ውብሸት ወርቃለማሁ -የኢትዮጵያ ማስታወቂያ ፈርቀዳጅ

35

አንጋፋ የማስታወቂያ ባለሙያ እና የመድረክ መሪ ናቸው። ለእንግድነት ከተጠሩ በአረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለማት የተዋበው ነጭ ልብስ ያዘወትራሉ፤ ከዚያም አጠር ካለው ቁመናቸው ጋር የሚሄድ ካባ በላዩ ላይ ይደርቡበታል። በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የሚተላለፉ የማስተወቂያ ስራዎች የእርሳቸው አሻራ አርፎባቸዋል። በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ማስታወቂያዎችን ሰርተዋል። ለዛ ባለውና በሚያስገመግመው ድምጻቸው ይታወቃሉ። ለወጣት የማስታወቂያ ባለሙያዎች አርአያ በመሆናቸው ብዙዎች ያከብሯቸዋል። የዛሬው የህይወት እንዲህናት እንግዳችን አቶ ውብሸት ወርቅአለማሁ። እኛም ከሰፊው የህይወት ተሞክሯቸው እንድትቋደሱ ልምዳቸውን እንዲህ አቀረብን። መልካም ንባብ!
ከመንዝ እስከ አዲስ አበባ
አቶ ውብሸት ወርቅአለማሁ የተወለዱት መንዝ በቀድሞው ይፋት አውራጃ ማፉድ ገበያ አንቃውሃ በተባለ አካባቢ ነው። የትውልድ ዘመኑን የሚያስታውሱት ከታሪክ ግጥጥሞሽ ጋር በማያያዝ እንጂ በስንት ዓመተምህረት እንደሆነ በውል አያስታውሱትም። እናም በወርሃ መስከረም ጃንሆይ ድል አድርገው ከገቡ በኋላ እንደተወለዱ ከእናታቸው መስማታቸውን ይናገራሉ። የግለታሪክ መፅሃፋቸው ደግሞ በ1934 ዓ.ም እንደተወለዱ ይናገራል።

አባታቸው አለቃ ወርቃለማሁ ወልደየሱስ ወንድ ከወለዱ እረኛ ሆኖ ያገለግለኛል ቢሉም ሳይጠቀሙባቸው ለስራ ወደ አርሲ ይሄዳሉ። ለቤተሰባቸው የመጨረሻ ወይም ሰባተኛ ልጅ የሆኑት አቶ ውብሸት በተወለዱ በዓመታቸው አባታቸውን በሞት ይነጠቃሉ። በዚህም በእናታቸው ወይዘሮ ተናኜወርቅ አበሩ እና በአያታቸው ወይዘሮ ዘነበች እጅ እንዲያድጉ ሆነ።

እናታቸው ወይዘሮ ተናኜወርቅ ልጃቸውን በቤት ውስጥ መምህር ቀጥረው ፊደል እንዲቆጥሩ አደረጓቸው። መምህር ሸዋለማ የተባሉት የቤተክህነት መምህር ደግሞ ቅስና፣ ዳዊት መደገም እንዲሁም ዜማን አስተማሯቸው። የትምህርት አቀባበላቸው ጥሩ ነበርና እድሜያቸው አስር ሳይደርስ ማፉድ ደብረኃይል ቅዱስ ሚካኤል ደብር በዲቁና ማገልገል ጀመሩ። ዲያቆን እያሉ ግን አንድ ቀን በተወለዱበት አካባቢ ማፉድ ገበያ ያለው ክንውን ቀልባቸውን ይስበዋል። የገበያው ትርምስ፣ የሸማች እና ሻጭ አለመገናኘት በአጠቃላይ የቀያቸው ንግድ ቀልባቸውን ቢስበው አንድ መላ ይዘይዳሉ።

ረጅም ሰው በረዳትነት በማቆም ገዢና ሻጩን እያገናኙ ገንዘብ እንደሚያገኙ በማሰብ ስራውን ጀመሩት። አብሯቸው የሚሰራው ደግሞ ሁለት ሜትር ከአስር ሳንቲሜትር ርዝመት ያለው ቁመተ መለሎ ሰው ነበር። በማፉድ ገበያ አንድ ጠዋት ረጅሙ ሰው ትከሻ ላይ ወጥተው «ይህን ያህል ሰንጋ፣ ይህን ያህል ጤፍ፣ ሁሉም በየአይነቱ ገብቷል» በማለት የመጀመሪያውን ማስታወቂያ በአየር ላይ አዋሉ። በማስታወቂያው የተሳበው ሸማች የትነው ያለው እያለ ከሻጭ ጋር እየተገናኘ ግብይቱ ሲጧጧፍ ዋለ። መጠነኛ ገቢም ከሻጮች በመቀበል የዕለት የማስተዋወቅ ውሏቸውን አጠናከሩት።

