በእናት እገዛ የተሳካ ጥረት

13

ተግባቢ እና ጨዋታ አዋቂ ናቸው። ልዩ የሀገር ፍቅር ስላላቸው ለኢትዮጵያ የበለጠ መስራትን አልመው ጉዞ ጀምረዋል። ቢሊዮኖች የሚያወጣ ሆስፒታል በቅርብ ዓመታት ገንብተው ሲጨርሱ በሙያቸው ዳግም እንደሚሰሩ ለእራሳቸው ቃል ገብተዋል። ጠይም መልካቸው እና ሳቂታ ተፈጥሮአቸው ደግሞ መለያዎቻቸው ናቸው። ከአማርኛ በተጨማሪ የደች ቋንቋን አቀላጥፈው ሲናገሩ የሰማ ኢትዮጵያዊነታቸውን ሊጠራጠር ይችላል።

በባህላዊ እቃዎች ያጌጠው ሎጃቸው ደግሞ የሀገር ፍቅር ስሜት የመቀስቀስ ኃይል አለው። ዘርፈ ብዙ ስራዎች ላይ የተሰማሩ ጠንካራ ሴት በመሆናቸው ለሌላውም አስተማሪ የሆነ ታሪክ እንዳላቸው በርካቶች ይመሰክራሉ። ኢትዮጵያውያን ከተረዳዳን ማንም ተጨማሪ ሰው ሳያስፈልገን እራሳችንን በእራሳችን ማቆም እንችላለን የሚል ጽኑ እምነት አላቸው።

የዛሬው እንግዳችን ዶክተር እመቤት ደምሰው ይባላሉ። ውልደታቸው ነቀምቴ ከተማ ሲሆን ወላጆቻቸው ለስራ ምክንያት በተለያዩ አካባቢዎች ይንቀሳቀሱ ነበር። እናም እናትና አባታቸው በኦሮሚያ ክልል በምትገኘው የአርበኞች መናኸሪያነቷ በምትታወቀው ነቀምቴ ከተማ ለስራ ምክንያት ለሶስት ዓመታት ቆይታ ሲያደርጉ የዛሬዋን ዶክተር እንስት ወልደው ለዓለም አበረከቱ። ህይወት በነቀምቴ ብዙም ሳትቀጥል ግን ገና አንድ አመት ሳይሆናቸው ቤተሰባቸው ወደ አዲስ አበባ በመመለሱ ህይወት መልሳ ወደ መዲናይቱ መራቻቸው። ቦሌ ሩዋንዳ አካባቢ በቤተሰባቸው መኖሪያም ከተሙ።

በወቅቱ ከታላቅ እና ታናሽ ሁለት ወንድሞቻቸው መሃከል የተወለዱት እንስቷ ከወንድሞቻቸው ጋር ነበር እየተጫወቱ ያደጉት። በተለይ እግር ኳስ እና የተለያዩ የወንድ ናቸው ተብለው በማህበረሰቡ ዘንድ የሚታሰቡ ጨዋታዎችን በማዘውተር ነበር የሚታወቁት። ‹‹ወንዲላ አይነት የምትባል ልጅ ነበርኩ›› ብለው ከሶስት አስርት ዓመታት በፊት የነበረ የልጅነት ትዝታቸውን የሚያስታውሱት ዶክተር እመቤት፤ በጊዜው ሴትነት ምንም ነገር ከማድረግ እንደማይገድብ ከጠንካራዋ እናታቸው ዘንድ እየተማሩ ማደጋቸውን ያስረዳሉ።

በቤታቸውም ከሁለት ወንድሞቻቸው በተጨማሪ በርካታ የቤተሰብ ልጆች በቤታቸው ስለሚኖሩ የማህበራዊ ህይወትን እና እንግዳ አክባሪነትን በህጻንነት ወቅት እንደተማሩት ነው የሚናገሩት። ስዕል መሳልና ንባብ መውደድ ደግሞ ብልህ ሴት እያደረጋቸው መምጣቱን አይረሱትም።

