‹‹ብሔራዊ ባንክ ጠንካራ እና ገለልተኛ መሆን አለበት››- ረዳት ፕሮፌሰር አጥላው ዓለሙበአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት መምህር

33

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር እንዲሁም ለኢንቨስትመንት ምቹ ምህዳር ለመፍጠር መንግስት በትኩረት እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጣይ በትኩረት ይሰራል ባሉዋቸው ሁለቱ ቁልፍ ተግባራት እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር አጥላው ዓለሙ ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

አዲስ ዘመን፡የዋጋ ንረት ምንድን ነው?

ረዳት ፕሮፌሰር አጥላው፡የዋጋ ንረት ገንዘብ ነክ ችግር ነው፡፡ በኢኮኖሚ ውስጥ የሚንቀሳቀሰው የገንዘብ ብዛት ዋናው የዋጋ ንረት ምክንያት ነው። በኢኮኖሚ ውስጥ የሚንቀሳቀሰው የብር ብዛት ዋጋው ወደ ላይ እንዲወጣ ያደርገዋል፡፡ የዋጋ ንረት አንድ ወይም ሁለት ዕቃዎች ዋጋ መጨመር ሳይሆን የሁሉም እቃዎች ዋጋ መጨመር ሲያጋጥም ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡የዋጋ ንረት መንስኤዎች ምንድን ናቸው?

ረዳት ፕሮፌሰር አጥላው፡ብሄራዊ ባንክ በራሱ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር የማይሰራ ከሆነ፤ የመንግስት ገቢ ከወጪው በሚያንስበት ጊዜ ገንዘብ ሲያጥረው ብሄራዊ ባንክን እያዘዘ የበጀት ጉድለት ለመሙላት ገንዘብ የሚወስድ ከሆነ ብሄራዊ ባንክ ገንዘብ የሚያሳትም ከሆነና፤ በተለያዩ ጊዜያት የገንዘቡን መጠን የሚጨምር ከሆነ የዋጋ ንረት ይከሰታል፡፡

የፖለቲካ ግፊትና ተቃውሞዎችን ለማስታገስ ሲል መንግስት የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመጀመር ብዙ የበጀት ቀዳዳዎችን ከከፈተ የግዴታ ከሚሰበስበው ገንዘብ በላይ ወጪው ስለሚሄድበት ይህንን ለማሟላት ሲል ብሄራዊ ባንኩን ገንዘብ አምጣ እያለ ሲወስድ በኢኮኖሚ ውስጥ የሚገባው ገንዘብ በጣም ብዙ ይሆንና የዋጋ ንረት እንዲከሰት ያደርጋል፡፡

ሌላው ኢትዮጵያ ከውጭ ከፍተኛ ብድርና ልገሳ ይቀርብላታል፡፡ ሀገሪቱ ወደ ውጭ የምትልካቸው ሸቀጦች ጥቂቱን ነው የሚሸፍነው። አብዛኛው የውጭ ምንዛሬ የሚገኘው በብድርና ልገሳ ነው፡፡ ሁለተኛ ገንዘብ ከብድርና ከልገሳ በተጨማሪ በሀዋላ ለቤተሰብ የሚላከው የውጭ ምንዛሬ አለ፡፡

የውጭ ምንዛሬዎች በሚገቡበት ጊዜ በውጭ ገንዘቦች ፋንታ መንግስት ገንዘብ በብር ተርጉሞ በሚሰጥበት ጊዜ በመንግስት በኩል እጥረት የሚገጥመውና የሚያራባ ከሆነም የዋጋ ንረት እንዲከሰት መንስኤ ይሆናል፡፡

ከባንኮች በተለያዩ ምክንያቶች በቀላሉ መበደር እና ገንዘብ አግኝቶ መንቀሳቀስ በቀላሉ የሚቻል ከሆነም በገበያ ውስጥ የሚንሸራሸረው ገንዘብ ይበዛና ለዋጋ ንረት የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ ሊኖረው ይችላል።፡

መንግስት ላይ ጥርጣሬዎች አሉ፡፡ መንግስት ያዳላል የሚል ነው።ይህ ደግሞ ኢኮኖሚውን ይጎዳል፡ ፡ ኢኮኖሚው ተጎዳ ማለት አቅርቦት አይኖርም ማለት ነው፡፡ ዕቃዎች ካሉበት ቦታ በአግባቡ አይጓጓዙም ማለት ነው፡፡ ከአምራቹ ወደ ሸማቹ እንዳይቀርብም እንቅፋት ይበዛበታል።

