ዜጎችን ከእንግልት የሚታደገው የሥነ ሥርዓት ሕግ

19

ዜጎች የተለያዩ ጉዳዮችን ለማስፈፀም ወደ መንግሥታዊ ተቋማት ይሄዳሉ። ጉዳያቸውን በቀላሉ ለማስፈፀም መጉላላት ሲደርስባቸው ይታያል፡፡ ተገልጋዩን ችላ የሚሉ ፊት የሚነሱ የሚያመናጭቁ ሠራተኞችም ያጋጥማሉ።

በፌዴራል ደረጃ ይህን ብልሹ አስተዳደር ለመለወጥና ቢሮክራሲያዊ ውጣ ውረዶችን ለማስተካከል የሚያስችል ረቂቅ ሕግ ተዘጋጅቷል፡፡

በዚህ የፌዴራል የአስተዳደር ተቋሞች የአስተዳደር ሥነሥርዓት ረቂቅ አዋጅ ላይ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች አማካሪ ጉባዔ በቅርቡ የውይይት መድረክ ያካሄደ ሲሆን፣ በውይይቱም ላይ የሕግ ባለሙያዎች፣ ሲቪል ማህበራትና የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም የተለያዩ ማኅበረሰቦች ተሳትፈውበታል፡፡

የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች አማካሪ ጉባዔ ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ አብዱላጢፍ ከድር እንደገለፁት፤ረቂቅ አዋጁ ዜጎች በየእለቱ ከአስተዳደር ተቋማት ጋር በሚያደርጉት ግንኙነት በሚጠይቁት አገልግሎት እና በሚተላለፉባቸው አስተዳደራዊ ውሳኔዎች ዙሪያ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ይረዳል።

ረቂቅ አዋጁ መከላከያ፣ ፖሊስና ደህንነት የመሳሰሉትን የፀጥታ አካላት እንደማያካትት ጠቅሰው፣የፖሊስ ሥራ በዋናነት በወንጀል መከላከልና በወንጀል ምርመራ ሥራ ላይ ያተኮረ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ለእዚህም ዝርዝር የሆነ የወንጀለኛ መከላከያ ሥነ ሥርዓትና ሕግ እንዳለ ተናግረዋል፡፡ እነዚህ ተቋማት የራሳቸውን የሥነሥርዓት ህግ እያሻሻሉ እንደሚገኙና በቅርቡም ይፀድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።

የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት፣ የውሃና ፍሳሽ፣ ኢትዮ ቴሌኮም እና የመሳሰሉት አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም እንዲሁ ረቂቅ ሕጉ አይመለከታቸውም። ያልተካተቱበት ምክንያትም አገልግሎት ሰጪ በመሆናቸውና ወደ ግልም ሊዛወሩ ይችላሉ በሚል እሳቤ መሆኑ ከመድረኩ ተገልጿል።

የአስተዳደር ሥነሥርዓት ሕግ ፍትሐዊነትን ለማስፈን፣ የዜጎችን የመሰማት ዕድል ለማስፋት ግልፅነትና ገለልተኝነት ያለው የመንግሥት አሠራር ለመዘርጋት፣ እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ መርሆዎችን ለማስጠበቅ፣ የሕግ የበላይነትና ተጠያቂነትን ለማስፈን ይረዳል።

ክልሎች በዚህ ላይ ተመስርተው የራሳቸውን የአስተዳደር ሥነሥርዓት ህግ ማውጣት እንደሚችሉ የተጠቆመ ሲሆን፣ በፌዴራል ደረጃ የቤተሰብ ሕግ ሲሻሻል ክልሎችም የቤተሰብ ሕግ እንዳወጡ ሁሉ በፌዴራል ደረጃ የሚወጣውን ይህን ረቂቅ ሕግ እንደሞዴል ተጠቅመው ከራሳቸው ክልል ባህል ጋር በማጣጣም የራሳቸውን ሕግ ያወጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተጠቁሟል።

አቶ አብዱላጢፍ እንዳሉት፤ ክልሎች የራሳቸውን ሕጎች እንዲያወጡ የሚመ ለከታቸው አካላት መንቀሳቀስ አለባቸው። ሲቪል ማኅበረሰቦች፣ መገናኛ ብዙሃን፣ የመን ግሥት አካላትና የፓርቲ አመራሮች ክልሎችም ክፍተቱ ትልቅ ስለሆነ ለመሙላት ጥረት ማድረግ ይገባቸዋል።

