ከሚሊዮኑ የችግኝ ታሪክ በኋላስ?

10

‹‹ስኬታማው የአረንጓዴ አሻራ የዓለምን ትኩረት ስቧል›› ይላል በወንድወሰን መኮንን ሐምሌ 25 ቀን 2011 ዓ.ም በዚሁ በ‹‹አዲስ ዘመን›› ጋዜጣ ‹‹ዓለም አቀፍ›› ገጽ ላይ ለገጸ ንባብ የበቃው ጽሑፍ፡፡

ጸሐፊ ወንደወሰን መኮንን መሠረት ያደረጉት ለሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስት ዐቢይ አህመድ ሀገራዊ ጥሪ ‹‹በመጪው የኢትዮጵያ ትውልድ ውስጥ ለዘመናት የሚዘልቅ ሀገራዊ ታሪክ ተመዝግቧል›› ያሉትን የችግኝ ተከላ ጉዳይ በማስመልከት ብዕርና ወረቀት ያዛመዱበትን ጹሑፍ ተመርኩዘው ነው፡፡

በውኑም ጉዳዩ እንዲህ እንደ ዋዛ ሊታለፍ የሚገባው እንዳልሆነ በብዙዎች ቅን አሳቢ ሰዎች ዘንድ የሚታወቅ ነው፡፡

በሀገራችን፣ እንዲያ ሲልም በዓለማችን የሚፈጠረው ድርቅ፣ ሰደድ እሳት በየወቅቱ ለሚከሰተው እጅግ አሳዛኝ ሁናቴ በግምባር ቀደምነት ተጠያቂ ሆኖ የሚቀርብ ዋናው ምክንያት የተፈጥሮ ሀብት መመናመን እንጂ ሌላ ሆኖ አልተገኘም፡፡ የተፈጥሮ ሀብት መመናመን ደግሞ ምክንያቱ የደን መጨፍጨፍ መሆኑ ዘወትር ሲነገር ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በዚህች የሀገራችን መዲና ዛሬ ደግሞ የአህጉራችንም ማዕከል ጭምር ልትሆን በበቃቸው አዲስ አበባ እንኳ ሲሶ ያህሉ በደን የተሸፈነ እንደነበር ለብዙዎቻችን የተሰወረ አይደለም፡፡ እንግዲህ ከመቶ ሰላሣው ያህል አረንጓዴ ነበር ማለት ነው፡፡ ዛሬስ? ለዚህ ጥያቄ የመስተዋት ፎቆች በጥሩ ምስክርነት ጭምር ምላሹን አይነፍጉንምና ብዙ የሚያከራክር አይመለስኝም፡፡

እንደ እውነቱ ከሆነ ‹‹ችግኝ ተከላ›› ተብሎ እንዲሁ እንደ ዋዛ ተነግሮ ‹‹የሰሞን ዘመቻ›› ብቻ ሆኖ መቅረት የሌለበት ጉዳይ መሆኑን ማንም አይስተውልም፡፡ እንደ አሁን በግሩም እቅድ ታላቅ መርሐ ግብር ተይዞለት ‹‹ሁለት ሚሊዮን ችግኝ በአንድ ጀምበር ለመትከልና ያን የድሮውን ተፈጥሯዊ ውበት ለመመለስ ታጥቀን የተነሣን አንሁን እንጂ እንዲሁ በአንድነት ‹‹ክተት ሠራዊት ምታ ነጋሪት›› ተብሎ ከልሂቅ እስከ ደቂቅ የተነሳ ሰው አይኑር እንጂ ባለፉት ዓመታት በክረምት ወቅት ችግኝ መተከሉ ያልቀረ ነገር ነበር፡፡

ይሁንና የተተከሉት ችግኞች የት ደረሱ? ዘወር ብሎ ያያቸው የተንከባከባቸው ሰው ባለመኖሩ ሳቢያ መክነው ወይም እንዲሁ ባክነው ሰው እጅግም ስለ እነርሱ በጋዜጣ፣ በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥን መነገሩ፣ ማስነገሩ ይቆየንና ከቶውንም ስለመተከላቸው እጅግም ሳያውቅ፣ ለወሬ ያህል እንኳ ሳያደምጥ ቆይቷል፡፡

