ሌላኛው የማሸነፍ ምስጢር

13

ከጊዜ ወደ ጊዜ የእግር ኳስ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው በእጅጉ እየጨመረ ነው። ከሁለት ባላጋራዎች የሜዳ ላይ ፉክክር አልፎ እያንዳንዳችን ቤት ገብቷል። ከሌሎች ስፖርታዊ ክንውኖች ባሻገር ዓለም አቀፍ ተፅእኖውም በጣም ከፍተኛ ነው። ክለቦች፣ ብሄራዊ ቡድኖች እንዲሁም የእግር ኳስ አካዳሚዎች ረብጣ ገንዘብ በስፖርቱ ላይ በማፍሰስ የድል ማማ ላይ ለመንጠልጠል ይፎካከራሉ። ማንኛውንም ነገር ስኬት ላይ የሚያደርሳቸው ከሆነ ያለማቅማማት ይተገብሩታል።

ድሮ ድሮ የእግር ኳስ ቡድኖች ተጫዋቾቻ ቸውን በታክቲክ እና በአካል ብቃት እንዲሁም በተለያዩ የተግባር ልምምዶች ይገነቡ ነበር። በዚህ ዘመን ግን በውድድሮች ሁሉ አሸናፊ ለመሆን እርሱ ብቻ በቂ ሆኖ አልተገኘም። የተጫዋቾች የስነ ልቦና ይዘት እና ያሉበት ሁኔታ ለአንድ ቡድን ማሸነፍ ከምንም ነገር በላይ አስፈላጊ ነው። በመሆኑም ያላቸውን አቅም እና ክህሎት በሚገባ እንዲጠቀሙበት፤ በራስ መተማመናቸው እና የስነ ልቦና ይዘታቸው ጥሩ ሁኔታ ላይ መገኘት ይኖርበታል።

ምንም እንኳን አንድ እግር ኳስ ተጫዋች የአካል እና የታክቲክ ብቃቱ ጥሩ ሁኔታ ላይ ቢገኝም፤ በተለያየ ምክንያት የስነ ልቦና ይዞታው ጥሩ ካልሆነ በሚፈለገው ደረጃ የሚጫወትበትን ቡድን ሊጠቅም አይችልም። ይህ በመሆኑን የእግር ኳስ ብሄራዊ ቡድኖች፣ ክለቦች እንዲሁም አካዳሚዎች የተጫዋቾቻቸውን የስነ ልቦና ደረጃ በመልካም ሁኔታ ለማሳደግ በዘርፉ ጠበብት የሆኑ ባለሙያዎቻቸውን በቡድናቸው ውስጥ ያካትታሉ።

ለዛሬ የዝግጅት ክፍላችን «ስነ ልቦና በእግር ኳስ መድረክ ላይ ያለውን ጠቀሜታ» ለመዳሰስ ይሞክራል። በተለይም ለአገራችን የእግር ኳስ እድገት የስፖርቱ ቤተሰቦች ይህንን ተግባራዊ እንዲያደርጉ አንዳንድ ነጥቦችን ለመጠቆም ይሞክራል። በዚህ ወቅት ብሄራዊ ቡድናችን እንዲሁም በአገሪቷ የሚገኙ ክለቦች፤ የስነ ልቦና ሳይንሱን በሚገባ ተረድተው ከጥቅሞቹ ለመቋደስ መሄድ የሚገባቸውን ርቀት እንዳልተጓዙ የሚያመለክቱ በርካታ ጉዳዮችን ማንሳት ይቻላል።

ሆኖም ለምን ተግባራዊ አላደረጉም የሚል ትችት ከመሰንዘር ባለፈ ዘርፉ ያለውን ጠቀሜታ ለመዳሰስ እና ጉልህ ሚናውን ለነዚህ የስፖርት ቤተሰቦች ለማሳየት እንሞክራለን። ይህ ዳሰሳ ስነ ልቦናን ከእግር ኳስ አንፃር ቢቃኝም ቅሉ ሳይንሱ ለሌሎች ስፖርቶች አይሰራም ማለት እንዳልሆነ ከግምት ውስጥ መግባት ይኖርበታል።

