የእንግሊዝ ፕርሚየር ሊግ ዛሬ ምሽት ይጀመራል

114

የእንግሊዝ ፕርሚየር ሊግ በ20 ክለቦች መካከል የሚደረግ የ38 ሳምንታት እልህ አስጨራሽ ትግል የአንድ ክለብ የዋንጫ አሸናፊነት ክብር የሚታወጅበት፤ ክለቦች በቻምፒዮንስ ሊጉ ተሳታፊ ለመሆን የሚያበቃቸውን ከአንድ እስከ አራት ያለውን ደረጃ ለመቆናጠጥ አንገት ለአንገት የሚተናነቁበት ሊግ ነው።

በአንጻሩ ደግሞ ሶስት ክለቦች ወደ ቻምፒዮን ሺፑ ላለመውረድ በሚያደርጉት እልህ አስጨራሽ ትንቅንቅ አንዱ ክለብ ለአንዱ በቀላሉ እጅ የማይሰጥበትና ይሄ ክለብ በቀላሉ ያሸንፋል ብሎ ለመገመት አዳጋች በመሆኑ፤ ሚሊየኖች የሚያብዱለትና እንባ የሚራጩበት በዓለም እግር ኳስ አፍቃሪያን ዘንድ በጉጉት የሚጠበቅ፤ የሁሉንም ስፖርት አፍቃሪ ቀልብና ስሜት የገዛ፤ ሃያላን ክለቦች የሚፋለሙበት ተወዳጁ የእንግሊዝ ፕርሚየር ሊግ የ2019/20 የውድድር ዓመት ዛሬ ምሽት አራት ሰዓት የመርሲ ሳይዱ ሊቨርፑል በአንፊልድ ከኖርዊች ሲቲ በሚያደርጉት ፍልሚያ አሃዱ ብሎ ይጀምራል፡፡

አዲሱን የውድድር ዓመት በአዲስ የቡድን መንፈስና ጥንካሬ ለመጀመር ቡድኖች ራሳቸ ውን በቅድመ ውድድር የወዳጅነት ጨዋ ታዎች ሲያዘጋጁና ትናንት በተጠናቀቀው የክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት አዳ ዲስ ተጫዋቾችን ወደ ክለባቸው በማዘዋወር ክለባ ቸውን ሲያጠናክሩ ቆይተዋል።

በመሆኑም የ2019/20 የእንግሊዝ ፕር ሚየር ሊግ የውድድር ዘመን ዛሬ ምሽት ሊቨርፑል ከኖርዊች ሲቲ በሚያደርጉት ፍልሚያ ሲጀምር፤ ነገ ሊጉ ቀጥሎ ሲውል ስድስት ጨዋታዎች የሚካሄዱ ይሆናል። ከነዚህ መካከል በምሳ ስዓት ጨዋታ ዌስት ሃም ዩናይትድ ከሊጉ ቻምፒዮና ማንቸስተር ሲቲ፣ ምሽት 11 ስዓት ክሪስታል ፓላስ ከኤቨርተን እና ምሽት አንድ ሰዓት ተኩል ቶተነሃም ሆትስፐር ከቻምፒዮን ሺፑ ከአደገው ከአስቶን ቪላ ጋር የሚያደርጉት ጨዋታዎች በጉጉት ይጠበቃሉ።

እሁድ እለት ቀጥሎ በሚውለው የሊጉ መርሐ ግብር ሶስት ጨዋታዎች የሚካሄዱ ሲሆን፤ ቀያይ ሰይጣኖቹ ማንቸስተር ዩናይትድ በኦልድትራፎርድ ቲያትር ኦፍ ድሪምስ ስታዲየም ከሰማያዊዎቹ ቼልሲ ጋር የሚያደርጉት የሳምንቱ ትልቁ ጨዋታ በዚሁ እለት የሚካሄድ ይሆናል።

