ሀበኒ!

7

ግርምት የሚፈጥሩ አስደናቂ መደመምን የሚያጭሩ ሰዎች በየሰፈሩ ሞልተዋል። በግለሰቦቹ ላይ የሚታዩት ባሕርያት የኋላ መነሻ ምክንያቶች አሏቸው። ውስጠ ምስጢሩን ካለባለቤቶቹ በቀር ማንም አያውቀው። ትላንትም ነበሩ።

ወደፊትም ይኖራሉ። የአንዳንዶቹ ታሪክ ሲገለጥ ግሩም እምግሩማን ያሰኛል። ‹‹ሀበኒ›› በያኔው ደርግ ዘመን በነበሩ ነዋሪዎች በእብድነቱ ይታወቃል። ሀበኒ የትግርኛ ቃል ነው፤ ትርጉሙ ስጠኝ ማለት ነው።

ይሄ ሰው አእምሮው ጤነኛ አይደለም፤ ወፈፌ ነው ተብሎ በሕብረተሰቡ ስለሚታመን ከሀዘኔታ በስተቀር ማንም ምንም አይለውም። አውቶቡስ ፌርማታ ላይ ነው አንጥፎ የሚተኛው። ከአግዳሚው ወንበር ስር። ብዙ ግዜ እንደዚሁ ነው የኖረው። በተለምዶ የድሮው አራተኛ ክፍለጦር፤ ጨርቆስ፤ ለገሀር አካባቢ በብዛት ያዘወትራል።

ሲለው በቅሎ ቤት እንዲያ ሲል መርካቶ ሶማሌ ተራ ከፍ ብሎ አውቶቡስ ተራ ተክለኃይማኖት ወዲህ ማዶ ይመለስና ስድስት ኪሎ ፈረንሳይ ሽሮ ሜዳም ሁሉ ይወጣል፤ ይወርዳል። አለባበሱ ቡትቶ ሁኖ ኮተቶች ይይዛል። ብዙ አይነት ቅራቅምቦዎች ይሸከማል። ጸጉሩ ላይ የሚሰካው ነገር አለው። እጆቹ ላይ የሌለ አይነት መዳብ የለም። እንደጌጥ መሆኑ ነው። ለሚያየው ያስፈራል፤ ሀበኒ ሀበኒ ።

ሀበኒ ረዥምና ዠርጋዳ የሚባል ነው። ጠይም መልከኛ። ጸጉሩ የድሮው አፍሮ። ሁሉም የሚያውቁት እብድ ነው ብለው ነው። ብዙ አይነጋገርም። የሚያውቁት ሳንቲም ይሰጡታል። ከ‹‹ሀባ፤ ሀበኒ›› ውጭ የሚለው የለውም። ‹‹ሀባ፤ ሀበኒ›› ብቻ።

በል ያለው እለት ዝምታውን ይሰብራል። በርግዶት ይወጣል። በሰውኛው ሳይሆን አንዳች መንፈሳዊ ኃይል ውስጡ ሆኖ የሚናገር ይመስላል። ድምጹ ያስገመግማል። ይናገራል። ይናገራል። ከእብድ ቁምነገር አይገኝም ባዩ ስለሚበዛ ማንም አይሰማውም። የሚሰማው ቢገኝም የሚለው አይገባውም። ድሮም እኮ ያው ነው ሰው አይሰማም።

መስሚያው በጥጥ ከተደፈነ ዘመናት አልፈዋል። ሀበኒ የትም ሄዶ የትም ዞሮ ዞሮ እዛችው አውቶቡስ ፌርማታ ላይ ተመልሶ ያድራል። ከአካባቢው ለቀናት፤ ለወራት ሲሰወር የት ሄደ ወዴት ጠፋ የሚል የለም። ስለእብድ ማን ደንታ አለው ብለህ። ሲመጣ መጣ ነው። ጠያቂ የለውም። ቢጠይቁትም አይመልስም።፡

ያኔም እኮ በደርግ ዘመን ሰው ከስራ ከወጣ በኋላ በአብዛኛው የሚፈሰው ወደ መዝናኛ ቦታ ነበር። እንደአቅሙ። ሕዝባዊ መዝናኛ መድረኮች አሉት። ባሕላዊ ጠጅ፤ ጠላ፤ አረቄ ቤቶች። በእነዚህ ቦታዎች ሁሉ እግሩ እስከሄደበት ጊዜ ድረስ ሀበኒ ይዘዋወራል። ይቀልዱበታል። ይስቃሉ። ውስጡ ይስቅባቸዋል። በል ሲለው አንዳንዴ ብቻ የአበሻ አረቄ ሲሰጡት ቁጭ ብሎ ትንሽ ይጠጣና በፍጥነት ይሄዳል።