ህጉ ተቋማት የሚያሳልፉት ውሳኔ እና የሚያወጡት መመሪያ በተቻለ መጠን ሁሉም ግልፅነት የተላበሰ እንዲሆን ያስገድዳል ያሉት አቶ አብዱላጢፍ፣ ይህም ተጠያቂነትን ለማስፈን እንደሚያስችል ይጠቁማሉ።

ተቋማት መመሪያ ሲያወጡ ቀጥታ አፅድቀው ወደ ሕዝብ መሄድ ሳይሆን ኅብረተሰቡን ማማከር እና ማወያየት እንዳለባቸው ጠቅሰው፣ ተጠያቂነት የሚያስከትሉ መመሪያዎችን ቀድሞ ለህዝብ አቅርቦ ማስገምገም እንደሚገባም ያስገነዝባሉ።

እንደ ምክትል ኃላፊው ማብራሪያ፤ አዋጁ ትልቁ የተጠያቂነት ሥርዓት የዳኝነት አስተዳደር ተቋማት ውሳኔ ሲያሳልፉ፣ በግለሰቦች ጉዳይ ላይ አጠቃላይ ድንጋጌ ወይም መመሪያ ሲያወጡ፣ ከሕግ ጋር የሚጋጭ ነገር ካለና የሰዎች መብት አላግባብ የሚጣስ ከሆነ፣ እነዚህ ዜጎች ፍርድ ቤት ሄደው ውሳኔዎቹን ማሻር የሚያስችላቸው ግልፅ የሆነ ሥነ ሥርዓት ያስቀምጣል ፤ይህም ዋነኛ የተጠያቂነት መገለጫ ነው።

የፖለቲካ ውሳኔ በባሕርይው በሕግ ያልተሸፈነ ነገር ማለት ነው የሚሉት አቶ አብዱላጢፍ፣ አንዳንድ ጊዜ ምናልባት ከዴሞክራሲና ሕገ መንግሥታዊ ባህል አለመዳበር ጋር ተያይዞ መሠረታዊ የሆኑ የአስተዳደር ጉዳዮች የፖለቲካ ውሳኔ ቢባሉም ይህ ግን ትልቅ ስህተት ነው ሲሉ ይናገራሉ።

‹‹ይህም በቅርብ ይስተካከላል ብለን እናስባለን›› የሚሉት ምክትል ኃላፊው፣ የሪፎርሙ ሂደት ከሚያስተካክላቸው አንዱም ይህ እንደሚሆን ተናግረዋል። አንድ ውሳኔ በሕግ የተቀመጠ ዋነኛ መለኪያ ወይስ የፖሊሲ አማራጭ አለው የሚለው ጉዳይ አንድ ነገር ነው። የፖለቲካ ጥያቄ የሚሆነው በሕግ ያልተሸፈነ ግልፅ ድንጋጌ መብትና ግልፅ መለኪያ ያልተቀመጠለት ሲሆን ነው በማለት አቶ አብዱላጢፍ ያብራራሉ ።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር ዶክተር መሐሪ ረዳ፣ የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች አማካሪ ጉባዔው አባል ናቸው። የአስተዳደር ሥነ ሥርዓት ረቂቅ አዋጅ ማለት የአስተዳደር ተቋማት በዕለት ተዕለት ሥራቸው ተገልጋዮችን ሲያስተናግዱ ሊከተሉት የሚገባውን ሥነ ሥርዓት የሚገዛ ሕግ ነው ሲሉ ይገልፃሉ።

‹‹እስካሁን የነበረው ሂደታችን የዘፈቀደ ነው›› የሚሉት ዶክተር መሐሪ ፣አቤቱታ ቀርቦ መቼ መልስ እንደሚገኝ እንደማይታወቅ፣ መልሱም በመረጃ እንደማይሰጥ ይገልጻሉ። አንዳንዴ በቃል በተላላኪ በፀሐፊ ይነገራል። ከእንደዚህ ዓይነት ሥርዓት ያልጠበቀ አካሄድ እንድንወጣ ዕድል የሚሰጥ ረቂቅ ነው ለውይይት የቀረበው ሲሉ አስረድተዋል።

ዶክተር መሀሪ የአቶ አብዱላጢፍን ሀሳብ በመጋራት የአስተዳደር ተቋማት ዜጎች ላይ ተፈፃሚ የሚሆኑ መመሪያዎችን ሲያወጡ መጀመሪያውኑ አሳትፈው ማውጣት አለባቸው ይላሉ። ሁለተኛ በሥልጣን የተሰጣቸውን ለማስፈፀም እንጂ አዲስ ግዴታ መጣል እንደሌለባቸውም ያመለክታሉ።

