በረከት እና ከበሮው

14

ልጆች እንዴት ሰነበታችሁ? ከተገናኘን ቆየት አልን አይደል? አያቴ ታሪኮችን በፊት ሳትነግረኝ ስትቀር በጣም ይናፍቀኝ ነበር። ብዙ ጊዜ እንደዚህ አይነት አጋጣሚ የሚፈጠረው አያቴ ወደ ሌላ አካባቢ ለዘመድ ጥየቃ ስትሄድ እንዲሁም እኔ ፈተና ሲኖርብኝ ነበር። ሆኖም ግን ከብዙ ቀናት በኋላ አያቴ ተረትና ታሪኮቿን ስትነግረኝ በናፍቆት ስለምሰማው ደስተኛ እሆን ነበር። እኔም አያቴ የነገረችኝ ታሪኮች ሳልነግራችሁ ለትንሽ ጊዜ የጠፋሁት በስራ መብዛት ምክንያት ነው። ታዲያ ዛሬ የምነግራችሁን ታሪክ በናፍቆት እንደምታነቡት እና እንደምትወዱት አልጠራጠርም።

ልጆች በህይወታችሁ ቢኖረኝ ብላችሁ የምታውቁት እና የምትውዱት እቃ አለ? ያንን እቃ ቤተሰቦቻችሁ ገንዘብ በማጣት ስላልገዙላችሁ ተከፍታችሁ ታውቃላችሁ? የምትወዱትን ነገር ለማግኘት ምን ማድረግ እንዳለባችሁ አስባችሁ ታውቃላችሁ? መልካም ዛሬ ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ የአያቴን ጣፋጭ ታሪክ ነው የምነግራችሁ። መቼም አያቶቻችን ለሁሉም ነገር መላ (ዘዴ) አያጡም አይደል? እስቲ ታሪኩ ምን እንደሆነ አብረን እናንብበው።

በአንድ አነስተኛ መንደር ውስጥ የምትኖር ሴት ነበረች። ይህቺ ሴት በረከት የሚባል 10 ዓመት የሆነው ወንድ ልጅም ነበራት። ልጇ በባህሪው የሚመሰገን እና በጣም አስተዋይ ነበር። እናቱ በማንኛውም ሰዓት እርዳታ ካስፈለጋት ሁሌም ሊያግዛት ፍቃደኛ ነው። በቂ ገንዘብ ስለሌላቸው ጥሩ ህይወት መምራት ባይችሉም እናት እና ልጅ ስለሚረዳዱ አስቸጋሪ ጊዜያቶቹን ያልፋሉ።

በረከት ልጅ ቢሆንም ልክ እንደሌሎች ጓደኞቹ ብዙ ነገሮች አያጓጉትም። ለምሳሌ ብዙ ልብስ እና መጫወቻ እቃዎች ባይኖሩትም ምንም አይከፋም። ነገር ግን ከሙዚቃ መሳሪያዎች ውስጥ አንዱ የሆነው «ከበሮን» እንዲኖረው በጣም ይመኛል። እናቱን በግልፅ ባይነግራትም ይህ ፍላጎቱ እንዲሟላለት ለብዙ ጊዜ ይፀልይ ነበር።

አንድ ቀን የበረከት እናት ከእርሻ ማሳዋ ያመረተችውን እህል ለመሸጥ ወደ ገበያ ወጥታ ነበር። በዚህ ጊዜ ልጇን «ከዚህ ገበያ የምትፈልገው ነገር ይኖራል» በማለት ትጠይቀዋለች። እሱም «ምንም እንኳን አቅም ኖሮሽ ትገዛልኛለሽ ብዬ ባላስብም ሁሌም እንዲኖረኝ የምፈልገው እና የምመኘው የሙዚቃ መሳሪያውን ከበሮ ነው። ነገር ግን ይሄ እንደማይሆን አውቃለሁ» በማለት ይመልስላታል።