የእኛ ሰው አብዝቶ ማውካካት መንጫጫት ግርግር ቸበር ቻቻ ይወዳል። ሀበኒ በል ሲለው ይናገራል። ቢናገርም ሰሚ የለም። ሰው አንዳች ጥሬ ስጋ ከምሮ ለብቻውም ይሁን በቡድን ያንን መጎርደም መፍጨት ጥሬ ከብስል እያማረጡ መጠጡን በአናት በአናቱ እየቸለሱ ማውካካት ነፍሱ ነው። ሀገሪቷ ላይ ችግር ረሀብ ያለ አይመስልም። ያኔም ዘንድሮም።

እነ ሀበኒን ማን ይሰማል። ኧረ ተው ተው። ተፋታን አሉ ሰዎቹ። ይጠጣል። ይሰከራል። ውስኪ ቤት ይቀያይራል። እነሆድ አምላኩ በልተው አይጠግቡ። አይጠረቁ። ያኔም ዛሬም። ሀበኒ ቤቱ አውቶቡስ ፌርማታ ስር የሆነ ቡትቶ ለባሽ እብድ ቢባልም ይሄን ሁሉ ዋጋ የሚከፍልበት አውቆ ያበደበት እብድም የተባለበት ምክንያት ይኖረዋል። ማን ያውቃል። ቡና ቤት፤ ስጋ ቤት ውስኪ ቤት፤ ሕዝቡ በብዛት ተሰብስቦ በሚያውካካበት ቦታ ሁሉ እየተገኘ እሱም ከእርሱ ያልተሻሉ እውነተኛ እብዶች መኖራቸውን ለማሳየት ደጋግሞ ይጮኸል።

በሄደበት ቦታ ሁሉ ግን ከጫጫታው መሀል ወጥተው ቀረብ ብለው የሚያነጋግሩት ሰዎች ነበሩ። ያው ትርምስ ስለሆነ ጉዳዬ ብሎ ስለምን እንደሚነጋገሩ የሚሰማም ሆነ የሚያውቅ የለም። አሄሄ ይሄኔ ሀበኒ እብድስ እናንተ ከንቱዎች ሳይል ይቀራል። ሹማምንት ቆነጃጅት ሆን ብለው በከፈቷቸው የማጥመጃ ውስኪ ቤቶችና መዝናኛ ስፍራዎች ሞቅ እስኪላቸው እየተዝናኑ የሀገርን ጥብቅ ምስጢር ሜዳ ላይ ያዝረከርኩታል።

ጨርቃቸውን ያልጣሉ እብዶች ያልተባሉ የሚሰሩትን ስራ በጥንቃቄ የሚከውኑ ብዙ ሺህ ሀበኒዎች እንዳሉ የሚያውቅ ስለመኖሩ መናገር ይከብዳል። ብዙው መንጋ ሆዱንና መጠጡን አጥብቆ ወዳጅ ነው። በዘፈኖች ድምጽና በቆነጃጅት ውበት ይሰክራል። በጫጫታ ይዋጣል። ለእነሱ ዓለምና መንግስተ ሰማያታቸው ሆዳቸው ነው።

ሁካታና ጫጫታው የትም ቢሆን የተለመደ ነው። አንዳንዴ በመደመም የሚያየው ሀበኒ እኔ አንድ ሰው ነኝ እነሱ በስሜታዊነት የሰከሩ ናቸው በሚል አይነት ራሱን የእብዶች ሁሉ አለቃ አድርጎ ይወስደዋል። ግለሰቦች በተናጠል ሕዝብም በቡድን ያብዳል ለካ በዘመነ እብደት። የዘመን ወፈፌነት።

ሀበኒ አንዳንዴ ዝምታው ሲሰበር የታመቀ ሳቁን አንፎልፉሎ ይለቀዋል። ለተመልካቹ የእብድ ሳቅ መሆኑ ነው። ይሄን ያዩ ምናባቱ ሆኖ ነው ይሄ እብድ የሚያስካካው ይላሉ። እዛው ለገሀር ከአውቶቡስ ፌርማታው ወደታች ባሉ ሰፈሮች ሁሉም ስለሚያውቁት ምግብ ይሰጡታል። ግን ደግሞ አንዷን ቡና ቤት ከምሽቱ አራትና አምስት ሰዓት አካባቢ ያዘወትራታል።

