የኢትዮጵያዊውና ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ወግ በኦሪገን

6

ከአንድ ወር በኋላ በኳታር ዶሃ በሚካሄደው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ለውጤት ከሚጠበቁ የዓለማችን አትሌቶች መካከል ኢትዮጵያዊው ዮሚፍ ቀጄልቻና ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ የሆላንድ አትሌት ሲፈን ሃሰን ግንባር ቀደሞቹ ስለመሆናቸው ጥርጥር የለውም። በዘንድሮው የውድድር ዓመት በተለያዩ ርቀቶች አስደናቂ ብቃት እያሳዩ የሚገኙት እነዚህ አትሌቶች የዓለም ቻምፒዮናው ላይ ለተለያዩ ሁለት አገራት የሚሮጡ ቢሆንም አሁን ላይ የሚያመሳስላቸውና የሚጋሩት በርካታ ነገሮች እንዳሉ የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ድረ ገፅ ፀሐፊው ስቲቭ ላንዴልስ ሰሞኑን ያስነበበው ሰፊ ሐተታ ይነግረናል።

ሁለቱ ኮከቦች በደም ኢትዮጵያውያን መሆናቸው መጀመሪያ የሚጋሩት እውነታ ሲሆን የሕይወት እጣ ፋንታቸው መንገዳቸውን ለየቅል አድርጎት ዓለም አቀፍ ውድድሮችን አንዱ ለትውልድ አገሩ ሲሮጥ ሌላኛው መጠጊያ ለሆነችው አገር ሰንደቅ አላማ ሲሮጡ እንመለከታቸዋለን። ይህን እውነታ የሚጋሩ በርካታ አትሌቶች በየአህጉሩ የሚገኙ ቢሆንም በአሜሪካ ፖርትላንድ ኦሪገን ግዛት ያለው የናይኪ (የስፖርት ትጥቅ አምራች ኩባንያ) የአትሌቲክስ ፕሮጀክት ሲፈንና ዮሚፍን በአንድ ካፕ አምጥቶ በርካታ ጉዳዮችን እንዲጋሩ አስችሏቸዋል።

ዮሚፍና ሲፈን በኢትዮጵያ ተወልደው ያደጉ ሲሆን አሁን ላይ በናይኪ ኦሪገን ፕሮጀክት አማካኝነት ኑሯቸውን አሜሪካን አገር ካደረጉ ሰንብተዋል። በአንድ አሰልጣኝ፣ በአንድ የልምምድ ቡድንና በአንድ ካፕ ውስጥ እየኖሩም ዘንድሮ የዓለም የማይል ክብረወሰንን ለመጨበጥ በቅተዋል።

በአስራ አምስት ዓመቷ ኢትዮጵያን ተሰናብታ ወደ ሆላንድ ሃገር ያቀናችው ሲፈን በሂደት የአትሌቲክስ ሕይወትን አዳብራ 2014 ላይ የአውሮፓ ቻምፒዮን ስትሆን በ2016 የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና የ1500 ሜትር አሸናፊ እስከ መሆን ደርሳለች። በ2016 ሪዮ ኦሊምፒክ በ1500 ሜትር አምስተኛ ሆና ካጠናቀቀች ወዲህ በሃያ ሦስት ዓመቷ የናይኪን ፕሮጀክት ተቀላቅላ ነበር ወደ ኦሪገን ያመራችው።

ድንቅ የሩጫ ተሰጥኦና ቁመናን የታደለው ወጣት ኢትዮጵያዊ አትሌት 2013 ላይ ገና በአስራ አምስት ዓመቱ የዓለም ከሃያ ዓመት በታች ቻምፒዮና አሸናፊ ከመሆን ባሻገር በቀጣይ ጥቂት ዓመታት የዓለም ከሃያ ዓመት በታች የ5ሺ ሜትር ቻምፒዮንና የወጣቶች ኦሊምፒክ የ3ሺ ሜትር ቻምፒዮን ለመሆን በቅቷል። 2016 ላይ በዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና አሸናፊ መሆኑን ተከትሎ የውድድሩ አዘጋጅና የአሁን መኖሪያው የሆነችውን ፖርትላንድን ተዋወቀ። የናይኪን ፕሮጀክት ተቀላቅሎም ኑሮውን እዚያው ለማድረግ ወሰነ። ዮሚፍ ከወጣቶች ጎራ ወጥቶ ወደ አዋቂዎች የውድድር ጎራ ያደረገው ሽግግር እንደታሰበው በውጤት የታጀበ አልነበረም። 2016 ሪዮ ኦሊምፒክ ላይ አገሩን ሳይወክል ከመቅረቱ ባሻገር በ2017 የዓለም ቻምፒዮና ለንደን ላይ በ5ሺ ሜትር አራተኛ ሆኖ ማጠናቀቁ ምቾት አልሰጠውም ነበር። ‹‹ለንደን ላይ አራተኛ ማጠናቀቄ አላስደሰተኝም ነበር፣ ይህም ከመም ውድድር ወጥቼ ወደ ጎዳና ላይ ውድድሮች እንዳተኩር ውሳኔ ላይ እስከመድረስ አድርሶኝ ነበር፣ ማኔጀሬ ግን ቢያንስ አንድ ዓመት በመም ውድድሮች ላይ እንድቆይ ነበር ምክር የለገሰኝ›› በማለት ዮሚፍ ከሁለት ዓመት በፊት የነበረውን ያስታውሳል።

