ተጽእኖ ፈጣሪ ሰዎች

27

ልጆች እንዴት ናችሁ? በዚህኛው አምድ ላይ ታዋቂ ፈላስፋዎችን፣ ጀግና የአገር መሪዎች፣ ሳይንቲስቶችን እና ለአለም ስልጣኔ የበኩላቸውን ድርሻ የተወጡ ሰዎችን እናስተዋውቃችኋለን። እስቲ ልጆች የአለም ስልጣኔ እዚህ እንዲደርስ ትልቅ ድርሻ አላቸው የምትሏቸውና ከዚህ ቀደም እናንተ ከምታውቋቸው ሰዎች መካከል ጥቂቶቹን አስታውሱ። የአገራቸውን ሉአላዊነት ያላስደፈሩ እና መልካም ስብእና ያላቸው መሪዎችንስ ታውቃላችሁ? መልካም ልጆች ሁሉም ሰው በእኩል ደረጃ ለአለም መሰልጠን እና ዘመናዊ መሆን ድርሻ ባይኖረውም ነገር ግን የራሱን ሀላፊነት መወጣት ይኖርበታል። እስቲ ለዛሬ ስለ ጀግናው ራስ አሉላ አባ ነጋ ከተለያዩ የታሪክ መጻህፍት ያገኘነውን እናስነብባችኋለን።

♦ራስ አሉላ አባ ነጋ በ1847 ዓ.ም በትግራይ ተምቤን ዙቁሊ ሚካኤል በተባለ ቦታ እንደተወለዱ ይነገራል።

♦የራስ አሉላ አባት እንግዳ ቁቢ አራት ልጆቻቸውን ሀገርን እና ራስን እንዴት መከላከል እንደሚቻል ያስተምሩ እንደነበር በተለያየ ጊዜ የተፃፉ መዛግብቶች ያመለክታሉ።

♦ራስ አሉላ ግን ከሁሉም ይልቁ ነበር፡፡ በዙቁሊ ሚካኤልም ከመምህር ወልደጊዮርጊስ ዘንድ ይማሩ እንደነበረ ማሞ ውድነህ አብራርተዋል፡፡

♦ራስ አሉላ የጉልምስና ስራውን በአጼ ዮሐንስ አጎት በራስ አርአያ ደምሱ ቤት አሽከር በመሆን እንደጀመሩም እነዚሁ የታሪክ ፅሁፎች ይገልፃሉ።

♦ ራስ አሉላ በስተኋላ ወደ ደጃዝማች በዝብዝ ካሳ ( አፄ ዮሐንስ 4ተኛ) ቤት ከተዛወሩ በኋላ ሹመትን በሹመት ላይ በመደረብ ከፍተኛ ስልጣን መያዝ ችለዋል፡፡ በመጀመሪያ እልፍኝ አስከልካይ ቀጥሎም አጋፋሪነትን ተሾመው ነበር፡፡

♦በ1873 ደጃዝማች ካሳ ንጉስ ነገስት አጼ ዮሐንስ አራተኛ ሲባሉ አሉላ የሻለቅነትን ማዕረግ የንጉሱ ሊጋባነት ማዕረግን ደርበው ያዙ፡፡

♦አሉላ አባ ነጋ ንቁ እና አርቆ አሳቢ እንደነበሩ ብዙ ጸሐፊዎች፣ በጦር ሜዳ ውሎ የሚያውቋቸው፣ በዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አብረዋቸው የሰሩ ሁሉ ይመሰክራሉ።

♦ ዛሬ ላይ ሆነው ነገን የሚመረምሩ ከራስ በላይ ሀገርን የሚያስቀድሙ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ ነበሩ።

♦በወቅቱ አፄ ቴዎድሮስን የመሰለ አንድ ሰው ቢኖር አሉላ አባ ነጋ ብቻ እንደነበሩ የታሪክ አዋቂዎች ይናገራሉ።

♦ ራስ አሉላ ከአጼ ቴዎድሮስ ጋር በተክለ ሰውነት ከመመሳሰል ባለፈ በሰብዕና እና በአመለካከት እንዲሁም በአርቆ አስተዋይነት ይመሳሰላሉ፡፡

♦ ግብርን ለሀገር ጥንካሬ ከማዋል ባለፈ አንድ የጦር መሪ ከተራው ወታደር የተለየ መብላት እና መልበስ እንደሌለበትም ያምኑ ነበር። አፄ ቴዎድሮስም እንደዛው ነበሩ።

♦ ራስ አሉላ በ1847 ዓ.ም እንደመወለዳቸው ስለ አፄ ቴዎድሮስ ጀግንነት እና ትልቅነት እየሰሙ አድገዋል።

♦ ራስ አሉላ ከነበራቸው የተዋጣለት ዲፕሎማት መሆን የተነሳ በአፄ ዮሐንስ ፊት ሞገስ እና ክብር ነበራቸው፡፡ ለዛም ነው ከአሽከርነት እስከ ራስነት ሹመት የደረሱት፡፡ በታሪክ ዘመናቸው በዋናነት ለአፄ ዮሐንስ የቀኝ እጅ ሆነዋል።

♦ ከሶስት ዋና ዋና የኢትዮጵያ የወቅቱ ጠላቶች ጋር ተዋግተዋል፡፡ በዋናነትም ከህዳር 16 ቀን 1875 ዓ.ም ከተደረገው የጉንደት ጦርነት እስከ መጋቢት 1 ቀን 1896 ዓ.ም እስከተደረገው የአድዋ ጦርነት ድረስ ራስ አሉላ አባ ነጋ አስራ ሁለት ጦርነቶችን ከውጭ ወራሪ ኃይሎች ጋር የተዋጉ ሲሆን በዋናነትም ከኦቶማን ግብጽ ተስፋፊዎች፣ ከማህዲስት የደርቡሽ ወራሪዎች እና ከጣሊያን ቅኝ ገዥዎች ጋር ያደረጓቸው ናቸው፡፡ ጣልያንን ካባረሩ ጀግኖች መካከል በመሆናቸው ስማቸው በድል ቀን ላይ በሰፊው ይነሳል።

♦እኝህን ታላቅ ሰው ብዙዎች «የኢትዮጵያ ታላቅ የጦር መሪ» እንዲሁም የውጭ ሰዎች ደግሞ «የመጀመሪያው የአፍሪካ የጦር ጄኔራል» ሲሉ ይጠሯቸዋል።

አዲስ ዘመን ነሐሴ 5 /2011