የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ለ23 ተጫዋቾች ጥሪ አደረገ

19

አዲስ አበባ:– ለ2020 የቶኪዮ ኦሎምፒክ የኢትዮጵያ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ተካፋይ ለመሆን በአፍሪካ ዞን የማጣሪያ ጨዋታ ሉሲዎቹ ነሐሴ 20/ 2011 ዓ.ም ከካሜሮን ጋር ለሚያደርጉት ፍልሚያ ብሔራዊ ቡድኑ ለ23 ተጫዋቾች ጥሪ አደረገ።

ሶከር ኢትዮጵያ በድረ ገጹ እንዳስነበበው፤ የኢትዮጵያ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሰላም ዘርዓይ ለ2020 የቶኪዮ ኦሎምፒክ የኢትዮጵያ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ተካፋይ ለመሆን በአፍሪካ ዞን ማጣሪያ ሉሲዎቹ ነሐሴ 20/ 2011 ዓ.ም ከካሜሮን ጋር ለሚያደርጉት ፍልሚያ ቀድሞ ለመዘጋጀት ለ23 ተጫዋቾች ጥሪ ያደረገች ሲሆን፤ በግብ ጠባቂነት ጥሪ ከተደረገላቸው ተጫዋቾች መካከል ማርታ በቀለ ከመከላከያ፣ ታሪኳ በርገና ከጥረት ኮርፖሬትና ዓባይነሽ ኤርቄሎ ከሃዋሳ ከተማ ይገኙበታል።

እንዲሁም በተከላካይ መስመር በብሔራዊ ቡድኑ ጥሪ ከተደረገላቸው ተጫዋቾች መካከል፤ መስከረም ካንኮ፣ ነጻነት ጸጋዬ፣ እፀገነት ቡዙነህና ናርዶስ ጌትነት ከአዳማ ከተማ፣ ገነሜ ወርቁና ብዙዓየሁ ታደሰ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ መሠሉ አበራ ከመከላከያ፣ ቅድስት ዘለቀ ከሃዋሳ ከተማ እንዲሁም ዓለምነሽ ገረመው ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ተካተዋል።

በአማካይ መስመር በአሰልጣኝ ጥሪ የተደረገላቸው፤ ሕይወት ደንጌሶና ብርቱካን ገ/ክርስቶስ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ እመቤት አዲሱና አረጋሽ ከልሳ ከመከላከያ እና ሰናይት ቦጋለ ከአዳማ ከተማ ጥሪ ተደርጎላቸዋል።

በተጨማሪ በአጥቂ መስመር ጥሪ ከተደረገ ላቸው ተጫዋቾች መካከል፤ ምርቃት ፈለቀና መዲና ጀማል ከሃዋሳ ከተማ፣ ሎዛ አበራ፣ ሰርካዲስ ጉታና ሴናፍ ዋቁማ ከአዳማ ከተማ እንዲሁም ሔለን እሸቱ ከመከላከያ ጥሪ የተደረገላቸው ተጫዋቾች ናቸው።

የዩጋንዳን ብሔራዊ ቡድን አሸንፈው ወደ ቀጣዩ ዙር ያለፉት ሉሲዎቹ ነሐሴ 20/2011 ዓ.ም ከካሜሮን ጋር ለሚያደርጉት ለ2020 የቶኪዮ ኦሎምፒክ የአፍሪካ ዞን የማጣሪያ ጨዋታ ከነሐሴ 1/2011 ዓ.ም ጀምሮ ዝግጅታቸውን ማከናወን የጀመሩ ሲሆን፤ ነሐሴ 11/2011 ዓ.ም ከኬኒያ ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

አዲስ ዘመን ነሃሴ 3/2011

ሶሎሞን በየነ