ወደ ፊት ጥሩ ጊዜ ይመጣል ወይም መጥፎ ጊዜ ይመጣል የሚለው ግምት በአቅርቦትና ፍላጎት ላይ ከባድ ተፅዕኖ አላቸው። ክፉ ቀን ሊመጣ ይችላል በሚል ስጋት ካለ አሁን ከሚያስፈልጋቸው በላይ የሚገዙም ይኖራሉ ይላሉ። ያም ዋጋው ከፍ እንዲል ያደርጋል።

የእቃ አቅርቦት ዝቅተኛ ከሆነና በሰው እጅ ብዙ ገንዘብ ካለ የዋጋ ፉኩኩር ውስጥ ይገባል፡፡ ገንዘብ በእጁ ካለ ነጋዴው የጠየቀውን ነገር ሸማቹ ይከፍላል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ፍላጎቱ ከፍተኛ በሆነበት ሁኔታ አቅርቦቱ ዝቅተኛ ከሆነ ማለትም እቃዎች ዝቅተኛ ከሆኑ ወይም ምርቱ ዝቅተኛ ከሆነ እጥረቱ ዋጋ ከፍ እንዲል ያደርጋል፡፡

አዲስ ዘመን፡ከመንስኤዎቹ ውስጥ ለዋጋ ንረቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ያለው የትኛው ነው?

ረዳት ፕሮፌሰር አጥላው፡በኢኮኖሚ ውስጥ ብዙ ገንዘብ ነው ያለው፡፡ እሱ ነው የዋጋ ግሽበት እንዲከሰት እያደረገ ያለው፡፡ ገንዘቡ ደግሞ ተሰርቶበት ሳይሆን በተለያዩ ምክንያቶች ገንዘብ ወጪ ተደርጓል። መንግስትም ሲቸግረው ገንዘብ ያወጣል፡፡ ገንዘብ ያትማል፡፡ ሲታተም ባላይም ምን ጊዜም የገንዘብ መጠን ከፍ ካላለ የዋጋ ንረት ሊኖር አይችልም፡፡

ገንዘብ ገበያ ውስጥ ባይገባ ኖሮ አንዱ እቃ ሲወደድ ሌላኛው ዕቃ ሊረክስ ይገባ ነበር፡፡ በኢኮኖሚው ውስጥ ያለው ገንዘብ ውስን ቢሆን ሁሉም እቃዎች ሲጨምሩ መግዣ ይጠፋ ነበር፡፡ ነገር ግን ብዙ ገንዘብ ኢኮኖሚው ውስጥ ስለተረጨ ሁሉም ዕቃዎች ዋጋ ጨምሯል፡፡ ስለዚህ ገንዘብ አያያዝ ነው ማለት ነው ዋናው መንስኤው። ሌሎች ምክንያቶች አባባሽ ናቸው፡፡ የሰላም ሁኔታም አባባሽ ነው፡፡ ሰላም ከሌለ ስራ በየጊዜው ስለማይሰራ አቅርቦት እንዲያንስ ያደርጋል። አቅርቦት ሲቀንስ ደግሞ ዋጋው ወደ ላይ ከፍ እንዲል ያደርጋል፡፡

የአቅርቦት ማነሱ በዚህ ሀገር ውስጥ እርግጥ ነው፡፡ ስራ አጥ በዝቷል፡፡ ስራ እየተሰራ አይደለም። የሰው አዕምሮም የተረጋጋ አይደለም፡፡ የሰላም እጦት ኢንቨስተሮች ኢንቨስት እንዳያደርጉ አድርጓቸዋል። በየቦታው ችግሮች አሉ፡፡ ስለዚህ ኢንቨስተሮች ገንዘብ አያወጡም፡፡ ገንዘብ ካልወጣና ካልተመረተ እጥረት መከሰቱ ይቀጥላል፡፡ ይህ በኢንዱስትሪውም በንግዱም ዘርፍ ይቀጥላል። ገበሬዎች መፈናቀላቸው በግብርናውም እንዲሁ ችግር እንዲከሰት አድርጓል፡፡ ህዝቡም ውጥረት ውስጥ ነው፡፡ የመንግስት አካልም የችግሩ አካል ነው፡፡ ሰላም ባልተፈጠረበት አቅርቦትና ፍላጎት ማጣጣም አዳጋች ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡በእኛ ሀገር የእቃና የአገልግሎት ዋጋ አንድ ጊዜ ከፍ ብሎ ሲቆም አይስተዋልም፡፡ በየጊዜው ሲጨምር ነው የሚታየው፡፡ ለምንድን ነው?