አያታቸው እና አንዳንድ የቤተሰብ አባላት ግን «እንዴት የጨዋ ልጅ በገበያ መሃል ይጮሃል» እያሉ የማስታወቂያ ስራቸውን እንዲተዉ መገሰፃቸው አልቀረም። እርሳቸው ግን ስራውን ከማቆም ይልቅ ይበልጥ ገፉበት። በድቁና ስራቸው በዓመት አምስት ማርትሬዛ የሚያገኙት አቶ ውብሸት፤ በማፉድ ገበያ የሆሳዕና ዕለት በሰሩት የማስታወቂያ ስራ ብቻ ከአጋራቸው ጋር አስር ማርትሬዛ ማግኘታቸውን ያስታውሳሉ። በወቅቱ ሲሸከሟቸው ለሚውሉት ቁመተ መለሎ የተወሰነውን ማርትሬዛ በመስጠታቸውና እርሳቸውም እኩል መካፈል አለብኝ በማለታቸው ትብብራቸው መፍረሱን ያስታውሳሉ።

ይህ ደግሞ ሰው ትክሻ ላይ ወጥተው ማስታወቂያ ከመስራት ይልቅ ወደ ጽሁፍ ማስታወቂያ እንዲሸጋገሩ አድርጓቸዋል። አጤፋሪስ እና የከሰል ድቃቂ አቀላቅለው ለሶስት ቀን በማቡካት ያገኙትን ቀለም የፍየል ቆዳ አስወጥረው መፃፍ ጀመሩ። በገበያው በሚገኝ ትልቅ ዛፍ ላይ ቆዳውን በአጋም እሾህ ይወጥሩትና የገባውን እህል እና ሰንጋ ብዛት እየጻፉ ማስተዋወቁንም ተያያዙት።

ቆዳው በየሳምቱ ቅዳሜ ዕለት ይታጠብና ሌላ ማስታወቂያ ይጻፍበታል። እንዲህ እንዲህ እያሉ የማስታወቂያ ስራ ታዋቂነታቸውን በመንዝና ይፋት አካባቢዎች አሰፉት። ከዚያ ከገበያ በኋላ ለእንጨት መጫኛ ከባድ መኪና አስተዋዋቂ ሆነው መስራት ጀመሩ። መኪናው እንጨት ከጫነ በኋላ ወደ አዲስ አበባና ወደተለያዩ ቦታዎች የሚሄዱ ተሳፋሪዎችን ይጭናል። አቶ ውብሸት ደግሞ «መኪናው ለአደጋ የማያጋልጥ ጠንካራ ነው አይገለበጥም ተሳፈሩበት» እያሉ ያስተዋውቃሉ። ይህ ስራቸውም ጋቢና ተቀምጠው በነጻ የፈለጉበት ቦታ ደርሰው እንዲመለሱ ረድቷቸዋል።
አንድ ቀን ግን ገበያው የደራለት ሾፌር አቶ ውብሸትን ከላይ ከህዝቡ ጋር ለመጫን ይወስናል። በድርጊቱ የተበሳጩት አቶ ውብሸትም ያኮርፉና የባለመኪናውን ስም እየጠሩ «የክብረት መኪና አይረባም፣ ይገለበጣል» በማለት አሉታዊ ማስታወቂያ በመስራት ተጠቃሚ እንዲያጣ እንዳደረጉት አይረሱትም። ከዚያ የመማር ፍላጎት ያደረባቸው አቶ ውበሸት የማስታወቂያ ስራቸውን ትተው አዲስ አበባ ታላቅ ወንድማቸው ጋር ለትምህርት መጡ።

