መሻገር በአንቀልባ ፣ በጀርባ ፣ በእሽኮኮ ወይስ በተቋም … ! ?

13

ካለፈው አንድ አመት ወዲህ ከአንዳንድ ተቃዋሚዎች፣

‘ ተሟጋቾች ‘ ፣ ልሒቃንና ጋዜጠኞች ዋሻ ጮህ ብለው ከሚሰሙ እና መልሰው ከሚያስተጋቡ ድምጾች እዝነ ህሊናን እረፍት የነሳው፣ አየሩን የተቆጣጠረው የሽግግር መንግስት ይቋቋም የሚለው ወለፈንዲ ጥያቄ ነው፡፡ ጥያቄውን ላይ ላዩን ሲመለከቱት ተገቢ ይመስልና ከሸግግር መንግስት አይነቶች አንጻር በጥሞና ሲመረምሩት ግን የለውጥ ኃይሉ የሀገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ ከግምት ባስገባ አግባብ አበክሮ እየመለሰው እያለ ሆን ብሎ እውቅና ላለመስጠት አልያም በውል ካለመገንዘብ በቅንነት የሚነሳ ግራ አጋቢ ጥያቄ ስለሆነ ወለፈንዲ ይሆናል፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር በወቅቱ በሰሜን አሜሪካም በአውሮፓም ከኢትዮጵያውያንና ከትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ባደረጓቸው ውይይቶችም ጥያቄው ቀርቦላቸዋል፡፡ እሳቸውም ቀለል አድርገው እኔ አሻግራችኋለሁ ማለታቸው ይታወሳል፡፡ በዘወርዋራ በወቅቱ ሌላው መሻገሪያ ድልድይ ተሰብሯል ማለታቸው ይመስለኛል፡፡ እኔ አሻግራችኋለሁ ሲሉ ምን ማለት እንደፈለጉ በቅጡ ተረድተናቸዋል ብዬም አላምንም፡፡ እኔ አሻግራችኋለሁ ሲሉ እኔ እና እኔ ብቻ ማለታቸውም አልነበረም፡፡ በእኔነታቸው ውስጥ የለውጥ ኃይሉ፣ የለውጥ ኃይሉ የሚመራው የፖለቲካ ድርጅት፣ መንግስትና እኛ ብዙኀን አለንበት፡፡ በተለይ ፓርላማውን ጨምሮ የመንግስት፣ የፓርቲው መዋቅር እንዳለ ስለቀጠለ በግልፅነት እኔ አሻግራችኋለሁ የማለታቸውን ሚስጥር ልብ ይሏል፡፡ ሆኖም ከአንድ አመት ከ4 ወራት በፊት የነበረው የ’ ቀዳማይ ‘ ኢህአዴግም ሆነ በእሱ ይመራ የነበረው መንግስት ትከሻም ሆነ ጀርባ ለማሻገር ዝግጁ አልነበረም:: ይሁንና በእግሩ የተተካውን ‘ ዳግማዊ ‘ ኢህአዴግንም ሆነ የመንግስቱን አሰራርና አደረጃጀት ለሽግግር ማዘጋጀት ቀዳሚ ተግባር ነበር፡፡ ከሞላ ጎደል ይህ ስራ በሚፈለገው ፍጥነትና በተገቢው ልክ ባይሆንም እየተከናወነ ይገኛል:: በእርግጥ ከአመት በፊት ተፎካካሪዎች፣ አቀንቃኞች እና ልሒቃን የሚጠይቁትን አይነት የሽግግር መንግስት በሀገሪቱ ለመመስረት ተጨባጭ እና አስቻይ ሁኔታዎች ነበሩን ! ? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ከመሞከር በፊት የሽግግር፣ የጊዜአዊ መንግስት ታሪካዊ ዳራን፣ ትርጉምንና ምንነትን እንመልከት፡፡