የእግር ኳስ ደረጃቸው ጫፍ ላይ የደረሱ ብሄራዊ ቡድኖች እና ክለቦች በስብስባቸው ላይ የተጫዋቾቻቸውን ስነ ልቦና ደረጃ ከፍ ለማድረግ፤ በሳይንሱ ብቁ ቦታ ላይ የሚገኙ ባለሙያዎችን በቡድናቸው ውስጥ ያካትታሉ። የስነ ልቦና ህክምና ወይም ድጋፍ በአውሮፓ የእግር ኳስ ቡድኖች ውስጥ የሚካተት ቢሆንም በስፋት ግን የመገናኛ ብዙሀንን ትኩረት አያገኝም። ምክንያቱም በባህሪው ለተጫዋቾች የሚደረገው የስነ ልቦና ድጋፍ ሚስጥራዊ ይዘት ስለሚኖረው ነው። ሆኖም ግን ተጫዋቾች ከተለመደው ልምምዳቸው እኩል የስነ ልቦና ድጋፍ ሲያስፈልጋቸው ጎን ለጎን መውሰዳቸው አዲስ አይደለም።

ዶክተር ቲም ኦብሪን በዘርፉ ከፍተኛ ዝናና አድናቆትን ያተረፉ የስነ ልቦና ባለሙያ ናቸው። በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ በርካታ ደጋፊ እና አስደናቂ ክብረ ወሰኖች ባለቤት ከሆነው አርሰናል ክለብ ጋር ከ10 ዓመት በላይ አብረው ሰርተዋል። እኚህ አንጋፋ የዘርፉ ጠቢብ በአርሰናል ቤት አሻራቸውን ጥለው ላለፉት ዴኒስ ቤርካምፕ፣ሮበርት ፒሬዝ፣ቴሪ ዳንኤል ሄንሪ እና ሌሎች ተጫዋቾች እርዳታ ባስፈለጋቸው ቁጥር ከጎናቸው ነበሩ። ዶክተሩ «የስነ ልቦና ህክምና» ለእግር ኳስ ያለውን ከፍተኛ ጠቀሜታ ይናገራሉ።

ዶክተር ቲም በስነ ልቦናው ሳይንስ «እሳቤ፣ስሜት እና ባህሪ» ያላቸውን የተወሳሰበ ግንኙነት ትኩረት በማድረግ ይሰራሉ። እነዚህ ሶስት አስፈላጊ ነገሮች ሲሆኑ በተጫዋቾች ብቃት ላይ በአሉታዊ እና አወንታዊ መልኩ ተፅእኖ ያሳድራሉ። ባለሙያው ተጫዋቾቹ ያላቸውን ትክክለኛ አቅም አውጥተው እንዲጠቀሙ፤ ስሜት፣ባህሪ እና እሳቤያቸው ጤናማ ግንኙነት እንዲያደርጉ እርዳታቸውን ይለግሷቸዋል። በእግር ኳስ ክለቦች የስነ ልቦና ባለሙያ ቀጥሮ ድጋፍ ማድረግ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ አስቆጥሯል። እንደ ዶክተር ቲም ገለፃ ግን በእግር ኳስ ላይ ብቻ ሳይሆን በሁሉም የሰው ልጅ እሳቤ የዚህ ሳይንስ ድጋፍ ጠቀሜታ የት የለሌ ነው።

