ወጣቱ ታሪክን ማወቅ አለበት ሲባል ምን ማለት ነው?

22

 አሁን አሁን ‹‹የተሳሳተ ትርክት›› የሚል ቃል በፖለቲከኞቻችን አንደበትና በፌስ ቡክ ላይ በየዕለቱ አይጠፋም፡፡ በገሃድ የሚስተዋሉ በርካታ ድርጊቶችም ይሄንኑ ሀቅ ሲያረጋግጡ ይስተዋላል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ወጣቶች የሀገራቸውን ታሪክ ማወቅ አለባቸው ሲባል ምን ማለት ነው? ታሪክን በአስተማሪነቱ በመቀበል በኩልስ?

በጎና የጋራ እሴትን የሚያጎለብቱ ታሪኮች እያደጉ ነው ወይ? ታሪክ ወደፊት የሚያስወነጭፍ እንጂ ወደኋላ የሚመልስ መሆን ነበረበት ወይ? ወጣቱስ የሀገሩን ታሪክ በምን መልኩ ተረድቶ የሀገር አስቀጣይነት ሚናውን እየተወጣ ይሆን? የሚሉና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን እያነሳን ከወጣቶች ጋር ሀሳብ ተለዋውጠናል፡፡

በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ጀማሪ ሐኪም ወጣት ዘላለም አዲስ እንደገለጸው አሁን በሚስተዋለው ሁኔታ ወጣቶች የሀገራቸውን ታሪክ ጠንቅቀው ያውቃሉ ማለት አይቻልም፡፡ የሰሙትን ታሪክ እንኳን እውነት ነው? ወይስ ሐሰት ይሆን? ብለው ጊዜ ወስደው ለማጣራት የሚሞክሩ በጣም ውስን ናቸው፡፡ በምክንያት የሚያምን፣ ለምን ብሎ የሚሞግት ወጣት እየተፈጠረ ሲመጣ የሀገራችን ታሪክ እውነታው እየታወቀ የሚመጣ ይመስለኛል፡፡

በአሁኑ ወቅት በየዩኒቨርስቲዎች እና በከተሞቻችን የምታስታውለው በስሜት የሚነዳ ወጣት ነው፡፡ በእርግጥ የሀገሩን እውነተኛ ታሪክ የሚማርባቸው እና የሚያውቅባቸው ቦታዎች፣ ትምህርት ቤቶችና ተቋማት አሉ ወይ? ስንል ዝንፈቱ ከዚያ መጀመሩን እንገነዘባለን።

‹የአንድ አውቶቡስ ተሳፋሪዎች ካሰቡት በሰላም እንዲደርሱ የሾፌሩ ጤናማነት ወሳኝ ነው› ልክ እንደዚያ ሁሉ የአንድ ሀገር ታሪክም ሳይዛነፍና ሳይበረዝ እውነቱ ለትውልድ መድረስ የሚችለው በጤነኛ የፖለቲካ አስተሳሰብ ሀገሪቱ ስትመራና ሕዝቦቿ ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር ሲችሉ ነው፡፡

አለበለዚያ ‹‹እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ›› የሚል ከንቱ ፍክክር ይኖርና የሀገሪቱን ታሪክም ‹‹እኔ እኔ›› የሚለው አካል ይጠቅመኛል ባለው መንገድ ቅኝቱን እያስተካከለ ለትውልዱ መጋት ይሆናል፡፡ በሥርዓተ ትምህርቱ ጭምር በዚህ መንገድ ትውልዱን በመቅረጽ መሰረት ያሥይዛል፡፡

ይሄ እንዳይሆን ግን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሊኖር ይገባል፡፡ የፖለቲካ መሪው ታሪክን በሚፈልገው መንገድ ለመምራት ቢሞክርም የታሪክ አዋቂ ምሁራን፣ታላላቅ ሰዎች፣የምርምር ማዕከላትና ሌሎችም ፈር የማስያዝ ሥራ መስራት ይችላሉ ብሏል ሐኪም ዘላለም፡፡

በዚህ ወቅት ደግሞ ወጣቱ ለብዥታ የሚያጋልጡ የታሪክ አካሎች ሲገጥሙት ሰከን ብሎ ማጤን ይኖርበታል፡፡ ምክንያቱም የማወቅ ጉጉት ካለው ሰፊ እድሎች ተመቻችተውለታል። ግን በርካታውን ሥታየው የሚነገረውን የሚያምን ነው፡፡ ወቅቱ እኮ ሁለቱንም እድሎች የያዘ ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ ማህበራዊ ሚዲያዎች ከሚያለሙት የሚያጠፉት የሚበልጥ ይመስለኛ ሲሉ ሐኪሙ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

የሀገሪቱ የታሪክ አካል መስለው ብዙ የሚያጋጥሙ የፈጠራ ታሪኮች አሉ፤ማህበረሰቡ እየበሰለና እየተማረ ሲመጣ ይስተካከሉ ይሆናል፡፡ በእርግጥ አሁን ላይ ቁጥሩ ብዙ ባይሆንም ወጣቱ በሀገሩና በሕዝቦች ታሪክ ላይ የተነሰነሱ ሴራዎችን ተረድቶ እስከ መቀየር እየደረሰ መሆኑን ወጣት ዘላለም ተናግሯል፡፡

በሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚንስቴር የወጣቶች ግንዛቤና ንቅናቄ ከፍተኛ ባለሙያው ወጣት አብይ ኃይለመለኮት እንዳለው ታሪክ የምንለው የትናንቱን፣ የዛሬውንና የነገውን የሚያቆራኝና የሚያስተሳስር ድልድይ ነው። በከተማም ሆነ በገጠሩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ወጣቶች ትኩረታቸው ታሪክን ፈልፍሎ እውነታውን ከመረዳትና ከማጥናት ይልቅ በሌሎች ጉዳዮች ላይ መጠመድ ይስተዋላል፡፡ የዓለም የሥልጣኔ ደረጃ ከወለዳቸው ጉዳዮች ጋር የመጣበቅ ሁኔታ ይታያል፡፡

መሰረታዊ የሆነውን የሀገር ታሪክ በቅጡ ከማወቅ ይልቅ በተደጋገሙ መረጃዎች አዕምሮውን ማጨናነቅ (አዲስ ነገር ለማወቅ አለመጣር) እና ጊዜውን ማባከን በሰፊው የሚስተዋል ችግር ነው ያለው አብይ መረጃው በተለያዩ መንገዶች ለወጣቶች ይረጫል። ለምሳሌ፡-ከማህበራዊ ሚዲያ፣ ከእድሜ አቻዎቻቸው፣ከሌሎችም ሊሆን ይችላል፡፡

ሌላው ደግሞ የንባብ ባህል እየተዳከመ መምጣት ነው፡፡ አዳዲስ ነገሮችን ለማግኘት የሚፈጠረው ስሜት መቀነስ፣ፍላጎት ማጣት ተጠቃሽ ችግር ነው፡፡ በንባብ የሚገኝ እውቀት ደግሞ የበሰለ ነው፤ ከአዕምሮ እስከ ሰብዕና የሚገነባ ነው፤ የተብላላ እውቀት ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ ከሚገኙት አንዱም ታሪክ እውቀት ነው።

ከዚህ በተጨማሪም በኢትዮጵያ ለታሪክ ትምህርት የሚሰጠው ግምት አነስተኛ ነው። በእርግጥ ለታሪክ ብቻ ሳይሆን ለማህበራዊ ሳይንስ የትምህርት እውቀት ዘርፎች ትኩረት እየተሰጠ አይደለም፤ ደካማ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ አንዱ ተጠቃሽ ደግሞ የታሪክ ትምህርት ነው። በዋናነትም ተመስጦ ማሰብ፣ ማስተዋልና ማጤንን የሚጠይቅ እንደሆነም ወጣት አብይ ይናገራል፡፡

‹‹ለሀገራችን ተማሪዎች የትኛውንም ዘርፍ ያጥኑ (ምህንድስናም ይሁን ጋዜጠኝነት ወይም ሌላ) የሀገራቸውን ታሪክ እንዲያውቁ በሥርዓተ ትምህርቱ መካተት አለበት ባይ ነኝ፡፡ ትውልዱ ሥነጥበብን የሚያደንቅና የሚወድ እየሆነ ሲመጣ የሀገሩን ታሪክ እየፈለፈለ ማጣጣም ይጀምራል የሚል እምነት አለኝ፤›› ብሏል፡፡

ወጣቶች የሀገራቸውን ዋና የታሪክ አካል እየረሱ ሲመጡ አነስተኛ በሆነችው ጉዳይ መነታረክ ይጀምራሉ፡፡ ወጣቶች አሁን የሚስተዋል ተጨባጭ እውነታም ይሄው ነው። የጋራ እሴቶቻቸውን እየጣሉ የየግል ግንጣይና ጎደሎ ታሪኮቻቸውን ያሳድዳሉ የሚል ሀሳብ ሰንዝሯል፡፡

ከዚያም አለፍ ሲል የኔ ብሔር፣ያንተ ብሄር፣ የኔ ቋንቋ፣ ያንተ ቋንቋ…ወዘተ ይባባላሉ፡፡ ነገር ግን ሀገርን ሀገር የሚያሰኛት ታሪክ የሁሉም ስብጥር ድምር ውጤት ነው። ‹‹እኔ በሰላም መኖር እንደምፈልግ ሁሉ ሌላውም እንደሚፈልግ መረዳት አለያም ማሰብ አለመቻል፡፡ ታሪካችንም እንደዚሁ እርስ በእርሱ ይማገራል፤›› ሲል ወጣት አብይ በንጽጽር አስረድቷል፡፡

በተጨማሪም ወጣት ስትሆን ደግሞ የድርብርብ ኃላፊነቶች ባለዕዳ ትሆናለህ፡፡ ከትውልድ ተቀብለህ ለትውልድ የምታሻግረው ታሪክ ጤናማና በሀቅ ላይ የተመሰረተ ሊሆን ይገባል፡፡ የተበላሸውን ታሪክ ለይቶና አርሞ ማስተካከል፣ማዋደድ፣አንድ ማድረግ ለወጣት ግዴታ እንጂ ውዴታ አይደለም፡፡