የመጀመሪያው የሽግግር መንግስት መቼ ? የት ? እንደተመሰረተ አንድ የጋራ ድምዳሜ ላይ ባይደረስም የሰው ልጅ መንግስት የሚባለውን ተቋም ካቆመበት ጥንታዊ ዘመን ጀምሮ እንደነበር ቢታመንም አንዳንድ የታሪክ ድርሳናት ግን የመጀመሪያው የሽግግር፣ ጊዜአዊ መንግስት እ አ አ 1641 _ 49 የእንግሊዝን ንጉሳዊ አገዛዝ አየርላንድ ላይ ለመሰየም የተመሰረተ መሆኑን ሰንደዋል፡፡ ከዚያ ቀጥሎ እንግሊዝ በአሜሪካ እ አ አ 1776 የመሰረተችው የሽግግር መንግስት በሁለተኛነት ተመዝግቦ ይገኛል፡፡ ከዚህ በኋላ በፈረንሳይ፣ በእስፔን፣ በአውስትራሊያ፣ በቻይና፣ ወዘተ . መሰል የሽግግር፣ ጊዜአዊ መንግስታት እንደነበሩ ድርሳናቱ አክለው ያትታሉ፡፡ ታሪካዊ ዳራውን እንዲህ በአጭሩ ከተመለከትን የሽግግር መንግስትን ምንነትንና ትርጉም ደግሞ እንደሚከተለው እንመልከት፡፡ በአንድ ሀገር ፖለቲካዊ ሽግግር ሲኖር አልያም የቀደመው መንግስት በእርስ በእርስ ጦርነት፣ በሕዝባዊ አመፅ፣ በውጭ ወራሪ ኃይል ወይም በመፈንቅለ መንግስት አልያም በፓርላማ የትምምን ድምፅ motion of no confidence ሲነፈግ ወይም ጥምር መንግስቱ ሲፈርስ፣ ሲወድቅ አዲስ መንግስት በምርጫ እስኪቋቋም ጊዜአዊ፣ የሽግግር መንግስት ይመሰረታል፡፡ ከዚህ አንጻር ከለውጡ በፊት የነበረውን የቀዳማይ ኢህአዴግ መር መንግስት በተመለከተ የሚከተሉትን ጥያቄዎችን ማንሳት ይቻላል:: በሕዝባዊ አመፅ ፣በእርስ በእርስ ግጭት፣ በውጭ ኃይል ወረራ አልያም በመፈንቅለ መንግስት ተገልብጦ ወይም ወድቆ ነበር ! ? መልሱ ግልፅ ነው፡፡ አልወደቀም፡፡ አልተገለበጠም፡፡ ሆኖም ከለውጡ ቀደም ብለው በነበሩ ተከታታይ አመታት በተካሄዱ ሕዝባዊ አመጾችና ይህን ተከትሎ በውስጠ ድርጅት በተፈጠረ ትግል እና ሕዝባዊ ወገንተኝነት በመዳከም ላይ እንደነበር አይካድም፡፡ ስለዚህ ለውጡን ያመጣው የሕዝባዊ አመጹና የውስጠ ድርጅት መተጋገሉ መገናኘት con­vergence መሆኑን ያጤኑአል፡፡ በእነዚህ ኃይሎች መካከል ደግሞ አንዱ ሌላውን አሸንፎ የመውጣት ትግል ሳይሆን በህቡዕም ሆነ በአደባባይ በአምባገነንነት የለዩትን ቡድን በአንድነት በመግፋት ገሸሽ ማድረግ ነበር፡፡ ይሄ ታክቲካዊ አጋርነት ከተሳካ በኋላ ቀጣዩ ሂደት ጊዜአዊ፣ የሽግግር መንግስት ማቋቋም ነበር፡፡ ሆኖም የደህንነት፣ የፀጥታ፣ የአስተዳደር፣ ወዘተ .መዋቅሩ ተሸናፊውን ቡድን በታማኝነት እንዲያገለግል ሆኖ ከጅምሩ የተዋቀረ ስለነበር ለአደራ፣ ለሽግግር መንግስት ምስረታ ዕምነት የሚጣልበት አልነበረም፡፡ የሽግግር መንግስት ለማቋቋም አስቻይ ተጨባጭ ሁኔታም አልነበረም፡፡ ይሄ ኃይል ከመንግስት መዋቅር ተገፍቶ እንኳ ምን ያህል እጀ ረጅም እንደሆነ እየተመለከትን ነው፡፡ ስለሆነም ተፎካካሪዎችም ሆኑ ሌሎች የሚጠይቁትን የሽግግር መንግስት ከመመስረት ይልቅ መቅደም የነበረበት በአንጻራዊነት ገለልተኛ የደህንነት፣ የመከላከያ፣ የዳኝነት፣ ወዘተ. ተቋም መመስረት እና ለውጡን በሁለት እግሩ ማቆም ነበር፡፡ ባለፉት 16 ወራት የሆነውም ይኸው ነው፡፡ በነገራችን ላይ ይህ ውሳኔ በፍፁም አስተዋይነትና አርቆ አሳቢነት የተከወነ ስለመሆኑ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል፡፡ በምንመኘው ፍጥነት፣ ጥራትና ጥልቀት ባይሆንም ማሻሻያውን ተቋማዊ ለማድረግ ፈታኙ ጉዞ ከተጀመረ ውሎ አድሯል፡፡ ሽግግሩን ተቋማዊ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ተስፋ ሰጭ ጅምር ስራዎችም ይበል የሚያስብሉ ናቸው፡፡

