‹‹መብትን ማወቅ ግዴታን ታሳቢ የማያደርግ ከሆነ ትርጉም አይኖረውም›› አቶ ይበቃል ግዛው የብሔራዊ ሰብአዊ መብት የድርጊት መርሐ ግብር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ

30

በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ2012 ዓ.ም ሁለተኛው ብሔራዊ የሰብአዊ መብት የድርጊት መርሃ ግብር የሚጠናቀቅ ቢሆንም፤ የመጀመሪያውም ሆነ ሁለተኛው የድርጊት መርሃ ግብሮች አፈፃፀማቸው ላይ ሰፊ ክፍተት መኖሩ ይገለፃል፡፡ መርሃ ግብሮቹ ከ350 ያላነሱ ተቋማት እንዲተገብሩት አቅጣጫ ቢቀመጥም፤ ከወረዳ እስከ ክልልም ሆነ የፌዴራል የመንግስት ተቋማት ድረስ የመተግበር ሰፊ ክፍተት እንዳለባቸው ይነገራል፡፡ ይህ ለምን ሆነ? በህብረተሰቡም ሆነ በመንግስት የሥራ አመራሩ ዘንድ በሰብአዊ መብት አያያዝ ላይ በቂ ግንዛቤ አለ? በሚሉና ሌሎችም ከሰብአዊ መብት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን በመያዝ ወደ ፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አምርተናል። በዚያም የተቋሙ የብሔራዊ ሰብአዊ መብት የድርጊት መርሃ ግብር ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ይበቃል ግዛው ምላሽ ሰጥተውናል። ከአቶ ይበቃል ጋር ያካሄድነውን ቃለመጠይቅ እንዲህ አቅርበነዋል፡፡

አዲስ ዘመን፡በቅድሚያ ለትብብርዎ እያመሰገንኩ፤ ጥያቄያችንን ሰብአዊ መብት ምንድን ነው በሚል ብንጀምር?

አቶ ይበቃል፡ጥሩ ሰብአዊ መብት ሰዎች ሰው በመሆናቸው ብቻ የሚያገኙት መብት ነው፡፡ ሌሎች ተቀጥላ ቅድመ ሁኔታዎች የሌሉት፤ ከመንግስትም ሆነ ከሌሎች ዜጎች በችሮታ የሚሰጥ ሳይሆን ልክ እንደህገመንግስቱ ባሉ ሰነዶች ዕውቅና የሚሰጠው እና ጥበቃ የሚደረግለት መሰረታዊ መብት ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡ይህ ሰብአዊ መብት እርሰዎ ባሉት ልክ በኢትዮጵያ ግንዛቤው ተፈጥሯል?

አቶ ይበቃል፡በጣም ብዙ ይቀራል፡፡ በእርግጥ ሰብአዊ መብት እንዲሁ በአጠቃላይ ቃሉን ብዙ ሰው አመራሩም ሆነ ትንሽ ፊደል የቀመሰው የህብረተሰብ ክፍል ያውቀዋል ብሎ መናገር ይቻላል፡፡ ነገር ግን ምንነቱ፤ ሰብአዊ መብት ሲባል ዝርዝሮቹ ጉዳዮች የትኞቹ ናቸው? ቢባል ምላሹ ላይ በጣም ያወያያል፡፡

መብትን ማወቅ ግዴታን ታሳቢ የማያደርግ ከሆነ ትርጉም አይኖረውም፡፡ ምክንያቱም እኔ ሰብአዊ መብቴ እንዲከበር ስፈልግ በዛው ልክ የሌሎችን ሰብአዊ መብት የማክበር እኩል ግዴታ አለብኝ፡፡ ስለዚህ በአጠቃላይ በህብረተሰቡ ውስጥ ሰብአዊ መብት የምትለዋ ቃል ብትታወቅም፤ ከዚህ ጋር ተያያዥ የሆኑ በርካታ ጉዳዮችን ከማወቅና ከመገንዘብ አንፃር ብዙ ይቀራል፡፡ በመንግስት በኩልም እንደዚያው ነው፡፡

ከህገመንግስቱ አጠቃላይ ይዘት አንድ ሶስተኛው ለሰብአዊ መብት ጥበቃ ያደርጋል፡፡ ነገር ግን ህገመንግስቱ ይህን ያህል ክፍሉ ለሰብአዊ መብት ካዋለ፤ ህገመንግስቱን ተከትለው የሚመጡ መንግስታዊ ሥርዓቶች ለሰብአዊ መብት ትኩረት መስጠት እንዳለበት እየነገረን ነው፡፡ ይህን ያህል ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ በዕለት ተዕለት መንግስታዊ አገልግሎቶች ላይ ምን ያህል እየተተገበረ ነው ካልን ያነጋግራል፡፡