ሀገር ፍቅር ቴአትር
አዲስ አበባ ከተማ ተስፋ ኮከብ የተባለ ትምህርት ቤት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን የጀመሩት አቶ ውብሸት፤ ከመደበኛ ትምህርታቸው ጎን ለጎን ሙዚቃ እና ቴአትር መማር ጀመሩ። በወቅቱ ፈረንሳይ አገር ተምረው የመጡት የቴአትር ባለሙያው አቶ ማቴዎስ በቀለ ነበሩ የሚያስተምሯቸው። እናም አንድ ተውኔት ተዘጋጅቶ የሀብታም ልጅ ገጸባህሪን ተላብሰው እንዲጫወቱ ተመረጡ። በወቅቱ ሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት የሃረርጌ የሀገር ፍቅር ቴአትር ስላቋቋመ አቶ ውብሸት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ሳይጨርሱ ወደ ድሬዳዋ እንዲሄዱ ተደረገ።
በሁለት ዓመት የሃረርጌ ሀገር ፍቅር ቆይታቸው ጭሮ፣ ገለምሶ፣ ኦጋዴን እና ቀብሪደሃር የመሳሰሉ አካባቢዎችን በመዘዋወር በርካታ ቴአትሮች ላይ ሰሩ። ከቴአትር ስራቸው በተጓዳኝ መድረክ መሪም ነበሩ። በመድረክ ላይ ቀልድ እና እያዋዙ በሚያቀርቡት መልዕክት ታዳሚዎቹን ያስደምሙ ነበር። በዚህም ብዙዎች መድረክ በመምራት ሙያ እንዲገፉበት ያበረታቷቸዋል። የሃረርጌው ሀገር ፍቅር ከሁለት ዓመት በኋላ ሲፈርስ ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው ዳግም ወደ ሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ተቀላቀሉ።

በዚህ ቴአትር ቤት በተለያዩ ቴአትሮች ላይ በመሳተፍ ከወጋየሁ ንጋቱ እና አንጋፋ ተዋናዮች ጋር የመስራት እድልን አግኝተዋል። በቴአትር ክፍሉም በተዋናይነት፣ በደራሲነት እና በመድረክ አስተዋዋቂነት ሰርተዋል። በወቅቱ ግን አጎታቸው አዝማሪ ቤት ስራ ገብተሃል ብለው አቶ ውብሸትን እስከማሳሰር ደርሰው እንደነበር ያስታውሳሉ። በሀገር ፍቅር መድረኮች የአፄ ኃይለስላሴን ገጸባህሪ ወክለው በመተወን ከንጉሱ ጭምር አድናቆትን ያተረፉት አቶ ውብሸት፤ ቴአትሩን በሚሰሩበት ወቅት መልካቸውም ሆነ ሁለመናቸው ንጉሱን ስለሚመስል ታዳሚዎች ልክ እንደ ንጉሱ እጅ እየነሱ ሰላምታ ይሰጧቸው እንደነበር ያስታውሳሉ።

ከሀገር ውጭም ቢሆን መድረክ የሚመሩበት አጋጣሚ ተፈጥሮ ነበር። የኢትዮጵያ የባህል ቡድን በቀድሞው የቀዳማዊ ኃይለስላሴ ቴአትር ቤት እና በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤቶች በሁለት ቡድኖች ሆኖ ቻይና እና የቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት ሲሄዱ እርሳቸውም ተጓዥ ነበሩ። በዚህም ለሁለት ወራት ያክል በየመድረኮቹ በመምራት ብቃታቸውን አስመስክረዋል። በዚያም ችሎታቸውን ይበልጥ ለማዳበር ሞስኮ እና ቻይና የቴአትር ትምህርት ለመከታተል ፍላጎት አደረባቸው። ሀገራቱ ኮሚኒስት በመሆናቸው ግን ውጣ ውረዱ ይበዛብኛል የሚል ስጋት ዕቅዳቸውን ሰርዘው ወደ አገራቸው ተመለሱ።

