የጎዳና ተዳዳሪዎችን ወደ መደበኛ ሕይወት ለመመለስ ከኅብረተሰቡ ጋር በቅንጅት እየተሠራ ነው

29

 አዲስ አበባ፡- በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ከጎዳና ላይ በማንሳት ወደ መደበኛ ሕይወት ለመመለስ ከኅብረተሰቡ ጋር በቅንጅት እየተሠራ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ፡፡

ቢሮው ከበጎ ፈቃደኞች ያገኛቸውን የትምህርት ቁሳቁሶችና አልባሳት ትናንት በቃሊቲ አረጋውያን ማዕከል የሴቶችና ሕፃናት ማገገሚያ ቦታ ለሚገኙ ሴቶችና ሕፃናት አስረክቧል፡፡

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አለሙ አሰፋ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፣ ቢሮው በጎዳና ሕይወት ላይ የሚገኙ ዜጎችን ለማቋቋም ካለፉት ዓመታት በተሻለ ሁኔታ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ ይገኛል፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ ዘንድሮ በመጀመሪያ ዙር ሦስት ሺ 500 የጎዳና ተዳዳሪዎችን ከጎዳና ላይ በማንሳት እንዲያገግሙና ወደ

ሥራ እንዲሰማሩ እያደረገ ነው፡፡ በሁለተኛ ዙር ደግሞ ለሴቶችና ለሕፃናት ልዩ ትኩረት በመስጠት 2000 የጎዳና ተዳዳሪዎችን ከጎዳና ላይ በማንሳት ለማቋቋም እየሠራ ነው፡፡

እንደርሳቸው ገለፃ፣ ለማህበራዊ ችግሮች ተጋላጭ የሆኑ ዜጎች ለችግር ከመዳረጋቸው በፊት በከተማ አቀፍ የማኅበረሰብ ጥምረት አደረጃጀቶች በኩል ችግሩን ለመከላከል ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም፣ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሚገኝ ድጋፍን ለማኅበራዊ ችግር ተጋላጭ የሆኑ ዜጎችን ለማቋቋም በማዋልና ጎዳና ላይ ልመና ማካሄድ እንዳይቻል የሚደነግግ ሕግ በማውጣት የችግሩን ምንጭ ለማድረቅ እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል፡፡

ጎዳና ላይ ልመና ማካሄድ እንዳይቻል የሚደነግገውን ህግ አስመልክቶም ረቂቅ ሕጉ አዋጅ ሆኖ በከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤቱ ከመጽደቁ በፊት ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች እንደሚወያዩበትም አቶ አለሙ ገልጸዋል፡፡

በጎዳና ሕይወት ላይ የሚገኙ ዜጎችን የማቋቋም ተግባር በመንግሥት ጥረት ብቻ ውጤት ሊያስገኝ ስለማይችል ከበጎ ፈቃደኛ ግለሰቦችና ድርጅቶች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ምክትል ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርና የዓለም ባንክ እና ባለፈው ዓመት ያካሄዱት ጥናት እንደሚያሳየው በአዲስ አበባ ከተማ ከ58ሺ በላይ ጎዳና ተዳዳሪዎች ይገኛሉ፡፡

አዲስ ዘመን ነሃሴ 1/2011

 አንተነህ ቸሬ