አሁንም በለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ አንዱና ትልቁ መገለጫው ከሰብአዊ መብቶች ጋር ተያይዞ የሚታዩ ጉዳዮች ናቸው፡፡ እንደመንግስት ሰራተኞች መብቶችን ሁላችንም ልናውቅ እንችላለን፡፡ ፖሊስ፣ አቃቤ ህግ፣ ማረሚያቤትና ሌሎችም ተቋማት ሰብአዊ መብትን ያውቃሉ፡፡ ነገር ግን የመብቱ ጉዳይ ከመፃፉ ባለፈ በዕለት ተዕለት ሥራችን ሊኖረው እና ሊሰጠው የሚገባው ክብደት እንዲሁም ከአስገዳጅነቱ በተጨማሪ የሥራ መመሪያ ከማድረግ አንፃር በጣም ብዙ ይቀራል። ስለዚህ ቃላቱን ከማወቅ ባለፈ ብዙ ግንዛቤ አለ ብሎ ለመውሰድ ያዳግታል፡፡

አዲስ ዘመን፡ዜጎች የራሳችን መብት ነው በሚል የሌሎችን ሰብአዊ መብት የሚገፉበት ሁኔታ ያጋጥማል፡፡ በስፋት ሲታይ የነበረው ሰዎችን ከኖሩበት ማፈናቀል ጥሩ ምሳሌ ሊሆን ይችላል።

አቶ ይበቃል፡- ህገመንግስቱ ያቋቋመው ፌዴራላዊ ሥርዓት አለ፡፡ ይህ ሥርዓት ዜጎች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ በቋንቋቸው እንዲዳኙ እና እንዲተዳደሩ ያለመ ነው፡፡ ስለዚህ በየአካባቢው ብሔር ብሔረሰቦች ራሳቸውን የሚያስተዳድሩበት አደረጃጀት ፈጥሯል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የመጣው ጥቅም እንዳለው ሁሉ የፈጠርነው የሰብአዊ መብት እና የዴሞክራሲ ግንዛቤ አነስተኛ በመሆኑ በርካታ ችግር ተፈጥሯል፡፡

ለምሳሌ አንድ ክልል ለክልሉ መጠሪያ የሆነው ብሔረሰብ ተወላጆች የሚኖራቸው መብቶች ምንድን ናቸው? በዛ ክልል አበበ ወይም ከበደ የሚኖረው መብት የዚያ ብሔር ተወላጅ ስለሆነ ነው? ቋንቋን በመናገር የሚገኙ መብቶችና ጥቅሞች የትኞቹ ናቸው? ቋንቋን ባለማወቅ የሚቀሩት መብቶች የትኞቹ ናቸው? በጣም ተንትኖ በግልፅ የማስቀምጥ ሥራ አልተሰራም፡፡

አዲስ ዘመን፡በዝርዝር የዚህኛው መብት ይሄ ነው፤ የዚያኛው ደግሞ ይሄ ብሎ ለይቶ መብቶችን ማስቀመጥ አይከብድም? ተቀባይነቱስ አያሳስብም?

አቶ ይበቃል፡እንደ ግለሰብ አይከብድም የሚል እምነት አለኝ፡፡ መጀመሪያ የግለሰብ እና የቡድን መብቶች የትኞቹ ናቸው ብሎ ማስቀመጥ ይቻላል። ራስን በራስ የማስተዳደር፣ ቋንቋን የመጠቀምና የማዳበር፣ በቋንቋ የመተዳደር መብት እንደ ቡድን የሚወሰዱ መብቶች ናቸው፡፡ በእዚህ ውስጥ ግን የማይሸራረፉ የግለሰብ መብቶች አሉ፡፡

ዜጎች በየትኛውም አካባቢ ተንቀሳቅሰው የመኖር፣ በየትኛውም የአገሪቷ ጥግ የመሥራት ንብረት የማፍራት፣ በአካባቢያቸው በሚሰጡ ውሳኔዎች ላይ ተሳትፎ የማድረግ መብት አላቸው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ነገሮች እንዴት ይጣጣሙ አንደኛው ሌላኛውን የሚከልልበት ቦታ አለ? ሁለቱ ፅንሰ ሃሳቦች የግለሰብና የቡድን መብቶች ይገፋፋሉ ወይስ እርስ በእርስ ይመጋገባሉ? የሚለው ጉዳይ በአገር ደረጃ ብዙ ትንተና ይቀረዋል፡፡

