ለደን ልማት 800 ኪሎሜትርወደኋላ መጓዝ ወደኋላ መጓዝ

9

ሰሞኑን አንድ ኢንዶኔዥያዊ አካባቢን ለማዳን የከወነው ለየት ያለ ድርጊት በመገናኛ ብዙኃን በዓለም ዙሪያ ርዕሰ ዜና መሆን ችሏል። መዲ ባስቶኒ የተባለው የ43 ዓመቱ ጎልማሳ ፕሬዚዳንቱን ለማግኘት ከመኖሪያ ሰፈሩ ከምሥራቅ ጃቫ እስከ ዋና ከተማዋ ጃካርታ 800 ኪሎ ሜትር ወደኋላ በእግሩ መጓዙ ተዘግቧል።

ባስቶኒ ምሥራቅ ጃቫ ከሚገኘው ከመኖሪያ መንደሩ ዶኖ ባለፈው ሰኔ 25 ቀን ተነስቶ የፊታችን ነሀሴ 24 ቀን 2011 በሚከበረው የሀገሪቱን 74ኛ ዓመት የነፃነት ቀን በወቅቱ ለመድረስና በዓሉን ጃካርታ በሚገኘው የፕሬዚዳንቱ ቤተመንግሥት ለማክበር ነበር የተንቀሳቀሰው። 800 ኪሎሜትር ወደ ኋላ በመራመድ ነፃነቱን ከፕሬዚዳንቱ ጆኮ ዊዶዶ ጎን ለማክበር አስቦ ነው የሚጓዘው።

ዋነኛ ዓላማውና ልዩ ጥረቱ ደግሞ የኢንዶኔዥያን ተምሳሌት የሆነውን የዛፍ ዝርያ ለመጠየቅና ችግኙ በዱርና በተራራ ላይ እንዲተከል ለመጠየቅ በመኖሪያ መንደሩ አካባቢም ዛፎችን በመጠበቅና በመንከባከብ ዙሪያ ግንዛቤ ለመፍጠር ነው።

አክቲቪስቶች አካባቢን ስለመጠበቅ ግንዛቤ እየፈጠሩ ደን መንጣሪዎችን በብዕራቸው እየተዋጉ ናቸው የሚለው መዲ ባስቶኒ ፣በዚህ ላይ የፕሬዚዳንቱ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ከታከለበት ጥረታቸውን ይበልጥ ያጎላዋል ሲል ይገልፃል። በእግሩ ያን ያህል ወደኋላ የተጓዘውም የአክቲቪስቶችን እንቅስቃሴ ለማጉላትና የኢንዶኔዥያን ፕሬዚዳንት ለማግኘት ነው።

መዲ በቀን 30 ኪ.ሜ በእግሩ ወደ ኋላ የሚጓዝ ሲሆን ጉዞውን እንደ መስታወት ሊያሳይ የሚችል ልብስ መልበሱንም ከኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል።ስምንት ኪሎ ግራም የሚመዝን 300ሺ (Rp) ሩፒ የሚወጣ ዕቃ የተሸከመ ሲሆን ዓላማውን ለማሳካት ወሰኑ ጫፍ ለመድረስ ዓቅዷል።

‹‹በረጅም ጉዞዎቼ እረፍቴን በመስኪዶች በፖሊስ ጣቢያዎች በአቅራቢያ በሚገኙ የፀጥታ ኬላዎች አደርጋለሁ።››ያለው መዲ ባስቶኒ በኢንዶኔዥያ መገናኛ ብዙኃን እንደተናገረው 800 ኪ.ሜ ወደ ኋላ መራመዱ ኋላችን እንድንመለከት ያስችለናል ብሏል። ደሴት የሆነችው እናት ሀገራችንን ተዋግተው ያቆዩልንን ጀግኖቻችን ያስታውሰናል ጉዞዬንም እንደ ትሩፋት እቆጥረዋለው ብሏል።

የሀገራችን አክቲቪስቶች ብሔርን ከብሔር ከመጋጨት ወጥተው የኢንዶኔዥያ አክቲቪስቶችን የልማት ጉዞ መቼ ይሆን የሚቀላቀሉት?

አዲስ ዘመን ሐምሌ 30/2011

ኃይለማርያም ወንድሙ