የብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን 70 ቢሊዮን ብር ዕዳ አለበት፤ የተወሰነ የፕሮጀክት ገንዘብ የት እንደገባ አያውቅም

242


57 ቢሊዮን ብር ዕዳ መንግሥት እንዲሰርዝለትና ወደ ካፒታል እንዲቀይርለት ጠይቋል፤

17 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው ለስድስት ዓመታት ጥቅም ሳይሰጡ የተከማቹ እቃዎች አሉት፤

በያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ እንዳልተሳተፈ ገልጿል፤

 አዲስ አበባ፡የብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን በመንግሥት ውሳኔና ኮርፖሬሽኑ በፈጸመው የተሳሳተ አካሄድ 70 ቢሊዮን ብር ዕዳ እንዳለበት ሲገልፅ፤ 57 ቢሊዮን ብሩን መንግሥት እንዲሰርዝለትና ወደ ካፒታል እንዲቀይርለት ጥያቄ ማቅረቡን አመለከተ። በያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ ከዲዛይንና ማስተባበረ ውጭ እንዳልተሳተፈም ገለፀ።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር ብርጋዴር ጀነራል አህመድ ሀምዛ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት በመንግሥት ውሳኔና ኮርፖሬሽኑ በፈጸመው የተሳሳት አካሄድ በተቋሙ ላይ 70 ቢሊዮን ብር ዕዳ ሲኖርበት፤ የተወሰነው ብር በፕሮጀክቶች በተሰሩ ሥራዎች በተከማቹ እቃዎች ላይ የሚገኝም፤ የተወሰነው ብር ግን የት እንደገባ

 አይታወቅም፣ ከዕዳው ውስጥ 57 ቢሊዮን ብሩን መንግሥት እንዲሰርዝለትም ጠይቋል።

ዕዳውን ለመቀነስ ሁለት አማራጮች ታቅደው እየሰሩ እንደሆነ እንዲሁም ትክክለኛ ባልሆነ መንገድ በኮርፖሬሽኑ ላይ ያረፉ ዕዳዎችን መንግሥት እንዲሰርዝና ወደ ካፒታል እንዲቀይር ጥያቄ መቅረቡን የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በተቋሙ ችግር የመጣውን 13 ቢሊዮን ብር ዕዳ እስከ 15 ዓመታት በሚደርስ ጊዜ እንከፍላለን ብለዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ እንዲሰረዝልንና ወደ ካፒታል እንዲቀየርልን ጥያቄ ያቀረብነው መንግሥት ሜጋ ፕሮጀክቶችን ለኮርፖሬሽኑ ሲሰጥና ሲያሰራ በህግና በአሰራር መሰረት ገንዘብ ያልሰጠባቸውንና ከሰጠም በኋላ ፕሮጀክቶቹ እንዲፈጸሙ ክትትልና ቁጥጥር ያላደረገባቸውን ነው። ስለዚህም ኃላፊነት መውሰድ ያለበት መንግሥት በመሆኑ ዕዳውን እንዲሰርዝልንና ወደ ካፒታል እንዲቀይርልን ጠይቀናል ብለዋል።

ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሥራ ኮርፖሬሽኑ ኮንትራቱን እንደፈጸመ 16 ቢሊዮን ብር ወሰደ። ይህ ብር ምን ላይ እንዳዋለው መንግሥት ሳያረጋግጥ ገንዘብ ሚኒስቴርን ዋስ አድርጎ ተጨማሪ 8 ቢሊዮን ብር ከንግድ ባንክ በብድር ወሰደ። በድምሩ ኮርፖሬሽኑ ፕሮጀክቱን ሲያጠናቀቅ የሚከፈለውን 24 ቢሊዮን ብር ሥራውን ሳያከናውን መንግሥት እንደሰጠው ብርጋዴር ጀነራል አህመድ ገልፀዋል።

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ መንግሥት ገንዘብ እየሰጠ ሥራውን አይቆጣጠርም ለኮርፖሬሽኑ በመጀመሪያ ከተከፈለው 16 ቢሊዮን ብር ሥራ የተከናወነው የ9 ቢሊዮን ብር ብቻ ነው። ሌላው ገንዘብ የት እንዳለ አናውቅም። ለምንጣሮ ከተወሰደው 2ነጥብ5 ቢሊዮን ብር የተሰራው በ500 ሚሊዮን ብሩ ብቻ ነው።

ዋና ዳይሬክተሩ ‹‹ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ገንዘብ ሚኒስቴርና ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ተቋሙ ከመስመር ሲወጣ ማስቆም ሲገባቸው ውሳኔ በማሳለፍና ዋስ በመሆን ጭምር ገንዘቡ እንዲባክን አድርገዋል። ዕዳው የመጣው ተቋሙ በአግባቡ ባለመመራቱ ነው። በመሆኑም መንግሥት ለአዋሽ ተርማል ማመንጫ፣ ለህዳሴ ግድብ ኤሌክትሮ መካኒካል ግንባታና ለደን ምንጣሮ ኮርፖሬሽኑ የወሰደውን በድምሩ 16 ቢሊዮን ብር እንዲሰርዝንል ጠይቀናል›› ብለዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ ስኳር ኮርፖሬሽን ለብረታ ብረትና ኢንጅነሪግን ኮርፖሬሽን ፋብሪካዎችን ለመገንባት 11 ቢሊዮን ብር በወቅቱ የዶላር ምንዛሪ በዶላር ለኮርፖሬሽኑ ከፈለ። ፋብሪካዎቹ 85 በመቶ፣ 65 በመቶና 25 በመቶ እንደተገነቡ በአቅም ችግር ውሉ መቋረጡን የገለፁት ዋና ደይሬክተሩ፤ውሉ ሲቋረጥ ስኳር ኮርፖሬሽን ላልተሰራው ሥራ በከፈለው ዓይነት በዶላር እንድንከፍለው ጠየቀን።