እነዚህን ትንተናዎች ስናደርግ ቀጣይ የፖሊሲ እርምጃዎችን መነሻዎች ማግኘት ይቻላል፡፡ የሚወጡ ህጎች የሚኖሩ የዕለት ተዕለት ሥራዎች እና የአስተዳደር ሥራዎች በእነዚህ ትንተናዎች ላይ የተመሰረቱ ሲሆኑ፤ የሚነሱ ግጭቶችን ለመቀነስ ያስችላል፡፡ ከዛ ባለፈ ግን በተደጋጋሚ የሚሰማው ይሄ ክልል የዚህ ብሔረሰብ ነው ሌላው ሰው አያገባውም፤ ሌላው ልክ ከውጪ እንደመጣ መጤ ነው ሲባል ይሰማል፡፡ ይህ ትክክል አይደለም፡፡

ኢትዮጵያዊ በመሆን የትም ቦታ ቢሆን የማይጣሱ መሰረታዊ መብቶች አሉ፡፡ ክልሎች ደግሞ አሁን ባላቸው አደረጃጀት፣ ባህሪ እና መነሻ ለተወሰኑ ቋንቋን መሰረት ላደረጉ ጉዳዮች የተለየ ፍላጎት ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ያንን መተንተን ይቻላል፡፡ ይህን ማጥናት ደግሞ ትልቅ የቤት ሥራ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡ስለዚህ አሁን የሚታየው ችግር የመንግስት ክፍተት ነው ማለት ነው?

አቶ ይበቃል፡አዎ! ይህ ራሱ በመንግስት መሰራት የነበረበት ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡ስለእናንተ ቀጥተኛ ሥራ እንነጋገር፡፡ የሰብአዊ መብት የድርጊት መርሃ ግብር መነሻው ምንድን ነበር?

አቶ ይበቃል፡- ብሔራዊ የሰብአዊ መብት የድርጊት መርሃ ግብር ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ያለ አይደለም፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና የተሰጠው ነው፡፡ እ.አ.አ በ1993 ኦስትሪያ ቬና ላይ የተደረገ የአለም የሰብአዊ መብቶች ኮንፈረንስ ነበር፡፡ እዛ ላይ የተባበሩት መንግስታት አባል አገር የሆኑ ሁሉም አገራት ተሰባስበው በዓለም የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ያለበትን ደረጃ ገምግመዋል፡፡

ይህንን ስብሰባ ሲያጠናቅቁ አንድ የመግባቢያ ሰነድ አቅርበዋል፡፡ እዛ ላይ ሁሉም የዓለም አገራት ያሉባቸውን የሰብአዊ መብት አፈፃፀም ችግሮችና ጠንካራ ጎኖች የሚለዩ እነዚህን ችግሮች ለማቃለል የሚያስችሉ ብሔራዊ የሰብአዊ መብት የድርጊት መርሃ ግብር ሰነዶችን እያዘጋጁ ወደ ሥራ እንዲያስገቡ የሚጠይቅ ስምምነት ነበር፡፡ ይህን ተከትሎ የተለያዩ የአለም አገራት ሰነዶቹን እያወጡ ሲተገብሩ ቆይተዋል፡፡

ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያ ብሔራዊ የሰብአዊ መብት የድርጊት መርሃ ግብሩ በምክረሃሳብ ደረጃ የተነሳላት እ.አ.አ በ2009 ነው፡፡ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ምክር ቤት ሁሉን አቀፍ የሰብአዊ መብት ግምገማ መድረክ አለው፡፡ ይህ በየአምስት አመቱ በተባበሩት መንግስታት ምክር ቤት በኩል የሚካሄድ ሁሉም አባል አገራት የሰብአዊ መብት አያያዛቸው የሚፈተሽበት መድረክ ነው፡፡

እዚህ መድረክ ላይ በ2009 ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ሪፖርቷን አቅርባለች፡፡ አፈፃጸሟ ላይ ያሏትን ጥሩ እና ደካማ ጎኖቿን ስታቀርብ ከአባል አገራት የሚሰጧት ምክረሃሳቦች ነበሩ፡፡ ከእነዚያ አንዱ የድርጊት መርሃ ግብሩን ብታዘጋጅ የሚል ነበር። ስለዚህ ይህንን ተከትሎ እ.አ.አ በ2011 የዝግጅት ሂደቱ ተጀምሯል፡፡

አዲስ ዘመን፡የድርጊት መርሃ ግብሩ በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት መከበር ላይ ምን ለውጥ አመጣ?

