለስምምነት ከህብረቱ የመፋታት ሃሳባቸውን ተቀባይ አማራጭ የሚሉትን በማቅረብ ነቃፊዎቻቸውን ከማንበርከክ ባለፈ በአገሪቱ ፓርላማ ፊት ቆመው መሞገታቸው አይቀሬ ነው።

ሰውየው ከሕብረቱ ጋር በፍቺው ሂደት ስምምነት ላይ መድረስ ካልቻሉና ሁሉም አማራጮቻቸው ውድቅ ከሆኑባቸው ደግሞ ምናልባትም የብሪኤግዚት ጉዳይ ስልጣናቸውን የነጠቃቸው ሶስተኛው የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆናቸው ሳይታለም የተፈታ ይሆናል።

አዲስ ዘመን ሐምሌ 30/2011

 በታምራት ተስፋዬ