በታሪክ አጋጣሚ አደራ የተጣለበት የዚህ ዘመን ወጣት ዓለምን አሻግሮ እያየ ከደረሱበት ለመድረስ መጣር ዓላማው መሆን ሲገባው ቆሞ ተቸንክሮ ባለፈ ታሪክ ለዚያውም እውነትና ውሸቱ በማይለይ መነታረክ ስብዕናን የሚያጎድፍ ነው፡፡ የሀገር ሕልውና በእጁ መዳፍ እንዳለ አካል ሆኖ ሲታሰብ ለወጣቶች ቅን እና በጎ መሆን አማራጭ አይደለም፤ ግዴታ እንጂ፡፡

‹‹አንድ በሚያደርጉን የጋራ እሴቶቻችን፣ የጋራ ጀግኖቻችን፣ የጋራ ድሎቻችን (እንደ አድዋ አይነት)፣ ሌሎችም ወዘተ በማንሳት ልንዋደድና ልንከባበር ይገባል፡፡ ጣፈጠንም መረረንም የሀገረ መነሻው ታሪክ ነው። በመሆኑም ከሥርዓተ ትምህርት እስከ ፖለቲካ ሰነዶቻችን ድረስ በማካተት አጉልተን ማሳየት ያለብን የጋራ እሴቶቻችንን መሆን ይኖርበታል።›› ብሏል፡፡

የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ተመራቂዋ ወጣት ሀያት ሰኢድ በበኩሏ ‹‹የተማረውም ይሁን ያልተማረው ዜጋ እኩል የሚናገርላቸውና የሚያስታውሳቸው ታሪኮችና ባህሎች በብዛት ያሏት ሀገር ናት ኢትዮጵያ፡፡ ይሄ በሆነበት ስለምን አይናችን በጠባቡ እንደሚያይ አይገባኝም፡፡›› ስትል አስተያየቷን ሰጥታለች፡፡

ሀገራችን የሁላችን ታሪክ ስሪት ነች፡፡ በዚች ሀገር ግንባታ ንጥረ ነገር ያላዋጣ አንዳችም ብሔር የለም፡፡ አሁን ላይ በወጣቱ ዘንድ የሚስተዋለው በሽታ ከብዙ ሺህ መልካም ነገሮች መካከል ቅንጣት ሕጸጽ ፍለጋ መኳተን፤ በዚያች ነገር ሌላውን በጎ ተግባር ማጠልሸት… ወዘተ ሲሆን ተምሬያለሁ የሚለውና ማዕረግ የደረደረውም በራሱ ጤናማ ያልሆነ አካል ብዙ ነው፡፡ በሀገሪቱ የታሪክ ትምህርት ከመሰረቱ ተከልሶ በጥብቅ ሥነምግባር (ዲሲፕሊን) መሰጠት ይኖርበታል፡፡ ወጣቱን እያምታታ እንጀራውን የሚያበስል አካል ካለም መታረም አለበት›› ስትል ተናግራለች፡፡

ወጣቱ ታሪክን ማወቅ አለበት ሲባል በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው አገር ታሪክ አላት ይህ ታሪክ ደግሞ የተሰራ እና የሚታወቅ መሆኑን መነሻ ያደርጋል፡፡ በዚህ አስተሳሰብ ስንጓዝ ታሪክ ለአንድ አገር ወሳኝ ድርሻ የሚኖረው ለመማሪያነት ሲውል እንጂ ለጥፋት ሲውል አይደለም፡፡ በመሰረቱ ተሰራ የምንለው ታሪክ በክፉም በደግም የሚነሳ ነው፡፡ ታዲያ መነጋገር የሚገባን ቁልፉ ነጥብ ይሕን ታሪክ ከማሳወቅ ጀምሮ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባን ነው፡፡

‹‹ወጣቱ ማወቅ የሚገባው እና ማወቅ የማይገባው ታሪክ›› ተብሎ መመረጥ የለበትም። ለየትኛውም የፖለቲካ አስተምህሮ ሲባል ተመርጦለትም መማርና ማወቅ አይገባውም፤ መጋት የሚል አስተያየት የሰጡት ወጣቶቹ እዚህ ላይ ነው፡፡ በመጥፎ የተሰሩ ታሪኮች አውቀናቸው እንዳይደገሙ ለማድረግ እና ለመማማር መጠቀም ሲሆን በመልካም የተሰሩትንም ደግሞ በትምህርትነት መውሰድ ይገባል፡፡

ይህ ሲሆን ነው ወጣቶች ታሪክን ማወቅ አለባቸው የሚባልበት ዋናው ምክንያት። ስለሆነም ወጣቶቹ ከላይ እንደሰጡት አስተያየት ከሆነ ታሪክን በጥሞና አይተን የተፈፀመበትን አውድና ዓላማ አውቆ መውሰድ የሚገባንን ትምህርት መውሰድ ሲንችል ነው የታሪክ አስተማሪነት የሚገለፀው፡፡

አዲስ ዘመን ነሃሴ 2/2011

 ሙሐመድ ሁሴን