አቶ ይበቃል፡- የድርጊት መርሃ ግብሩን ለማዘጋጀት እ.አ.አ 2011 ላይ እንቅስቃሴ ቢደረግም፤ መተግበር የጀመረው እአአ በ2015 ላይ ነው፡፡ ምን ያህል ተተገበረ? የሚለው ግን ሰፊ ውይይትን ይጠይቃል፡፡ ሰነዱ እንደማንኛውም የመንግስት ዕቅድ በተለይ ሰብአዊ መብት ላይ ሊከናወኑ የሚገቡ ተግባራትን እና መወሰድ ያለባቸውን እርምጃዎች አስቀምጧል፡፡

ዝርዝር ተግባራትንና ሊሰራ የሚገባውን አካል ለይቶ ለመንግስት ተቋማት የቤት ሥራ እየሰጠ የሄደ ሰነድ ነው፡፡ ሰነዱ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መፅደቁን ተከትሎ ግን ወደ ሥራ ሲገባ በጣም ብዙ ፈታኝ ነገሮች ነበሩ፡፡ በወቅቱ መንግስት ከሰብአዊ መብት አፈፃፀም አንፃር ውስንነት ነበረበት፡፡

በአጠቃላይ መንግስትም ሰብአዊ መብትን ከፍትህ አካላት፣ ከማረሚያ ቤት እና ከፖሊስ አያይዞ የማየት ሁኔታ አለ፡፡ ትምህርት፣ ጤና እና መሰረተ ልማትን በሙሉ እንደሰብአዊ መብት አጀንዳ አለማየት እና የድርጊት መርሃ ግብሩን በሙሉ ቁርጠኝነት መተግበር ያለመቻል ችግር ነበር፡፡ ይህ የመጀመሪያው የድርጊት መርሃ ግብርም ላይ ሆነ ሁለተኛው የድርጊት መርሃ ግብር ላይ የታየ ነው፡፡

የድርጊት መርሃ ግብሩን የሚፈፅሙት 350 የሚደርሱ ተቋማት ናቸው። እነዚህን የምናስተባብረው እኛ ነን፡፡ በየአመቱ በተሰጧቸው አቅጣጫዎች መሰረት የሚያቅዱ እና በአመት ሁለት ጊዜ ሪፖርት የሚቀርቡ ቢሆንም፤ አፈፃፀማቸው ላይ ትልቅ ክፍተት አለ፡፡

በሁሉም ተቋማት ለሚመለከታቸው አካላት ተደጋጋሚ ሥልጠናዎችን እንሰጣለን፡፡ ተቋማቱ ዕቅድና ሪፖርት እንዲያወጡ ለማድረግ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ይሰራል፡፡ ነገር ግን አመራር የሚለዋወጥበት ሁኔታ አለ፡፡ አንድ አመራር ግንዛቤ ተፈጥሮለት ወደ ሥራ ሲገባ፤ የሚቀየርበት ሁኔታ ይፈጠራል፡ ስለዚህ ለሚመጣው አመራር ወዲያውኑ ተከታትሎ ግንዛቤ የመፍጠር እና ቁርጠኝነት እንዲዳብር የማድረግ ሥራው በጣም ፈታኝ ሆኗል። ታች ያለው ቀርቶ በአመራሩ ደረጃ እንኳን የድርጊት መርሃ ግብሩን ለመፈፀም ሰፊ ክፍተቶች አጋጥመዋል።

በእርግጥ የድርጊት መርሃ ግብሩ ኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩትን እጅግ አብዛኞቹን የሰብአዊ መብት ችግሮች አንጥሮ ያወጣል፡፡ አንድ መንግስት የሚያዘጋጀው ሰነድ የሰብኣዊ መብት ችግሮችን የሚያነሳ ከሆነ እውቅና በሚሰጠው ደረጃ ብቻ በመሆኑ የነበሩ የፖለቲካ ክፍተቶች የገደቡት መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ለምሳሌ የመጀመሪያውም ሆነ ሁለተኛው የድርጊት መርሃ ግብር የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት አዋጅን ወይም የፀረ ሽብር አዋጁ ላይ ችግር እንዳለባቸው እውቅና ሊሰጥ አይችልም፡፡

ምክንያቱም የሚገልፃቸው ችግሮች በወቅቱ መንግስት የተቀበላቸውን ብቻ በመሆኑ ክፍተቶች ቢኖሩበትም፤ የማይጠበቁ ትልልቅ ጉዳዮችንም ያካተተ ነበር፡፡ ለምሳሌ ከሃይል አጠቃቀም አንፃር ታራሚዎችን በአግባቡ መያዝ ላይ በምርመራ ሂደትም ከዱላ የፀዳ የምርመራ ሂደትን ከማካሄድ አንፃር ችግር እንዳለ እውቅና የሚሰጥ ሰነድ ነው፡፡

