የኢትዮጵያ ካራቴ ብሄራዊ ቡድን ዝግጅት

26

12 ኛው የመላ አፍሪካ ጨዋታ ከነሐሴ 13 እስከ 25 ቀን 2011 ዓ.ም በሞሮኮ ራባት ከተማ የሚካሄድ ሲሆን ኢትዮጵያም ተሳታፊ ከምትሆንባቸው 13 የስፖርት አይነቶች አንዱ ካራቴ ነው።

በውድድሩ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ካራቴ ብሄራዊ ቡድን ልኡክ ከወዲሁ ቅድመ ዝግጅቱን እያደረጉ እንደሚገኙና በውድድሩም ጥሩ ውጤት ያስመዘግባሉ የሚል እምነት መያዙ ተጠቁሟል። ተሳታፊ ስፖርተኞችም ውጤታማ ለመሆን እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ካራቴ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሠፋ አንጀሎ ዝግጅቱን አስመልክተው እንደተናገሩት ፤ ለውድድሩ ትኩረት በመስጠት ከግንቦት ወር ጀምሮ ዝግጅት መጀመሩንና ሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተሳተፉበት ሻምፒዮና በማካሄድ ውጤታማ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሎ የታመነባቸው 25 ወጣት ስፖርተኞች ዕጩ የብሔራዊ ቡድን አባል የማድረግ ስራ መከናወኑን ተናግረዋል፡፡

ከተመለመሉት ዕጩ የብሔራዊ ቡድን አባላት ውስጥም አስፈላጊውን ማጣሪያ በማድረግ 3 ሴትና 6 ወንድ ስፖርተኞች ለውድድሩ ተመርጠዋልⵆ ስፖርተኞቹም በቀን 2 ጊዜ የስልጠና መርሃ ግብር ወጥቶላቸው ዝግጅታቸውን በማድረግ ላይ ሲሆኑ መንግስትም በቂ የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ በውድድሩ የተሻለ ውጤት እንደሚመዘገብ ፍላጎት ማሳየቱን ተናግረዋል። እገዛው ጥሩ ቢሆንም ብሄራዊ ቡድኑ በተወሰነ መልኩ ውስንነቶች እንዳሉበት ጠቁመዋል።

ከውስንነቶቹ መካከል ዓለም አቀፉ የካራቴ ፌዴሬሽን ያረጋገጠው የመወዳደሪያ ልብስ “ቲሞኖ” በሀገር ውስጥ አለመኖሩ ነው ያሉት አቶ አሰፋ ይህን ችግር ለመፍታትና ለውድድሩ ሙሉ ሆኖ ለመገኘት ከአንዳንድ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመጻጻፍ ላይ ነን ብለዋል፤ ጥረቱ ተሳክቶም ለውድድሩ እንደሚደርስ ያላቸውን እምነት ጠቁመዋል።

የብሄራዊ ቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ኢንስትራክተር ዮሴፍ ተበጀ በበኩላቸው ዝግጅቱ ጥሩ መሆኑን ተናግረው ተወዳዳሪ ስፖርተኞች የሚሰጣቸውን ስልጠና በአግባቡ እየተቀበሉ መሆኑን እና በስነ ልቦና ፣ በታክቲክ እና በቴክኒክ በመዘጋጀት ሙሉ የማሸነፍ አቅምም መፍጠራቸውን ተናግረዋል ፡፡

ኢንስትራክተር ዮሴፍ እንደሚሉት ቡድኑ እየተደረገለት ያለው ድጋፍ ከወትሮው የተለየ ነው ተወዳዳሪዎችም በድጋፉ ልክ ውጤት ለማስመዝገብ ጥረት እያደረጉ መሆኑን ገልፀዋል ፡፡

በዝግጅቱ ዙሪያ አስተያየቱን የሰጡት የነጠላ ካታና የቡድን ካታ ተወዳዳሪ የሆኑት ሄዋን እና ሰለሞን እንደገለፁት ፤ በፌዴሬሽኑ እየተደረገ ያለው ድጋፍ እና በአሠልጣኙ እየተሰጣቸው ባለው ስልጠና ደስተኞች መሆናቸውን በመግለጽ ለሀገራቸው ውጤት በማስመዝገብ አዲስ ታሪክ ለመስራት መዘጋጀታቸውን አብራርተዋል፡፡

በሞሮኮ ራባት በሚካሄደው 12ኛው መላ አፍሪካ ጨዋታ በካራቴ ስፖርት ኢትዮጵያ በ 3 ሴት በ 6 ወንድ ስፖርተኞች ተወክላ የምትሳተፍ ሲሆን በነጠላ ካታ እና ኩምቴ (fight) በወንድ እና በሴት እንዲሁም በቡድን ካታ በወንድ ትካፈላለች ፡፡

አዲስ ዘመን ነሃሴ 2/2011

ዳንኤል ዘነበ