አሳይ ትምህርት ቤት አንደኛ ደረጃ በሚማሩበት ወቅት በትምህርታቸው ጎበዝ ከሚባሉት መካከል ይመደቡ ነበር። እናም ‹‹ስፔሻል ክላስ ›› ተብሎ በውጤታቸው መሰረት ከጎበዝ ተማሪዎች ጎራ በመመደባቸው ከሌሎች ተማሪዎች ጋር በመሆን ወደ ቦሌ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተሸጋገሩ። በዚያም እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል ድረስ ከተማሩ በኋላ ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ኔዘርላንድ/ደች/ አገር የመሄድ እድሉን አገኙ። በወቅቱ ጉዞ ወደ አውሮፓዊቷ አገር ሲደረግ ከቤተሰብ ተለይቶ መሄድ ችግር ቢሆንባቸውም ሁለት ወንድሞቻቸውም ዕድሉን አግኝተው አብረዋቸው በመሄዳቸው ነገሮች ያን ያህል ከባድ አልነበሩም፡፡

በኔዘርላንድ የአየር ለውጡን፣ አዲስ ባህሉንና የቤተሰብ ናፍቆቱን ተቋቁመው የሜዲሲን እና ሜዲካል ባዮሎጂ ትምህርቶችን ጎን ለጎን ማስኬድ ጀመሩ። አላማ ለነበራቸው እንስት የደች ቋንቋ ትምህርትን በአጭር ጊዜ ተከታትሎ መደበኛውን ትምህርት ማስከተሉ አልከበዳቸውም። ይልቁንም የሜዲካል ባዮሎጂውን ትምህርት ትተው የሜዲስኑን ዘርፍ ጠበቅ አድርገው መማሩን ተያያዙት፡፡ በትምህርት ቆይታቸው አንደኛ ደረጃ ይዘው በመውጣት ከአገሩ ዜጎች የበለጠ ውጤት ያስመዘግቡ እንደነበርም ያስታውሳሉ።

‹‹እኩል ብሆን በውጤቴ ማንም አይጠይቀኝም፣ እናም ሁል ጊዜም በልጬ ለመገኘት ነበር የምፈልገው›› የሚሉት እንግዳችን፤ በልጠው ሲገኙም ይህች ሴት ማናት ሲባል በልበ ሙሉነት ስለአገራቸው እያስተዋወቁ ትምህርታቸውን ይከታተሉ እንደነበር ይናገራሉ። አይታለፍ የለ የዩኒቨርሲቲ ቆይታ እና ፈተናቸውን አልፈው በመጨረሻ ተመረቁ። በህክምና ዶክተር የሆኑት ወይዘሮ እመቤት በተማሩበት ሙያ በዚያው አገር ተቀጥረው መስራት ጀመሩ። አካላቸው በነጮቹ አገር ቢሆንም ቅሉ ልባቸው ግን ሁል ጊዜም እትብታቸው በተቀበረባት ኢትዮጵያ ነበርና በየጊዜው እየተመላለሱ ቤተሰብ ይጠይቁ እንደነበር አይረሱትም።

አቅማቸው ጠንከር ሲል ደግሞ በኔዘርላንድ አገር የራሳቸውን ክሊኒክ ከፍተው የህክምና አገልግሎት መስጠት ጀመሩ። በዚያም ትዳር መስርተው ሁለት ልጆችን ወልደዋል። ስምንት ዓመታትንም በኔዘርላንድ ቆይተው በርካቶችን በሙያቸው አክመዋል። የደች ዜግነት ካላቸው ባለቤታቸው የወለዷቸውን ሁለት ልጆች ኢትዮጵያ አምጥተው ማሳደግ የፈለጉት እናትም ቢዝነስ ውስጥ ገብተው ቤተሰባቸውን ይዘው ወደ ሸገር ለመትመም አስበዋል። በወቅቱ ደግሞ በቤተሰባቸው ምክንያት በተፈጠረ አለመግባባትን ምክንያት አድርጎ የአዲስ አበባውን ያደጉበትን ቤት ሊያጡ መሆኑን ይሰማሉ።

