የዓለማችን ሌላኛው ስጋት- የኮሌራ ወረርሽኝ

21

የኮሌራ በሽታ በዓለም ዙሪያ ከምን ጊዜውም በላይ እየተስፋፋ መምጣቱ ይነገራል። የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ገለፃ፤ በሽታው ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ውስጥ የበርካቶችን ህይወት አመሳቅሏል። የአገራት ኢኮኖሚ መሰናክልም ሆኗል። በተለይም እአአ በ2016ና 2017 ወረርሽኙ በስፋት የተስተዋለባቸው አገራት የአሜሪካዋ ሃይቲን ጨምሮ የመን፤ ታንዛኒያ፤ ኮንጎና ሶማሊያ ተጠቃሽ ናቸው። አፍጋኒስታንና ኢራቅም ወረርሽኙ መከሰቱን የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያመላክታል።

ከቀናት በፊት የወጣ አዲስ መረጃ እንደ ሚያመለክተው ደግሞ ከምርጫ ውዝግብ ያልወጣችው አገር ዚምባቡዌ የኮሌራ በሽታ እየፈተናት መሆኑ ታውቋል። በቀናት ውስጥም በሽታው ሃያ አንድ የአገሪቱ ዜጎችን ህይወት እንደቀጠፈ ተነግሯል። ከአገሪቱ ጤና ቢሮ በወጣ መረጃ መሰረት ሦስት ሺ ዜጎች በበሽታው የተጠቁ ሲሆን፣ በዋና ከተማዋ ሐራሬ ጭምር በሽታው እየተስፋፋ መሆኑ ተገልጿል። የአገሪቱ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር ኦባዲ ሆሞዮ ለመገናኛ ብዙኃን እንደገለፁት፣ እአአ ከ2008 በኋላ በአገሪቱ አስከፊ የሆነ የኮሌራ ወረርሽኝ ተከስቷል። ይህንንም አውቆ የአገሪቱ ዜጋ መንግሥት የሚያስተላልፈውን በመከተል ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥሪ አስተላልፈዋል።

ከአስር ዓመት በፊት በሮበርት ሙጋቤ የአገዛዝ ዘመን አራት ሺ የአገሪቱ ዜጎች ህይወታቸውን ሲነጠቁ ከአርባ ሺ በላይ የሚሆኑት የበሽታው ተጠቂ ሆነው ተመዝግቦ ነበር። አሁን ላይ የበሽታው የመስፋፋት መጠን ከ2008ቱ ልቆ መታየቱ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ስጋት ሆኗል። ይህ በሽታ በዋና ከተማዋ ሐራሬ መከሰቱ በሌሎች መሰረተ ልማት ባልተሟላላቸው አካባቢዎች የከፋ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል ተነግሯል።
የኮሌራ በሽታ ገዳይነቱ እየጨመረ መጥቶ አሁን ላይ በየዓመቱ በመቶ ሺ ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞት ምክንያት ሆኗል። በየመን የተባባሰውን ይህን ወረርሽኝ ለመታገል እየተሠራ መሆኑ ቢገለፅም መግታት ያልተቻለበት ደረጃ ላይ ይገኛል። በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ካልተፈጠረ በበሽታው ምክንያት ህይወታቸው የሚያልፍ ህፃናትን ቁጥር መቀነስ አዳጋች እንደሆነ የህፃናት አድን ድርጅት አስታውቋል።