በመሠረቱ በ‹‹ዘመቻ›› መልክ መሆኑ ‹‹ለምን?›› አሰኝቶ ብዙ ያጠይቃል፡፡ ከቃሉ መንስኤ ‹‹ሀ›› ብለን ብንጀምር ‹‹ዘመቻ›› የተሰኘው ስም ‹‹ዘመተ›› ከሚለው ግሥ የወጣ ሲሆን ‹‹ዘመቻ›› ለጦርነት ለውጊያ፣ ለልዩ ልዩ የተግባር እንቅስቃሴ የሚደረግ፣ በተወሰነ ጊዜም ውስጥ እንዲከናወን እንዲጠናቀቅ፣ በኅብረት እና በመረባረብ የሚካሄድ ሥራ ነው፡፡

በአሁን ጊዜም ስናየው የጽዳት፣ የክትባት፣ የትራፊክ ቁጥጥር ሳይቀር የሚደረግ የተግባር እንቅስቃሴ እውን ሊሆን መብቃቱን ሳናስተውል የቀረን አልሆንም፡፡ ዛሬ በተያያዝነው ተግባር ደግሞ ‹‹የችግኝ ተከላ›› መኖሩን ተገንዝበናል፡፡ ብሎም ቢሆን ‹‹ዘመቻ›› ከተባለ ‹‹በተወሰነ ጊዜ ውስጥ ……›› ተብሎ በዚያው ማክተሙ እጅግ የሚያስጨብጭብ አይደለም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እንዳሉት ‹‹….. ችግኝ በመተከሉ ሀብታሞች ጥሩ አክሲጂን የሚተነፍሱበት፣ ድሆች የሚከለከሉበት ሁኔታ የለም፡፡ ችግኝ ሲተከል ዝናብ ይዘንባል፣ አርሶ አደሩ ይጠቀማል ….. ግድቦቻችን ይሞሉና የፈረቃ መብራት ይቀራል … ችግኝ ሲተከል ተገማች ባልሆነ ምክንያት የአየር ጠባይ የማይቀያየር ከሆነ በረሃብ የሚጠቃ ሰው አይኖርም….. ዝናብ ከቀነሰና እንደ ዘንድሮ ካነሰ መብራት በፈረቃ ይሆናል……ያኔም ጄኔሬተር ያላቸው ሀብታም ሰዎች ይጠቀማሉ፣ ድሃው ግን ይጎዳል …. እርሻውም እንደዚሁ፡፡….›› በዚህ መልክ ነው ጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ አህመድ የችግኝ ተከላን ጥቅም በማለፊያ አማርኛ አብራርተው የገለጹት፡፡

ይህ እንግዲህ እንዲየው የሰሞን ተግባር ሆኖ በአንድ ወቅት ተዘምቶ፣ በዚያው አብቅቶ፣ በዚያው ተረስቶ ሊቀር የተገባው አይደለም፡፡ ‹‹ክብካቤ›› ያሻዋል፡፡ ይህን መስል ክብካቤ ማድረግ የሚያሻው ደግሞ ከተጠያቂነት ጋር ሲጣመር እንጂ ‹‹አቶ እገሌ የተከለውን ችግኝ ይኮትኩት፣ ውሃ ያጠጣ፣ ይንከባከብ….›› ብሎ በዚያው ሲተው ብቻ አለመሆኑን ማወቅ የግድ ይላል፡፡

በመሠረቱ ለእነዚህ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ፣ በብዛታቸው እጅግ በርክተው ለሚዘረዘሩ ችግኞች ተጠሪነቱ የታወቀ፣ በኃላፊነቱ የጸደቀ ተቋም የሚያስፈልገው ይመስለኛል፡፡ ነገ ይህ የሕዝብ ሀብት የሆነ፣ ብዙ ገንዘብ የፈሰሰበት፣ የብዙ ዜጎች ጉልበት፣ የብዙ ሰዎች ላብ የተንጠፈጠፈበት ችግኝ በከንቱ የትም መቅረት አይኖርበትም፡፡ አንድ ኃላፊነቱ የተወሰነ፣ ሥልጣኑም የተለገሰው ተቋም ሲኖር ያ መሥሪያ ቤት ደግሞ በፊናው ተንካባካቢ ቡድን በማደራጀት ለሌሎች የተግባር ክንዋኔ ሰዎችን በማቀናጀት ተገቢውን ስራ ከዳር ያደርሳል፡፡

እንዲህ በሚሆንበት ሰዓት ያለማው ተሞግሶ፣ ያጠፋው ተወቅሶ ሊገኝ የሚችልበት ሁኔታ ይፈጠራል፡ ፡ እንዲያውም የልማቱ ዋና ተዋናይ የሆነው ያለማበትን ምክንያት እጅግም ‹‹አከራካሪ›› የማድረግ ሁኔታ ሳያሳይ ግዴታው መሆኑን አውቆ፣ በግንዛቤ ጸድቆ ይገኝ ዘንድ ያለማውም እንዲሁ በከንቱ አለመሆኑን እንዲረዳም፣ ደስም እንዲለው ‹‹አንድ ነገር›› ሲደረግለት ለተከታዩ ዓመት ደግሞ ይበልጥ ለብዙ ችግኝ እንዲነሣ የተበረታታ ይሆናል፡፡