ከስራቸው በኋላ ማታ ማታ መደበኛ ትምህርታቸውን የሚከታተሉት አቶ ውብሸት፤ በስራ ቦታቸው ላይ ደረጃቸውን እያሳደጉ በቴአትር ቤቱ እስከ ምክትል ዳይሬክተር ደረጃ ደርሰው እንደነበር ይናገራሉ። ቴአትር ቤቱን ለቀው ሲወጡም በብሔራዊ ሎተሪ ድርጅት የማስታወቂያ ባለሙያነት ተቀጠሩ። ከቴአትር ሙያቸው ጋር በተያያዘ «እኔና ሰባት ገረዶቼ፣ ማም መክቶት፣ 3 ለ1፣ የጥንቆላው መዘዝ፣ ውለታ በጥፊ፣ ሁለተኛ ምዕራፍ እና ባሻህ ዘመኑ» የተባሉ ድርሰቶችን አዘጋጅተዋል። ሰባት የቴሌቪዥንና ሁለት የመድረክ ስራዎችንም አቅርበዋል። «የክትነሽ» የሚል ፊልም ደግሞ በአሜሪካን ስቱዲዮ አቀናብረው ለእይታ አብቅተዋል።

የሙሉ ጊዜ ማስታወቂያ ሥራ
ብሔራዊ ሎተሪ ትኬቶቹን የሚያሻሽጥለት እና ወደተሻለ ትርፍ የሚያመራው ሁነኛ የማስታወቂያ ሰው ይፈልግ ነበርና በመድረክ ስራቸው የሚታወቁትን አቶ ውብሸት ወርቃለማሁን ያገኛል። የብሄራዊ ሎተሪ ድርጅትን ኢ ቦኑሜር የተባሉ ስራ አስኪያጅ አቶ ውብሸትን የማስታወቂያ ክፍል ሹም አድርገው ይሾሟቸዋል። በወቅቱ ዜጎች በሬዲዮን የሚነገረውን የሎተሪ ዕድል አላምን ብለው ነበርና አቶ ውብሸት ሎተሪ የደረሳቸውን ሰዎች በእማኝነት ያቀርቡ ነበር። «ትከብራለህ ሎተሪ ግዛ!» እያሉም በራዲዮን እና በድምጽ ማጉያ በከተሞች እየተዘዋወሩ ቅስቀሳ ያሰሙ ነበር።
በከተማዋ ለማስታወቂያ ስራ ሲዞሩ ግን አንድ ዘዴ ይመጣላቸዋል። ወዲያው ሰበታ ሄደው በ25 ብር አህያ ከገዙ በኋላ የብሄራዊ ሎተሪ ድርጅት ቀለብ እና ማረፊያዋን እንዲያዘጋጅ ያደርጋሉ። ከዚያም አህያዋ ላይ ብር በማዳበሪያ አድርገው ጠመንጃ በያዙ ጠባቂዎች እንድትታጀብ ያዛሉ። ማዳበሪያው ለይምሰል ከላይ የተወሰኑ የብር ኖቶች ጣል ይደረግበት እንጂ አብዛኛው በጭድ የተሞላ ነበር። አህያዋንም በከተማ እያዞሩ «ብሩ መጥቶልሃል ትኬትህን ቁረጥ» እያሉ የሎተሪ ማስታወቂያቸውን አጧጧፉት። አህያዋ በባቡር እስከድሬዳዋ፤ ጅማ ድረስ በመኪና ተጉዛ ማስታወቂያው እንድትሰራ ያደርጉ ነበር።

በሌላ በኩል በማስታወቂያ ስራቸው በእነምኒልክ ወስናቸውና ታዋቂ ሙዚቀኞች ጭምር የሚታጀብ ስለነበር በርካታ የሙዚቃና የንግግር እንዲሁም የማስታወቂያ ሥራዎችን በሬዲዮ እንዲያዘጋጁ እድል ተፈጥሮላቸው ነበር። በጊዜው ደመወዛቸው 400 ብር ሲሆን፤ ሎተሪ ድርጅቱም በእርሳቸው ዘመን ትርፋማነቱ ጨምሮ እንደነበር ያስታውሳሉ። ከሶስት ዓመት የሎተሪ አስተዋዋቂነት ሙያ በኋላ ደግሞ በተሻለ ደመወዝ ወደ ፊሊፕስ ኩባንያ ማስታወቂያ ባለሙያነት ተሸጋግረዋል።