ከምዕራቡ ዓለም ድሃዋ አገር የምትባለው ሃይቲ ሌላኛዋ በኮሌራ የሚንገላቱ ህዝቦች ያሉባት አገር ናት። በአገሪቱ በመጀመሪያ የኮሌራ ወረርሽኝ በ2010 በተከሰተውና የሁለት መቶ ሃያ ሺ ዜጎችን ህይወት በቀጠፈው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ በኋላ ነው። በሽታው በአገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ከተከሰተ ሰባት ዓመታትን ያሳለፈ ቢሆንም አሁንም ድረስ በፍጥነት እየተስፋፋና ለብዙዎች ህይወት ማለፍ ምክንያት እየሆነ ይገኛል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ጨምሮ በርካቶች አገሪቱን ከኮሌራ ለመታደግ እየሠሩ እንደሆነ ቢገለፅም ማቆም የተቻላቸው አይመስልም። የኮሌራ በሽታ ከዚህ በላይ የከፋ ጥፋት ከማስከተሉ በፊት ለመከላከልና ወረርሽኙን ለመቀነስ በዓለም ዙሪያ ያሉ የጤና ኃላፊዎች ባሳለፍነው ዓመት በፈረንሳይ መሰብሰባቸው ይታወሳል። ጉዳዩን አስመልክቶ የአገራት የጤና ኃላፊዎች የዓለም የጤና ድርጅት በጎ አድራጊና ለጋሽ ድርጅቶች በጋራ ሲሰባሰቡም የመጀመሪያው ነበር። በጉባዔው እስከ 2030 ድረስ ባለው አስራ ሁለት ዓመታት ውስጥ የኮሌራ ወረርሽኝ መጠንን ዘጠና በመቶ ለመቀነስ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተደርጓል። የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም በሽታው በድህነት ውስጥ ያሉና ደካማ አገሮችን የሚያጠቃ እንደመሆኑ በጭራሽ ልንቀበለው የማይገባ መሆን አለበት ማለታቸው ይታወሳል።

የቀድሞ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ማርጋሪን ቻን የኮሌራ በሽታን በመከላከል ረገድ በሥልጣን በቆዩባቸው ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት የበሽታው መጠንና ስፋት እያደገ የመጣበት በመሆኑ ተገቢውን ትኩረት አልሰጡትም ተብለው ይወቀሳሉ። በእርግጥም ባለፉት ጊዜያት በበሽታው የተጠቁትን ለመድረስና የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት በተጋላጭ አካባቢዎች እንዲኖር ከሌሎች የተራድኦ ድርጅቶች ጭምር የሠራቸውን ሥራዎች ድርጅቱ ይገልፃል። ያም ሆኖ በሽታውን በማስቆም ረገድ ባለፉት ዓመታት በበሽታው ሳቢያ ህይወታቸው የሚያልፍ ዜጎች በተለይም የህፃናት ተጠቂነት ቁጥር መጨመር የተሠራው ሥራ ስኬታማ እንዳልነበር አመላካች ነው።

በኮሌራ ምክንያት የሚከሰት እያንዳንዱን ሞት በቀላሉ መከላከል እንደሚቻል የሚገልፁ ምሁራን ወረርሽኙን ለማስቆም የተቀረፀው ፍኖተ ካርታ ወሳኝ እንደሆነና ካለፈው ዓመት ጀምሮ ሊተገበር እንደሚገባ ሲናገሩ ቆይተዋል።

በአውሮፓና ሰሜን አሜሪካ አገራት ላለፉት በርካታ አስር ዓመታት ከኮሌራ ነፃ ሆነው መቆየት የቻሉት በንፅህናና የንፁህ ውሃ አቅርቦት ላይ በቀረፁት ፖሊሲ እንደሆነ የጤና ድርጅቱ ይገልፃል። በአገራቱ አንድ ዜጋ በማንኛውም ጊዜ ንፁህ ውሃ ማግኘት ሰብዓዊ መብቱ እንደሆነ ይቆጠራል። አሁንም ድረስ ደህንነቱ የተጠበቀ ውሃ የማያገኙ ከሁለት ቢሊዮን በላይ ዜጎች በዓለም ዙሪያ መኖራቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በፍኖተ ካርታው የንፁህ ውሃ አቅርቦት ተደራሽ ነትን ለማስፋት ከታቀዱ ሥራዎች በተጨማሪም የኮሌራ መከላከያ ክትባት ተደራሽ እንዲሆን ይሠራል ተብሏል። በአሁኑ ወቅት በስድስት የአሜሪካን ዶላር የሚገዛው የአንድ ሰው ክትባት በተከታታይ ሦስት ዓመታት ከበሽታው ለመከላከል ያስችላል። የዚህ ክትባት ተደራሽነት በተለይም በኮሌራ ምክንያት የሚከሰተውን የህፃናት ሞት በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ታምኗል።

