ሰብዓዊ መብት የቅድሚያ ቅድሚያ ይሰጠው!

28

 ‹‹መጀመሪያ መቀመጫዬን›› አለች አሉ ጦጣ። መቅደም ያለበትን ማስቀደም እጅግ ተገቢ እንደሆነ ለማስረገጥ የሚያሳስብ አቋም ነው። እርግጥ ነው ከውስጥ ልብሱ ቀሚሱ አይቀድምም። ለዘመናት የዘለቅንበት የሰብዓዊ መብት እርምጃ በመንታ መንገዶች የተመታ ነው። መጀመሪያ መቀመጫዬን ያለችው እንስሳ በህይወት ጉዞ ውስጥ መቅደም ያለበትን ነገር ለማወቅ፤ ከእኛ የተሻለ እውቀት ኖሯት እንዳልተረተችው አያጠራጥርም።

ተረቱን ተራቿ ተረተችም አልተረተች መሆን ያለበት ነገር ትኩረት እንዲያገኝ ከመናገር ወደ ኋላ ማለቱ አይበጅም። ብዙ ጊዜ ወደ ኋላ የሚያስጎትቱን ነገር ግን ከሁሉ በፊት ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮችን ባለማስቀደም የሚፈለፍሉ አያሌ ችግሮች ያጋጥማሉና።

በአገራችን የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ ከአእላፍ ነቀፌታዎቹ አንዱ በሰብዓዊ መብት ላይ ያለው ክፍተት ነው። መፈጠርን በሚያስረግም ግርፋት፣ ቁም-ስቅል፣ እስራት፣ ጫካ ውስጥ መጣል፣ በአውሬ ማስበላት ወዘተ ከእስር ቤት ውጭ ያለው ዜጋም ቢሆን በመፍራት በመንቀጥቀጥ የኖረ፣ ጸጥታ አስከባሪው ደስ ባለው ቀን ያሰረበትን ዘመዱን መጠየቅ እንደ ሰማይ ርቆት፣ ጭቆናው ገላጋይ የሌለው መርገም መስሎት፣ እስር ቤት ባይገባም ቤቱን እስርቤት አድርጎ በስነልቦና መረበሽ የማቀቀበት ጊዜ አሁን ላለው ትውልድ የሩቅ ጊዜ ትዝታ አይደለም። በዚህ ጉዟቸው ውስጥ የተረጋጋው ኑሯቸው የተናጋባቸው፣ ለዱብዳ ስደት የተዳረጉ፣ ቤተሰብ የተበተነባቸውና ህይወት የተመሰቃቀለባቸው ዜጎቻችን በርካታ ናቸው።

የልጆቻቸውን እጅ የሚሹና መጦር የሚገባቸው፣ ያለ ምርኩዝ መንቀሳቀስ የማይችሉ አቅመ ደካማ አዛውንት የታሳሪ ወላጆች ስንቅ ተሸክመው ከከተማ ዳር ባሉ እስርቤቶች ሲንከራተቱ መቆየታቸውም እውነት ነው። በአምባገነኑ ደርግ በመጨቆኑ አዝኖ ጫካ ገብቶ፣ ቧጥጦ የታገለ መንግሥት እንኳን ላለፉት ዓመታት በሰብዓዊ አያያዝ ላይ ቀይ መስመር ማለፉና በሰው ደም ላይ ተመቻችቶ ተቀምጦ የስልጣንን ማረፊያ ሲያመቻች እንደነበርም አይረሳም።

ዜጎች በተለይም ወጣቶች ኢፍትሃዊነትንና ጭቆናን በመታገላቸውና መስዋዕትነት በመክፈላቸው ከመሰረታዊ የሰውነት ባህሪ ጋር ሲጋጭ የኖረው የሰብዓዊ መብት ጥሰት አሁን ላይ በእጅጉ እንደቀነስ የዓለም መገናኛ ብዙኃን ሳይቀሩ ዘግበውታል።

አሁንም መሰረታዊ የሰብዓዊነትን መርህን ችላ ብሎ ለስልጣን መደራደር ቅድሚያ የሚሰጠው አለመሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። አገር በሰው ልጅ ህይወት ላይ በደል ያደረሰን አካል ከተጠያቂነት ነፃ ሆኖ ሲንጎራደድ ማየትን አትሻም። ጥረቱ ደግሞ በሰብዓዊ መብት ላይ ጉልህ ወንጀል የሰሩትን አካላት ለፍትህ በማቅረብም ጭምር መገለጽ ይኖርበታል።

ሰብዓዊ መብትን ከማክበር ያለመጀመር የችግሮች ሁሉ ችግር ነው። ‹‹ስትፈጭ የነበረች ማንጓለል አቃታት›› እንዳይሆንብን ከወጡ እንስራውን እናስቀድም። ለሰብዓዊ መብቶች ኩራዝ ነስተን ለሌሎች ጉዳዮች ፋኖስ የምንለኩስ ከሆነ እርባና ያለው ተግባር ስለመፈጸማችን አጠያያቂ ይሆናል።

ሰብአዊ መብትን በማክበርና በማስከበር ረገድ የታዩት ጅምር ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አሁንም ለሰብዓዊ መብቶች የምንሰጠውን ጊዜ አንጣ። የከዚህ ቀደሙን በአንባገነናዊ ሥርዓቱ በተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የጎበጠውን ለማቃናት ቁም ስቅል ከማየቱ በዘለለ መስመር እየያዘ ያለውን የሰብዓዊ መብት አያያዝ ከዳር ማድረስ ይገባል። አሁን ላይ ያለው መንግሥት በባህሪው ህልሙ ሩቅ ነው። ህልሙ ሩቅ የሆነ ደግሞ ተግባሩ አያጥርም። ማድረግ ያለበትን ነገር እያደረገ የሚጎድልበት ነገር እንደሚኖር አይረሳም።

በቀድሞ በደል ዛሬን ስለ እውነት የሚማፀኑና ፍትህ የሚሹ ወገኖች አሉ። ፖለቲካውም፣ ኢኮኖሚውም፣ ማህበራዊውም ጉዳይ የሚኖረው ሰብዓዊ ፍጡር እስካለ ድረስ ብቻ ነው። በመሆኑም የለውጥ አመራሩ የጀመረውን ጠንካራ የተጠያቂነት መንፈስ በማስቀጠል ሰብዓዊ መብትን ያለ ድርድር ከሁሉ ሊያስቀድም ይገባዋል። መንግሥት ሰብዓዊ መብትን ለማክበር ይህን ያህል ቁርጠኛ እርምጃ እንደመውሰዱ ህዝብም ለህግ የበላይነት በመገዛት ጅምሩን ለውጥ ለፍሬ ማብቃት ይጠበቅበታል።

በደልን ረስቶ፣ ጥፋትን ሁሉ ይቅር ብሎ ማለፍ ኢትዮጵያዊ ባህላችን ቢሆንም ለሰብዓዊ ፍጡር እንግልት የሚዳርጉትን መታገልና ዜጎች በሁሉም አካባቢ ሰብዓዊ መብታቸው በእጅጉ ተጠብቆ እንዲኖር ማድረግ ደግሞ የመንግሥት የቅድሚያ ቅድሚያ ሥራ መሆን አለበት።  

አዲስ ዘመን ነሃሴ 3/2011