‹‹እንዲያው ዝም ብለህ ብቻ…›› ቢባል ግን እምብዛም የሚያነሣሣው መንፈስ አይኖርም፡፡ ቢነሣሣም ለይሉኝታ ወይም እንዲሁ ለ ‹‹የውርድ ከራሴ›› አጉል ተግባር ይሆንና ይቀራል፡፡

ሌላው ደግሞ እንደ እውነቱ ከሆነ የሀገራችን የኢትዮጵያ ሕዝብ ለአንድ ነገር ‹‹ተነሥ!›› ከተባለ የማይነሣበት ምክንያት የለም፡፡ ሁሉም የወገኑን በተለይም ደግሞ የመንግሥትን ተማጽኖ በማክበር የሚቀበል ‹‹ኅብረት›› ማለት ምን እንደሆነ የሚገነዘብ፣ ለሀገሩ፣ ለወገኑ የሚጨነቅና የሚያሰብ እንጂ ‹‹እኔ ምን አገባኝ… ምን ቸገረኝ›› የሚል አይደለም፡፡

በዚህም ሳቢያ ይመስለኛል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ‹‹…. በዚሁ አጋጣሚ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለመላው ዓለም አስተማሪ በሆነ መንገድ፣ በአንድ ድምጽ፣ በመደመር እሳቤ የችግኝ ተከላውን በተመለከተ ከዚህ ቀደም ያመሰገንኩ ቢሆንም በድጋሜ አመሰግናለሁ —–›› ያሉት

አንዳንድ ሰዎች ግን የድሮውን ደርግ ‹‹እድገት በኅብረት ዘመቻ›› ከአሁኑ የችግኝ ተከላ ዘመቻ ጋር በማነፃፀር ለመተረክ ሲሞክሩ የመገኘታቸው ነገር በጣም አስገርሞኛል፡፡

ደርግ በመፈክርና በመዝሙር እንደለፈፈው ለሰፊው ሕዝብ የሕይወት ፋና ይዞ ሳይሆን ለብዙኃን ድንቁርና፣ ለብዙኃን ስቆቃው ሕሊና ጦር መዞ የመጣ፣ ለድፍን ኢትዮጵያ የጭንቀት ሕልውና መትረየስ ያነገበ፣ ፈጣሪ አምላክ በቸርነቱ በሰጠው አእምሮ ሳይሆን በጠመንጃ አፈሙዝ ያሰበ፣ በሰው ልጅ ደም የታጠበ ማን ዘራሽ ሀገር በቀል ፋሺስት በመሆኑ ለአሥራ ሰባት ዓመታት ምድሪቱን ያጨቀየ፣ በስመ ሶሻሊዝም ሕዝቡን ያደኸየ፣ ታሪኳን እንዳልነበር ያደርግ ዘንድ በዚያ ርዕዮተ አጋንንት፣ ራዕየ ዲያቢሎስ የተነበየ እነርሱ እንደሚያሞካሹት ‹‹የምርጥ መኮንኖች ስብስብ›› ሳይሆን የምራጭ መኮንኖች ጥርቅም ነው፡፡ እኔ ስለ ደርግ የምለው ይህን ብቻ ነው፡፡ ‹‹ጨምርልን›› ከተባልኩ በሌላ መድረክ መምጣት እችላለሁ፡፡

ጸሐፊ ወንድወሰን መኮንን እንዳሉት ይህቺን ‹‹ድንቅና በተፈጥሮ የታደለች ሀገር ይዘን የተራብነው የታረዝነው እኛው ነን፡፡ ተፈጥሮ የሰጠችንን ጸጋ ገፈን ከዳቦ ቅርጫትነት ወጥተን፣ ክብራችን ተዋርዶ ወደ ተረጂነት ራሳችንን በምግብ መቻል ተስኖን ወደ ተመጽዋችነት የተሸገርነውም እኛው ነን፡፡