ዘመነ ጓዴነት contemporaries ባይኖረውም የግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ ፊውዳላዊ አገዛዝ ተገርስሶ ደርግ የሽግግር መንግስት ለማቋቋም የቻለበትን አውድም ሆነ በቅርቡ ጎረቤታችን ሱዳንም ሆነ ሌሎች የሽግግር መንግስት ለማቆም ከእኛ የተለየ ምን አስቻይ ሁኔታ ነበራቸው ብሎ በወፍ በረር ከመመልከታችን በፊት አሁን እየተከተልነው ያለው የሽግግር መንግስት እና ተፎካካሪዎች የሚጠይቁት የሽግግር መንግስት የትኛው ላይ እንደሚወድቁ ለመመልከት የሽግግር መንግስት አይነቶችን እንይ፡፡ እንደ የቴላቪቭ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰሩ ዮሲ ሼን እና እንደ የል ዩኒቨርሲቲው የስነ ህብረተሰብና የፖለቲካል ሳይንስ ፕሮፌሰር ዋን ጆዜ ሊንዝ አራት አይነት የሽግግር መንግስታት አሉ ፡፡

እነሱም ፦

1ኛ . ስልጣን ላይ ያለው መንግስት የሽግግር መንግስቱን ተግባርና ኃላፊነት ተክቶ ሲወስድ ስልጣን ላይ ያለ የሽግግር መንግስት ይባላል፡፡ አሁን በሀገራችን እየተካሄደ ያለው የሽግግር ሂደት የዚህ አይነት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ኢህአዴግ መር የሆነው መንግስት አሁንም ስልጣን ላይ ነው፡፡ የደህንነት፣ የፀጥታና ሌላው መንግስታዊ መዋቅሩ እንዳለ ነው፡፡ ሆኖም ይህን መዋቅር ከሞላ ጎደል ገለልተኛ ለማድረግ የሚያግዙ ማሻሻያ እርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ እየተወሰዱም ነው፡፡ የዳኝነት አካሉን፣ ምርጫ ቦርድን፣ ሚዲያውንና ሌሎች የዴሞክራሲ ተቋማትን ነፃና ገለልተኛ ለማድረግም በአሰራርና በአደረጃጀት የታገዙ ለውጦች እየተተገበሩ ይገኛል:: ከለውጡ በፊት የነበረው አገዛዝ ለጭቆና ለአፈና ይጠቀምባቸው የነበሩ አዋጆች ተሻሽለዋል:: በመሻሻል ላይም ናቸው፡፡ አዳዲስ አዋጆችና ሕጎችም በሒደት ላይ ይገኛሉ፡፡ በተጠናቀቀው የበጀት አመት በምክር ቤቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የሽግግር ሂደቱን የሚያግዙ 61 አዋጆችና 32 ውሳኔዎች ፀድቀው ስራ ላይ ውለዋል፡፡ ከፀደቁት መካከል የምርጫ ቦርድ የማቋቋሚያ እና የሲቪል ማህበራት አዋጆች ይገኝበታል፡፡ ለሽግግር ሂደቱ አጋዥ ከሆኑ ውሳኔዎች የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት መዓዛ አሸናፊ ፣ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ክብርት ብርቱካን ሚደቅሳ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ዳንኤል እና የመንግስት መገናኛ ብዙኃን የስራ አመራር ቦርድ አባላት ምደባን በአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ እነዚህ ሹመቶች መንግስት ነፃና ገለልተኛ የዴሞክራሲ ተቋማትን በመገንባት ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመሸጋገር ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል፡፡ የፀረ ሽብር፣ የመገናኛ ብዙኀንና የመረጃ፣ የምርጫና የፖለቲካ ድርጅቶች አዋጆችና ሌሎችም በሂደት ላይ ናቸው፡፡ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር የሚመራው የለውጥ ኃይል አንድ የሽግግር መንግስት እንደሚያደርገው ቀደም ባለው አገዛዝ በተለያዩ ወንጀሎች ተፈርጀው እና የፖለቲካ ምህዳሩ በመከርቸሙ በእስር፣ በስደትና በትጥቅ ትግል ለነበሩ ዜጎች፣ ድርጅቶችና ሚዲያዎች ይቅርታና ምህረት አድርጓል:: አንዳርጋቸውን፣ አንዷለምን፣ እስክንድርን፣ ተመስገን፣ እማዋይሽን፣ ንግስትን ጨምሮ በመላ ሀገሪቱ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እና የህሊና እስረኞች ተፈተዋል:: አርበኞች ግንቦት 7 ፣ የኦሮሞ ነፃ አውጭ ግንባር እና የኦጋዴን ነፃ አውጭ ግንባር የፖለቲካ ድርጅቶች በምህረትና በይቅርታ ወደ ሀገር ተመልሰው ሰላማዊ ትግሉን ተቀላቅለዋል፡፡ እንደ ኢሳት፣ ኦ ኤም ኤን ያሉ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች፣ ድረ ገጾች፣ ጦማሮች፣ ጋዜጦችና መፅሔቶች እንደገና ወደ ስራ ተመልሰዋል፡፡ ፍትሕን፣ ኢትዮጲስን፣ ዘሀበሻን፣ ሳተናውን ለአብነት ማንሳት ይቻላል፡፡ የለውጥ ኃይሉ በአደባባይ የሽግግር መንግስት ነኝ ብሎ ባይለፍፍም ከላይ የተመለከትናቸው ማሻሻያዎች ግን በዚሁ ተራ ቁጥር ያየነው ማለትም ስልጣን ላይ ባለ የሽግግር መንግስት የሚተገበሩ ተግባራት ናቸው፡፡ ታዲያ አንዳንድ ልሒቃን፣ ተቃዋሚዎች፣ ተሟጋቾች በተለይ ግጭት አለመግባባት በተከሰተ፣ ኮሽ ባለ ቁጥር ተሽቀዳድመው የሽግግር መንግስት ይቋቋም የሚሉት ለምንድን ነው ? ነው ለእነሱ የሽግግር መንግስት ማለት በአንቀልባ ታዝሎ አልያም በትከሻ እሽኮኮ ተብሎ የሚያሻግር ነው ! ? ካልሆነ ከላይ ለማየት እንደሞከርነው ለመሸጋገሪያ የሚሆኑ አሰራሮች እየተዘረጉ ተቋማት እየተገነቡ መሆኑን ለመቀበል ማንገራገር ለምን አስፈለገ ! ? ነው እኛ ካልተሳተፍንበት ምኑን ሽግግር ሆነ ለማለት ነው ! ? ለማንኛውም ጥያቄው ግልፅነትም ቅንነትም የጎደለው ሆኖ ይሰማኛል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ቁጥራቸው ቀላል ያልሆነ pragmatist ተፎካካሪዎች፣ አቀንቃኞች፣ ጦማርያን፣ ልሒቃን፣ ወዘተ . ሀገሪቱ በለውጡ ማግስት የሽግግር መንግስት ለማቋቋም ገለልተኛ ተቋማትም አስቻይ ሁኔታዎች እንደሌላት በአደባባይ ስለተሟገቱ ባርኔጣዬን በማንሳት አክብሮቴን እገልጻለሁ፡፡

