ጥራት የሌላቸው የሶላር ኢነርጂ ምርቶች ወደ አገር እንዳይገቡ የሚመክት ሰነድ

11

በሶላር ኃይል ቴክኖሎጂ ላይ ባለፉት አምስት ዓመታት የግል ዘርፉ በስፋት እየገባበት መሆኑ ታይቷል። በተመሳሳይ ደግሞ ህብረተሰቡ ኃይል የሚገኝበትን አማራጭ ለማስፋት ሲል በሶላር ኃይል የሚያገለግሉ ምርቶች ላይ ፍላጎቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱም እሙን ነው። ይሁንና በተጭበረበረ የሶላር ኃይል ምርት ተጠቃሚው፣ አስመጪውና አገርም አንዳንዴ ሲጎዱ ይስተዋላል። ይህ እንዳይሆን ግን አንድ ፕሮግራም ተነድፎ እንደ አገር ሰነድ ተዘጋጅቷል። በሰነዱ ላይም ውይይት እየተደረገበትና ግብዓትም እተሰበሰበበት ይገኛል።

ይህ ፕሮግራም የሶላር ኃይል ምርቶች ወደ አገር ውስጥ ከመግባታቸው አሊያም ወደ ኢትዮጵያ ከመላካቸው በፊት ሀገሪቱ ካወጣቻቸው ደረጃዎች ጋር የሚጣጣሙ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ (Pre-Export Verifica­tion of Conformity) (ፒቪኦሲ) በመባል የሚጠራ ሲስተም ነው።

ፕሮግራሙ የምርቱ ተጠቃሚዎች፣ አስመጪዎችና አገርም እንዳይጎዱና ተጠቃሚውም ለሚያወጣው ገንዘብ ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኝ የሚያግዝ እንደሆነም ይገለፃል። ፕሮግራሙን በዋናነት የሚመራው የቴክኒክ ኮሚቴም ከሚመለከታቸው የተለያዩ ተቋማት በተውጣጡ አባላት የተዋቀረ ነው፤ ሰነዱን ለማዘጋጀት የአገራት ተሞክሮዎች መቀመራቸውንም ሰሞኑን በቢሾፍቱ ከተማ ሰነዱ ለባለድርሻ አካላት በቀረበበት ወርክሾፕ ላይ ተጠቁሟል።

በአሁኑ ወቅት የአገሪቱ ትልቁ ችግር እየተፈጠረ ያለው ወደ አገሪቱ እየገቡ በሚገኙት በተለይ ደግሞ ከአስር ዋት በላይ ባሉት የሶላር ኃይል ምርቶች ላይ ነው። እስከ አስር ዋት በአገር ውስጥ ለመፈተሽ ተሞክሯል። ከዛ በላይ የሆኑት ግን እየገቡ ያሉት በውጭ አገር ላቦራቶሪዎች ተፈትነው ነው በሚል በእምነት ነው። ይህ አሰራር በአሁኑ ወቅት ሲታይ በአገሪቱ ውስጥ ከደረጃ በታች የሆኑ የሶላር ኃይል ምርቶች ተስፋፍተው እንዲታዩ ያደረገ ሆኗል።

የቴክኒክ ኮሚቴው አባል የኢትዮጵያ ኢነርጂ ባለስልጣኑ አቶ ዘውገ ወርቁ፤ሰነድ ማዘጋጀት ያስፈለገበት አንዱ ምክንያት የሶላር ኃይል ምርቶችን የሚያስመጡ አካላት እየገጠማቸው ያለው ችግር መሆኑን ይገልጻሉ። በመሆኑም ችግሩን ወጥ በሆነ መልኩ ለመፍታት ታስቦ የተለያዩ አገራትን ልምድ በመቀመር ሰነዱ መዘጋጀቱን ያመለክታሉ።

ፒቪኦሲ የሶላር ኢነርጂዎች ወደ አገር ውስጥ ከመግባታቸው አሊያም ወደ ኢትዮጵያ ከመላካቸው በፊት ከወጡ ደረጃዎች ጋር የሚጣጣሙ ስለመሆናቸው ማረጋገጫ የሚደረግበት ሲስተም ነው። ገና ወደ አገር ውስጥ ከመግባታቸው በፊት እዛው ምርቱ ባለበት አገር ላይ እያለ ምርቱ ጤናማ መሆኑን ማረጋገጥ እንዲሁም ኢትዮጵያ ካለው ደረጃ ጋር የሚጣጣም መሆኑን ማረጋገጥ ማለት ነው። ይህ ፒቪኦሲ ብዙ ጊዜ ተግባራዊ የሚደረገው በአፍሪካና በኢስያ አገራት ውስጥ እንደሆነም ነው አቶ ዘውገ የሚገልፁት።

