ሕንዳዊቷ ታዳጊ ኩላሊት ለጋሽ ለምን አጣች?

25

የኩላሊት ህመም የዓለማችን ዋነኛው የጤና ችግር ከሆነ ዋል አደር ብሏል፡ ፡ህክምናውን ለማግኘት ከፍተኛ ገንዘብን ይጠይቃል፤በተለይ የደሃውን የማህበረሰብ አቅም በእጅጉ እየፈተነ መሆኑም ችግሩን ይበልጥ አሳሳቢ አድርጎታል፡፡

የኩላሊት እጥበቱም ሆነ ንቅለ ተከላውን ለማካሄድ ብዙ ገንዘብ ከማስፈለጉም በላይ ህክምናው በሀገር ውስጥ መገኘት የግድ ይላል፡፡ይህ ካልሆነ ደግሞ ስቃዩም ሆነ እንግልቱ በእጥፍ ይጨምራል፡፡

በአብዛኛዎቹ ሀገሮች በገንዘብና በኩላሊት ለጋሾች አለመገኘት ሳቢያ ህክምናውን ማግኘት አስቸጋሪ ከሆነም ቆይቷል፡፡የኩላሊት ንቅለ ተከላው ፈተና ከሆነባቸው መካከልም ህንዳዊቷ የ16 ዓመት ታዳጊ አንዷ ናት፡፡

ታዳጊዋ ከሁለት ሳምንት በፊት ክፉኛ ትታመምና ወደ ሆስፒታል ትወሰዳለች፡፡የተለያዩ ምርመራዎች ይደረግላታልም፡፡ ችግሩ ሁለቱም ኩላሊቶች አገልግሎት መስጠት ወደ ማቆም መቃረባቸው መሆኑ ለቤተሰቦቿ ይነገራቸዋል፡፡

ጤናዋን ማግኘት የምትችለውም ሁለቱም ኩላሊቶች ሲቀየሩ መሆኑ ይገለጽላቸዋል፡፡ውድ የሆነው የኩላሊት ንቅለ ተከላ ከመካሄዱ አስቀድሞ ግን ኩላሊት የሚለግስ ፈቃደኛ ቤተሰብ ወይም ለጋሽ ማግኘትን ይጠይቃል፡፡

የታዳጊዋ ቤተሰቦች ግን ቤተሰቦቿ የሀኪሞቹን ውሳኔ ሲሰሙ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት፣ ኩላሊት ለጋሾችን ለማፈላለግም አሊያም ራሳቸው ኩላሊታቸውን ለመለገስ ሙከራ ወደ ማድረግም አልገቡም፡፡ይህ ለምን ሆነ? ቤተሰቦቿ ምን ነካቸው? የማን ጎፈሬ ያበጥራሉ? ኩላሊታቸውን አይለግሱላትም ወይ ? ከሰው ልጅ አልተፈጠረችም ወይ? ሊያሰኝ ይችላል፡፡

ይሁንና በህንድ ሽይክፑራ ኤቪጂል መንደር ነዋሪ የሆነችው ካንቹን ኩማሪ የተባለችው ይህች ታዳጊ ሞቷን ለመጠባበቅ ተገደደች፡፡ ቤተሰቦቿ ሊረዷት ያልፈለጉት በሀገሪቱ ለሴት ልጅ ካለው መጥፎ አመለካከት በመነጨ መሆኑን ኦዲቲ ሴንትራል የተሰኘው ድረ ገጽ ሰሞኑን ይዞት በወጣው ጽሁፍ አስነብቧል፡፡

እንደ ዘገባው ከሆነ በህንድ ለሴት ልጅ መጥፎ አመለካከት አለ፡፡ሴት ልጅ እንድትወለድ የሚፈልግም የለም፡፡ እናቶች አርግዘው የጽንስ ምርመራ ሲደረግላቸው የተረገዘችው ሴት መሆኗ ከታወቀ ማስወረድም ልምድ ሆኗል፡፡ይህ ሁሉ ደግሞ የመጣው ሴት ልጅ ስታገባ ለወንዱ የምትሰጠው ጥሎሽ ከፍተኛ በመሆኑ ነው፡፡