ከእናታቸው እና ወንድሞቻቸው ጋር በመነጋገር ያደጉበትን ቤት ለሌላ ሰው ሳይተላለፍ አንድ ስራ ለመጀመር በማሰብ ገዝተው የግላቸው አደረጉት። አርዓያ የሆኗቸውን እናታቸውን ሲያማክሩም ቤቱን ሎጅ አድርገው ቢሰሩበት አዋጭ እና ምቹ ኢንቨስትመንት እንደሚሆን ይነገራቸዋል። በወላጃቸው ምክር የታገዙት እንስትም ኔዘርላንድ ሆነው የሎጁን ግንባታ በቦሌ ሩዋንዳ አካባቢው በሚገኘው ቤት አስጀመሩ። እናታቸውም ደፋ ቀና እያሉ የተወሰነውን ግንባታ ሲያከናውኑ እርሳቸው ከኔዘርላንድ መጥተው ሙሉ ትኩረታቸውን በግንባታው ላይ አደረጉ።

ሎጁ ሲገነባ ዶክተር እመቤት በሲሚንቶ እና በጠጠር እያስዋቡ ስዕል ጭምር በማዘጋጀት ተሳትፈዋል። እናም አገርኛ ቃና ባላቸው የእንጨት እና የቆዳ ውጤቶች ያጌጠው እንዲሁም ሰላም የሰፈነበት ሎጅም ከተማ መሃል ተገንብቶ ተጠናቀቀ። 16 ቋሚ ሰራተኞች ያሉት ሎጅ አሁን ላይ በርካታ ታዋቂ የውጭ አገር ዜጎችን እና የተለያዩ እንግዶችን እያስተናገደ ይገኛል። በተለይ በቻይና ፎቆች እና በመስታወት ከተከበቡ ግንባታዎች ራቅ ብለው ኢትዮጵያዊ ቃና ባለው ማረፊያ መዝናናት የሚፈልጉ ነጮች በየቀኑ ዚየስት በተሰኘው ሎጅ ማረፊያቸውን አድርገዋል።

ስድስት ዓመታትን ያስቆጠረው ሎጅ አስር የማደሪያ ክፍሎች ሲኖሩት አንድም ማናጀር የሌለው ሰራተኛው በመወያየት እና የእኔነት ስሜት ተሰምቶት እንዲሰራ በመደረጉ ሰላማዊ ቦታ መሆኑን ዶክተር እመቤት ያስረዳሉ። በዚህም ድርጅታቸው የተለያዩ ዓለም አቀፍ እና የአገር ውስጥ የጥራት ተሸላሚ ሆኗል።

የህክምና ሙያውን ትተው ወደ ሎጅ ስራ ያመሩት እንስት ታዲያ በሌሎች የቢዝነስ ስራዎች ላይም በንቃት ይሳተፋሉ። በተለይ ያለ ነዳጅ የሚሰራ ጄኔሬተር የማምረት ስራን ከአንድ የውጭ ዜጋ ጋር በመሆን ሲያከናውኑ ቆይተዋል። በዋናነትም በሞሮኮ ያለኤሌክትሪክ የሚሰራ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ፈጠራ ላይ ኢንቨስት በማድረግ አመርቂ ውጤት አስመዝግበዋል። ቴክኖሎጂውን በተለይ ኤሌክትሪክ ለማያገኘው የገጠሩ ኢትዮጵያዊ ለማዳረስ ጽኑ ፍላጎት ስላላቸው በቀጣይ ዓመታት አገር ውስጥ በዘርፉ ለመስራት እቅድ እንዳላቸው ይናገራሉ። ኤሚ የተሰኘውን ጄኔሬተር በሶማሌ ላንድ እና በተለያዩ አገራት እያቀረቡ ሲሆን፣ በኢትዮጵያም ፋብሪካውን ገንብተው ለመስራት ዝግጅት እያደረጉ ነው። በማዕድን እና የውጭ ፋይናንስ ድርጅቶችን በማማከር ስራዎች ላይም ተሰማርተዋል፡፡ ሴት ከበረታች እና በእራስ መተማመን ካላት ብቁ የቢዝነስ ሰው መሆን እንደምትችል በተግባር እያሳዩ ይገኛል።