እነዚህ ውስንነቶች እንዳሉ ቢሆንም በተቀመጠው መጠን እንኳ ተግባራዊ ቢደረግ፤ ረዥም ርቀት መሄድ ይቻል ነበር፡፡ ይህ ማለት ግን መርሃ ግብሮቹ ምንም ለውጥ አላመጡም ማለት አይደለም፡፡ ተግባር ላይ በዋለባቸው ጊዜዎች በርካታ አመራሮች መንግስታዊም ሆኑ መንግስታዊ ያልሆኑ በአገር አቀፍ ደረጃ በዝግጅት ሂደቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ ስለዚህ ይህ በሚሆንበት ጊዜ የመንግስት አካላት እነርሱ እውቅና ከሚሰጡትም ባለፈ አንዳንድ ጊዜ ያሉት ችግሮች ላይ በሰፊው ውይይት ለማድረግ ዕድል ፈጥሯል፡፡ ከግንዛቤና ከመነቃቃት አንፃር አስተዋፅኦ ነበረው፡፡

ሌላው ተቋማቱ በተፈጥሯቸው ወይም በተቋቋሙበት ዓላማ ምክንያት የሚሰሩት ሥራም መርሃ ግብሩ ውስጥ ነበረ፡፡ ለምሳሌ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ የጤና ጉዳይን ማስፈፀም መደበኛ ሥራው በመሆኑ ጤና ጣቢያና ሆስፒታሎችን ያስፋፋል የመድሃኒት አቅርቦት ላይ ይሰራል፡፡ ይህ ተፈፅሟል፡፡ ነገር ግን መርሃ ግብሩ ከዚህ ወጣ ያሉ አዳዲስ ነገሮችን አስተዋውቋል፡፡

ለምሳሌ መንግስት በወቅቱ ሰፊ የሆነ የመብት ጥሰት አለ ብሎ ዕውቅና ባይሰጥም የሃይል አጠቃቀማችንን ግን ትንሽ በቁጥጥር ሥር ልናውለው ይገባል ብሎ ስላመነ ያንን ጋብ ለማድረግ የፖሊስ ማረሚያ ቤቶች ሃይል አጠቃቀምን የሚቆጣጠር የህግ ማዕቀፍ እንዲበጅ የድርጊት መርሃ ግብሩ አስገብቷል፡፡

አደረጃጀቱ ጥራቱን የጠበቀ በቂ የሆነ ተቋማዊ ራሱን የቻለ ሞያዊ አካሄድ ይጎድለዋል፡፡ በዚህም መነሻነት በመብት ጥሰት ምክንያት የሚጠየቁ የፖሊስ አባላት በጣም ቁጥራቸው አነስተኛ ነበር፡፡ የነበረው የፖለቲካ ቁርጠኝነት ችግር እንዳለ ሆኖ አደረጃጀቱ በራሱ ችግር ያለበት በመሆኑ በዚህም ምክንያት ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የተጠያቂነት ሥርዓት መዘርጋት እንዳለብን እምነት ተወስዶበት ይህንን ሥርዓትም የመዘርጋት ሁኔታ እንዲጀመር ትልቅ አስተዋፅኦ ማበርከት ተችሏል፡፡

አሁን ከለውጡ በኋላም በርካታ ጠንካራ ሥራዎችን ማከናወን ተችሏል፡፡ የተወሰዱትን እርምጃዎች ተቋማዊ ለማድረግ ያግዛሉ፡፡ ተቋማዊ ብቻ ሳይሆን በዘለቄታው ጥሰት እንዳይፈፀም የምንጠብቅበት፤ ጥሰት ሲፈፀም ደግሞ እርምጃ ለመውሰድ የምንችልበት ጠንካራ በህዝብ ተአማኒ አደረጃጀት ለመፍጠር ዕድል ይሰጣል፡፡ ስለዚህ የድርጊት መርሃ ግብሩ የሃይል አጠቃቀምን በአግባቡ የምንቆጣጠርበት መንገድን ከፍቷል፡፡

ለምሳሌ አንድ ፖሊስ አንድ ቦታ ህግ እንዲያስከብር ጥሪ ሲደርሰው እንደመጣ “ጥይት ይጠቀማል፤ በዱላ ይማታል ወይስ አስለቃሽ ጭስ ይተኩሳል” ፤ “ጥይት ሲተኩስ ወደ እግር ነው ወይስ ወደ ጭንቅላት” እንዲህ አይነት ነገሮች በህግ አልተቀመጡም፡፡ ይህ በመሆኑ የፖሊስ ሃይል ህግ የማስከበር ስራ ሲሰራ የሚወስደው የሃይል እርምጃ እና በሌሎች ላይ የሚደርሰው ጉዳት የሚወሰነው በፖሊሱ በራሱ ነው፡፡ ይህ ሰፊ ለሆነ የመብት ጥሰት በር ይከፍታል፡፡