 ባለቤትዋ ሀበኒ መጣ የሚበላ ስጡት ከማለትም ባለፈ በርህራሄ አይን ነበር የምታየው። ሀበኒ በሁሉም ስለሚታወቅ ምግብ ፍለጋ ጦር ሰፈርም ያስገቡታል። የሰጡትን ሰብስቦ የሚያየውን አይቶ ይወጣል። አውቶቡስ ፌርማታው ጋ ሌሊት ተኝቶ ወይንም ሲያሻው ከላይ እታች እየተንጎራደደ በሌሊት ሠራዊት በስንት መኪና እንደተንቀሳቀሰና ወዴት አቅጣጫ እንደሄደ እብዱ ሀበኒ ያያል።

በል ሲለው የጨሰው መንደር ካዛንችስ ጎራ ብሎ ስካሩን ሁካታውን ዝሙቱን እያየ ሀበኒ ሀበኒ እያለ ያመሻል። መጨረሻ ወደ መሹዋለኪያው ይመለሳል። ሀበኒ በሁሉም አካባቢ የታወቀ እብድ ስለሆነ የይለፍ ፈቃድ አለው። የማያውቁት አዲስ የተመደቡ ፖሊሶች ወይንም አብዮት ጠባቂዎች ካልሆኑ በስተቀር የፈለገው ሰዓት ቢሆን እንዳሻው ሲሄድ የሚነካው አልነበረም። ሀበኒ ሀባ።

ግርግሩ እስኪያልፍ ያስቀምጡታል። ወይ እዛው ያሳድሩታል። ሲነጋ ወደልመናው ወደሚሄድበት ይሄዳል። ምድረ ሆድ አምላኩ፤ ደንደሳምና ቀፈታም ሁሉ ለዝሙት ያበደ እብድ መሆኑን እየረሳ እኔን ሀበኒን እብድ ሲለኝ ስቄ አላባራም የሚል ይመስላል ሀበኒ። ሀበኒ የልቡን የውስጠቱን ተናጋሪ እብድ ነው። በሚያየው ይገረማል። ሰው ጉንጩ እስኪለጠጥ በለው ሊቀደድ እስኪደርስ ይበላል። ይስቃል። ያስካካል ይዘሙታል። ከዚህ ያለፈ ቁም ነገር የለውም እንዴ ይላል ሀበኒ።

ሀበኒ ያገኘውን ቀምሶ ውሎ ያድራል። ሲሰጡት ይበላል። ወይንም በፌስታል ይዞ ይሄዳል። እንዲያ እንዲያ እያለ ሲኖር የነበረው ሀበኒ ከአካባቢው ከሰፈሩ ከመንደሩ ይታይ ከነበረባቸው ቦታዎች ሁሉ በድንገት ተሰወረ። አንድ ዓመት ግዜ ተቆጠረ። አውቶቡስ ፊርማታው ላይ እቃዎቹ ነበሩ። አብዛኛው ሰው አይ በቃ ሞቶ ማዘጋጃ ቤት ቀብሮት ነው ብሎ ደመደመ።

የመንግስት ለውጥ ተደርጎ የኢህአዴግ ሠራዊት አዲስ አበባ በመጀመሪያ ሲገባ የጦር መሪ ሆኖ ሠራዊት ይዞ የገባው አንዱ ሀበኒ ነበር። ጸጉሩ ጎፍሮአል። መሳሪያ ታጥቆአል። በቀጥታ ረዥም ግዜ በእብድነት ወደኖረበት ሰፈር ሄደ። በተለይም ያቺ ምሽት ወደሚያዘወትራት ባለቤቷ በርህራሄ አይን ታየው ወደነበረው ቡና ቤት። በእብድነቱ ወይንም ለልመና አልነበረም የሄደው። ውለታውን ቆጥሮ ተራውን ጓደኞቹን አስከትሎ ሊጋብዝ እንጂ። ማንም አልጠረጠረም። አልገመተምም። ባለቤቷን አስጠራ። መጥታ ተቀመጠች። ረሳሽኝ እንዴ ሀበኒ ነኝ። የያኔው እብድ ፌርማታው ጋ እተኛ የነበርኩት ሀበኒ አላት። ፊትህ መጣልኝ አለችውና ጮኸች። ሀበኒ ሀበኒ እያለች። ሰው ተሰባሰበ።እውነትም ሀበኒ

አዲስ ዘመን ነሃሴ 2/2011

ወንድወሰን መኮንን