እሷም ልጇ በነገራት ነገር በጣም አዘነች። ምክንያቱም እሱ ትክክል ነበር። ከበሮውን ለመግዛት የሚያስችል አቅም አልነበራትም። ከገበያ ወደ ቤት በምትመለስበት ሰዓትም ይህንኑ የልጇን ስሜት እያሰበች እና እየተጨነቀች ነበር። ልጇ የጠየቃትን ነገር ማሟላት ባለመቻሏ የተከፋችው እናት በመንገድ ላይ ቁጭ ብላ ማልቀስ ጀመረች።

የበረከት እናት ቁጭ ብላ በምታለቅስበት ስፍራ ላይ አንድ ትንሽ ልጅ እያለፈ ነበር። ሀዘኗ ስላስጨነቀው ጠጋ ብሎ ለምን እንደምታለቅስ ጠየቃት። እሷም የተፈጠረውን ነገር በግልፅ ነገረችው። በዚህ ጊዜ እንግዳው ሰው አንድ ቁራጭ እንጨት ሰጥቷት «ይሄ እንጨት ልጅሽን ምናልባት ሊረዳው ይችላል። በውስጡ ምትሀት አለበት» ይላታል። እሷም የልጇን ፍላጎት ማሟላት ስለምትፈልግ የእንግዳውን ስጦታ ተቀብላ ወደ ቤት ትሄዳለች።

ለበረከትም ከበሮውን ልትገዛለት እንዳልቻለች ነግራው እንጨቱን ትሰጠዋለች። በዚህ ጊዜ በረከት በሰጠችው እንጨት ምን ማድረግ እንደነበረበት አላወቀም። ልጇ ግራ መጋባቱን ያወቀችው እናት በመንገድ ላይ ያገኘችው ልጅ እንጨቱን ሲሰጣት ምን እንዳላት ነገረችው። ልጁም እናቱን አመስግኖ የተሰጠውን እንጨት ይዞ ከጓደኞቹ ጋር ለመጫወት ወደ ውጪ ወጣ።

በረከት በአካባቢው በሚገኝ አንድ ስፍራ በመጫወት ላይ እንዳለ ከርቀት አንድ እድሜያቸው ከፍ ያለ ሴት ዳቦ ሊጋግሩ እሳት ለማያያዝ ሲሞክሩ አስተዋለ። እሳት ለማያያዝ ሲሞክሩ እንጨቱ እርጥብ በመሆኑ አስቸግሯቸው ነበር። ጭሱ በመብዛቱም አይናቸው በእንባ ሞላ። ትንሹ በረከትም ጠጋ ብሎ ለምን እንደሚያለቅሱ ጠየቃቸው። እሳቱ አልያያዝ ስላላቸው ጭሱ እንዳስቸገራቸው ነገሩቱ።

እርሱም በእጁ የያዘውን እንጨት እያቀበላቸው «በዚህ ሞክሩት ምናልባት እሳቱ ሊያያዝሎት ይችላል። እናቴ እንጨቱ ምትሀት አለው ብላኛለች» በማለት ይነግራቸዋል። በዚህ ጊዜ እሳቱ ተቀጣጠለላቸው። በሆነው ነገር ደስ የተሰኙት ሴትዮም መጀመሪያ ከጋገሩት ዳቦ ላይ በምስጋና አንዱን ሰጥተው በረከትን አሰናበቱት።

