የእምነቱን አስተምህሮ በተግባር !

11

በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት የሚከበረው የ1440ኛው ዓመተ ሒጅራ ዒድ አል-አድሃ ወይም ዒድ አል-ዓረፋ በእስልምና አስተምህሮት መሠረት ከሚከበሩት በዓላት አንዱ እና ትልቁ ነው። በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ ልዩ እና ትልቅ ክብር ተሰጥቶት በዛሬው ዕለት በድምቀት እየተከበረ ይገኛል

ነቢዩላህ ኢብራሂም ከአምላካቸው የተሰጣቸውን ትዕዛዝ ተቀብለው ለፍቅር ሲሉ ልጃቸውን ነቢዩላህ ኢስማዒልን በመስዋዕትነት ለእርድ ያቀረቡበት ተምሳሌታዊ በዓል ነው። በመሆኑም በተለይም በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ በፍቅር በአንድነት እና በመተሳሰብ ይከበራል። ያለው ለሌለው ሰጥቶ፤ ከጎረቤቱ ጋር ብሄሩን ሳይጠይቅ። ውልደቱን ሳይመረምር እና የመጣበት አካባቢ ሳያጠና ሙስሊም ወንድም እና እህት በመሆኑ ብቻ አብሮ ይበላል፤ ይጠጣል።

ዒድ አል-ዓረፋ ከሌሎች የእስልምና በዓላት ልዩ በዓል ነው። ይሄውም በዓረፋ ከብት ያረደ ሰው ስጋውን የሚበላው ለብቻው ሳይሆን ለቤት። ለጎረቤት። ለደሃ ብሎ በማካፈል ነው። ከክርስቲያን ጎረቤትና ዘመዶች ጋርም በጋራ በመጠራራት የሚከበርም በዓል ነው። ይሄ ሀይማኖቱ የሚያዘው የእምነቱ ተከታዮችም የሚከውኑት የፍቅር መግለጫ ተምሳሌት ነው፡፡

ይሄ የፍቅር መግለጫ መተሳሰብ እና አንድነት ዛሬ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ያስፈልገናል። የሀይማኖት። የዘር። የፆታና የቀለም ልዩነት ሳናደርግ በፍቅር እየተሳሰብን፤ ላጣው እያካፈልን ፤ እንዲሁም በሀገራችን እየታየ ያለውን የመገፋፋት መጥፎ አስተሳሰብ ከራሳችን አርቀን በሰላም ልንኖር ይገባል። የዚህ የዚያ ብሄር ተባብለን ሳይሆን ሁሉም ሰው በፈጣሪ አምሳል የተፈጠረ ሰው መሆኑን በማመን ብቻ ልናከብረው ። ልናቀርበው እና የተቸገረውንም ልንረዳው ያስፈልጋል። ለሰላምና ለአንድነት አብረን ልንሰራ ስለ ሰላም በጋራ ልንዘምር ግድ ይሆናል፡፡

ዛሬ እያንዳንዳችን ያለንበት ቦታ በታሪክ አጋጣሚ እንጂ ፈልገንና መርጠን የተገኘንበት አይደለም። ነገም በዚሁ ቦታ ብቻ እንኖራለን ማለትም አይቻልም። እንኳንስ በገዛ ሀገራችን በመላው ዓለም ኢትዮጵያውያን በመኖር ላይ ናቸው። በሀገራችንም በየትኛውም ክልል እና ቦታ ሁሉም ሰው ያለ ከልካይ የመኖር መብት አለው፡፡ይሄንን መብት ደግሞ እያንዳንዳችን ገፊ ሆነን ሳይሆን አቃፊ ሆነን ልናከብርና ልናስከብር ይገባል፡፡

ሀገራችን አሁን ለአለችበት ደረጃ የደረሰችው፤ እኛም እየኖርን ያለነው ህይወታቸውን ሰውተው ። አጥንታቸውን ከስክሰውና ደማቸውን አፍስሰው ለሀገር ፍቅር መስዋዕትነት በከፈሉ አባቶቻችን ነው። እኛም ይሄንን ውለታቸውን የምንከፍለው ሀገራችንን በአንድነት። ህዝቦቿን ደግሞ በፍቅር መያዝ ስንችል ነው። ነብዩ ኢብራሂም ልጃቸውን እስማኤልን ለፈጣሪያቸው መሰዋዕትነት እስከማቅረብ የደረሱት ለፍቅር ብለው በመሆኑ እኛም ለፈጣሪያችን ፍቅር ብለን አብሮን ያለውን ወንድም እና እህት በፍቅር በአንድነት መያዝ ይጠበቅብናል፡፡

በእምነቱ አስተምህሮ እስላም ማለት ሰላም ማለት ነው። ሰላምን የሚወድ ሰላምን የሚሰብክ ሁሉ ለሰላም ትልቅ ዋጋ መስጠት እና ሰላምን መጠበቅ አለበት። በየትኛውም የሀገራችን ክፍልና ክልል ሁሉም ሰው በሰላም ወጥቶ በሰላም የሚገባበት። ካለ ስጋት የሚኖርበትና የብሄር ልዩነት የማይደረግበት መሆን አለበት። ይሄ ሲሆን ነው ሁላችንም የፈጣሪን ትዕዛዝ የምናከብረው። የኢድ አልድሃ በዓልም ለእምነቱ ተከታዮች ብቻም ሳይሆን የእምነቱ ተከታይ ላልሆኑትም የሚያስተምረን ይህንኑ ነው። መፋቀር፡፡ያለንን ለሌላቸው ማካፈልንና አብሮ መኖርን ነው። ይሄንን ደግሞ ሁላችንም ልናከብር ያስፈልጋል፡፡

ተፈናቅለው የነበሩ በርካታ ዜጎች ወደ ቀያቸው ተመልሰዋል። ይሁን እንጂ ወደነበሩበት ህይወት ለመመለስ ብዙ ድካምና ልፋት ይጠብቃቸዋል። ለረጅም ዓመታት ያፈሩትንና ያጠራቁሙትን ሀብት ንብረት መልሰው ለመተካት በጣም ሰፊ ጊዜም ይጠይቃቸዋል ። ስለዚህ እነዚህ ተመላሽ ወገኖቻችንን ወደ ዘላቂ የህይወት መስመራቸው እስኪገቡ ድረስ መደገፍ ይገባል። የኢድ አል አድሀ(ዓረፋ) በዓልን ስናከብርም ይሄንን እያሰበንና እርዳታና ድጋፍ እያደረግን መሆን አለበት። የሀይማኖቱ አስተምህሮንም በተግባር ማረጋገጥ ይጠበቅብናል፡፡

አዲስ ዘመን ነሀሴ 5/2011