በፖለቲካ ፓርቲ መነገድ ይቁም

64

 ባሳለፍነው ሳምንት የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባካሄደው ስብሰባ ቀጣዩ ሀገር አቀፍ ምርጫ ህገመንግስቱ ባስቀመጠው መሰረት ላይ እንዲካሄድአቋም በመያዝ እንደ ድርጅትም ሆነ እንደ መንግስት ዝግጅት እንዲደረግ አቅጣጫ አስቀምጧል።

ይሁን እንጂ በአገራችን የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይህን ምርጫ ለማካሄድ ያላቸው ቁመና ምን ላይ ይገኛል ህብረተሰቡስ አሁን ባለው ሁኔታ በፖለቲካ ፓርቲዎች ፕሮግራሞችና አጠቃላይ አላማ ላይ ምን ያህል ግንዛቤ አለውየሚለው ያልተመለሰ ጥያቄ ነው። ለዚህ ደግሞ የተለያዩ ማሳያዎች አሉ።

ከጥቂት ወራት በፊት የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ አሰራር የቃልኪዳን ሰነድ የተፈራረሙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥር 107 እንደነበር ይታወሳል። በወቅቱ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ቁጥር መብዛት እውነተኛ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ለመፍጠር እንደማያስችል የጠቆሙት የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተመሳሳይና ተቀራራቢ ኣላማና ፕሮግራም ያላቸው ፓርቲዎች ሰብሰብ ብለው በመዋሃድ ህብረት ቢፈጥሩ ጠንካራ ሆኖ ለመውጣት ያግዛል በሚል ፓርቲዎች እንዲጠናክሩ ምክረሃሳብ ለግሰው ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ብዙም ተግባራዊ የሆነ አይመስልም። ምክንያቱም ጥቂት ፓርቲዎች ጥሪውን ተቀብለው ውህደት ቢፈጥሩም የአዳዲስ የፓርቲዎች መፈልፈል ግን አሁንም አልተገታም። ሰሞኑንም የፓርቲዎች ቁጥር 137 መድረሱ ታውቋል።

ለመሆኑ አሁን ባለው ሁኔታ በአገራችን ሁሉንም አስተሳሰቦች የሚወክሉ የፖለቲካፓርቲዎች የሉንም አዳዲስ ፓርቲዎችን የሚፈጥሩትስ አካላት አሁን ያሉት ፓርቲዎች የያዙትን ፕሮግራምና አላማ አውቀው ከእነሱ የተለየ ለህዝብ የሚጠቅም ሃሳብ ይዘው ለመምጣት ነውወይስ በጊዜያዊ ስሜት ነው አዲስ ፓርቲ የሚመሰርቱት የሚለው ሊጤን ይገባል።

በሌላ በኩል የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ሃሳብ ላይ የተመሰረተ ልዩነት ያራምዳሉ ወይ ብሎ ለሚጠይቅም በቂ መልስ ላያገኝ ይችላል። ምክንያቱም በዓለም ላይ ያለው የርዕዮተ ዓለም ልዩነት ከአራት ግፋ ቢል ደግሞ ከአምስት የዘለለ አይደለም። እነዚህ አስተሳሰቦች የዜጎችን መሰረታዊ ጥያቄዎች የመመለስ ብቃት እንዳላቸውም ሳይንስ ያረጋግጣል። ታዲያ ይህ የአገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች ግሽበት እንዴት ተከሰተ ብለን ስንጠይቅ የፖለቲካ ፓርቲ ንግድ ውስጥ ገብተን እንደሆነ ያሳያል።

በሌላ በኩል አብዛኞቹ የፖለቲካ ድርጅቶች ህዝባዊ መሰረት አላቸው ወይ የሚለውም አጠያያቂ ነው። ለዚህ ሰሞኑን የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ያወጣውን የመመዝገቢያ መስፈርት ተከትሎ የተነሳው ውዝግብ ማሳያ ነው። በዚህ የምርጫ ቦርድ መነሻ ጥናት ላይ አንድ ፓርቲ