የእነ በረከት መንደር በጣም ሰፊ ነው። እሱም አካባቢውን በሚገባ ስለሚያውቀው እየተዘዋወረ ነው የሚጫወተው። በዚህ ጊዜ ዳቦ የሰጡት እናትን ተሰናብቶ ወደ ሌላ ቦታ በሚሄድበት ወቅት አንድ የልጅ እናት በመንገድ ላይ ያገኛል። ያቀፈችው ልጅ እያለቀሰ ነበር። ባየው ነገር ያዘነው በረከት እናትየውን ልጁ ለምን እንደሚያለቅስ ጠየቃት። እሷም «ልጄ የሚያለቅሰው እርቦት ነው። አሁን ደግሞ ዳቦ ልሰጠው አልችልም» በማለት ትነግረዋለች። እሱም በእጁ ዳቦ ይዞ ስለነበር ለልጇ ይሰጠዋል። በዚህ ጊዜ በበረከት ደግነት የተደነቀችው የልጁ እናት በእጇ ልትሸጣቸው ከያዘቻቸው የልብስ ማጠቢያ ሰፋፊ ሳፋዎች መካከል አንዱን በምስጋና መልክ ትሰጠዋለች። እሱም ለስጦታው አመስግኖ ሴትየዋን ይሰናበታል።

የእነ በረከት መንደር ውስጥ አንድ ወንዝ አለ። ወደ ሌላኛው አካባቢ አቋርጦ ለመሄድም ወንዙን መሻገር የግድ ይላል። እሱም ሴትየዋን ከተሰናበታት በኋላ የተሰጠውን ሳፋ ይዞ በዚያ ወንዝ ዳር እያለፈ ነበር። በወንዙ ዳር ደግሞ ልብስ በማጠብ የሚተዳደሩ ባልና ሚስቶች ነበሩ። በሰዓቱ ባልየው ሚስቱ ላይ እየጮህ ነበር። በረከትም ለምን እንደሚጣሉ ጠየቃቸው። እሱም «ሚስቴ አንድ ያለንን የልብስ ማጠቢያ ሰበረችው።

አሁን ውሀ አፍልተን ማጠብ አንችልም» በማለት በንዴት ነገረው። በረከት የያዘውን ሳፋ ተመልክቶ እሱ በዚህ ስለማይጠቀምበት ለነሱ ሰጣቸው። እንዳይጣሉም መከራቸው። በዚህ ጊዜ ልብስ አጣቢው በደግነቱ አመስግኖት አንድ ቆንጆ ጃኬት በምስጋና መልክ ሰጠው። በረከትም ስጦታውን ተቀብሎ ከአጠገባቸው ሄደ።

በረከት በመንገድ ላይ ስላጋጠመው ነገር እያሰበ በመጓዝ ላይ እንዳለ አንድ ሰው ፈረስ እየጋለበ አጠገቡ መጣ። ሰውየው እግሩ ላይ ነጠላ ጫማ እና የውስጥ ሱሪ በሰውነቱ ከማረጉ ውጪ ሌላ አካላቱ በልብስ አልተሸፈነም ነበር። ከዚህም ሌላ ፀጉሩ እና ሰውነቱ እርጥብ ነበር። ከብርዱ የተነሳም እየተንቀጠቀጠ ነበር።

በረከት ምን ሆኖ እንደዚህ እንደሆነ ሰውየውን ጠየቀው። ሰውየውም «በዚህ መንደር ዘመዶቼን ለመጠየቅ ነበር የመጣሁት። መንገድ ላይ ሌቦች ዘረፉኝ። እንዲሁም ውሀ ውስጥ ገፍትረው ከተቱኝ። ፈረሱንም አንድ ደግ ሰው ነው የሰጠኝ» አለው በዚህ ጊዜ በረከት በእጁ የያዘውን ልብስ ለሰውየው ሰጠው። በስጦታው ደስተኛ የሆነው ሰው ወደ ዘመዶቹ ጋር መድረሱን ነግሮት ፈረሱን ስለማይፈልገው እሱ እንዲወስደው በስጦታ መልክ አበረከተለት። ሁለቱም ተመሰጋግነው ተለያዩ።