2ኛ. ስልጣን ላይ የነበረው መንግስት በሕዝባዊ አመፅ ከተወገደ በኋላ ስልጣን በአስወጋጁ ኃይል ቁጥጥር ስር ሲውል አብዮታዊ የሽግግር መንግስት በመባል ይታወቃል፡፡ ይሄን አይነት የሽግግር መንግስት ሀገራችንን ጨምሮ በአፍሪካ፣ በላቲን አሜሪካና በእስያ በብዛት ተቋቁሟል፡፡ የጊዜአዊ ወታደራዊ አስተዳደር (ደርግ)ን እዚህ ላይ ያስታውሷል፡፡

3ኛ. የሽግግር መንግስቱ በነባሩ መንግስትና በለውጥ ፈላጊው ኃይል ጥምረት የሚመሰረት ሲሆን ስሙም የጋራ የሽግግር መንግስት በመባል ይታወቃል:: እዚህ ላይ ሰሞነኛውን የጎረቤታችንን የሱዳን የሽግግር መንግስት በአብነት ማንሳት ይቻላል:: የነባሩ መንግስት የጦር ኃይል እና የደህንነቱ ተቋም ከተቃዋሚው ኃይል በጋራ የሽግግር መንግስት ማቆማቸው የአለማቀፍም ሆነ የሀገር ቤት ሚዲያዎች ሰሞነኛ ማሟሻ ዜና ነበር፡፡

4ኛ. የሽግግር መንግስቱን አለማቀፉ ማህበረሰቡ ሲረከብ አለማቀፍ የሽግግር መንግስት ይሰኛል፡፡ ይሄ የሽግግር አይነት ፍትሕን ለማስፈንና በቀጣይ የሽግግር መንግስቱ ተሳታፊ የሚሆኑ ኃይሎችን ለመለየት የሚያግዝ የሽግግር መንግስት ነው፡፡ ለዚህኛው አይነት የሽግግር መንግስት ጥሩ ማሳያ የሚሆነው አሜሪካን መራሹ ኃይል የሳዳም ሁሴንን አገዛዝ ከስልጣን ካወረደ በኋላ በኢራቅ አቋቁሞት የነበረው የሽግግር መንግስት ነው፡፡

