ዒድ ሙባረክ

22

አሰላሙ አለይኩም!

እንዴት ናችሁ ሀቢቢዎቼ? የአላህ ሠላምታ በእናንተ ላይ ይሁን። ሠላምታው ለመላው ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ ነው። ወአለይኩም አሰላም በሉ እንጂ? በእናንተም ላይ ሰላም ይሁን ማለት ይከብዳችኋል እንዴ? ጎበዝ ለፈጣሪ ሠላምታ ንፉግ አንሁን እንጂ። ስንቱ አለ መሠላችሁ ይህን የአረብኛ ሠላምታ አጠያየቅ ወደ አንድ ጥግ ብቻ ወስዶ ጎራ ለመለየት የሚዳዳው።

ከጥቂት ዓመታት በፊት የግብጹ ፓትርያርክ አቡነ ቴዎዶር ዳውድ ለጉብኝት ወደ ሐገራችን በመጡ ጊዜ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ እና በወቅቱ አቀባበል ላደረጉላቸው ጳጳሳት ሠላምታ ሲያቀርቡ መቸም እናስታውሳለን። “አሰላሙ አለይኩም…” ሲሉ ብዙዎች ለአፍታም ቢሆን በድንጋጤ እንደተዋጡ ዛሬም ከአዕምሯችን አይረሳንም። እርሳቸው አማርኛ ተናጋሪ ቢሆኑ “እንደምን ናችሁ” ብለው ሠላምታ እንደሚያቀርቡት ዓይነት ተደርጎ ይወሰድ። የኔም ይኸው ነው። ቋንቋ ብሔርም፣ እምነትም፣ ሀገርም የለውም።

እና ከሐገራችን ቋንቋዎች በተጨማሪ የዓለም ቋንቋዎችንም አንድ ሁለት እያልን ብንለምድ መልካም ነው እላለሁ በዚሁ አጋጣሚ። ምክንያቱም ሀገራችን በተለይ በዙሪያዋ ካሉ የአረብኛ ቋንቋ ተናጋሪ ጎረቤት ሐገሮች እና ወንድም ህዝቦች ጋር ዝምድናችንን ለማጥበቅ እና ጉርብትናችንንም ለማጠንከር ለራሳችን የአረብኛ ቋንቋ ብንለማመድ በጣም ተጠቃሚዎች እንሆናለን። የአድዋ ጦርነት መነሻ የወራሪ ሀገርን ቋንቋ አለማወቅ እንደሆነ የውጫሌው ታሪክ ትዝ ይለናል። አረብኛ እና እስልምና ለየቅል ናቸው ለማለት ነው።

ያ ጀማዓ! ወገኖቼ ኑሮ እንዴት ነው? ክረምቱስ እንዴት ይዟችኋል? ችግኞቹስ ከምን ደረሱ? “በአንድ ሳምንት?” አትበሉኝ እንጂ። መቸም አደራችን እንደተጠበቀ ነው አይደል? አይዞአችሁ “ኢንሻአላህ” በእርሱ ፍቃድ እንኳንስ በእጃችን የተከልነው ችግኝ ወፍ የዘራችውንም ያበቅላል የሀገሬ ምድር። እንደ ሰው አማና አይበላም። እንክብካቤው ግን የዘወትር ተግባራችን ይሁን።

እንግዲህ ከዘመቻ መለስ ብለን ይህን በተፈጥሮ ውለታ መክፈያ ግብራችን ያገኘነውን የህሊና እርካታ በመንፈሳዊ ተግባራት ማጠናከር ያለብን ወቅት ላይ ነን። የተዘራው እንዲበቅል፣ የተተከለው እንዲጸድቅ፣ የተወለደው እንዲያድግ፣ ተፈጥሮም ፈጣሪም እንዲታረቁን በጾም በጸሎት የምንበረታበት፤ ከክረምቱ ጨለማ ወደ በራው ጸደይ እንዲያሻግረን አምላካችንን እንደየእምነታችን አጥብቀን የምንለማመንበት፤ ለከርሞ ታጥቀን ዘንድሮን ደግሞ በተራው አምና ለማሰኘት ውስጣችንን የተሻለ ተስፋ የምንሰንቅበት ምዕራፍ ላይ እንገኛለን።

ክርስቲያን የሀገሬ ልጆች በጾመ-ፍልሰታ የጸሎት መርሐግብሩን በቡራኬ ከፍተውታል። ፈጣሪ ይቀበላቸው! ለኢትዮጵያ መዳን አምላክ ሰበብ ያድርጋቸው! አሜን!

ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችም ልክ ዘንድሮ የዐቢይ ጾም እና የረመዳን ጾም ያደረጉትን ተምሳሌታዊ ቅብብሎሽ አይነት በፍልሰታ የተለኮሰውን የስጋም የመንፈስም ቀለብ እና የሀገር ህዳሴ ችቦ የሚያጅብ ታላቁ የዓረፋ በዓል በማክበር ላይ እንገኛለን። ክረምቱን አልፈን የከርሞ ሰው ሁነን መስከረም ሲጠባ ደግሞ የሁለቱም መንፈሳውያን ማሳረጊያ ይሆነን ዘንድ ለዋቃ ምስጋና የምናቀርብበት የኢሬቻ ክብረ በዓልንም ከወዲሁ አሻግረን እያየን ነው። ይች ናት ሀገሬ ይች ናት ኢትዮጵያ! ኢትዮጵያዊነት እንዲህ ሲታይ እንዴት ደስ ይላል መሰላችሁ። ወላሂ እውነቴን ነው የምላችሁ!

“ቅዳሴ እና አዛኑን አጥር ቢለያቸው

ፈጣሪ ከሰማይ በአንድነት ሰማቸው”

አይደል እንዴ ቴዲ ማኛው ያለው? ስንኙን ወይም ይዘቱን አዛብቼው ከሆነ አውፍ በሉኝ። እኔ እንጃ! ይህን መሰል በረከት ከኢትዮጵያ በቀር በሌላ ዓለም ስለመገኘቱ እርግጠኛ አይደለሁም። ደግሞስ ምን ይመጣል ወደ ኢትዮጵያዬ ሺህ ጊዜ ብጠብ? ሰው በቀበሌ እና በጎጥ እየተወሸቀም አይደል? ሲጀመር ሀገሬን መውደዴ እንዲህ አስባለኝ እንጂ ስለሌላው ዓለም ጥላቻ ኖሮኝም አያውቅ። እንዲያውም እኛ ሐበሻውያን ከራስ በላይ ለባዳ፣ ከቤተኛው በላይ ለእንግዳ ያለን አክብሮት እኮ በምድር ላይ ያለ አይመስልም። ስንወድም ስናከብርም ከልብ ነው። የኔ ነገር ወሰድ ያደርገኛል ዘባረቅኩባችሁ አይደል? ወደ እለቱ ርዕሴ እንግባ…

ዛሬ እንኳን በነሐሴ መባቻ ስለሚከበረው የበዓላት ሁሉ ንጉስ ስለሆነው ኢስላማዊ በዓል ቋጥሬ የመጣሁትን ላካፍላችሁ ነው። እሁድ ነሐሴ አምስት 2011 ዓመተ ምህረት በመላው ዓለም በሚገኙ ወደ ሁለት ቢሊዮን በሚጠጉ የእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት የሚከበረው የ1440ኛው ዓመተ ሒጅራ ዒድ አል- አድሃ ወይም ዒድ አል-ዓረፋ በእስልምና አስተምህሮት መሠረት ከሚከበሩት ሁለት ክብረበዓላት አንዱ እና ትልቁ ነው። በዚሁ መሠረት የሀገራችን ሙስሊም ወንድም እህቶቼም ይህንኑ ቀን በልዩ መንፈስ ለማክበር ከፍተኛ ጉጉት እና ቅድመ ዝግጅት አድርገዋል። እለቱ “ዒድ ሙባረክ! ኩሉ ዓም ወ አንቱም ቢ ኸይር!” የምንባባልበት ቀን ነው። እንኳን ለተከበረው ዓመት በዓል አደረሳችሁ! አሁንም ዓመት ዓመት ያድርሳችሁ ነው በአማርኛችን።

እንግዲህ በዚህኛው ዒድ ታላቅነት ላይ አንድ አቋም ያላቸው የዓለማችን ሙስሊሞች ክብረበዓሉን በተለያየ ስያሜም ይጠሩታል። የራሳቸውን ስም በመስጠትም ያንቆለጳጵሱታል ልክ እንደ “አሸንዳ” እና “አሸንድዬ” አችን። ዒድ አል-አድሃ፣ ዒድ አል-አረፋ፣ ዒድ አል-ሐጅ ወዘተ ስያሜዎች በየሀገሩ ባሉ ምዕመናን እንደ መጠሪያ ጥቅም ላይ ይውላል።

የክብረ በዓሉ አመጣጥ

አንድ ሰው የእስልምና እምነትን ለመቀበሉ አምስት መሠረታዊ አስገዳጅ ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላት ይኖርበታል። “አርካኑል ኢስላም” የሚባሉትን። የመጀመሪያው “ሸሃዳ” ነው- ከአላህ በቀር ሌላ አምላክ የለም ሙሐመድ መልዕክተኛው ነው ብሎ መመስከር። ሁለተኛው ደግሞ “ሶላት” ነው- ማንኛውም ዕድሜው ለስግደት የደረሰ አማኝ ። 18 ዓመት የሞላው።

