የፖሊሶቹ ከልክ ያለፈ ውፍረት

14

በወታደራዊ እና የፖሊስ ተቋማት በአካል ቀልጣፋ ሆኖ መገኘት የግድ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ይህ ደግሞ ለግዳጅ ዝግጁ ለመሆን ይጠቅማል፡፡ ውፍረት ቢኖር እንኳ የእለት ተዕለት ስራ ለማካሄድ የሚቸግር ሊሆን አይገባም፡፡ እነዚህ አካላት ሁሌም ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ስለሚያደርጉም ውፍረት ቢኖር እኗ አካል ለመታዘዝ ብዙም የሚቸገርበት ሁኔታ አይኖርም፡፡

በኢንዶኒዥያ ምስራቃዊ ጃቫ ግዛት ግን የፖሊሶች ውፍረት አሳሰቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ሮይተርስ ሰሞኑን ያሰራጨው ዘገባ አመልክቷል፡ ፡ በዚህ የተነሳም ከ50 ኪሎ ግራም በላይ ክብደት ያላቸው ፖሊሶች የአካል እንቅስቃሴዎችን እንዲያደርጉ፣ እንዲዋኙ፣ ዱብ ዱብ እንዲሉ ትዕዛዝ ተላልፎባቸዋል፡፡ ይህ ካደረጉ ሰውነታቸው ለስራቸው ምቹ እንደሚሆንም ታምኖበት እየተሰራ ነው፡፡

በሀገሪቱ ምዕራብ ጃቫ ግዛት የሚገኙ የፖሊስ መኮንኖች ውፍረት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የጠቀሰው ዘገባው፣ፖሊሶቹ በጥብቅ ክትትል የሚደረግበት የሁለት ሳምንት የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ ይህ ብቻም አይደለም የኒውትሪሽን ባለሙያዎች ድጋፍ እንደሚደረግላቸውም የአካባቢው ፖሊስ ቃል አቀባይ ፍራንስ ባሩንግ ማንጌራ ተናግረዋል፡፡

ቃል አቀባዩ እነዚህ ፖሊሶች ያላቸው የሰውነት ክብደት ከእነሱ የማይጠበቅ እና ከፍተኛ ነው ሲሉ ገልጸው፣ የሀገሪቱ የፖሊስ ተቋማት ፖሊሶች ሊኖራቸው የሚገባው ክብደት ከቁመታቸው ጋር የሚመጣጠን መሆን እንዳለበት ከማመልከትም አልፎ ገደብ አስቆምጦበታል፡፡

ዘገባው እንዳመለከተው፤ሀገሪቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ካለቅጥ ውፍረት እየተቸገረች ስትሆን፣የአለም ጤና ድርጅት እአአ በ2016 ከኢንዶኔዢያ 250 ሚሊየን ህዝብ 28 በመቶዎቹ ካለቅጥ የወፈሩ ናቸው፡፡ እአአ በ2018 በ300 ሺ አባወራዎች ላይ በተካሄደ የጤና ቅኝት ደግሞ ከአምስቱ አንዱ ሰው ካለቅጥ የወፈረ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ለእዚህ እንደ ችግር የተጠቀሱትም የአካል እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ ተቀምጦ መዋል፣በዘይትና በስኳር የተከሸኑ ምግቦችን ማዘወተር ናቸው፡፡

‹‹ከላቅጥ መወፈር በግዳጅ ላይ ችግር እያስከተለብኝ ነው፤ብዙዎቻችን ከግዳጅ በሁዋላ እየታመምን ያለው›› ያለው የፖሊስ መኮንኑ ኢዋን ሱታንቶ 3 ነጥብ 5 ኪሎ በአካል እንቅስቃሴ በመቀነሱ ጤነኛነት እየተሰማው መሆኑን ተናግሯል፡፡

የፖሊስ ቃል አቀባዩ ማንጌራ የአካል እንቅስቃሴ መርሀ ግብሩ ወደ መላ ምስራቅ ጃቫ ግዛት እንዲስፋፋ እንደሚደረግም የተጠቆመ ሲሆን፣ የአካል ብቃት የፖሊስ መኮንኑ ለህዝብ ተገቢውን አገልግሎት መስጠት የሚችል እና የማይችል ስለመሆኑ ወሳኝ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

አዲስ ዘመን ሐምሌ 30/2011

ዘካርያስ