«እኔ በስፖርት ውስጥ የምሰራ የስነ ልቦና ባለሙያ እንጂ፤ የእግር ኳስ ስነ ልቦና ባለሙያ አይደለሁም። እኛ እያወራን ያለነው ስለ ሰው ልጆች ነው። ስለዚህ ሁሉም እሳቤውን እና አእምሮውን በጥልቅ እንዲገነዘብ ማድረግ ተገቢ ነው። በጥልቅ አእምሯችን ውስጥ ያለው ታሪክ እሳቤያችንን፣ስሜታችንን እና ድርጊታችንን ይመራዋል። ሁላችንም በአእምሯችን ውስጥ የተለያየ ጥልቅ ታሪክ አለን።

ስለዚህ ይህ ታሪካችን እኛነታችንን እንዴት እንደሚገድበን እና እንደሚቀይረን መረዳት መቻል ይኖርብናል። አብዛኛው የስፖርት ቤተሰብ ተጫዋቾችን እንደ ቲያትረኛ ይመለከታቸዋል። ነገር ግን የእግር ኳስ ቲያትረኛ ከመሆናቸው በፊት ሰዎች ነበሩ» በማለት ዶክተር ቲም የተጫዋቾችን ጥልቅ ስሜት፣እሳቤ እና ባህሪ በመረዳት ውጤታማ እንዲሆኑ እንደሚረዷቸው ይናገራሉ።

የብቃታቸው ጫፍ ላይ የደረሱ ተጫዋቾች ቢኖሩ እንኳን የስነ ልቦና ጥንካሬያቸው በዚያን ወቅት ጥሩ ካልሆነ በፈለጉት ደረጃ ቡድናቸውን መጥቀም አይችሉም። የአጠቃላይ ቡድኑ ጥንካሬ በእነርሱ ወቅታዊ ብቃት ላይ የተመሰረተ ነው። በማለት በተለያዩ ጉዳዮች የእግር ኳስ ተጫዋቾች የስነ ልቦና ችግር ሊያጋጥማቸው እንደሚችል ይናገራሉ። በዚህ ጊዜም ከባለሙያ ድጋፍ ማግኘት እንደሚኖርባቸው ይጠቁማሉ።

አንድ እግር ኳስ ተጫዋች 90 ደቂቃ ሊጫወት ይችላል። እግር ኳስ የታክቲክ፣ የሰውነት ንክኪ እና የፈጠራ ብቃት ላይ የተመሰረተ ጨዋታ ነው። ነገር ግን ይህ ጨዋታ የስነ ልቦና ቁማርንም «psychological game» እንደሚጨምር መረዳት ይኖርብናል። ወደ አገራችን ስንመለስ በተለያዩ ክለቦች እና ፕሮጀክቶች በርካታ ተጫዋቾች አሉ።

አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የአገራችንን ክለቦች ስንመለከት ለቡድናቸው አስፈላጊውን ሁሉ በማሟላት ቡድናቸውን ውጤታማ ለማድረግ ሙሉ አቅም ላይኖራቸው ይችላል። ነገር ግን ለስኬታቸው ቁልፍ የውጤታማነት መሰረት የሆኑ ጉዳዮችን መረዳት እና መተግበር ይኖርባቸዋል። ከእነዚህ መካከል ደግሞ ተጫዋቾቻቸውን በስነ ልቦና ሳይንስ የተሻለ ደረጃ ላይ እንዲደርሱ ባለሙያዎችን በቡድናቸው ውስጥ ማካተት ቀዳሚው ተግባር ነው።

ዶክተር ቲም ከላይ ያነሳነውን ጉዳይ የሚያጠናክር ሀሳብ ያነሳሉ «ለምሳሌ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ላይ ያሉ ተጫዋቾችን እንመልከት። ሊጉ በጣም ፍጥነት የተቀላቀለበት ነው። ተጫዋቾቹ በዚያ ሁኔታ ላይ ሆነው እንኳን በጣም አስደናቂ ነገሮችን በሰከንድ ውስጥ ሲወስኑ እና ሲተገብሩ እንመለከታለን። ከቡድናቸው ጋር በቀላሉ መናበብ ይችላሉ። በሙሉ የራስ መተማመን እና ጥንካሬ ከተፋላሚያቸው ጋር ይፋጠጣሉ። ይህ እንዲሆን ከተፈለገ አንድ የእግር ኳስ ቡድን ተጫዋቾቹን የሚደግፍ፣የሚያበረታታ እንዲሁም ጭንቀታ ቸውን እና የአእምሮ ውጥረታቸውን የሚያስ ወግድ የስነ ልቦና ባለሙያ ያስፈልገዋል» ሲሉ አስተያየታቸውን ያስቀምጣሉ።