ያኔ የኦሪገንን ፕሮጀክት ሲቀላቀል የእንግሊዘኛ ቋንቋ ይቸግረው የነበረው ዮሚፍ አሁን ላይ የቋንቋ ችሎታውን እያሻሻለ ይገኛል። ለዚህ ደግሞ ፕሮጀክቱን ሲቀላቀል ያገኛት ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ሲፈን ሃሰን እሱ የሚናገረውን የአፋን ኦሮሞ ቋንቋ ተናጋሪ መሆኗ በእጅጉ ነገሮችን አቅልሎለታል።‹‹መጀመሪያ ላይ አሜሪካን አገር ለመኖር ተቸግሬ ነበር፣ እንግሊዝኛ ቋንቋ መናገር ስለማልችል የምትረዳኝ ሲፈን ነበረች፣ ከሁለት ሳምንታት በኋላ ግን እንግሊዝኛ ለማውራት ራሴን ማስገደድ ጀመርኩኝ›› ይላል ዮሚፍ።

ከትውልድ አገሯ ለረጅም ዓመታት የራቀችው ሲፈን አብዛኛውን የወጣትነት ዘመኗን በአውሮፓውያን ባህል ውስጥ እንደማሳለፏ የዮሚፍን የቋንቋ ክፍተት ለመድፈን የምትቸገር አይደለችም። ‹‹ዮሚፍ ወደ ፕሮጀክቱ ለመምጣት የወሰነው እኔ እዚህ እንዳለሁ ስለሚያውቅ ነበር፣ ይህም አስተርጓሚው ሆኜ በፕሮጀክቱ የሚኖረውን ሕይወትና የአሜሪካን አገር ቆይታውን ቀላል አድርጎለታል›› በማለት ሲፈን በተለመደ ፈገግታዋ ታጅባ ትናገራለች።

ይሁን እንጂ ለወጣቱ አትሌት ከቋንቋ ጀምሮ የአካባቢውን ባህልና አዲስ አካባቢ መላመድ ቀላል አልነበረም። በእውቁ አሰልጣኝ አልቤርቶ ሳላዛር የሚሰጠውን የልምምድ ጫናም መቋቋም በቀላሉ የሚለመድ አልሆነለትም። ‹‹ከስድስት እስከ ስምንት ባሉት የመጀመሪያ ወራት ብዙ መሰዋዕትነት መክፈል ነበረብኝ፣ በነዚህ ጊዜያት ወደ አገሬ ለመመለስ ያሰብኩበበት አጋጣሚ ሁሉ ነበር፣ ያም ሆኖ በነዚያ ጊዜያት ያመጣሁትን ለውጦች ዞር ብዬ እመለከት ነበር፣ ስለዚህ እዚሁ መቆየት ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑን አመንኩኝ›› ይላል ዮሚፍ አስቸጋሪውን ጊዜ ሲያስታውስ።

ሲፈን በበኩሏ‹‹ እኔ ልክ እንደ እህቱ ነኝ፣ የትም ቦታ ቢሆን ይዤው እሄዳለሁ›› ትላለች። ሁለቱ አትሌቶች አንድ ካምፕ ውስጥ ከመኖር በዘለለ ፊልሞችን የሚመለከቱትና የሚመገቡት ጭምር አንድ ላይ ነው። ሲፈን የዮሚፍ አብሯት መኖር እሷን የበለጠ ተጠቃሚ እንዳደረጋት ትናገራለች። በተለይም በለጋ እድሜዋ ከተለየቻት አገሯ ኢትዮጵያ ጋር የበለጠ እንድትቀራረብ በማድረግ ረገድ በእጅጉ መጠቀሟን ታብራራለች። ከኢትዮጵያ ማርና ቅቤ አንስቶ በርካታ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች እስከሚያዘወትሩት የገብስ በሶ ድረስ እንዳስታረቃትም ታወሳለች። ‹‹ባለፈው ዓመት ሁለት ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ሄጃለሁ፣ ወደ ኢትዮጵያ ባህል በመጠኑም ቢሆን መጠጋቴ ጥሩ ነው›› ስትልም ሲፈን የትውልድ አገሯን ታስታውሳለች።