ዶክተር እመቤት ከሁሉም በላይ እውን እንዲሆን የሚፈልጉት ለአገር የሚተርፍ ስራም አለ። ወደኢንዶኔዢያ እና ህንድ እንዲሁም የተለያዩ አገራት ዶላር ከፍለው ለህክምና የሚሄዱ ኢትዮጵያውያንን እንግልት ለመቀነስ ብሎም ለአገር ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ለማምጣት ትልቅ ፕሮጀክት ይዘዋል። ፕሮጀክቱ ሰብ ስፔሻላይዝ ህክምና የሚሰጥ እና በዓለም ላይ አሉ የተባሉ ቴክኖሎጂዎችን እና የዘርፉን ባለሙያዎች ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት ያቀደ ነው። ለስራው ከተለያዩ የፋይናንስ ድጋፍ አድራጊ ተቋማት 300 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደሚያገኙ አረጋግጠዋል።

የፋይናንስ ተቋማቱ ለተለያዩ መንግስታት እንጂ ለግለሰቦች ገንዘብ የማይሰጡ ቢሆንም ዶክተር እመቤት ግን በዘርፉ አማካሪ በመሆናቸው እና የስራ እንቅስቃሴያቸውም በለጋሾቹ ዘንድ የሚታወቅ በመሆኑ ተፈቅዶላቸዋል። እናም ቀጣዩ ስራ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ተነጋግረው ለገንዘቡ ማስተማመኛ ወይም ጋራንቲ የሚባለውን ማረጋገጫ እንዲሰጣቸው ነው። ማረጋገጫው ሲገኝ ቦታ ተረክበው በአዲስ አበባ እጅግ ዘመናዊውን ሰብ ስፔሻላይዝ ሆስፒታል ከሁለት እስከ ስድስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ አቅደዋል። ለዚህም የተለያዩ የመንግስት ተቋማት ዘንድ ቀርበው እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ናቸው።

ከግንባታው ገንዘብ ትልቅነት ጋር ተያይዞ የሚገነባው ሆስፒታልም ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶችን በጥራት የሚሰጥ እንደሚሆን ይታመናል። በመሆኑም መንግስት ሆስፒታሉ ሲጠናቀቅ ከውጭ አገራት ጭምር በህክምና አገልግሎት የሚያስገባውን የውጭ ምንዛሬ ገቢ አስቦ በጊዜ ማረጋገጫውን እንደሚሰጣቸው ተስፋ አድርገዋል። እርሳቸውም ሆስፒታሉ ለውጭ አገር ሰዎች በከፍተኛ ገንዘብ ሲያስከፍል ለአገሬው ሰዎች ደግሞ በድጋፍ መልክ በአነስተኛ ወጪዎችን የተወሳሰቡ ህክምና አገልግሎቶችን ለመስጠት አቅደዋል። ይህ ዘርፈ ብዙ አላማቸው ታዲያ ለበርካቶች አርዓያነት የሚተርፍ መሆኑን መመስከር ይቻላል።

በርካታ የገጠር ሴቶች ብሩህ አዕምሮ እና የጠንካራነት መገለጫዎች መሆናቸውን የሚያወሱት ዶክተር እመቤት፤ በዚህ እውነታ ላይ በራስ መተማመን ጨምረውበት እና ለሚሰሩት ጉዳይ አላማ ይዘው ከተነሱ በየትኛውም የንግድ ህይወት ስኬታማ መሆን እንደሚችሉ ይመሰክራሉ። ዋናው ቁም ነገር በእራሳቸው መቆም እንደሚችል አምነው ለመነሳት መሞከር ነው፤ ከዚያ በኋላ ያለውን ማሸነፍ እችላለሁ ብሎ በመነሳት ለትልቅ ደረጃ መድረስ ይቻላል የሚለው ደግሞ ምክራቸው ነው።

አዲስ ዘመን ቅዳሜ  ነሀሴ 4/2011

ጌትነት ተስፋማርያም