የስፖርት አካዳሚው የ2012 ዓ.ም ዕጩ ስፖርተኞችን ሊመለምል ነው

32

የኢትዮጲያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ የ2012 ዓ.ም የስልጠና ዘመን ዕጩ ስፖርተኞችን ምልመላ ሊያካሂድ መሆኑን በይፋዊ የማህበራዊ ገጹ አስታውቋል ።

አካዳሚው በዚሁ መረጃ ላይ እንዳሰፈረው፤ የ2012 ዓ.ም የስልጠና ዘመን ዕጩ ስፖርተኞችን ምልመላ ሊያካሂድ መሆኑን ገልጾ፤ በአስር የስፖርት አይነቶች በርካታ ቁጥር ያላቸውን ስፖርተኞችን በአስር የስፖርት አይነቶች ተቀብሎ ለማሰልጠን እቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። በዚህ መሰረት በእግርኳስ፣ አትሌቲክስ፣ ቮሊቮል፣ ቅርጫት ኳስ፣ ብስክሌት፣ ቦክስ፣ ወርልድ ቴኳንዶ፣ ዉሃ ዋና፣ ፓራሊምፒክ፣ ጠረጴዛ ቴኒስ ስፖርት ነው ብሏል።

የስልጠና መስፈርት ማስቀመጡን የገለጸው አካዳሚ፤ ከ15 በታች እና ከ17 ዓመት በታች ታዳጊዎች በማንኛውም የትምህርት ደረጃ የሚገኙ ፍላጎት ያላችው ታዳጊዎች ለመመልመል ማቀዱን ይፋ አድርጓል።

አካዳሚው ምልመላውን ከነሐሴ 1 እስከ 15 ቀን 2011 ዓ.ም እንደሚያካሂድ የገለጸው አካዳሚው የሰልጣኝ ምልመላ የሚደረግባቸው አካባቢዎች በአራቱም የሃገሪቱ አቅጣጫዎች በሰባት ቡድን በመዋቀር ወደ ተለያዩ ክልሎች ከትናንት ጀምሮ መንቀሳቀስ መጀመሩን አስታውቋል።

በዚህ መሰረትም ወልቂጤ፣ ጅማ፣ መቱ፣ ጋምቤላ ደምቢዶሎ፣ ግምቢ፣ ቤኒሻንጉል፣ መቀለ፣ ሽሬ፣ አክሱም፣ አዲግራት፣ አብአላ፣ ሰመራ፣ አዋሽ አርባ፣ ጅግጅጋ፣ ሀረር፣ ምስራቅ ሀረርጌ፣ ድሬዳዋ፣ ጭሮ፣ መተሀራ፣ሀዋሳ፣ ሻሸመኔ፣ ሀላባ፣ ወላይታ፣ አርባምንጭ፣ ጂንካ፣ ሆሳእና፣ ወራቤ፣ዲላ፣ ጉጂ፣ ቦረና፣ በባሌ ፣ አርሲ፣ ሰሜን ሸዋ፣ ደብርማርቆስ፣ ኮሶበር፣ ባህርዳር፣ ጎንደር፣ ወልዲያ፣ ደሴ፣ ደብረ ብርሀን መሆኑን አስታወቋል።

አካዳሚው ሰልጣኞችን የሚመለምል በትን መንገድ በተደጋጋሚ ጥያቄን ሲያስነሳ የነበረ እንደመሆኑ በቀጣይ ወር ለማከናወን የጀመረው ጉዞ ከዚሁ ትችት የሚያወጣው መሆኑ ተገልጿል። በአራቱም የሃገሪቱ አቅጣጫዎች የሚገኙ ክህሎት ያላቸውን ታዳጊ ስፖርተኞችን በጥራትና በብዛት ማግኘት የሚያስችለው እንደሚሆን ተጠብቋል።

የኢትዮጲያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ በ2005 ተመርቆ በ2006 ዓ.ም ስፖርተኞችን መልምሎ ስራውን የጀመረ ሲሆን ፤በ2011 ዓ.ም ዘንድሮ በጥሩነሽ ዲባባ ማሰልጠኛ ማዕከል ለሰባተኛ ጊዜ፣ የአዲስ አበባ ካምፓስ ደግሞ ለሶስተኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን 105 ስፖርተኞች ማስመረቁ የሚታወስ ነው።

አዲስ ዘመን ነሃሴ 2/2011

ዳንኤል ዘነበ