እግር ኳስ በጣም በርካታ ተመልካች ባለበት ሜዳ ላይ ለ90 ደቂቃዎች የሚደረግ ፍልሚያ ነው። ከዛም ባለፈ በመገናኛ ብዙሀን ላይ ሰፊ ሽፋን ያገኛል። በተለይ አሁን የማህበራዊ ድረ ገፆች መስፋፋትን ተከትሎ በእያንዳንዷ ሰከንድ ከተጫዋቾች እና ከክለቦች ጋር የተያያዙ መረጃዎች ይወጣሉ። በበጎም ሆነ በመልካም ነገር የሚዛመት የተጫዋቾች መረጃ ለስነ ልቦና ጫና ያጋልጣሉ። ይህ ደግሞ የተጫዋቾቹን የግል ህይወት ሲጨምር ጫናው እንዲበረታ ያደርገዋል። በዚህ ጊዜ ነው እንግዲህ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው።

የስነ ልቦና «ጫና» እና «ውጥረት» የየራሳቸው ባህሪ አላቸው። በእግር ኳስ አምጥተን ከተመለከትናቸው ደግሞ አንዳንዶቹ ተጫዋቾች በጫና ውስጥ ሆነው ጥሩ ብቃታቸውን ሊያሳዩ ይችላሉ። ጫናውን ይወዱታል። ምክንያቱም በእያንዳንዷ ጨዋታ ላይ ያዳበሩት ልምድ እንዲቋቋሙት አስችሏቸዋል።

ዶክተር ቲም ሲናገሩ «በህይወት ውስጥ ጫና ወደ ውጥረት ሲቀየር፤ ነገሮችን ለመቋቋም የሚያስችል የስነ ልቦና ብቃት እንደሌለህ ልታስብ ትችላለህ። ይህ በስፖርቱ ዘርፍ ላይ ተመሳሳይ ነው። በዚህ ጊዜ እርዳታ ያስፈልግሀል። የባለሙያ እርዳታ ደግሞ በጫና ውስጥ ሆነህ እንዴት ስኬታማ እንቅስቃሴ እንደምታደርግ መንገዱን ያመላክትሀል» በማለት በእግር ኳስ ህይወት ላይ ምን ያህል ህክምናው ጠቀሜታ እንዳለው ለማስረዳት ይሞክራሉ።

የሰው ልጅ አእምሮ ውስብስብ እና በጣም ሚስጢራዊ አሰራር ያለው ነው። ይህ በመሆኑ በስነ ልቦና ህክምና ላይ ብቁ የሆኑ ባለሙያዎችን በስራዎቻችን ላይ ማሳተፍ ለውጤታማነታችን አሌ የማይባል አስተዋጽኦ ያበረክታል። በእግር ኳስ ዘርፉ ላይ የስነ ልቦና ባለሙያዎችን በቡድናቸው ውስጥ ከሚያካትቱት ውስጥ እንደ ምሳሌ ከላይ ያነሳነው የእንግሊዙን አርሰናል ክለብ ነው። በአሁኑ ሰዓት ክለቡ በቦርዱ ውስጥ ዶክተር ሴሪ ኢቫንስን አካቷል። እርሳቸው የስነ አእምሮ ባለሙያ ናቸው።