ፊሊፕስ ኩባንያ ውስጥ በርካታ የኤሌክትሮኒክስ ምርቶችን ያስተዋውቃሉ። ሥራቸው የተቃና እንዲሆን ኩባንያው መኪና ሰጥቷቸዋል። ለማስተዋወቅ ስራቸው ለየት ያሉ ስራዎችን ይጠቀሙ የነበሩት አቶ ውብሸት፤ ለአብነት ፊሊፕስ ኩባንያ ቸርቸል ጎዳና የመንገድ መብራቶችን ግራና ቀኝ ተክሎ ስለነበር እርሳቸው ሌሊት ጭምር መብራቱ ስር ቆመው ጋዜጣ ያነባሉ። ይህም የመብራቱን ኃይል ለማስተዋወቅ አስበው ያደረጉት ነበር። ኩባንያው ገበያው እየደራለት ሲመጣ አቶ ውብሸትን ለተጨማሪ ማስታወቂያ ትምህርት ሆላንድ አገር ላካቸው።
በሆላንድ የሶስት ወራት ቆይታ ስለማስ ታወቂያ ቴክኒኮች፣ ድምጽ ቀረጻና አርት ኦት ተማሩ። ስድስት ዓመታትንም በፊሊፕስ ኩባንያ የራዲዮን እና የተለያዩ ኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች ማስታወቂያ ሰሩ። ከበርካታ ድርጅቶች ጋር ለመተዋወቅ ቻሉ። ከዚህ በኋላ የእራሳቸውን ማስታወቂያ ድርጅት በማቋቋም ከሚወዷቸው እንስሶች መካከል አንዱ የሆነውን አንበሳን መጠሪያ በማድረግ በ1656 ዓ.ም አንበሳ የማስታወቂያ ስራዎች ድርጀትን ከፈቱ። ከአንድ አርመናዊ ወዳጃቸው ያገኙትን ሁለት ሺ ብር እና ከሌላ ሰው አምስት ሺ ብር በመበደር መቅረፀ ድምፅና የተለያዩ መሳሪያዎች ገዝተው፣ ቢሮ ተከራይተው ስራ ጀመሩ።

ፊሊፕስ ኩባንያን ጨምሮ አምስት ድርጅቶችን ይዘው በአንድ ወር ውስጥ 10 ሺ ብር በመስራታቸው ብድራቸውን መለሱ። የማስታወቂያ ድርጅቱ አሁንም ድረስ በስራ ላይ ያለ ሲሆን፤ በስሩም 12 ቋሚ ሰራተኞች ይዟል። 10 በትርፍ ጊዜ የሚሳተፉ ሙያተኞች አሉት። አቶ ውብሸት በማስታወቂያ ድርጅታቸው በአቢሲኒያ ባንክ እና በመድን ድርጅት ማስታወቂያዎች በይበልጥ ይታወቃሉ፤ ለበርካታ ድርጀቶች ለዘመናት ማስታወቂያዎችን አዘጋጅተዋል። ይሁንና በደርግ ዘመን ይህ ሙያቸው ሊያስገድላቸው እንደነበር አይረሳቸውም። ለዚህ መንስኤውም የሰሩት የበረሮ ማስታወቂያ ነበር።

በራዲዮ «ቢንቢ የት ልትገቢ፣ በረሮ መጥፊያሽ ነው ዘንድሮ» የሚል የነፍሳት ማጥፊያ ማስታወቂያ ሰርተው ነበር። በአየር ላይ ከዋለ በኋላ በመኪናቸው ሜክሲኮ ላይ ሲዘዋወሩ አንድ የደርግ አባል ያስቆማቸዋል። ከዚያም ለጥያቄ እንደሚፈለጉ ይነግራቸዋል፤ ፖሊስ መኮንኖች አካባቢ በሚገኘው የደህንነቶች ቢሮ እንዲሄዱ ያዛቸዋል። ይሁንና ቤቱ በወቅቱ ሰዎች ይገረፉበት የነበረና ጭካኔ የሚፈጸምበት መሆኑን በወሬ ሰምተዋልና መንገድ አሳብረው ወደሌላ ቢሮ ይሄዳሉ።