‹‹ለዚህች ታዳጊ ማን ኩላሊት ይለግስ›› ሲል አባቷ ራማሽራይ ያዳቭ ለመገናኛ ብዙሃን ጭምር መግለጹንና የታዳጊዋ እናትም እንዲሁ ስለኩላሊት ልገሳ ምንም አለማለቷን አስደንጋጭ ሲል ዘገባው አስነብቧል፡፡

ይህ የእናትና አባቷ ኩላሊት በመለገስ በኩል ምንም አይነት እርምጃ ያለመውሰድ ተግባር የዓለም መነጋገሪያ መሆኑን የጠቀሰው ዘገባው፣ዜናው በዓለም ከተሰራጨ በኋላ ግን አባቷ ቤተሰቡ የደረሰበትን ውሳኔ በመግለጽ ይቅርታ ጠይቋል፡፡ይቅርታውም እሱ ኩላሊት ለመለገስ ፈቃደኛ ያልሆነው የቤተሰቡ ሕይወት የተመሰረተው በእሱ የቀን ሥራ ላይ መሆኑን በመጥቀስ ነው፡፡ኩላሊቱን ለገሰ ማለት መላ ቤተሰቡ ለአደጋ እንደሚጋለጥ በማሰብ ለመለገስ እንዳልፈለገ ተናግሯል፡፡

በቀን ሥራ ለሚተዳደረው አባት አንድ ኩላሊቱን ለልጁ ቢለግስ በአንዱ ኩላሊቱ ብቻ ስራውን በማከናወን የቤተሰቡን ህልውና መጠበቅ አይችልም ስትል ባለቤቱ ባሌሸዋር ያዶቭ ለመገናኛ ብዙሃን ገልጻለች፡፡

ሀኪሞች በበኩላቸው የታዳጊዋ ሁለቱም ኩላሊቶች አገልገሎት መስጠት በማቆም ላይ መሆናቸውን በመጥቀስ አስቸኳይ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡ ኩላሊቱ ቢገኝ እንኳ የኩላሊት ንቅለ ተከላው በራሱ 100 ሺ ዶላር እንደሚጠይቅ ጠቅሰው ታዳጊዋን ለመታደግ አስቸጋሪ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

የታዳጊዋ ቤተሰብ በደህነት ውስጥ የሚኖር እንደመሆኑ የኩላሊት ንቅለ ተከላ የሚፈልገውን ወጪ በመሸፈን በኩል ሊቸገር እንደሚችል ዘገባው ጠቁሞ፣ የህንድ መገናኛ ብዙሃን ዘገባዎች ቤተሰቦቿ ታዳጊዋ ያለችበትን አሳሳቢ ደረጃ በመጥቀስ ሌሎች ለጋሾችን ለማፈላለግ አለመሞከራቸውን ጠቁመዋል፡፡

አንድ የእርዳታ ፈንድ በተመሳሳይ ችግር ውስጥ የነበሩ በርካታ የሀገሪቱን ዜጎች በመርዳት ላይ መሆኑን ዘገባው አመልክቷል፡፡ቤተሰቦቿ ካልቻሉ ልጃቸውን ቤት ውስጥ ወስዶ ማስታመም ይጠብቃቸዋል፡፡

ባለፈው ወር መጨረሻ የታዳጊዋ አሳዛኝ ታሪክ በማህበራዊ ሚዲያዎች የተለቀቀ ሲሆን፣ታሪኳም በመላ ዓለም የሚገኙ የሚሊዮኖችን ልብ ነክቷል፤በርካታ የሚሆኑት በገንዘብ እየደገፉ ይገኛሉ፡፡

ይህ ችግር የህንድ ሴቶችን ችግር አሁንም አውጥቶ ያሳየ መሆኑን ዘገባው ጠቁሟል፡፡ ዘ ታይምስ ኦፍ ኢንዲያ በዘገባው በህንድ ቢሃር ከተማ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ከተካሄደላቸው አብዛኛዎቹ ወንዶች ናቸው፡፡ልገሳው ግን ከችግሩ ስፋት አንጻር ሲታይ ውስን መሆኑን አመልክቷል፡፡ ከሁለት ሆስፒታሎች የተገኘ መረጃን ጠቅሶ ዘገባው እንዳመለከተው፤በፓንታ ከተማ 77 የኩላሊት ንቅለ ተከላ ህክምና ሲደረግ ከኩላሊት ለጋሾቹ መካከል 77 በመቶው ሴቶች ናቸው፡፡

አዲስ ዘመን ሐምሌ 30/2011

ዘካርያስ