ፍኖተ ካርታውን ለመተግበር አገራት፤ ለጋሾችና ቴክኒካዊ አጋሮች በጋራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል። ይህ ከሆነ ጦርነትና ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች በሽታው በተስፋፋባቸው እንደ የመን ያሉ አገራት ጭምር ውጤታማ ሊሆን እንደሚችል ይታመናል።

ድርጅቱ ከዓመት በፊት ያወጣው መረጃ እንደሚያመላክተው በአንድ ዓመት ህንድ ውስጥ ብቻ ስድስት መቶ ሰባ አምስት ሺ አንድ መቶ ሰማንያ ስምንት ሰዎች በኮሌራ በሽታ ይያዛሉ። ከነዚህም መካከል ከሃያ ሺ ሁለት መቶ በላይ የሚሆኑት እጣ ፋንታቸው ሞት ነው። በሃይቲ ሁለት መቶ አስራ አንድ ሺ የሚሆኑ ሰዎች በዓመት በበሽታው ሲጠቁ ከሁለት ሺ አምስት መቶ በላይ የሚሆኑት ህይወታቸው አልፏል። በናይጄሪያ ከሁለት መቶ ሃያ ሺ ሰዎች በላይ በዚሁ በሽታ ተጠቅተው ከስምንት ሺ በላይ የሚሆኑት ሞተዋል። በኢትዮጵያም ከሁለት መቶ ሰባ አምስት ሺ በላይ ሰዎች ተጠቅተው ከአስር ሺ በላይ የሚሆኑት ህይወታቸው እንደሚያልፍ መረጃዎች ያመለክታሉ።

በተጠቀሱት አገራት ወረርሽኙ ምን ያህል እንደተንሰራፋ ከመረጃዎቹ መረዳት ቢቻልም በየመን ያለው ቀውስ ግን ከነዚህም አገራት በእጅጉ የከፋ ነው። በእርስ በርስ ጦርነት እየታመሰች የምትገኘው የመን በዓመት ሰባት መቶ ሰባ ያህል ዜጎቿ በኮሌራ ይጠቃሉ። አፋጣኝ እርዳታና ህክምናን በቀላሉ ማግኘት የተሳናቸውም በበሽታው ምክንያት ከሁለት ሺ በላይ ሰዎች ህይወታቸው ይቀጠፋል። ከነዚህ መካከል አብዛኛውን ቁጥር የሚይዙት ህፃናት መሆናቸው ደግሞ ሁኔታውን አሰቃቂ ያደርገዋል።

አውሮፓና አሜሪካ ይህን በሽታ መቆጣጠር የቻሉት ከመቶ ሃምሳ ዓመታት በፊት እንደሆነ የቢቢሲ መረጃ ያመለክታል።
በዓለም ጤና ድርጅት የኮሌራ ፕሮግራም መሪ የሆኑት ዶክተር ዶሚኒክ ሊግሮስ ከዓመት በፊት «በበሽታው ይህን ያህል የተጋነነ ወረርሽኝ በየዓመቱ መመልከት አንፈልግም፤ ወረርሽኙን የማጥፊያው መሳሪያ በእጃችን ይገኛል፤ እንጠቀምበት፤ ንፁህ ውሃና ሳኒቴሽን ካለ በሽታውን በቀላሉ እንዳይስፋፋ ማድረግ እንችላለን» በማለት መናገራቸው ይታወሳል።

አዲስ ዘመን ታህሳስ 6/2011

ቦጋለ አበበ