 ባሳለፍነው የውድድር ዓመት በቀያይ ሰይጣኖቹ ቤት ስኬታማውን አሰልጣኝ ጆሴ ሞሪንሆን ተክተው ኦልትራፎርድ የደረሱት የቀድ ሞው የቀያይ ሰይጣኖቹ የፊት መስመር ተጫዋች የነበረውና አሁን ላይ የክለቡ ዋና አሰልጣኝ የሆነው ኦሌ ገነር ሶልሻየር የዘንድሮውን የሊጉን ዋንጫ ከክለቡ ጋር ከፍ አድርጎ ለመሳምና በቻምፒዮንስ ሊጉ ተሳታፊ የሚያደርጋቸውን ውጤት ለማስመዝገብ በክረምቱ የዝውውር መስኮት በንቃት በመሳተፍ ክለቡን በወጣት ተጫዋቾች ያጠናከሩ በመሆኑ፤ ቀያይ ሰይጣኖቹ ከወዲሁ ይሄንን ትልማቸውን ለማሳካት የሚያ ስችላቸውን ስንቅ ለመሰነቅ ከሰማያዊዎቹ ጋር የሚያደርጉት ትንቅንቅ ጨዋታውን ተጠባቂ አድርጎታል።

ቀያይ ሰይጣኖቹ ባሳለፍነው የውድድር ዓመት በሊጉ ስድስተኛ ደረጃን ይዘው ያጠናቀቁ ሲሆን፤ በክለቡ በተከላካይ መስመር ላይ የሚታየውን ክፍተት ለመሙላት እንግሊዛዊውን የሌስተር ሲቲ ተከላካይ ሃሪ ማጉዌርን የዓለማችን ውዱ ተከላካይ በማድረግ በ80 ሚሊዮን ፓውንድ አስፈርሟል።

ተጫዋቹም በቀያዮቹ ቤት ቪዲችና ሪዮ ፈርዲናንድ ያሳዩትን ጥምረት ዳግም በኦል ትራ ፎርድ ለመድገም እንደሚጥር ከወዲሁ የተናገረ ሲሆን፤ በዚህ ጨዋታ የዓለማችን ውዱ የቀያዮቹ የተከላካይ ክፍል በሰማያዊዎቹ ቼልሲ ይደፈር ይሆን? የሚለው ጨዋታውን ተጠባቂ ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ ነው።

በአንጻሩ ባሳለፍነው የውድድር ዘመን ሰማያዊዎቹ ቼልሲ በጣሊያናዊው ማውሪዚዮ ሳሪ እየተመራ በቻምፒዮንስ ሊጉ መሳተፍ የሚያስችለውን የሶስተኛ ደረጃን ይዞ ከማጠ ናቀቁ ባሻገር የዩሮፓ ሊግ ዋንጫን ማንሳት የቻለ ቢሆንም፤ አሰልጣኙ ወደ ጣሊያን ማቅናታቸውን ተከትሎ በቻምፒዮን ሺፑ ደርቢ ካውንቲን በአሰልጣኝነት ይዞ ድንቅ ብቃቱን ያሳየው የሰማያዊዎቹ የቀድሞው የመሃል ሜዳ ፈርጥ ፍራንክ ላምፓርድ የክለቡን ዋና አሰልጣኝነት ዙፋኑን ከማውሪዚዮ ሳሪ ተቀብሏል።

በመሆኑም አሰልጣኙ ስታምፎርድ ብሪጅን በአሰልጣኝነት በተቀላቀለ ማግስት ሰማያዊዎቹ በሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ከቀያዮቹ ጋር በሚያደርጉት ፍልሚያ አሃዱ ብለው ይጀምራሉ። ላምፓርድም ይሄን ጨዋታ በበላ ይነት በማሸነፍ ለቦታው እንደሚመጥን እራሱን የሚያሳይበት በመሆኑ፤ ጨዋታውን ከመቼውም ግዜ በላይ ተጠባቂ ያደርገዋል።

እንዲሁም ሰማያዊዎቹ ቼልሲ በቁርጥ ቀን ልጃቸው በፍራንክ ላምፓርድ እየተመራ በቅድመ የውድድር የወዳጅነት ጨዋታዎች ላይ ክለቡ ድንቅ ብቃቱን አሳይቷል። በተለይ ቼልሲ ከባርሴሎና ባደረጉት የወዳጅነት ጨዋታ ላይ ሰማያዊዎቹ በፍጹም የጨዋታና የጎል የበላይነት የዓለማችንን ሀያል ክልብ ባርሴሎናን አምበርክከዋል።

ስለዚህ ሰማያዊዎቹ በቅድመ ወድድር የወዳጅነት ጨዋታ በባርሴሎና ላይ የፈጸሙትን ጀብድ ዳግም በኦልትራፎርድ ቲያትር ኦፍ ድሪ ምስ ስታዲየም ሊደግሙት ይችላሉ የሚል መላምት ከወዲሁ በስፖርት ቤተሰቡ እየተሰጠ በመሆኑ፤ በጨዋታው ማን ያሸንፋል የሚለውን በጉጉት እንዲጠበቅ አድርጎታል።