ረዳት ፕሮፌሰር አጥላው፡ገንዘብ እየታተመ ስለሚገባ ነው ሁሌም ዋጋ እየጨመረ የሚሄደው። ዋጋው ከፍ ባለ ቁጥር ገንዘብ እየታተመ የሚገባ ከሆነ ቀጣይ ዋጋ ንረት ይከሰታል ማለት ነው። ነገር ግን አቅርቦቱ አነስተኛ በሆነበት ጊዜ አንድ ጊዜ ከፍ ይልና በዚያው ላይ ይረጋጋል፡፡ ዋጋ ንረቱ እንዳይቆም እያደረገ ያለው ገንዘብ ቁጥጥሩ ዝቅተኛ ስለሆነ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡የዋጋ ንረቱን ለመቆጣጠር ምን መደረግ አለበት?

ረዳት ፕሮፌሰር አጥላው፡የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር መንግስት ራሱን መቆጣጠር አለበት። ብሄራዊ ባንክ ጠንካራ እና ገለልተኛ መሆን አለበት። በህግ እንጂ በፖለቲከኞች ግፊት መስራት የለበትም። አምባገነን የሚባል ደርግ በነበረበት ወቅት እንኳ ብሄራዊ ባንክ በጣም ጠንካራ እንደነበር ይታወቃል። ከዚያ በኋላ ግን ልቅ ሆኗል፡፡

ዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር መፍትሄ ወደ ኢኮኖሚው ውስጥ የሚገባውን የገንዘብ ፍሰት መጠን መገደብ ነው፡፡ ተቋሙ ጠንካራ ካልሆነና በህግ መሰረት የሚሰራ ካልሆነ፤ የመንግስት የመበደር ፍላጎትን በህግ የማይገድብ ከሆነ፤ አብዛኛውን ጊዜ ፖለቲከኞች አጭር ርቀት ስለሚያዩ ስልጣን ላይ ለመቆየት ይደግፈናል የሚሉት ህዝብ እንዳይቀየማቸው የማድረግ ዝንባሌ ስላላቸው፤ ስለ ሀገሪቱ የረጅም ጊዜ ተጽዕኖ ላያስቡ ይችላሉ፡፡

በመሆኑም ብዙ ገንዘብ ኢኮኖሚ ውስጥ ሊረጩ ይፈልጋሉ፡፡ ብሄራዊ ባንክ ግን በህግ ሊገድብ ይገባል። ስለዚህ ተቋሙ መጠንከር አለበት፡፡ ተቋሙ ገንዘብ እንቅስቃሴን መቆጣጠር መቻል አለበት፡፡ ብሄራዊ ባንክ አሁን ባለው ሁኔታ የገንዘብ እንቅስቃሴን የመቆጣጠር አቅም አለው ወይ የሚለውም ሊታሰብበት ይገባል፡፡

እሱን ለመቆጣጠር ደግሞ ነጻ የሆነ ብሄራዊ ባንክ ያስፈልጋል፡፡ ብሄራዊ ባንኩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወይም የገንዘብ ሚኒስትሩ ወይም የፖለቲካ ድርጅቶች እንዲህ አድርግ ስላሉት ሊያደርግ አይገባም፡፡ ዋጋ ንረትን ዓላማው አድርጎ የሚሰራ ብሄራዊ ባንክ ያስፈልጋል፡፡

የዋጋ ንረትን ለመቆጠጠር ከምንም በላይ መንግስት ትክክለኛ ሚናውን መጫወት አለበት። መንግስት መንግስት የሚሆነው ደግሞ ለሁሉም ዜጋ በእኩልነት ሲያገለግልና ፍትሃዊ ሆኖ የህግ የበላይነትን አክብሮ የሚንቀሳቀስ ከሆነ በሌላውም ዘንድ ተቀባይነት ይኖረዋል፡፡ ተቀባይነት ካገኘ ደግሞ አቅጣጫውን ወደ ስራ እንዲያዞረው ያደርጋል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ አቅሙን ለማምረቻነት ይጠቀማል፡፡