እንደ ዶክተር መሐሪ ማብራሪያ፤ መመሪያዎቹ ከወጡ በኋላ በመመሪያዎቹ ለሚገዙ ዜጎች ተደራሽ መሆን አለባቸው አሳትመው ሊያሠራጩ ወይ ድረገፃቸው ላይ ሊጭኑና ተደራሽ እንዲሆኑ ማድረግ ይገባል ። መደርደሪያ አልያም መሳቢያ ላይ ተቆልፎ ሲያስፈልግ ብቻ እያወጡ መልሰው እየቆለፉ የሚሄዱበት አሠራር የግልፀኝነት የፍትሐዊነት የብልሹ አስተዳደር ችግር ያስከትላል። በዚህ መንገድም መቀጠል አይገባም።

የአስተዳደር ውሳኔ በዕለት ተዕለት የሚያጋጥም ሊሆን ይችላል ፤ ካርታ ስጡኝ ብለው መንጃ ፈቃድ ለማደስ ወይ ለመቀበል የሚሄዱ ይኖራሉ። እነዚህ ነገሮች ከተሟሉ ለሁለት ሰው የተለያየ ውሳኔ ሊሰጥ አይገባም ።

አንዳንዴ ሁለት ሰዎች የሚጠበቅባቸውን አሟልተው ላንደኛው ሲሰጥ ለሌላኛው የሚከለከልበት ጊዜ አለ የሚሉት ዶክተር መሀሪ፣ እንደዚህ ዓይነት የዘፈቀደ አሠራር በትውውቅና በቅርርብ ከሚሠሩ አስተዳደራዊ አገልግሎት አሰጣጥ ልንወጣ ይገባል ይላሉ።

ውይይት የተደረገበት የፌዴራል የአስተዳደር ተቋሞች የአስተዳደር ሥነሥርዓት ረቂቅ አዋጅ ሁሉንም ይመለከታል፤ የመንግሥት ሠራተኛ በአንዳንድ ቦታ አገልግሎት ሰጪ ሲሆን ሌላ ቦታ ደግሞ አገልግሎት ተቀባይ ይሆናል።

ከሁለት ሳምንት በፊት ከመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የመጡ የሕግ ባለሙያዎች አወያይተናል ያሉት ዶክተር መሐሪ፣ ‹‹አዋጁ የፌዴራል ቢሆንም ወደ ክልሎች ሄደን ግብዓት እናሰባስባለን ፤ከክልሎች ጋር ምክክር ከተደረገበት አስፈላጊነቱን አምነውበት በራሳቸው የሕግ አወጣጥ ሥርዓት ሕጋቸው አድርገው ሊወጡት ይችላሉ ብለዋል።

ረቂቅ አዋጁ እንደመነሻ ሲዘጋጅ የነበሩ ችግሮችን ከግምት በማስገባት ነው የሚሉት ዶክተር መሐሪ፣ የመልካም አስተዳደር ችግር ለመፍታት መንግሥት ሲንቀሳቀስ በተለያየ መንገድ የተጀማመሩ ሥራዎች እንደነበሩ ይጠቅሳሉ።

ዶክተር መሐሪ ‹‹የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አስተዳደር ሥነ ሥርዓት ረቂቅ አውጥቶ ነበር። የዓለም ባንክም ጥናት አካሂዶ ነበር ፤ያለው የመልካም አስተዳደር ችግር ስፋቱና ጥልቀቱ ምን ይመስላል የሚለው ያ ጥናት የተወሰኑ መረጃዎች ነበሩት፡፡ እሱን ተከትለናል። ሕገ መንግሥቱ አለ፤ የመልካም አስተዳደር ስትራቴጂ የሚባሉም አሉ፤ እንደ ግብአት ተጠቅመንባቸዋል›› ሲሉ አብራርተዋል።

ረቂቅ አዋጁ ለዓቃቤ ሕግ እንደሚቀርብ ጠቅሰው፣ እነሱ ደግሞ ወደ ሚኒስትሮች ምክር ቤት እንደሚልኩት እና በሚኒስትሮች ምክር ቤት ታይቶ ማሻያያም አድርጎም ሆነ ባለበትም ካፀደቀው በኋላ አዋጅ ሆኖ እንዲወጣ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚላክ አብራርተዋል።