ከብሔራዊ ቤተመንግስት አካባቢ ሲደርሱ ቀድሞ የሚያውቋቸው የሚኒስትሮች ምክርቤት ሰብሳቢ በኋላም ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ፍሰሃ ደስታ ቢሮ ዘው ብለው ገቡ። በማያውቁት ሁኔታ ሰዎች እንደሚያሳድዷቸው አስረዷቸው። የደርግ አባሉ ተከተሏቸው ኖሮ ለአቶ ፍስሃ ደርግን የሚሳደብ ማስታወቂያ ሰርተዋል «ትጠፊያለሽ በረሮ ያለው ደርግን ነው» ብሎ ወነጀላቸው። ክሱ ተቀባይነት ባያገኝም አቶ ፍሰሃ «የማስታወቂያ ጽሁፉ ሳንሱር እየተደረገ ይለፍ» የሚል ትዕዛዝ ሰጥተው ያሰናብቷቸዋል። የተባለው ቢሮ ቢሄዱ ኖሮ ሊፈጠር የሚችለውን መከራ ሲያስቡ አሁን ድረስ ይዘገንናቸዋል።

የበጎ አድራጎት ስራ
አቶ ውብሸት የበጎ አድራጎት ተግባርን የጀመሩት በወጣትነት እድሜያቸው ነው። በ1977 ዓ.ም በድርቁ ወቅት «ስጋውን ብሉ ቆዳውን አምጡ» በማለት በእርድ ወቅት ቆዳዎችን ለእርዳታ ለማዋል ያሰባስቡ ነበር። ለገና በዓል ከፊታውራሪ አመዴ ለማ እና ከተለያዩ ወጣቶች ጋር በመሆን በአንድ ቀን ከቆዳ ገቢ የሰበሰቡትን 77 ሺ ብር ለድርቅ ተጎጂዎች መለገሳቸውን ያስታውሳሉ። በዚህም ሳያበቁ ሰዎች ለድርቅ ድጋፍ እንዲለግሱ የገንዘብ ሳጥን አዘጋጅተው በየመንገዱ በመዞር ገቢ አሰባስበዋል።

በወቅቱ የአንገታቸውን ወርቅ እና የያዙትን ሁሉ የሰጧቸው ሩህሩህ ሰዎች መኖራቸውንም አይዘነጉትም። የእርሳቸውን ፈለግ የሚከተሉ ተማሪዎችን ከተኩ በኋላ የገንዘብ ማሰባሰብ ተግባሩን ለሌሎች ወጣቶች አስተላልፈዋል። ከሶስት አስርት ዓመታት በፊት ደግሞ አባያ ሐይቅ ሞልቶ አካባቢውን በጎርፍ ሲያጥለቀልቅ አቶ ውብሸት ለወገን ደራሽ ነበሩ። የአራት ነገስታትን ፎቶ አሰርተው ፎቶዎቹን ለቴሌቶን ጨረታ በማቅረብ ከመቶ ሺ ብር በላይ በመሸጥ ለተፈናቃዮች አበርክተዋል።

ከ11 ዓመታት በፊት በድሬዳዋ አሰቃቂ የጎርፍ አደጋ ሲያጋጥምም በሙያቸው ተጎጂዎችን አገልግለዋል። የእርዳታ ማስተባበሪያ ኮሚሽን በሸራተን ሆቴል ቴሌቶን ሲያዘጋጅ መድረኩን በመምራት በአንድ ቀን 125 ሚሊዮን ብር ቃል እንዲገባ አድርገዋል። ቃል የተገባው ገንዘብ እንዲሰጥ ሌት ተቀን በመስራት አንድ መቶ ሚሊዮን ብሩ እንዲገኝ ጥረዋል። ድሬዳዋ ድረስ ሄደውም ለተጎጂዎች የተሰሩትን ቤቶች እና ዳግም ጎርፍ እንዳይመጣ የሚከላከለውን ግድብ በመጎብኘት ቃል የተገባው ገንዘብ የዋለበትን ስራም ገምግመዋል።
አሁን ደግሞ የብሔራዊ ደም ባንክ የክብር አምባሳደር በመሆን ዜጎች በደም እጦት ምክንያት እንዳይሞቱ ቅስቀሳ እያደረጉ ይገኛሉ። በየጊዜው ደም በመለገስ ተሞክሯቸውን ያካፍላሉ። «ደም በመለገሴ የሰው ህይወት ተርፏል» የሚለውን ማስታወቂያ በእራሳቸው ወጪ ከነዜማው አዘጋጅተዋል። የደም ባንክን ብቻ ሳይሆን ከአፄ ኃይለስላሴ ዘመን ጀምሮ በመቶዎች ለሚቆጠሩ በጎ ምግባሮች የሚውሉ ማስታወቂያዎችን ያለክፍያ ማዘጋጀታቸውን የሚያውቋቸው ይመሰክራሉ።