ዋጋ ንረት ሊከሰት እንደሚችል መንግስት በሚያይበት ጊዜ ባንኮች በብሄራዊ ባንክ የሚያስቀምጡትን የገንዘብ መጠን ከፍ ማድረግ አለበት፡፡ ለአብነት ያህል የንግድ ባንክ በብሄራዊ ባንክ ውስጥ የሚያስቀምጠውን የገንዘብ መጠን ከፍ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ገንዘብ እንዳይንቀሳቀስ ያደርገዋል፡፡ ሁለተኛው ቦንድና ሌሎች ቢሎችን በመሸጥ ገንዘብ ወደ መንግስት እጅ እንዲገባና በዋጋ ንረት ላይ ግፊት የሚፈጥረውን መቀነስ ይቻላል፡፡

አዲስ ዘመን፡መንግስት ለኢንቨስትመንት ምቹ ምህዳር ለመፍጠር እንደሚሰራ ገልጸዋልይህን እንዴት ማሳካት ይቻላል?

ረዳት ፕሮፌሰር አጥላው፡መንግስት ተዓማኒ መሆን አለበት፡፡ መንግስት የሚናገራቸውንና የሚተገብራቸውን መጣጣም አለባቸው። ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጠር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቃል አውርተዋል፡፡ መንግስት የሚላቸው ነገሮች እውነት ናቸው ብሎ ኢንቨስተሩ የሚያምነው መንግስት ባሳለፋቸው ጊዜያት ውስጥ ተዓማኒነትን ያገኘ መንግስት ሲሆን ነው። የሚናገረውና የሚያከናውነው የተለያየ ከሆነ ዛሬ ኢንቨስተሮች ገብተው መዋዕለ ንዋያቸውን አያፈሱም፡፡ መንግስት ተዓማኒነት መፍጠር አለበት፡፡ መልካም አስተዳደር ለማስፈን መስራት አለበት፤ ዲሞክራቲክና ፍትሃዊ መሆን አለበት፡፡

መልካም አስተዳደር ካልሰፈነ መንግስት ሊታመን አይችልም፡፡ ተዓማኒ ካልሆነ ኢንቨስትመንት አምኖ አይመጣም፡፡ የሚታመን መንግስት ካልሆነ እውነተኛ ኢንቨስተር አይመጣም፡፡ መንግስት የማይታመን ከሆነ አጭበርባሪ ኢንቨስተሮች ናቸው የሚመጡት። ከዚህ በፊትም አቅም ሳይኖራቸው ከተለያዩ ሀገራት አቅም የሌላቸው አቅም አለን ብለው መጥተዋል። መንግስትም እውነተኛ ኢንቨስተሮች ናቸው ብሎ በማሰብ በጉጉት ይቀበላቸዋል፡፡ ጭራሽ ዘርፈው ይሄዳሉ፡፡

ውጭ ኢንቨስተርን ለመሳብ በቅድሚያ ሀገር ውስጥ ኢንቨስተርን በአስተማማኝ ሁኔታ መሳብ ያስፈልጋል፡፡ የሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንት ማሳመን ይፈልጋል፡፡ ሀገሬው ራሱ ኢንቨስት ላድርግ ብሎ የስራ ተነሳሽነቱ ሲበዛ፤ የሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንትን ያየ የውጭ ኢንቨስተሮች ከሀገር ውስጥ ኢንቨስተር ጋር እየተባበረ ሀገር ውስጥ ያለውን ነገር አይቶ ይመጣል፡፡

ከዚህ ቀደም ኢንቨስትመንት አካባቢ አድሏዊ አሰራሮች ነበሩ፡፡ አሁንም የተስተካከለ አይመስልም። ብዙ ቅሬታዎች ይሰማሉ፡፡ እነዚህ ችግሮች ካልተስተካከሉ የሀገር ውስጥ ኢንቨስተሮች ዘንድ ተዓማኒነቱ አይኖርም፡፡ የሀገር ውስጥ ኢንቨስተሮችን በአግባቡ መሳብ ካልተቻለ የውጭ ኢንቨስተሮች ተማምነው ገብተው መዋዕለ ንዋይ አያፈሱም፡፡

ሰላም ሳይኖር ኢንቨስትመንት ሊኖር አይችልም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢንቨስትመንቱን ለማበረታት የሚያስችሉ አሳማኝ ስራዎችን ሊሰሩ ይገባል። ይህ ባልሆነበት አዳጋች ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡ለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን።

ረዳት ፕሮፌሰር አጥላው፡እኔም አመሰግናለሁ፡፡

አዲስ ዘመን ነሃሴ 2/2011

መላኩ ኤሮሴ