አንድ ፖሊስ ህግ ሲያስከብር በምን አይነት ሁኔታዎች ምን አይነት እርምጃ መውሰድ አለበት የሚለው በህግ መቀመጥ አለበት፡፡ ይህ ክፍተት በመኖሩ ተጠያቂነትን ያደናቅፋል፡፡ አንድ ፖሊስ እየሮጠ ሊያመልጥ የሚሞክርን ተጠርጣሪ ለማስቆም ጥይት ተኩሶ ጭንቅላቱን ቢመታው “አቃቤ ህግ በከባድ ግድያ ነው የሚከሰሰው?”፤ “ፖሊሳዊ ግዴታውን ለመወጣት ነው ብሎ ይተወዋል?” አይታወቅም።

ይህ ብዙ ህጋዊ ትንታኔ ያስፈልገዋል፡፡ ህግም ስለሌለ ለመጠየቅ አስቸጋሪ ነው፡፡ ፖሊሱንም ለመጠበቅ እነዚህ ህጎች ያስፈልጋሉ፡፡ ፖሊስ ሲያውቅ ያልተገባ ተግባር ላለመፈፀም ጥንቃቄ ያደርጋል፡፡ ስለዚህ እጅግ የተለጠጠውን የመወሰን ነፃነት የመገደብ ሥራ ይሰራል፡፡ በዚህም ምክንያት የዜጎችን መብቶች የመጠበቅ ጉዳይ እንዲደነገግ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ ይህ እየተከናወነ ነው፡፡

በሌላ በኩል ነፃ የህግ ድጋፍ ላይ ዜጎች በየፍርድ ቤቱ ፍትህ ፍለጋ ይንከራተታሉ፡፡ የፍትህ ሥርዓቱ የህግ ባለሞያዎች የሞሉበት ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ በሴቶች፣ ህፃናት፣ እናቶች እና አረጋውያን አባቶች ላይ ጥቃት የሚደርስባቸው ሁኔታ ይኖራል፡፡ እነዚህ ከህግ ዕውቀት መጓደል የተነሳ ፍትህ ያጣሉ፡፡ ይህንን መፍታት የምንችለው አቅሙ ለሌላቸው ጥሩ የሆነ የነፃ የህግ ድጋፍ አገልግሎት መስጠት ስንችል ነው፡፡

ይህንን ለማድረግ የድርጊት መርሃ ግብሩ በርካታ ሥራዎችን አስቀምጧል፡፡ ከዚህ ውስጥ ዋነኛው መንግስት ይህንን ሥራ የሚመራበት ፖሊሲም ሆነ ስትራቴጂ የለውም፡፡ ስለዚህ ነፃ የህግ ድጋፍ አገልግሎትን የሚመራበት ስትራቴጂ እንዲዘጋጅ ያስቀምጣል፡፡ ይህ ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ የመጨረሻው ሰነድ ለመንግስት ሊቀርብ ነው፡፡

የድርጊት መርሀ ግብሩ ያላስተዋልናቸው ወይንም በሌሎች ሰነዶች ያልተካተቱ አዳዲስ ተግባራትን እንድናከናውን በር ከፍቷል፡፡ ስለዚህ በርካታ ጥቅሞችን አስገኝቷል፡፡ በዚያው ልክ ደግሞ ለሰብአዊ መብቶች የነበረን ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት አጥጋቢ ያልነበረ ወይንም በጣም ደካማ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ይህ አፈፃፀሙ ላይ ያደረሰው ሰፊ ውስንነት አለ፡፡ ሙሉ ለሙሉ ይህንን የድርጊት መርሃ ግብር ለመተግበር የሚያስችል የፖለቲካ ቁርጠኝነት ቢኖር ኖሮ ባለፉት ዓመታት የተፈፀሙትን በርካታ ችግሮች ለማስቀረት ይቻል ነበር ብዬ አምናለሁ፡፡

ለሶስተኛው የድርጊት መርሃ ግብርም ሰፊ መሰረት ጥሏል፡፡ ተጠያቂነት ስንል የህግ ማዕቀፍ ለፖሊስ ተቋም ነው፡፡ ከዛ ሰፋ ባለ መንገድ ዕቅዱ ሲወጣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚያፀድቀው ሲሆን፤ እያንዳንዱ እንዲያስፈፅም ሃላፊነት የተሰጠው የመንግስት ተቋም ሥራዎችን የመወጣት ሃላፊነት ይኖርበታል፡፡ ስለዚህ ያንን ያጓደለ ዕቅዶችን እንደማያሳካ እየተገመገመ እርምጃ የሚወሰድበት ሁኔታ ይኖራል፡፡

አዲስ ዘመን፡ያልፈፀሙት የሚጠየቅበት ሁኔታ በእርግጥ ተፈጥሯል?