ሁሉ በቀን አምስቱን ግዴታዊ “ፈርድ” ስግደቶችን መስገድ፤ ሶስተኛው ”ዘካ“- ፈጣሪ ከለገሰው ፀጋ አሥራት ማውጣት ወይም ምጽዋት መስጠት ነው፤ አራተኛው “ሶውሙ ረመዳን”- በዓመት አንዴ በኢስላማዊ አቆጣጠር በዘጠነኛው ወር የረመዳንን ጾም መጾም ሲሆን አምስተኛው ደግሞ ሐጅ ነው- አቅሙ ሲፈቅድ በህይወት ዘመን አንዴ ከቻለ ከዚያም በላይ መንፈሳዊ ጉዞ ማድረግ የሚሉት ናቸው። እንደ ማንኛውም ኃይማኖት የእስልምና እምነት ተከታዮችም በአተገባበር አቅማቸው እንደየሰው ቢለያዩም በመቀበል ደረጃ ግን የተጣለባቸው ግዴታ አንድ ነው።

በመሆኑም የመጀመሪያዎቹ አራቶቹ አስገዳጆች አንድን አማኝ ሙስሊም መሆኑን እና አለመሆኑን የሚያረጋግጡ የማዕዘን ድንጋዮች ናቸው። አምስተኛው አስገዳጅ የማዕዘን ድንጋይ ግን ከአካላዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ የአቅም ቅድመ ሁኔታ አኳያ የሚመዘን ይሆናል። ለዚህም ነው “የቻለ ሰው በዓመት አንዴ የሐጅ ጉዞን አድርጎ ፀሎቱን ያድርስ” የሚል ትዕዛዝ በቅዱስ ቁርዓኑ የተቀመጠልን።

ለዛሬው ክብረ በዓላችን መሠረት የሆነውም ይህ አምስተኛው የማዕዘን ድንጋይ ወይም “አርካን” ነው፤ ሐጅ። ሙስሊሞች ከመላው ዓለም አቅሙ ሲፈቅድላቸው በዓመት አንድ ጊዜ በሂጅራ አቆጣጠር 12ኛ በሆነው የዙል ሂጃ“ ወይም የሐጅ ወር ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ መካ መንፈሳዊ ጉዞ በማድረግ ኃይማኖታዊ ግዴታቸውን ይወጣሉ። የሐጅ መርሐግብር በድምሩ አሥር ቀናትን የሚፈጅ ሲሆን በዚህም ለእምነቱ አስተምህሮት እና ቀኖና መሠረት የጣሉ ሶስት አበይት መንፈሳዊ ተግባራት በዋናነት ይዘከራሉ። እነዚህም ነቢዩላህ ኢብራሂም ወይም አብርሃም ከአምላካቸው የተሰጣቸውን ትዕዛዝ ተቀብለው ልጃቸውን ነቢዩላህ ኢስማዒልን ወይም እስማኤልን።

ዐለይሂሙ ስ ሰላም። በመስዋዕትነት ለእርድ ያቀረቡበትን፤ አባታችን አደም እና ሐዋ ወይም አዳም እና ሄዋን የፈጣሪን ህግጋት ባለማክበራቸው ከገነት ወደ ምድር ተባርረው ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙበት ያወቃት ያወቀችው የተዋወቁበት- በነገራችን ላይ የበዓሉ መጠሪያ የሆነው “ዐረፈ” የሚለው የአረብኛ ቃል አወቀ የሚለውን ትርጉም የሚሰጠን ከዚህ በመነሳት እንደሆነ ይታወቅ፤ እና የእምነቱ ታላቅ አባት የነበሩት የመጨረሻው ነቢይ ሙሐመድ ቢን አብዱላህ (ሰለላሁ ዐለይሂ ወ ሰለም- ሰላት እና ሰላም በዕርሳቸው ላይ ይውረድ) ”ሐጀቱል ወዳእ” የሚባለውን የስንብት ንግግራቸውን እና የመጨረሻውን ሐጅ ያደረጉበትን እለት ሙስሊሞች በፀሎት የምንዘክርበት እለት ነው።

ይህ ቀን አላህ በቅዱስ ቁርዓኑ ታላቁ የሐጅ ቀን በማለት ከቀናት ሁሉ ያላቀው እለት ነው። ይህን ቀን በአካል ቦታው ላይ ተገኝተው ጸሎታቸውን ማድረስ ያልቻሉ ምዕመናን ካሉበት ሆነው ዘክረውት ይውላሉ። በክብረ በዓልነቱም እጅግ አድርገው በተመሳሳይ ፀሎት እና ምፅዋት ያከብራሉ። ይህን እለት ነው እንግዲህ ዒድ አል አድሃ ብለን የምንጠራው።…

አዲስ ዘመን ነሐሴ 5 /2011

 ሐሚልተን አብዱልአዚዝ