ሁለቱ ክለቦች ባለፈው በተገናኙበት ስድስት ጨዋታዎች ሁለት ሁለት ጊዜ ሲሸናነፉ፤ ሁለት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥተዋል። በጥቅሉ ሁለቱ ክለቦች በፕርሚየር ሊጉ በተገናኙበት ጨዋታዎች 78 ጊዜ ቀያይ ሰይጣኖቹ ሲያሸንፉ፤ በአንጻሩ ሰማያዊዎቹ ደግሞ 54 ጊዜ ረትተዋል። በ51 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ወጥተዋል።

በአጠቃላይ በዚህ የውድድር ዓመት የፕሪሚየር ሊጉ ቻምፒዮና ማንቸስተር ሲቲ የሊጉን ዋንጫ ሶስት ጊዜ በተከታታይ በማንሳት ‹‹ሀትሪክ›› ለመስራት ይፋለማል፤ ሊጉ እንዳዲስ ከተቋቋመ ጀምሮ የሊጉን ዋንጫ ማሳካት የተሳነው የቻምፒዮን ሊጉ አሸናፊ የመርሲ ሳይዱ ሊቨርፑል ባሳለፍነው የውድድር ዓመት በአንድ ነጥብ ልዩነት የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ በውሃ ሰማያዊዎቹ ማንቸስተር ሲቲ በመነጠቁ፤ በዚህ የውድድር አመት ቀያዮቹ ከስተታቸው በመማር የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ይፋለማሉ።

እንዲሁም የእግር ኳስ ጠበብቱ አርሴን ቬንገር ከ22 ዓመታት የኤምሬትስ ቆይታ ከተሸኙ በኋላ መድፈኞቹ አርሴናል በኡና ኤምሬይ እየተመሩ ሁለተኛ የውድድር አመታቸውን የሚያካሂዱ ሲሆን፤ አሰልጣኙ በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት በንቃት በመሳተፍ የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ከወዲሁ ቆርጠው ተነስተዋል።

ስለዚህ የ2019/20 የእንግሊዝ ፕርሚየር ሊግ የውድድር ዘመን የሊጉ ሃያላን ክለቦች የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ከመቼውም ጊዜ በላይ ቆርጠው የተነሱበት በመሆኑ፤ የስፖርት ቤተሰቡ አስደሳች የውድድር አመት የሚያሳልፍበትና ታላላቅ የእግር ኳስ ትዕይንት የሚታይበት የውድድር ዓመት እንደሚሆን ከወዲሁ እየተ ተነበየ ይገኛል።

ተወዳጁ የእንግሊዝ ፕርሚየር ሊግ እንደ አዲስ ከተጀመረ እ.አ.አ ከ1992 ወዲህ 28ኛ የውድድር ዘመኑን ዛሬ ምሽት በይፋ ሲጀመር፤ ባሳለፍነው የውድድር አመት በኮከቡ አሰልጣኝ ጋርዲኦላ የሚመራው ማንቸስተር ሲቲ 98 ነጥቦችን ሰብስቦ ቻምፒዮን ሆኖ ሲያጠናቅቅ፤ በአንፃሩ ደግሞ ካርዲፍ ሲቲ፣ ፉልሃምና ሁደር ስፊል ታውን ከፕርሚየር ሊጉ ወደ ቻምፒዮንስ ሺፑ ተሰናብተዋል።

በነዚህ ክለቦች ምትክ በ2018/19 የውድድር ዓመት ሶስት አዳዲስ ቡድኖች ከሻምፒዮን ሺፑ ፕሪሚየር ሊጉን የተቀላቀሉ ሲሆን፤ ክለቦቹም ኖርዊች ሲቲ፣ ሼፍልድ ዩናይትድና አስቶን ቪላ ናቸው። እነዚህ ክለቦችም ወደ ቻምፒዮን ሺፑ ተመልሰው ላለመውረድ በሚያደርጉት እልህ አስጨራሽ ትንቅንቅ የ2019/20 የእንግሊዝ ፕርሚየር ሊግ የውድድር ዘመን ድምቀት ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

አዲስ ዘመን ነሃሴ 3/2011

ሶሎሞን በየነ