‹‹ጥያቄው ከዚህ እንውጣ ነው፡፡ ይሄ መደፈርና ውርደት ተሰምቶት በሁሉም መስክ ሀገርን ለመለወጥ የማይነሣ ዜጋ ካለ ሕያው ሳይሆን በድን ብቻ ነው የሚሆነው፡፡ ዓለምን የሞላነው የሠውን ሀገር ያጣበብ ነው እኛው ሆነን ሳለን እዚህ አገራችን ውስጥ በሰላም መኖር ተስኖን እንባላለን፣ እንጋደላለን …….. ከመንደሬ ውጣ፣ ልቀቅ የምንል የዘቀጥን መንደርተኞች ሆነናል፡፡ ›› ይላል የወንድወሰን መኮንን ማለፊያ ጽሑፍ:: በውኑ ደግሞ እንዲህ ካሉ በኋላ በዚያው ኋላ ቀር አስተሳሰብ የዘመኑ ‹‹መንደርተኛ›› እንሆን የበቃነው በዚያ ከጥንቱ ኢትዮጵያዊነታችን በወረስነው አኩሪ እና ድንቅ የሰው ወዳድነት ባሕርያችን አይደለም፡፡ ሃያ ሰባት ዓመት ሙሉ በሕ.ወ.ሓ.ት መራሽ አገዛዝ እንደ ግሩም መርሕ በተላበስነው ክፉ በሽታ ሳቢያ መሆኑን ማንም አይስተውም፡፡ ዛሬ ደግሞ በአሁኑ የለውጥ ጊዜ ያገኘነውን የብርሃን ጭላንጭል እንኳ በተገቢው ሁኔታ እንዳንጠቀምበት አንዴ እንደተባለው በጎሳ፣ አንዴ በዘር፣ አንዴ በጎጥ ወዘተ …… ነጣጥለው ሊለያዩን የሚጥሩ ተንኮለኞች አልጠፉም፡፡

ጸሐፊው ሄድ፣ ራመድ ብለውም ሲ.ኤን.ኤን ‹‹አለ›› ያሉትን ጠቅሰው እንዲህ ያስነብቡናል፡፡

‹‹ባሕር በር አልባ የሆነችው ሀገር በአየር ንብረት ለውጥ ትሰቃያለች፡፡ የመሬቱ መጎዳት፣ የአፈሩ መሸርሸር፣ የደኑ መመናመን፣ ተደጋጋሚ ድርቅ፣ በእርሻ ላይ የሚከሰት ጎርፍ በተደጋጋሚ አጋጥሟታል›› ሲል ሲ.ኤን.ኤን መዘገቡን አስነብበውናል፡፡

ጸሐፊው ስለ ሀገራችን ወቅታዊ ሁናቴ ሲጽፉ በኃዘን መሆኑ የተጠቀሙበት ዘይቤ ይመሰክራል:: በርግጥም ያሳዝናል እኔም እንግዲህ አንዳንድ ነገር በማለት የኃዘናቸው ተካፋይ እሆን ዘንድ በመውደዴ ነው ይህንን የዛሬውን ጽሑፍ ላበረክት የተነሣሁት፡፡

‹‹ባሕር አልባ የሆነችው ሀገር…..›› አለ ሲ.ኤን.ኤን፡፡ አዎን! ዛሬ ደግሞ ያም ከቁም ነገር ገብቶ፣ እንደ ብርቅ ታይቶ ‹‹የደረቅ ወደብ›› መረጣ ውስጥ ገብተን ስንጨነቅ እና ስንቸገር መታየታችን ራሱ ልብ ክፉኛ የሚሰብር ነው፡፡

የዚህ የአሁኑ ዘመን የችግኝ ተከላ ተግባር እንኳ በትክክል እንዳይከናወን የሚጥሩ ሴረኞች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ የችግኝ ተከላው ግን ይበልጥ ሊበረታታ የተገባው ነው፡፡ የክብካቤው መርሐ ግብርም መረሳት የለበትም፡፡ ይልቁንስ እኔ እንደማስበው ‹‹ይህን ያህል ሚሊዮን ችግኝ ….›› በማለት በአኃዝ ማስቀመጡ ብቻውን እጅግም ዋጋ ላይኖረው ይችላል፡፡ ከዚያስ? ምን ይሁን?

የሚሊዮኑ ታሪክ ሳይዘነጋ ቁጥሩ እንዳለ ሆኖ ከዚያ የሚከተለው የወቅት ከወቅት ክትትል ዓይነተኛ ቦታ ሊሰጠው ይገባል፡፡ ሰው ያቦካውን ሊጥ ሳይሆን የጋገረውን ዳቦ ቢቆጥር የተሻለ ነውና!!

አዲስ ዘመን ቅዳሜ 4/12/11

አሸናፊ ዘደቡብ