በአሁኑ ወቅት የአንድ ዶላር ምንዛሪ 28 ብር ሲሆን፤ በዚያን ወቅት 17 ብር ነበር። ይህ ማለትም የ11 ብር ልዩነት አለው። እኛ በዶላር የምንከፍል ከሆነ የገነባነው አጠቃላይ ግንባታ የ2 ቢሊዮን ብር ብቻ ነው የሚሆነው። በአንፃሩ ከ11 ቢሊዮን ብር ቀሪውን እንከፍላለን ማለት ነው። ስኳር ኮርፖሬሽን ከውል አንፃር ክፈሉኝ ማለቱ ትክክል ቢሆንም፤ ከመርህ አንፃር ትክክል ስላልሆነ መንግሥት እንዲወስን ጥያቄ ማቅረባቸውን ገልጸዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ የጉምሩክ ታክስ ዕዳ 11 ቢሊዮን 349 ሚሊዮን 278 ሺ 678 ብር በየሶስት ዓመቱ እየታሰበ መከፈል የነበረበትና ያልተከፈለ በመሆኑ ኮርፖሬሽኑ ሙሉ በሙሉ መንግሥት እንዲሰረዝለት ያቀረበው ሌላው ጥያቄ መሆኑን ተናግረዋል።

ብርጋዴር ጀነራል አህመድ ‹‹ ኮርፖሬሽኑ ለምድር ባቡር ሎኮሞቲቭ ለማምረት ኖሪንኮ ከሚባል የቻይና ኩባንያ ጋር ውል ገብቶ ሁለት መቶ ተሳቢዎችን አምርቶ ምርቱ ቆመ። በአካውንቱ ውስጥም ምንም ገንዘብ የለም፤ ይህን ዕዳ ወደካፒታል እንዲቀየርልን ጥያቄ አቅርበናል›› ብለዋል።

ኮርፖሬሽኑ በትክክል ምን ያህል ተሰብሳቢ እንዳለው ገና ማጥራት እንደሚያስፈልግ ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ እስካሁን ግብረ ኃይል በማቋቋም በመዝገብ ላይ ተመስርተው ባደረጉት ማጣራት 12 ቢሊዮን ብር እንዳለ፣ የመሰብሰቢያ ጊዜው ያለፈበት፣ በተሰብሳቢ ተመዝግቦ የተከፈለና በሌሎች ምክንያቶች የማይሰብሰብ ሊኖር እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል።

በኮርፖሬሽኑ በሁሉም ኢንዱስትሪዎች ተመርተው ገዥ አጥተው እስከ ስድስት ዓመት ሳይሸጡ የተቀመጡ 14 ቢሊዮን ብር የሚያወጡ እቃዎች መኖራቸው፣ለምርት ገብተው ሳይመረቱ የተቀመጡ 3ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው እቃዎች እንደሚገኙና በድምሩ 17 ቢሊዮን ብር የሚያወጡ ንብረቶች ጸሐይና ዝናብ እየተፈራረቀባቸው እየተበላሹ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።

በ2011 ዓ.ም ብቻ ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ዕዳ ከፍሏል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ኮርፖሬሽኑ በትክክል ከተመራ ከዚህ በላይ መክፈል ይችላል ፤ ተቋሙን ውጤታማ ለማድረግ የተለያዩ ማሻሻያዎች እየተተገበሩና ጥናት እያደረገ በመሆኑ በሚቀጥለው ዓመት ምርት ለማሳደግ የሚችሉ ፋብሪካዎችን ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ እንደሚያስገቡ ተናግረዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘም ሜቴክ የያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ ፕሮጀክትን ዲዛይን ከመስራትና ሥራውን ከማቀናጀት ውጪ ግንባታ አለማከናወኑን አስታውቋል።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር ብርጋዴር ጀነራል አህመድ ሀምዛ እንደተናገሩት፣ የያዩ ማዳበሪያ ፕሮጀክት ከያዛቸው ሶስት ፋብሪካዎች መካከል በማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታው ብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽኑ አልተሳተፈም፤ የግንባታ ሥራው ለተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን፤ ተርማል ፕላንቱ ደግሞ ራንፓወር ለተባለ የቻይና ተቋራጭ የተሰጡ ናቸው።

በወቅቱ በኦሮሚያ ክልል ወለጋ አካባቢ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር የቻይናው ተቋራጭ ድርጅት ወደ ሥፍራው አልገባም ሲል የተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን በመከላከያ ጥበቃ አድርጉልኝ የሚል ጥያቄ በማንሳቱ የእኛ ተቋም መከላከያ ማሰማራት ስለማይችል ከኦሮሚያ ክልል ጋር በመነጋገር ችግሩ እንዲፈታ በማድረግ የቻይናው ኩባንያ የፓወር ፕላንቱን ርክክብ ሲፈፅም፤ የተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን ግን እስካሁን ርክክቡን እንዳልፈፀመ ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። ብርጋዴር ጀነራል አህመድ ለፋብሪካዎቹ ግብዓት የሚሆነው የድንጋይ ከሰል ሳይመረት ተርማል ፓወርና ማዳበሪያ ፋብሪካ መገንባት ትርፉ ኪሰራ እንደሆነና አሰራሩ ንብ ሳይኖር 50 ቀፎ ታቅፎ ማር እንደመፈለግ የሚቆጠር ነው፤ በአጠቃላይ የፕሮጀክቱ ሥራ የተበላሸ ነው ብለዋል።

አዲስ ዘመን ነሃሴ 1/2011

 አጎናፍር ገዛኸኝ