በስኬታማነት ከሚጠቀስላቸው ስራ መካከል የሲውዘርላንድ የራግቢ ብሄራዊ ቡድንን በሙያቸው እየረዱ የዓለም ዋንጫ ማንሳት መቻላቸው ነው። ከዚህም ሌላ በዋናው ቡድን ላይ የስነ ልቦና እና የስነ አዕምሮ ማበልፀጊያ ክፍል ሃላፊው ዴቪድ ፕሪስትሊ ይገኛሉ።

የእግር ኳስ ቡድኖች የሙሉ ጊዜ የስነ ልቦና ባለሙያ ለመቅጠር የሚገደዱት ስፖርቱ በተጫዋቾች ላይ ይዞት የሚመጣው ውስብስብ ተፅእኖ ስላለ ነው። ነገር ግን የእግር ኳስ ቡድን ስንል ምን ማለታችን ነው? የእግር ኳስ ቡድን በአንድ መንደር ውስጥ እንደሚኖሩ እና በጥብቅ ማህበራዊ ግንኙነት እንደተሳሰሩ ማህበረሰቦች ይመሰላል። ዝም ብሎ 11 ተጫዋቾች ከሌላ ባላጋራቸው ጋር በሜዳ ላይ የሚያደርጉት ፍልሚያ አይደለም። በጨዋታው ለማሸነፍ በሜዳ ላይ ብቻ አብሮ መግባት በቂ አይደለም።

ከዚህ ሌላ ቡድኑ አሸናፊ ለመሆን የአይበገሬነት እና በጣም የጠነከረ አንድነት ሊኖረው ይገባል። ይህ ሲሆን የሚፈለገው ውጤት ይመጣል። አንድ ተጫዋች የራሱ ማንነት እና ጥንካሬ ሊኖረው ይችላል። አንድ ቡድንም እንዲሁ በተመሳሳይ የራሱ ማንነት ፣ ጥንካሬ እንዲሁም ድክመት ይኖረዋል። በአንድ ቡድን ውስጥ ያሉ ተጫዋቾች ደግሞ የተለያየ ማንነት፣ባህል፣ ብቃት እንዲሁም የስነ ልቦና ጥንካሬ ላይ የሚገኙ ሊሆኑ ይችላሉ። እነዚህን ሁሉ የተሟላ እና ጥሩ በሆነ የራስ መተማመን አሸናፊነትን እንዲላበሱ እንደ እነ ዶክተር ቲም ያለ የስነ ልቦና ሳይንስን ጠንቅቆ የሚያውቅ ባለሙያ ቡድኑ ሊኖረው ይገባል።

ዶክተር ቲም መጀመሪያ ከእግር ኳስ ተጫዋቾች ጋር መስራት ሲጀምሩ ያጋጠማቸውን ነገር ሲገልፁ እንዲህ ይላሉ «ልክ ስራዬን ስጀምር በአብዛኛው እግር ኳስ ተጫዋቾች ላይ አንድ ድምዳሜ ነበር። ይሄም አንዳንድ ተጫዋቾች በስነ ልቦና ደካማ አንዳንዶቹ ደግሞ ጠንካራ አድርጎ የመውሰድ የተሳሳተ አመለካከት ነበር። በስነ ልቦና ባለሙያ የሚረዱ ተጫዋቾች በደፈናው ደካማ እንደሆኑ ይቆጠር ነበር።

ይህ ግን ፍፁም የተሳሳተ ነው። የስነ ልቦና ባለሙያ ከነበረህ ጥሩ አቋም የተሻለ ጥንካሬ እና ብቃት እንድትጨምር ያግዛል እንጂ፤ ችግር ያለባቸውን ሰዎች ብቻ ህክምና አያደርግም» በማለት የአእምሮ ደካማነት «mental weak­ness» እንዲሁም የአእምሮ ጥንካሬ «men­tal strength» ፤ በምርምር ላይ ተመስርቶ በሚገኝ ውጤት የሚረጋገጥ እንጂ በደፈናው አንድ ተጫዋች በስነ ልቦና ባለሙያ ስለተደገፈ እና ስላልተደገፈ የሚታወቅ አለመሆኑን ያስረዳሉ። ባለሙያው በቡድን ውስጥ በዋናነት የሚያስፈልገውም ቀለል ያሉ ማህበራዊ እና ግላዊ ችግሮችን በመቅረፍ ውጤታማነትን ስለሚያጎናፅፍ መሆኑን ይገልፃሉ።