እንደ መውጫ

ከለውጡ በፊት በነበሩ 27 አመታት በብሔርና በማንነት ላይ ብቻ ተመስርቶ የነበረው አስመሳይ ፌደራሊዝም pseud Federalism እንደ ቀድሞዋ ሶቪየት ሕብረት ግዛቶች ከየአንዳንዱ ክልል እና አባል እንዲሁም አጋር ድርጅት ጀርባ አፋኙ ቡድን በጨለማም በጠራራም ነበር፡፡ በአንዳንድ ክልሎች ደግሞ ጭፍራዎቹን በቀጥታ እስከ መመደብ ደርሶ እንደነበር ፀሐይ የሞቀው ሀቅ ነው፡፡ ከዚህ በላይ አንድን ቡድን ስልጣን ላይ ለማቆየትና የበላይነቱን ለማስጠበቅ የልዩነትና የጥላቻ ፖለቲካ መዋቅራዊና ተቋማዊ ሆኖ በሕዝብና በሀገር ሀብት ሌት ተቀን ይሰበክ እንደነበር የሚታወቅ ነው፡፡ በማንነቶች መካከል ልዩነት መጠራጠር እንዲፈጠር መግፍኤ ከመሆን ባሻገር ከፋፍሎ ለመግዛት ያመቸው ዘንድ ሀገራዊ ቁመና ያላቸው የመከላከያ፣ የደህንነት፣ የፖሊስ፣ የዳኝነት፣ የምርጫ፣ ወዘተ. ተቋማት እንዳይኖሩ ሌት ተቀን አሻጥሯል፡፡ በመከላከያው ከነበሩ ጄኔራሎች በደህንነት መዋቅሩ ከታች እስከ ላይ የነበሩ ቁልፍ የአመራር ቦታዎች በማን ተይዘው እንደነበሩ ስናስታውስ የደህንነትና የፀጥታ መዋቅሩ የአንድን ቡድን ፍላጎትና ጥቅም የሚያስጠብቅ እንጂ ሀገራዊና ሕዝባዊ ጥቅሞችን የሚያስከብር እንዳልነበረ ያረጋግጣል፡፡ እንግዲህ የለውጥ ኃይሉ ወደ አመራርነት በመጣ ማግስት ነው በእነዚህ መዋቅሮች የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም ነጋ ጠባ ሲወተወት የነበረው፡፡

በእነዚህ መዋቅሮች ተቋማት አይደለም የሽግግር መንግስት ምንም አይነት ማሻሻያ ማድረግ እንደማይቻል የተገነዘበው የለውጥ ኃይል የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ እና ከፊቷ ተደቅኖባት የነበረውን አደጋ በመገንዘብ በመጀመሪያ የወሰደው እርምጃ ጥበብ፣ ማስተዋልና ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ የደህንነቱንና የፀጥታ ተቋማቱን እንደገና ማደራጀት ነበር፡፡ የለውጥ ኃይሉ ይሄን ሳይተገብር ለውጥ ላምጣ ቢል ኖሮ አንድ ጋት ሊራመድ አይችልም ነበር፡፡ ከፍ ሲልም ለውጡ ከመቀልበስ አልፎ እንደሀገር የመቀጠላችን ጉዳይ አጠያያቂ ይሆን ነበር፡፡

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እንዳሉት እኔም ለውጡ በመለኮታዊ ጣልቃ ገብነት የሆነ እንጂ በሰው አእምሮ ብቻ የተመራ አልነበርም ብዬ አምናለሁ፡፡ ከዚያ ጭንቅ ጠብ የአንድ ጥይት ድምፅ ሳይሰማ መውጣታችን ሁል ጊዜ እንደ አዲስ ያስገርመኛል:: ከላይ እንደገለፅሁት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር እኔ አሻግራችኋለሁ እንዳሉት እያሻገሩን ስለሆነ የሽግግር መንግስት ይቋቋም የሚለው ጥያቄ በሽግግር ውስጥ ሌላ ሽግግርን እንደመቃዠት ይቆጠራል፡፡ ይህ ደግሞ ሀገሪቱ ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ ካለማጤን አልያም ሆን ብሎ መደናገርን ለመፍጠር የሚደረግ የሴራ የደባ ፖለቲካ አካል ይመስለኛል፡፡ ይልቁን ከእነ ውስንኖቶቹ ከሽግግሩ ጎን ብንቆም ባጠረ ጊዜ በትንሽ መስዋዕትነት ተስፋ ወደ ምናረጋት የሁላችን ሀገር እንደርሳለን፡፡

ይህ ዓምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ አስተያየታቸውን የሚሰጡበት ነው። በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሑፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።

አዲስ ዘመን ቅዳሜ 4/12/11

በቁምላቸው አበበ ይማም ( ሞሼ ዳያን )