የውይይቱ ተሳታፊ የብሔራዊ ባንኩ አቶ ሙሉቀን ምህረቴ ረቂቅ ሕጉ ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ እንደቆየ ጠቅሰው፣ጥሩ ማዕከል እንዲኖረን ይረዳናል ሲሉ ገልፀዋል።

የአገው ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አገዴፓ ሊቀመንበር አቶ አንዱዓለም ጥላሁን የመንግሥት አስተዳደር በጣም በርካታና ውስብስብ የሆኑ ጉዳዮችን የህዝብ አገልግሎት የሚያገኙበት መሆኑን ጠቅሰው፣የብልሹ አስተዳደር ምንጭ ሆኖ ብዙዎች በመንግሥት ላይ ቅሬታ እንዲያሳድሩ ሲያደርግ እንደነበር ይጠቅሳሉ፡፡ውይይቱም በጣም ወሳኝ መሆኑንም ይግልጻሉ።

‹‹የድርጅት ማዕቀፍ አባላትን ብቻ ሊሆን ይችላል የሚያስተናግደው፤ መንግሥት ግን ሁሉንም የድርጅት አባል የሆነውንም ያልሆነውንም የሚቃወመውንም የሚደግፈውንም በሙሉ የማስተናገድ ኃላፊነት አለበት››ያሉት አቶ አንዱዓለም፣ህዝቡ እንዴትና በምን ዓይነት አግባብ ማስተናገድ እንዳለበት ሂደቶች ከተቀመጡለት የተጠያቂነት ሥርዓት እንደሚሰፍን ይናገራሉ፡፡ በሚፈለገው ጊዜና ወቅት የኅብረተሰቡ ጥያቄዎች ምላሽ እንደሚያገኙ እምነታቸው መሆኑን ይገልጻሉ ።

የኢትዮጵያ አንድነት አርበኞች ግንባርን በመወከል ተሳታፊ የነበሩት አቶ ጌታነህ ዘለቀ በሀገሪቷ ላይ ተንሰራፍቶ የኖረው ፍትሐዊ ያልሆነ አሰራር ጥሎት ማለፉን ጠቅሰው፣ ህጉ እንቅፋቶቹን ለማስወገድ እንደሚጠቅም ተናግረዋል።

ሕግ ከሌለ ሀገርም ሥርዓት የለም ያሉት አቶ ጌታነህ፣በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የተዘጋጁ ሰነዶች ለውጡን የሚያግዙና ወደፊት ለማስኬድ የሚረዱ ጥርጊያ መንገዶች ናቸው ሲሉ ያብራራሉ።

ከዚህ በፊት ለፖለቲካ ፓርቲዎች እንደዚህ ዓይነት የውይይት መድረክ አይከፈትም ነበር ያሉት ፣ በሚወጡ ህጎች ላይ አስተያየቶች መስጠት የሚያስችል ሁኔታ ቢኖር ችግር አይፈጠርም ነበር ይላሉ።

የካፋ አረንጓዴ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ወንድሙ ወደኤሮ ሕግ ተፈፃሚ እስከሆነ ድረስ ለሰው ልጆች መሠረታዊ ፍላጎቶች እንደ አንዱ እንደሚታይ ይገልጻሉ።‹‹ሀገራችን የሕግ ችግር ሳይሆን የአፈፃፀም ችግር ነው ያለባት›› የሚሉት አቶ ወንድሙ፣ ‹‹ሕግ ሲወጣ ህዝብን እንዲጠቅም ታስቦ ነው እንጂ አስፈፃሚውን እንዲጠቅም ታስቦ መሆን የለበትም›› ይላሉ።

በኢፌዴሪ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች አማካሪ ጉባዔ አባላት የሕግ ማሻሻያ ሥራ የሚያከናውኑት በፈቃደኝነትና ከክፍያ ነፃ በሆነ መልኩ ነው።ምክክር የተደረገበት በፌዴራል የአስተዳደር ተቋሞች የአስተዳደር ሥነ ሥርዓት ረቂቅ አዋጅ ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ተልኮ ወደ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የሚታይ ሲሆን ወሳኝ ማሻሻያ ከታከለበት በኋላ ወደ ተወካዮች ምክር ቤት ተልኮ በመጪው ዓመት እስከ ታኅሳስ ባሉት ጊዜያት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

አዲስ ዘመን ሐምሌ 30/2011

ኃይለማርያም ወንድሙ