በቅርቡ የእግር ኳስ ተጫዋቾች የስነ አእምሮ ይዞታ መሰረት አድርጎ የወጣ «ፊፍ ፕሮፕ» የተባለ ጥናት እንደጠቆመው በአሁን ሰዓት በዓለም ዙሪያ ላይ እየተጫወቱ ከሚገኙ 607 ተጫዋቾች (ጥናቱን ለመስራት ከተመረጡት) ውስጥ 38 በመቶ ( 219 ተጫዋቾች ) በጭንቀት፣ ጥልቅ በሆነ ድብርት እንዲሁም ውጥረት የተጠቁ መሆኑን አረጋግጧል። ሌላ ተጨማሪ ማረጋገጫ እና አስተያየት ሳንጠብቅ የጥናቱ ውጤት ላይ ብቻ ተመስርተን ምን ያህል የስነ ልቦና ባለሙያ በእግር ኳስ ቡድን ውስጥ አስፈላጊ መሆኑን መገመት አያዳግተንም።

ዶክተር ቲም «ስሜትህ ሁል ጊዜ ዓለምን በምትረዳበት ልክ ነው የሚሆነው። ለምትሰራው ስራ ዋጋ የምትሰጥ ከሆነ ያ በእርግጠኝነት ደስተኛ ያደርግሀል። ይህን ለመረዳት ደግሞ የባለሙያ እገዛ ያስፈልግሀል። ምንም ስራ ምን፤ የመጨረሻ ግብ ሊኖርህ ይገባል። የእግር ኳስ ደረጃቸው በጣም ከፍተኛ በሆነ አገር ውስጥ ረብጣ ገንዘብ እየተከፈለህ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ፍላጎትህን፣ ስሜትህን እንዲሁም አስተሳሰብህን ሊከፋፍል የሚችል ጉዳይ ከገጠመህ ደስታህን ይነጥቀዋል። ይሄ ደግሞ በአቋምህ እና ወቅታዊ ብቃትህ ላይ ተፅእኖ ይፈጥራል» በማለት ይናገራሉ። ይህ በሚሆንበት ሰዓት ደግሞ ቡድኑን ለመርዳት አብረው የሚገኙ የስነ ልቦና ባለሙያዎች ትልቁን ሚና ይጫወታሉ በማለት ያስረዳሉ።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ በጣም ዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ ሰፊ ርቀት መጓዝ አይጠይቅም። ለእድገቱ መጓተት ብሎም ባለበት ደረጃ ላይ መቆም፤ በርካታ ምክንያቶች ይነሳሉ። ከነዚህ ውስጥ ደግሞ በዋናነት እግር ኳሱ ዘመኑ ከፈቀደው የስልጣኔ እና ቴክኖሎጂ ትሩፋት ለመቋደስ ባለመቻሉ መሆኑን የተለያዩ ባለሙያዎች በየፊናቸው ይናገራሉ። እኛም ይህንኑ መነሻ በማድረግ ነው የዛሬውን ዘገባችንን ከአካላዊ እንቅስቃሴ ውጪ ባለው የእግር ኳስ ስነ አእምሮ ላይ ማተኮር የፈለግነው። በመሆኑም ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሁሉ ዳሰሳውን በያዘው የመረጃ ልክ ተገንዝበውት ወደዚህ አሰራር ቢገቡ አንድ እርምጃ ወደፊት መጓዝ ይችላሉ የሚል እሳቤ አለን። ሰላም!

አዲስ ዘመን ነሐሴ 5 /2011

 ዳግም ከበደ