አቶ ይበቃል፡- የድርጊት መርሃ ግብሩ ላይ ጠንካራው አጋር የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲሆን፤ ሁሉም የፌዴራል የመንግስት ተቋማት ለቋሚ ኮሚቴዎች ሪፖርት በሚቀርብበት ጊዜ በመርሃ ግብሩ የተሰጣችሁን ሥራ የት አደረሳችሁት ተብለው ይጠየቃሉ፡፡ ስለዚህ ጥሩ የክትትል እና ድጋፍ ሥራ ሲሰራ ቆይቷል፡፡

ይህ በሶስተኛውም መርሃ ግብር የሚጠናከር እንደሆነ እናስባለን፡፡ ባለፈው አንድ አመት መንግስት አጠቃላይ በአገር ደረጃ ከፍተኛ ለሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ቁርጠኛ ሆኗል፡፡ ይህ ከምንግዜውም በበለጠ ሶስተኛው የድርጊት መርሃ ግብር ለመፈፀም በቀሪ ጊዜ ደግሞ ሁለተኛውንም የድርጊት መርሃ ግብር ለመፈፀም ትልቅ አቅም እንደሚሆን እናምናለን፡፡

አዲስ ዘመን፡የድርጊት መርሃ ግብሩ የያዛቸው ጉዳዮች እጅግ በጣም ብዙ እና ሰፊ አቅምን የሚጠይቁ ናቸው፡፡ በስፋት ሲፈፀሙም አይታይም፡፡ ለአብነት በስህተት የተከሰሱና የታሰሩ ሰዎች ካሳ እንደሚገባቸው ያስቀምጣል፡፡ በተጨማሪ በተቋማት ለሰራተኞች ልጆች የህፃናት ማቆያ መኖር አለበትም ይላል፡፡ ይህ በስፋት አይተገበርም ለምን?

አቶ ይበቃል፡የተነሱት ጉዳዮች ምሳሌዎች ናቸው፡፡ በእርግጥ በአለም ትልቅ ስፋት ያለው የድርጊት መርሃ ግብር የኢትዮጵያ ነው፡፡ ሌሎቹ አገሮች ሲያቅዱ ውስን ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው ይፈፅማሉ፡፡ የኢትዮጵያው በጣም ትልቅ ነው፡፡ ሁለተኛው መርሃ ግብር 24 መብቶችን ይይዛል፡፡

መርሃ ግብሩ ያካተታቸው ጉዳዮችን ለሁለት መክፈል ይቻላል፡፡ አንደኛው የተቋማቱ የራሳቸው ሥራ ነው፡፡ ለምሳሌ የሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ የሰራተኞችን የሥራ ላይ ደህንነት የማስጠበቅ ሥራ ይሰራል፡፡ የትምህርት ሚኒስቴር ትምህርትን የማስፋፋት መደበኛ ሥራውን ያከናውናል፡፡

ከዛ ደግሞ በድርጊት መርሃ ግብር ውስጥ ያሉ እነሱ በዕቅዳቸው ውስጥ ሲያካትቷቸው ያልነበሩ የሰብአዊ መብት ጥበቃን ለማጎልበት ያስችላል የተባሉ አዲስ ተግባራት አሉ፡፡ ለምሳሌ የፖሊስ ሃይል አጠቃቀም ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ለመገምገም ቀላል የሆኑት ተቋማቱ በሃላፊነታቸው ውስጥ ያለውን ሥራቸውን ያስቀድማሉ፡፡ ከዚህ አንፃር በብዙ ግንባር ስኬታማ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን እኛ ትኩረት የምናደርገው ያስተዋወቅናቸው አዲስ ተግባራት አፈፃፀም ምን ላይ ነው በሚል ይገመገማል፡፡ እዚህ ጋር ፈተና ነው፡፡ ተቋማት ቅድሚያ የሚሰጡት ለመደበኛ ሥራ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡እንግዲህ መርሃ ግብሩ የተቋማት መደበኛ ሥራንም የሚያካትት ከሆነ በክልሎች መካከል ያለውን ፍትሃዊነትስ ታያላችሁ?