በርካታ የሙያ ልጆችን በማፍራት ሳይሰለቹ ሰርተዋል። እነ ሰራዊት ፍቅሬ፣ ሙሉአለም ታደሰ፣ ጥላሁን ጉግሳ እና ሌሎችም አርቲስቶችን በሙያቸው ቀርፀው ለአገር አበርክተዋል። እነርሱም «የማስታወቂያ ስራ አባታችን» እያሉ በተደጋጋሚ ይጠሯቸዋል። ከማስታወቂያው ጎን ለጎን ደግሞ በንግድ ምክር ቤቶች ተሳትፎ አድርገዋል። የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ኮሚቴ አባል ሆነው ሰርተዋል። በዓመቱ ደግሞ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ተመርጠዋል።

የአዲስ አበባ እና የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤቶች ፕሬዚዳንት ሆነው ያለደመወዝ አገራቸውን አገልግለዋል። በወቅቱ ከቤልጂየም፣ ከሳዑዲ አረቢያ፣ ከጅቡቲ እና ከዱባይ ጋር ሰባት የተለያዩ ስምምነቶችን በመፈራረም የንግድ ግንኙነት እንዲካሄድ መንገድ ያበጁ ናቸው። በዚህም የሳዑዲ አረቢያ መንግስት በስራቸው ተደስቶ መኪና ሸልሟቸዋል።

ሽልማቶች
የአንጋፋው የማስታወቂያ ባለሙያ አቶ ውብሸት ወርቃለማሁ ሽልማት ዘርዝሮ ለመጨረስ ከባድ ነው። በእርግጥ ለዕርሳቸው ትልቁ ሽልማት የህዝብ ፍቅር ነው። ይሁንና የሚታዩትን ጥቂቱን ስናነሳ በቴአትር ጥበባቸው ጃንሆይን መስለው ሲሰሩ አፄ ኃይለስላሴ ካባ እና የወርቅ ሜዳሊያ ተሸልመዋል። በንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንትነታቸው ደግሞ የሳዑዲ መንግስት የንጉሳቸውን ምስል የያዘ ነጭ ወርቅ ሸልሟቸዋል። አውሮፓ ልዑክ መርተው ሲሄዱም እንዲሁ የወርቅ ማንኪያ ተበርክቶላቸዋል። በማስታወቂያ ስራቸው ጣሊያን ጎልድ ሜርኩሪ ኢንተርናሽናል የክብር ሽልማት ሰጥቷቸዋል። እ.አ.አ በ1981 ቬንዙዌላ ካራካስ በተዘጋጀ ሽልማት ከአፍሪካ «The first African in Advertisement & public relation» በሚል ዘርፍ ተሸላሚም ናቸው።

የመካከለኛው ምስራቅ የማስታወቂያ ማህበር «የአገሩን ምርቶች የሚያኮራ ባለሙያ» በሚል በወቅቱ ብርቅ የነበረውን የምስል እና ድምጽ ማጫወቻ መሳሪያ ሸልሟቸዋል። የአሜሪካ ባዮግራፊካል ኢንስቲትዩት ደግሞ እ.አ.አ1989 በ18 ዓይነት የማስታወቂያ ማስተላለፊያ መንገዶች የሚሰራ ሰው ብሎ ልዩ ሽልማት አበርክቶላቸዋል። እስራኤል እና ጀርመን ላይ በስራቸው እውቅና ተሰጥቷቸዋል። የጉማ ሽልማት የ2010 ዓ.ም የህይወት ዘመን ተሸላሚ ናቸው። ስለስራቸው ድካም እና ጥረት እውቀና ለመስጠት «ለመድረስ» የተሰኘ ፊልም ማስተዋሻነቱን ለእርሳቸው ተደርጓል።

በጎ ሥራ የጠራው ትዳር
በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን በማስታወቂያ ስራቸው የኢትዮጵያ ሴቶች የበጎ ስራ አገልግሎት ማህበርን ማስታወቂያዎች በነጻ ይሰሩ ነበር። በመሆኑም ከመንግስቱ ወርቁ ጋር የማህበሩ አባል ሆነው ይመረጣሉ። በየትምህርት ቤቱ እየተዘዋወሩ ለማህበሩ አባላት ለመመልመል ቅስቀሳ ሲያደርጉ ግን ሴንትሜሪ የተሰኘው አዳሪ ትምህርት ቤት ውስጥ አንዲት እንስት ላይ ዓይናቸው አረፈ። እየተመላለሱ ስለእርሷ ከጠየቁ በኋላ ትውውቃቸው ተጠናከረ።