 አቶ ዘውገ እንዳብራሩት፤ፒቪኦሲ የሚያስፈልግበት አንዱ ምክንያት አገሮች ጥራታቸው ከደረጃ በታች የሆኑ ምርቶችን የሚፈትሹበት አቅም ዝቅተኛ ሲሆን ነው። አሁን ባለው ሁኔታ ይህ ፒቪኦሲ የተዘጋጀው በዋናነት እስከ 350 ዋት ድረስ ላሉ የሶላር ኃይል ምርቶች ሲሆን፣ በእርሱ ላይ የሚተገበር ፕሮግራም ነው።

‹‹ላለፉት ስምንት ዓመታት ችግር እንደነበር አስመጪዎች አሳምረው ያውቃሉ፤ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የምርቱ የጥራት ደረጃን ለይቶ ለማወቅ በአገራችን ያለው ፍተሻ ውስን መሆኑ ነው።›› የሚሉት አቶ ዘውገ፣ በአገር ውስጥ ፍተሻ ለማድረግ መሞከሩንም ይጠቅሳሉ። ‹‹እሱም ብዙ ችግር አጋጥሞታል። ፍተሻው ራሱ እስከ ሶስትና አራት ወር ድረስ የሚቆይና አስቸጋሪም ነበር። በባለሙያ በኩልም ውስንነት ያለው በመሆኑ ችግሩን ለመፍታት ፒቪኦሲ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።›› ብለዋል።

የፒቪኦሲ ዓላማ ከሆኑት መካከል አንዱ ተገልጋዩን ከጤና፣ ከደህንነት፣ ከአካባቢ አየር ብክለት አንፃር መከላከል ነው። ሁለተኛው ደግሞ ከደረጃ በታች የሆኑ ምርቶች ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ እዛው ውጭ አገር እያሉ መከላከል ነው።

ከደረጃ በታች በሆኑ ምርቶች ላይ ተፅዕኖ ለመፍጠር ፒቪኦሲ ነገሮችን እንደሚያቀል ጠቅሰው፤ ‹‹በጥቅሉ የፍተሻ ስርዓቱ እንደ አገር ስለሌለን ሰነዱን ተግባራዊ ለማድረግ ነው በመንቀሳቀስ ላይ ያለነው።›› ይላሉ። በአሁኑ ወቅትም አንዳንድ ምርቶች ላይ ተግባራዊ ለማድረግ እቅድ መያዙን፣ የሚመለከተውም እስከ 350 ዋት ያሉ የሶላር ምርቶችን ብቻ መሆኑን ይጠቁማሉ።

እንዴት ተግባራዊ ይደረጋል? ሂደቱስ ምን ይመስላል? በሚለው ላይ ማብራሪያ ሲሰጡ እንደገለፁት፤ ምርቱን ወደ አገር ውስጥ ሊያስገባ የፈለገ አንድ ላኪ በመጀመሪያ ማድረግ ያለበትና ከእርሱ የሚጠበቀው ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከመረጠው የፒቪኦሲ ኩባንያ ጋር በመነጋገር ማመልከቻ ማስገባት ነው። ይህን የሚያደርጉት የሲኦሲ

 coc) ሰርተፍኬት ለማግኘት ሲባል ነው። ይህም ማለት ምርቱ ከኢትዮጵያ ደረጃ ጋር የሚጣጣም ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ለመለየት እንዲያስችለው ውል ማድረግ ማለት ነው። ሰርተፍኬቱን ሲጠይቅ ለኩባንያው የሚያቀርባቸው ሰነዶች አሉ አንዱ ፋክቱር (ኢንቮይስ) ነው። ይህም ማለት የሚያመርተውን የምርት አይነት፣ ዋጋና መሰል ነገሮችን የያዘ መረጃ ለፒቪኦሲ ኩባንያ መስጠት ነው። ያመረተውን እቃ ከደረጃው ጋር መጣጣሙን ለማወቅ እንዲያስችል አቀማመጡንም ይገልፃል።

ላኪው ክፍል ሲኦሲውን ለማግኘት ሶስት ዋና ዋና ጉዳዮች ይታያሉ። ለሶስቱም የተለያየ ክፍያ ይፈጸማል። በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተመረጠው የፒቪኦሲ ኩባንያ፣ በላኪው የቀረቡትን ሰነዶች በመመርመር እና ከኢትዮጵያ ደረጃ ጋር ተስማሚ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይጠበቅበታል።