በረከት ከወዲያኛው ማዶ ባለው ሰፈር ያለው ጓደኛው ፈረሱን ይዞ ጉዞውን ቀጠለ። በድንገት ግን ከአንድ ቤት ፊት ለፊት የቆሙ ሰርገኞች ተመለከተ። አብረዋቸው የሙዚቃ መሳሪያ የያዙ ሰዎችም ነበሩ። ሙሽራው፣ አባት እና እናቱ እንዲሁም የመንደሩ ሰዎች ተሰብስበዋል። ነገር ግን ሁሉም ደስተኞች አልነበሩም። በዚህ ጊዜ በረከት አባትየውን ጠጋ ብሎ ምን እንደሆኑ ጠየቃቸው።

አባትየውም «ልጄ በሰርጉ ላይ ፈረስ ካልጋለበ መጥፎ እድል ያጋጥመው በባህላችን መሰረት ተቀምጧል። ፈረስ የሚያከራየን ሰው ደግሞ ዘገየብን ለዚያ ነው ያዘንነው» በማለት ነገሩት። እርሱም በነገሩ ተገርሞ የያዘውን ፈረስ እንዲጠቀሙበት ሰጣቸው። ለሱ ባይጠቅመውም እነሱ እንዲገለገሉበት ነገራቸው። ሰዎቹም በጣም ደስ ብሏቸው አመሰገኑት። ከሁሉም ከሁሉም ግን አንዱ ሙዚቀኛ ደግነቱ በጣም ስለማረከው ከያዛቸው ሁለት ከበሮዎች መካከል አንዱን ሸለመው።

በረከት በሆነው ነገር እጅግ ደስተኛ ሆነ። ከበሮውን ለሰጠው ሰው «ይሄ ለብዙ ጊዜ ስመኘው እና ስፈልገው የነበረው ከበሮ ነበር። እጅግ በጣም አመሰግናለሁ» በማለት እናቱ የሰጠችው ምተሀተኛ እንጨት መስራቱን አመነ። ይሄን ጉዳይ ለእናቱ ለመናገር በመቸኮሉም ወደ ቤቱ ከበሮውን ይዞ ተመለሰ። ለእናቱ የሆነውን ነገር ለማሳየት በጣም ጓጉቶም ነበር።

ልጆች የበረከት እና የእናቱ ታሪክ ብዙ ቁምነገሮችን እንዳስተማራችሁ እርግጠኞች ነን። የታሪኩ ዋና መልክትም እናንተ ያላችሁን ለሰዎች በደግነት እና በሀዘኔታ ማካፈል ስትችሉ ሌሎች የምትፈልጉትን ነገር በተመሳሳይ ይሰጧችኋል። ስለዚህ ደግነት የምንመኘውን ነገር የማድረግ ሀይል እንዳለው ተረድተን ሁላችንም ደጎች መሆን ይኖርብናል። የተቸገሩን በአቅማችን ማገዝ ቅንና ታዛዥ መሆን ይገባል።

ልጆች በተለያየ ጊዜም ተመሳሳይ አስተማሪ እና አዝናኝ ተረትና ታሪኮችን ይዘንላችሁ እንቀርባለን።እናንተም የምታውቁትን ታሪክ ተረተ ጨዋታ አስደናቂ ነገሮች በተለይ ልጆችን የሚያዝናኑና የሚያስተምሩ መልዕክቶችን ጽፋችሁ ብትልኩል እናስተናግዳችሁለን። የምትልኩበት የኢሜል አድራሻና የምትደው ሉበትን የስልክ ቁጥር ጽፈንላችሁል። መልካም የእረፍት ጊዜ ይሁንላችሁ።

መረጃ ለመላክ ወይም ለማግኘት ለምትፈልጉ፣

ስልክ…0111264210 0111569873

ኢሜል….. addiszemen@press.et

ፋክስ…….. 251-0111-56 98 62 ብላችሁ ብትልኩ ወይም ብትደውሉ ታገኙናላችሁ፡፡

አዲስ ዘመን ነሐሴ 5 /2011

ዳግም ከበደ