የትዳር ሃሳብ ሲመጣ ሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት ስር በነበረው ዲላ ከተማ ድረስ ሄደው ስለቤተሰቦቿ ሁኔታ አጠኑ። በወቅቱ የሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት እንደራሴ የነበሩት ደጃዝማች በቀለ በየነ ጋር የስጋ ዝምድና ነበራቸውና ጉዳዩን ቢያማክሯቸው ፖሊሶች መደቡላቸው። ያለምንም ችግር ዲላ ቆይተው የስለላ ስራቸውን አካሂደው ተመለሱ። ከዛ በኋላ የአቶ ውብሸት እና የተማሪዋ ፍቅር ጠነከረ።
የልጅቷ አባት አዲስ አበባ በሚገኘው ማረፊያ ቤታቸው ሲመጡ ደግሞ የጋብቻ ጥያቄ ለማቅረብ ሽማግሌ ተላከ። በወቅቱ አባቷ የአቶ ውብሸትን ስራ ሲጠይቁ ፊሊፕስ ኩባንያ የማስታወቂያ ሰራተኛ መሆናቸው ተነገራቸው። ፊሊፕስ ኩባንያ ባትሪ ድንጋይ ያስመጣ ነበርና አባቷ «ባትሪ ድንጋይ ለሚያሻሽጥ ሰው ልጄን አልሰጥም» ብለው ይከለክላሉ። አባቷ ወደ ዲላ ሲመለሱ ግን የአገር ግዛት ሚኒስትር ዴኤታ የነበሩት ደጃዝማች ለገሰ በዙ እና ሌሎችም አንጋፋ ሰዎች ተመርጠው በድጋሚ ለሽምግልና ተላኩ። የሲዳሞ እንደራሴ ደጃዝማች በቀለም «በዕለቱ እንግዳ ስለሚመጣ ተዘጋጅታችሁ ጠብቁ» የሚል የስልክ መልዕክት ለአባቷ አስቀመጡ። አባቷም የሽማግሌዎቹን ሁኔታ ሲያዩ በወቅቱ ለፈረንጅ መስራት እንደነውር ስለሚቆጠር «ታዲያ የእናንተ ልጅ ከሆነ ለምን የፈረንጅ ተላላኪ ይሆናል?» ብለው ጥያቄ ያቀርባሉ። ስለሙያውም ማብራሪያ ተሰጥቶ እና የጨዋ ልጅ መሆኑ ይነገራቸውና እሺታቸውን ይሰጣሉ።

አቶ ውብሸት ወርቅአለማሁ እና ወይዘሮ ወርቅአለማሁ አበበ ተጋቡ። በ1963 ዓ.ም አዲስ አበባ እና ዲላ ላይ ትልቅ ሰርግ ተዘጋጅቶ የቤተሰብ ትውውቅ ተደረገ። በትዳር ህይወት ሁለት ወንድ ልጆችን የወለዱት ጥንዶቹ ሚስት ከልጆቻቸው ጋር አሜሪካ ባል ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ይኖራሉ። አቶ ውብሸት «ኢትዮጵያን መውደዴ ልዩ ነው። ከሶስት ወር በላይ ከኢትዮጵያ ተለይቼ መኖር አልችልም። ለዚህም ነው ከቤተሰቤ ተለይቼ ኢትዮጵያ የመኖሬ ምክንያት» ይላሉ።

ሁልጊዜም ወደውጭ አገራት ሲጓዙ አዋዜ እና የአገር ባህል ልብስ እንዲሁም ካባ አይለየኝም የሚሉት አንጋፋው የማስታወቂያ ባለሙያ፤ 45 አገራትን የማየት እድል አጋጥሟቸዋል። እንደ ኢትዮጵያ የሚመቻቸውና የሚናፍቁት አገር ግን እንደሌለ ስሜት በተቀላቀለበት ንግግራቸው ያስረዳሉ። ሰላም!

አዲስ ዘመን ታህሳስ 7/2011

ጌትነት ተስፋማርያም