ላኪው ያቀረበው ሰነድ ልክ ከሆነ የማረጋገጫ ሰርፍኬት ይሰጠዋል። ካላደረገ ደግሞ የተረጋገጠ አለመሆኑን የሚያሳይ ሰርተፍኬት ይሰጠዋል። ምርቱ ማጋገጫ ካገኘ ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ ፈቃድ ይሰጠዋል ማለት ነው።

አቶ ዘውገ እንደሚናገሩት፤ በዚህ ፕሮግራም ላይ ተቋማት የተለያየ ኃላፊነት ያላቸው ሲሆን፣ ከአነዚህም ኃላፊነቶች መካከል ለምሳሌ አስመጪዎች ወይም አቅራቢዎች ምርቱን ወደአገር ውስጥ ከማስገባታቸው በፊት ነጋዴው ማለትም ላኪው የሲኦሲ ሰርተፍኬት እንዳለውና እንደሌለው ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል።

ላኪው ወይም ነጋዴው ደግሞ ምርቱን ወደ ኢትዮጵያ ከመላኩ በፊት የኢትዮጵያን ደረጃ የያዘ ስለመሆኑ ማረጋገጥና ትክክለኛ ሰርተፍኬት መያዝ ይጠበቅበታል። ሌሎቹ ደግሞ በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተመረጡ የፒቪኦሲ አጋሮች ዋና ስራቸው የፍተሻና የቁጥጥር ስራ መስራት ነው። ለመፈተሽም ማሳያ ይወስዳሉ። ከዛም ለማረጋገጫ ሰርተፍኬት ይሰጣሉ።

ሌላው ኃላፊነት ያለበት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ይሆናል። ባንኩ መመሪያ ይሰጣል፤ ይህ የመመሪያ አቅጣጫ ደግሞ ለሁሉም ባንክ ይደርሳል። ባንኮች መረጃው ስለሚደርሳቸው ላኪዎች ሲኦሲ ከሌላቸው ወደአገር ውስጥ ማስገባት አይችሉም። የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ ኃላፊነት ደግሞ ሲኦሲ ለያዘ ኩባንያ የጥራት ምልክት ማድረግ ነው።

እርሳቸው እንዳብራሩት፤ ዋናውን ስራ የሚሰራው የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ነው። ዋና ኃላፊነቱም ምርቶች ወደ አገር ውስጥ ሲገቡ ሲኦሲው ልክ ነው አይደለም የሚለውን መመርመር ነው። ሲኢሲ ይዞ የማይመጣ ኩባንያ ምርቱን እንደገና እንዲመልስ ያደርጋል። ምናልባትም ለአገሪቱ የአየር ሁኔታ ስጋት የማያመጣ ከሆነም እዚሁ እንዲወድም ይደረጋል።

የዚህ ፕሮግራም ዋና ጥቅም ተጠቃሚዎችን ደረጃውን ካልጠበቀ ምርት መታደግ ነው። የአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎችን በማስመሰል ከተሰራ ምርት ይጠብቃል። የተጭበረበረን ነገር ያስቀራል። ከደረጃ በታች የሆኑ ምርቶችን እና ሚዛናዊ ያልሆነ ፉክክርንም ያስቀራል። እንዲሁም ይህ የፒቪኦሲ ፕሮግራም የምርትንም ዋጋ የዚያን ያህል የሚጨምር አይሆንም። በተጨማሪም ፕሮግራሙ እውነተኛ የሆኑ ላኪዎችን የሚያበረታታ ነው።

በውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር በዩኤንዲፒ የገጠር ኢነርጂ ቴክኖሎጂ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ማናጀር አቶ ያሬድ ሹመቴ እንደሚናገሩት፤ ፕሮጀክቱ የተለያዩ ተግባሪ አካላት የሚሳተፉበትና በአገር አቀፍ ደረጃም የሚተገበርም ነው። ዩኤንዲፒ ለኢትዮጵያ መንግስት ድጋፍ በማድረግ የተለያዩ ስራዎችን አብሮ ይሰራል። ኢነርጂ በቀላሉ ሊያገኙ የማይችሉ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚያስፈልጋቸውን የኃይል አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉ የሚያስችላቸውን ስራ ይደግፋል።