 አገራዊ ፓርቲ ሆኖ ለመመዝገብ አስር ሺህ ፊርማ እንዲሁም ለክልላዊ ፓርቲ አራት ሺህ ፊርማ ያሰባስባል የሚለው ምን ያህል አንዳንድ ፖርቲዎችን እንዳስቆጣ ስናስብ አንዳንዶቹ የቤተሰብ አባላቸውን እንጂ ህዝብን አስበው እንዳላቋቋሙት ያሳብቅባቸዋል።

በሌላ በኩል ለስም ብቻ የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ ፓርቲዎች ለአገርና ለህዝቦች እድገት ትልቅ አስተዋፅኦ ሊያበረክቱ የሚችሉና ትክክለኛ የህዝብ ጥያቄን ይዘው የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎችንም ሞራልና ክብር ዝቅ የሚያደርግ ነው።

በሚሊዮን የሚቆጠር የህዝብ ድጋፍ ያላቸውና ለህዝባቸው ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ለአመታት የታገሉ ፓርቲዎች በየመንደሩ በጥቂት ደጋፊዎችና ቡድኖች ተፈጥረውና የጠራ አላማ ሳይኖራቸው እንታገላለን ከሚሉ የስም ፓርቲዎች ጋር እኩል በአንድ መድረክ መሰለፋቸውም የሞራል ጥያቄን ያስነሳል።

ከዚህም ባሻገር ፓርቲን የገንዘብ ማግኛና መተዳደሪያ ያደረጉ አካላት መኖራቸው የፓርቲዎች ህልውና ላይ የራሱን አሉታዊ አሻራ ያሳርፋል። አንዳንድ ፓርቲዎች ለህዝብ ታግለው ለውጥ ከማምጣት ይልቅ ከመንግስትና ከጥቂት ደጋፊዎቻቸው በሚሰፈርላቸው ቀለብ ህልውናቸውን ለማቆየት ይጥራሉ። ይህ ደግሞ ለህዝብ ተገቢውን አስተዋፅኦ ከማድረግ ይልቅ አደርባይ እንዲሆኑ እንዲሁም ለመንግስትና ድጎማ ለሚያደርግላቸው አካል ተገዢ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ የሚፈልገው ሰላምና ብልፅግናን ነው። ህዝባችን ለዘመናት ወደኋላ ያስቀረውና በአለም ማህበረሰብ ዘንድ ጭምር መዘባበቻ ያደረገው ድህነትና ኋላቀርነት ተወግዶ እንደበለፀጉት አገራት የተሻለ ኑሮ መኖርን ይመኛል። ለዚህ ደግሞ አስተማማኝ ሰላምን የሚያረጋጥለት፣ በእኩልነትና በፍትሃዊነት የሚያስተዳድረው፤ለዚህምየተሻለ ፖሊሲና ስትራቴጂ ቀርጾ የሚሰራለትን የፖለቲካ ድርጅትናመሪ ይፈልጋል።

በመሆኑም አሁን ያሉት የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆኑ መሪዎቻቸው ደጋግመው ሊያስቡበትና ከፓርቲ ህልውና ይልቅ የሃገር ህልውናና እድገት ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ መረዳት አለባቸው። ከሚመሩት ፓርቲ ይልቅ የአገር ህልውና እንደሚበልጥም ሊገነዘቡ ይገባል።

አሁን እንደሚታየው አንዳንድ የፓርቲ አመራሮች የፓርቲ ቁጥር ሲያንስ ወይም ጥምረት ሲፈጠር የመሪነት ሚናዬን አጣለሁ ከሚል መንፈስ ወጥተው መሪም ሳይሆኑ ለአገራቸው ጠቃሚ ስራ መስራት እንደሚችሉ ሊገነዘቡ ይገባል።ለዚህ ደግሞ ፓርቲዎቻችን ከልዩነት ይልቅ በጋራ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በመስጠት ለጋራ እድገትና ብልፅግና መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል። ይህ ሲሆን ህዝቡም የሚበጀውን ለመለየት አይቸገርም፤ የአገር ሃብትም አይባክንም፤ የምንፈልገው እድገትም ይከተላል።

 አዲስ ዘመን ነሃሴ 6/2011