ዮሚፍ አዲሱን ኑሮ ለመላመድ እንደተቸገረው ሁሉ ሲፈንም በፕሮጀክቱ የሚሰጣትን የልምምድ ጫና ለመቋቋም ተቸግራ ነበር። በተለይም ልምምዷን ከዮሚፍ ጋር መስራት በጀመረችባቸው ሳምንታት የበለጠ ጫናና ድካም እንደነበረባት ታስታውሳለች። ሆላንድ በነበረችበት ወቅት ከምትሰራው ልምምድ በበለጠ ከዮሚፍ ጋር ጠንካራ ልምምድ እንደምታደርግም ትናገራለች። ‹‹በአንድ ማለዳ አራት መቶና ሁለት መቶ ሜትርን በተደጋጋሚ ልምምድ ስንሰራ ከአቅሜ በላይ ሆኖ ነበር፣ መሞቴ ነው እንዲህ አይነት ልምምድ ከምሰራ በጥይት ብትገድሉኝ ይሻለኛል አልኩ፣ ለምን ያህል ድግግሞሽ ልምምዱን እንዳረኩኝ ባላስታውስም ልምምዱን ከጨረስኩኝ በኋላ ሰውነቴ ዝሎ መንቀሳቀስ እንዳልቻልኩኝ አስታውሳለሁ›› በማለት ሲፈን በፕሮጀክቱ ስለሚያደርጉት ጠንካራ ልምምድ ታብራራለች።

በአጭር ጊዜ ውስጥ ሁለቱ አትሌቶች የልምምዱን ጫና እየተላመዱ አካል ብቃታቸው እያደገ መምጣቱ አልቀረም። ይህም ባለፈው ዓመት በብቃታቸውና በውጤታቸው ላይ ለውጥ አምጥቶላቸዋል። ዮሚፍ በርሚንግሃም ላይ በዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና የ1500 ሜትር ክብሩን ከማስጠበቅ ባለፈ በተመሳሳይ ርቀት ከቤት ውጪ 3፡32፡59 የሆነ የራሱ ፈጣን ሰዓት ማስመዝገብ አስችሎታል። በ3ሺ ሜትር 7፡28፡00 የሆነ የዓመቱ ፈጣን ሰዓት ሲያስመዘግብም በ5ሺ ሜትር 12፡46፡79 የሆነ ፈጣን ሰዓት ባለቤት መሆን ችሏል። በኮፐንሃገን ግማሽ ማራቶን ለመጀመሪያ ጊዜ በርቀቱ ተወዳድሮ ያስመዘገበው 59፡17 ሰዓትም አይን ውስጥ የሚገባ ነበር።

በተመሳሳይ ሲፈን 2018 የውድድር ዓመት ላይ የአውሮፓ የ5ሺ ሜትር ቻምፒዮን ስትሆን በአንድ ማይል ውድድር 4፡14፡71፣ በ3ሺ ሜትር 8፡27፡50፣ በ5ሺ ሜትር ደግሞ 14፡22፡34 የሆነ ሰዓት በማስመዝገብ የሆላንድን ክብረወሰኖች መጨበጥ ችላለች። ዮሚፍ ለመጀመሪያ ጊዜ በተወዳደረበት የኮፐንሃገን ግማሽ ማራቶን ሲፈንም ለመጀመሪያ ጊዜ በርቀቱ ተወዳድራ 1፡05፡15 በሆነ ሰዓት የአውሮፓን ክብረወሰን ከማስመዝገብ ባለፈ በርቀቱ ያላትን እምቅ አቅም አሳይታበታለች።

ሲፈን የ 8 መቶና የ1500 ሜትር ሯጭ በነበረችበት ወቅት የ5ሺ ሜትር ሯጭ ብትሆን የተሻለ እንደሚሆን ሃሳብ ነበራት። ይሁን እንጂ አሰልጣኟ ግማሽ ማራቶንን በ68ና 69 ደቂቃ ማጠናቀቅ እንደምትችል ምክር ከለገሳት በኋላ ኮፐንሃገን ላይ እንደተወዳደረች ትናገራለች። በዚህ ውድድር ከጠበቀችው በላይ ግማሽ ማራቶንን በ65 ደቂቃ ማጠናቀቅ በመቻሏ መደነቋን አልሸሸገችም።