የገጠር ማስፋፊያ ፕሮጀክት አራት ተግባራት ላይ እየሰራ ሲሆን፣ ዓላማውም በገጠሩ የአገሪቱ ክፍል የሚኖሩ የሕብረተሰብ ክፍሎች አማራጭ የኢነርጂ ቴክኖሎጂዎች እንዲደርሳቸው ማድረግ ነው። በተጨማሪም ህብረተሰቡ ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ ጥራት ያለው የሶላር ኃይል ምርት ገዝቶ መጠቀም እንዲያስችለውም ታስቦም አላማው የተቀመጠው። የቴክኖሎጂ አስመጪዎችና አከፋፋዮች ወደአገር ውስጥ የሚመጣው ምርት ጥራቱን የጠበቀ የቴክኖሎጂ ወጤቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያቀርቡ ለማስቻልም ነው።

‹‹ሌላው የፕሮጀክቱ የትኩረት አቅጣጫ ደግሞ ለቴክኖሎጂ አቅራቢዎች የሚደረገውን ድጋፍ ማጠናከር ነው።›› ሲሉ ገልፀው፤ ‹‹ይህን ፕሮጀክት ከሌሎች ፕሮጀክቶች በአቀራረብ የሚለየው የግሉ ዘርፍ ገበያው በፈቀደውና በመራው መንገድ ቴክኖሎጂዎች እንዲሰራጩ የሚያደርግ አካሄድ በመከተሉ ነው። በፕሮጀክቱ አስፈላጊውን የቴክኖሎጂ ውጤት ተጠቃሚው መርጦና በራሱ ወስኖ መግዛት እንዲችል የምናደርግበት የፕሮጀክት አተገባበር እንከተላለን ።›› ብለዋል።

አቶ ያሬድ እንደሚሉት፤ ፒቪኢሲ በሶላር ኃይል ምርቶች ላይ በአገር አቀፍ ደረጃ ያለውን የጥራት ጉድለት ችግር ለመፍታት የራሱ የሆነ ከፍተኛ ድርሻ አለው። ከዚህ በፊት የነበረው አካሄድና አተገባበር ላይ ምቹ ሁኔታዎች ለአስመጪዎችም ሆነ ዘርፉን ለሚመሩ ተቋማት እንዲሁም ለተለያዩ መስሪያ ቤቶች ምቹ ሁኔታዎችን ሊፈጥር የሚችል ሰነድ ነው።

እንደ ሚኒስቴር መስሪያ ቤትና እንደ ፕሮጀክት ቢሮ ስራው በሰነድ ደረጃ እንዳይቀር መሬት ላይ ወርዶ የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት እንዲችል የሚሰራ መሆኑን አቶ ያሬድ ይገልፃሉ። በተለይ በዋናነት ደግሞ ወደአገር ውስጥ የሚገቡ የሶላር ኃይል ውጤቶች ጥራታቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ እንዲሁም በተለያዩ የአገሪቱ ጠረፋማ አካባቢዎች የሚገቡ ጥራታቸውን ያልጠበቁ ምርቶች የሚቀንሱበትና በተቻለ መጠን ጥራቱ የጠበቀ የቴክኖሊጂ ውጤት ወደ ተጠቃሚው እንዲደርስ የሚያስችሉ ስራዎችን ለመስራት የእያንዳንዱ ባለድርሻ አካል ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑንም ያመለክታሉ።

በዕለቱ የተሳተፉ ባለድርሻዎች ቁልፍ የሚባሉ ተግባሪ አካላት መሆናቸውንም ጠቅሰው፤ ሰነዱን በመጠቀም ውጤታማ ስራ በአገር አቀፍ ደረጃ መስራት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል ብለው እንደሚያምኑ አስረድተዋል።

በውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የአማራጭ ኢነርጂ ዳይሬክተር አቶ አስረስ ወልደጊዮርጊስ ‹‹እኛ የገዛናቸው ትክክለኛ መሳሪያዎች መሆናቸውን የምንፈትሽበት የራሳችን ስታንዳርድ የለንም። የፀሐይ ኃይል መሳሪዎችን ግን እንጠቀማለን።››ይላሉ። ‹‹ሌሎች አገሮች ስታንዳርድ አላቸው በሚል ነው እየተጠቀምን ያለነው።›› የሚሉት አቶ አስረስ፣አሁን ሀገሪቱ የራሷን ስታንዳርድ እንደሚያስፈልጋት ታምኖበት የስታንዳርድ ደንብ እየወጣ መሆኑን ይገልጻሉ። ደንቡን ወደ ስራ ለማስገባት የሚያስፈልገው የህግ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ መሆኑንና በመጪው ዓመት እንደሚጠናቀቅ ይጠቁማሉ።

አዲስ ዘመን ሐምሌ 30/2011

አስቴር ኤልያስ