አቶ ይበቃል፡መደበኛ አገራዊ ዕቅዶች ራሳቸው ፍትሃዊ ክፍፍልን ማዕከል ያደርጋሉ፡፡ መርሃ ግብሩም ፍትሃዊ ተደራሽነትን በተቻለ መጠን ማዕከል ማድረግ አለበት እንላለን፡፡ ከሰብአዊ አይን ስለሚታዩ ልዩ ትኩረት የሚሰጣቸው አሉ፡፡ ለምሳሌ አካቶ ትምህርት አካል ጉዳተኞች የትምህርትና የጤና አገልግሎት እያገኙ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡ ተስፋፍቷል ሲባል የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ምን ያህል ተሳትፈዋል የሚለውን እናያለን፡፡ በምንሰራቸው ሥራዎች ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች እኩል ተጠቃሚ መሆናቸውን እናያለን ነገር ግን ቀላል አይደለም፡፡

አዲስ ዘመን፡የድርጊት መርሃ ግብሩ አፈፃፀም ከተገመገመ በኋላ ምን ታደርጋላችሁ?

አቶ ይበቃል፡- በመርሃ ግብሩ ያንን ለመከታተል የሚያስችል ሁኔታ ነበር፡፡ የሚከታተል ቦርድ አለ። በቦርዱ ሰብሳቢ አማካኝነት ለምክር ቤቱ ሪፖርት ይቀርባል ይላል፡፡ ነገር ግን የድርጊት መርሃ ግብሩ እንዲተገበር ከማድረግ በኋላ ሪፖርት ማቅረብ ከባድ ሆኗል፡፡ ምክንያቱም ከተቋማት ሪፖርት ማግኘት አልተቻለም፡፡ ነገር ግን ምክር ቤቱ ተቋማትን ሲገመግም በዛው የድርጊት መርሃ ግብሩ አፈፃፀም ይገመግማል።

ነገር ግን አንዳንድ ተቋማት የሚሰሯቸውን ወይም የሰሯቸውን ሥራዎች እንኳን ሪፖርት አያደርጉም። ለምሳሌ የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ምን ያህል ክስ እንደመሰረተ ካልገለፀ ግምገማው አገራዊ ምስል አይኖረውም፡፡ ይህን ለመከላከል የሪፖርት ደረጃ በመለየት ቆጥረን ሰጥተን ቆጥረን ለመቀበል ብንሰራም አንዳንዱ ተቋም ሪፖርት አይልክም፡፡ ሌላው ደግሞ መደበኛ ሪፖርቱን ይልካል፡፡ በዚህ ምክንያት አገራዊ ምስል ለመፍጠር አልተቻለም፡፡ ሶማሌ 10 ትምህርት ቤት ሰርቻለሁ ብሎ አፋር ላይ 10 በመቶ አዳርሻለሁ ቢል ማጣጣም አስቸጋሪ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡ብዙ እሰራለሁ ብሎ መንጠራራት ትንሹም እንዳይሰራ ያደርጋል፡፡ የድርጊት መርሃ ግብሩ ብዙ ድስት ጥዶ አንዱን ማማሰል ያቃተ አላስመሰለውም?

አቶ ይበቃል፡ትክክል ነው፡፡ በፊት የተሰጠን አቅጣጫ ያ ስለነበረ ነው፡፡ ነገር ግን ሌሎች አገሮች ውስን ጉዳይን አንስተው ያንን ይሰራሉ፡፡ ምክንያቱም አንዱ ሲሰራ ሌላው ተያይዞ ይከበራል፡፡ ተቋማት ከሚሰሩት የተለየ አንኳር ችግሮች ላይ ትኩረት መስጠት ያስፈልግ ነበር፡፡ ነገር ግን በወቅቱ መንግስት ይዞት የነበረው አቋም ሁሉም ኢኮኖሚያዊውም፣ ፖለቲካዊም ሆነ ማህበራዊ እንዲሁም ባህላዊ ሁሉም መብቶች እኩል ክብደት ስለሚሰጣቸው ሁሉም ላይ ይታቀድ ተባለ፡፡

አዲስ ዘመን፡እንዳይፈፀም እንቅፋት አልሆነም?

አቶ ይበቃል፡ሆነ እኮ! እንዳይፈፀም ያደረገው መለጠጡ ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን ያም አስተዋፅኦ አለው፡፡ ስለዚህ የትኩረት ነጥቡ ውስን መሆን አለበት፡፡

አዲስ ዘመን፡ስለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ።

አቶ ይበቃል፡እኔም በጣም አመሰግናለሁ፡፡

አዲስ ዘመን ነሃሴ 3/2011

ምህረት ሞገስ