ሁለቱ አትሌቶች ከ2018 በተሻለ በ2019 የውድድር ዓመት በዓለም አትሌቲክስ ላይ የሚያሳድሩት ተፅዕኖ እየጨመረ መጥቷል። ባለፈው የካቲት ሲፈን ሞናኮ ከተማ በጎዳና ላይ 5 ኪሎ ሜትር ውድድር 14፡14 የሆነ የዓለም ክብረወሰን መስበር ስትችል፣ ዮሚፍ ቦስተን ላይ 3፡47፡01 የሆነ የአንድ ማይል የዓለም ክብረወሰን አሻሽሏል። ዮሚፍ በዘንድሮ የውድድር ዓመት በተለይም በ5ሺ ሜትር የዳይመንድ ሊግ ውድድሮች አስደናቂ ብቃቱን እያሳየ ይገኛል። ስታንፎርድ፣ ሻንጋይና ሉዛን ከተሞች ላይ በርቀቱ የተካሄዱ የዳይመንድ ሊግ ውድድሮችን ማሸነፉ የሚታወስ ሲሆን ከሦስት ሳምንት በፊት ሄንግሎ ላይ በተካሄደው የኢትዮጵያውያን የማጣሪያ ውድድር በ10ሺ ሜትር ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳትፎ 26:49.99 ሰዓት በማስመዝገብ ሦስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል። ይህም በዶሃው የዓለም ቻምፒዮና ኢትዮጵያን በ10 ሺ ሜትር ከሚወክሉ አትሌቶች መካከል አንዱ አድርጎታል።

ሲፈን በበኩሏ በ3ሺ ሜትር 8፡18፡49ና በ5ሺ ሜትር 14፡22፡12 የሆነ የአውሮፓ ክብረወሰን ማስመዝገብ የቻለች ሲሆን ስታንፎርድ ዳይመንድ ሊግ ላይ 10ሺ ሜትርን 31፡18፡12 በሆነ ሰዓት ማጠናቀቅ ችላለች። እነዚህ ስኬቶች ሁለቱ የአንድ አገር አትሌቶች በዜግነት ቢለያዩም የአትሌቲክስ ሕይወታቸው በኦሪገን ፕሮጀክት ውስጥ እያበበ የብቃታቸው ጥግ ላይ እየደረሱ እንደሚገኙ ነው።.

በናይኪ ኦሪገን ፕሮጀክት ውስጥ አሰልጣኝ የሆነው ቲም ሮውበሪ ሁለቱ አትሌቶች ፕሮጀክቱን ከተቀላቀሉ ወዲህ እያሳዩ የሚገኘውን ለውጥ ሲናገር፣ ዮሚፍና ሲፈን ጠንካራ ሰራተኛ ለመሆን ያላቸውን ከፍተኛ ፍላጎት ብቻም ሳይሆን አዳዲስ ፈተናዎችን ለመጋፈጥ ያላቸውን ቁርጠኝነት ሳያደንቅ አያልፍም።

ሁለቱ አትሌቶች የአትሌቲክሱን ስልጠና ያግዛቸው ዘንድ የውሃ ዋና እንዲደፍሩ በየጊዜው እንደሚያበረታታቸው የሚናገረው አሰልጣኙ፣ አትሌቶች የመዋኘት ልምድ ባይኖራቸውም ለመልመድ ደስተኛ ሆነው እየሰሩ እንደሚገኙ ያብራራል። በተለይም ዮሚፍ ከጥቂት ወራት በፊት ምንም አይነት የመዋኘት ልምድ የሌለው አትሌት እንደመሆኑ በፍጥነት እየለመደ መምጣቱ አስገራሚ መሆኑን ይናገራሉ። ሁለቱ አትሌቶች በዶሃው የዓለም ቻምፒዮና ትኩረት የሚሰጣቸው እንደመሆኑ በናይኪ ኦሪገን ፕሮጀክት መታቀፋቸው አሰልጣኙን ደስተኛ እንዳደረገው ይናገራል። ሁለቱ አትሌቶች በፕሮጀክቱ ውስጥ መኖራቸው ለሌሎች የፕሮጀክቱ አትሌቶች የሚጨምርላቸው ነገር እንደሚኖር እምነቱ ነው። ዮሚፍና ሲፈን አስደናቂ የሩጫ ተሰጥኦ ያላቸው ከመሆኑ ባሻገር አዲስ ነገሮችን በፍጥነት የመላመድ ችሎታቸውን አሰልጣኙ ያደንቃል።‹‹ ከዚህ በፊት እንደነዚህ አይነት አትሌቶች አሰልጥኜ አላውቅም፣ሁለቱም የተለዩ አትሌቶች ናቸው›› ሲልም አሰልጣኙ ይመሰክርላቸዋል።

አዲስ ዘመን ቅዳሜ 4/12/11

 ቦጋለ አበበ