የሰላም ጉባዔው ትሩፋት ለሁሉም እንዲደርስ በትጋት ይሠራ!

9

 ‹‹ …ቀዳዳ ነጋሪት በከንቱ ጎስሞ፤

እልቂትን የሚያውጅ ከእሳት ዳር ቆሞ፤

ኀሊናው ታውሮ ለሆድ ስላደረ፤

ቅዠቱ ከሽፎበት ባዶ እጁን ቀረ!

በረሃ እንዳለ ሰው ልቡ በጣም ደክሟል፤

በሥልጣን ናፍቆቱ ሰማይ ይቧጥጣል፤

ክብሪት መጫር እንጂ ችግኝ መች ይተክላል፤

ልፋ ብሎ ፈጥሮት በወሬ ይኖራል … ››

ይህንን ከሙሉ ሃሳብ ላይ በከፊል የተቀነጨበ ጥልቅ መልዕክት ያለው የነፃነት አምሳሉ (ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፃፉት) ግጥምን መነሻ ስናደርግ ያለምክንያት አይደለም፡፡ ዛሬ የመላው ኢትዮጵያውያንን የመኖር ህልውና የሚገዳደሩ የፖለቲካ ጥማታቸውን ህዝብን በማፈናቀልና ሕይወት በማጥፋት ለማርካት የሚሞክሩ፤ ዕድሜ ያላስተማራቸውም፤ በዕድሜ ከበሰሉት ፖለቲከኞች ትምህርት ማግኘት ያልቻሉትም ለጋ /አማተር/ ፖለቲከኞች ከወሬ ያለፈ ምንም መስራት ያለመቻላቸውን እንዲገነዘቡና አቅጣጫቸውን እንዲያስተካክሉ ለማሳሰብ ነው፡፡

የሰላም እጦት በሀገር ላይ የሚያስከትለው ችግር ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም። ሰርቶ መግባት፣ ተምሮ በዕውቀት መበልፀግ፣ ልጅ ወልዶ ስሞ ለወግ ማዕረግ ማብቃት፣ ዘርቶ መሰብሰብና ሠርቶ መብላት የሚቻለው የሰላም ዋጋ ሲገባንና ተንከባክበን ስናቆየው ብቻ ነው።

ባለፉት በርካታ ዓመታት አገራችን የማሽቆልቆል ጉዞዋን ገትታ ዓለም አቀፋዊ ዕውቀናን ባገኘ የእድገት ጎዳና ተጉዛ ፈጣንና ተከታታይ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ማስመዝገቧ እንዳይቀጥል የሕዝብን ጥያቄ መሰረት አድርጎ የተጀመረው ለውጥም እንዲጨናገፍ አድብተው የሚሰሩ አስመሳዮች በመበራከታቸው ለዕድገታችን መሰረት የሆነው ሰላማችን አደጋ ላይ እንደነበር ይታወቃል፡፡

ይሁን እንጂ በህዝባችን ፅኑ ፍላጎት፣ አብሮ የመኖር ባህል፣በችግርና በደስታ የመደጋገፍ ዘርፈ ብዙ እሴቶች ላይ የተገነባው አንድነታችን በቀላሉ ሊናጋ የሚችል አለመሆኑን ከተቃጡብን የማለያየት ሙከራዎች ክሽፈት መገንዘብ ይቻላል፡፡

ባለፈው አንድ ዓመት ብቻ ብሄርን መሰረት ባደረጉ የተንኮል ደባዎች በርካታ ወገኖቻችን ተፈናቅለዋል፤ ሕይወታቸው ጠፍቷል፤ ለችግር ተዳርገዋል፡፡ ይሁን እንጂ ምንም ዓይነት የማለያየት ሙከራዎች ቢነዙም ለዘመናት አብሮ የቆየው አንድነታችንና የሕዝቡ የመከባበር እሴት እንዳንለያይ አድርጎ እነሆ ዛሬ ላይ ለምናየው የአማራና የሶማሌ፣ የኦሮሞና የአማራ ፣የኦሮሞና የሶማሌ ሕዝቦች የአንድነት የሰላም ጉባዔ ላይ አድርሶናል፡፡

ዛሬ ሰላሟ በተረጋገጠው ጅግጅጋ ህዝቦች ተገናኝተው በሰላም ጉዳይ ላይ የመከሩትና አብሮነታቸውን ያጸኑት ባለፈው ዓመት እርስ በእርስ እንዲባሉ የሸረበላቸው እኩይ ሴራ በተለመደ ኢትጵያዊ ጨዋነትና መተሳሰብ ማክሸፍ በመቻላቸው ነው። የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ “በኦሮሞና ሶማሌ ህዝቦች መካከል የገቡ ትናንሽ ሰይጣኖች ነበሩ እነርሱ አሁን ታስረዋል፤ በመሆኑም ትናንት ለተፈጠረው ችግር ይቅር ተባብሎ እነዚህ ትናንሽ ሰይጣኖች ዳግም በመካከላችን እንዳይገቡ ተግተን መስራት አለብን” ያሉትም ከእዚህ መሰረታዊ ሀቅ ተነስተው ነው።

የእስካሁኑ የሰላም ጉባዔ በመላ ሕዝቡ ዘንድ ፍሬ አፍርቶ አንድነቱ የጋራ እንዲሆን ያላሰለሰና ተከታታይ ሥራ የሚጠይቅ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም፤ በተለይም እንደመድረኩ ስያሜ ግንኙነቱን የህዝቦች ለማድረግ የተጀመረው በጎ ሥራ እስከታች ድረስ ሊዘልቅ ይገባል። የክልል መሪዎች የበጎ ተግባራቸውን ውጤት ለማየት የሚችሉበት ደረጃ እስኪደርሱ ድረስ ከእርምጃቸው ሊገታቸው የሚችል አንዳች ሃይል ሊኖር አይገባም፤ ሰላም ወዳዱ ሕብረተሰብም የግል የፖለቲካ ፍላጎታቸውን ሊጭኑበት አድብተው ከሚቀሰቅሱትና መልካም ሲደረግ አይናቸው ደም ከሚለብስ እኩይ ተግባር ፈፃሚዎች ራሱን በማቀብ ለሰላሙ መረጋገጥ እገዛ ሊያደርግ ይገባል፡፡

 አዲስ ዘመን ነሃሴ 1/2011