“ሥመ-ጥር”ን ፍለጋ

17

አንዳንድ ጊዜ የሚያጋጥሙን የሀሳብ ትግሎች የቃላት ጨዋታ ሊመስሉን ይችላሉ። ለምሳሌ “አዋቂ” እና “ታዋቂ”ን እንኳን ብንወስድ ሁለቱን አንድ አድርገን የምንወስድበት አጋጣሚ ሰፊ ነው። የእኛ አንድ አድርጎ መውሰድ ብዙም ላያወዛግብ ይችላልና እዳው ገብስ ነው። ሁለቱን ለያይቶ፤ ምናልባትም በፀጉር ቅጥነት ደረጃ ሰነጣጥቆ የሚያያቸው የመጣ ጊዜ ግን ስህተታችን ወለል ብሎ ይታያል። ምክንያቱ ደግሞ ሁለቱ የተለያዩ ስለሆኑ ነው።

“ሥመ-ጥር”ን በርእሰ-ጉዳይነት ይዘን ስንመጣ ያለ ምክንያት አይደለም። ከበቂ በላይ ምክንያት አለን። እንደውም ምክንያታችን ማህበረሰብ አቀፍ፤ ፍትህንና ርትእን አካታች ነው።

ሰኔ 8 ቀን 2011 ዓ.ም በኢንተር ኮንቲኔንታል አዲስ ሆቴል በ“ፍትህ አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ” ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ለመምከር ይቻል ዘንድ የውይይት መድረክ ተዘጋጅቶ ነበር። በመድረኩም ላይ የተዘጋጀውን ረቂቅ ሰነድ አስመልክቶ ሰፊ ውይይት የተካሄደ ሲሆን፤ ውይይት ከተደረገባቸው፣ የተለያዩ ሀሳቦች ከተንሸራሸሩባቸው ምእራፎች አንዱ ምእራፍ ሁለት ሲሆን “የዳኝነት አስተዳደር ጉባኤ ስለማቋቋም” በሚለው ርእስ ስር በተራ ቁጥር 7 “የጉባኤው አባላት” (ፊደል ተራ “ተ”) ስር የሰፈረውና “በዚህ አዋጅ አንቀፅ 2፣ ንኡስ አንቀፅ 13 እና ጉባኤው በሚያወጣው መስፈርት መሰረት በጉባኤው ጠቅላላ ስብሰባ የሚመረጡ ሁለት ሥመ-ጥር ግለሰቦች” የሚል አለ። እዚህ ጋር ነው እንግዲህ እንደሌሎቹ ሁሉ “ሥመ- ጥር”ም ያወያየው፤ ያነጋገረው።

“ሥመ-ጥር” ማን ነው፣ እንዴትስ ይለያል፣ ይመረጣል፤ ምን ምን ተግባራትን ያከናወነ ነው “ሥመ-ጥር” ሰው፣ የተላበሰው ባህርይስ እና የመሳሰሉት ሀሳቦች ተነስተው አወያይተዋል። እኛም ጉዳዩ የተነሳበትን አውድ ትተን፣ “ሥመ- ጥር”ን ወስደን ከማህበረ-ባህላዊ እሴት አንፃር እንመልከተው። ከዛ በፊት ግን አንድ ነገር እንበል።

በውይይቱ በ“ሥመ-ጥር” ላይ ሲነሱ የነበሩ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ማብራሪያ ያገኙ ዘንድ ጉዟቸውን ወደ መድረኩ አቀኑ። ማብራሪያም ተሰጠባቸው። ከማብራሪያዎቹም አንዱ የህግ ባለሙያና የዳኝነት ስርአት ማሻሻያ አማካሪ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ አሸናፊ አየለ የሰጡት ሲሆን እንዲህም ይላል።

“እርግጥ ስመ-ጥር ሰው ማግኘት ከባድ ነው። በጣም ከባድ ነው። በአንድ የኦሞና ከረሜላ ማስታወቂያ ‘ታዋቂ’ መሆን ይቻላል። ‘ሥመ- ጥር’ መሆን ግን እንደዚህ ቀላል አይደለም። አንድ አገር ደግሞ የሚያስፈልጋት (ከህግ አኳያ ማለታቸው ነው) ‘ሥመ-ጥር’ ሰው ነው። በሰለጠነው ዓለም ቢሆን የ‘ስመ-ጥር ማህበር’ አለ። ‘ሥመ-ጥር’ ሰው ሲያስፈልግ ጥያቄው ለዛ ማህበር ይቀርብና ከበርካታ ‘ሥመ-ጥር’ ሰዎች መሀል የበለጠ ሥመ-ጥር የሆነው ይወሰዳል። እኛ ገና ለዛ አልደረስንም።” አዎ፤ ገና አልደረስንም።

ከላይ እንዳልነው አሁን “ሥመ-ጥር”ን ከፍትህ አውዱ ነጥለን ወደ ራሳችን እንውሰደውና እንጨዋወት።

ዛሬ ዛሬ ግራ የሚያጋቡት ሰዎች ብቻ አይደሉም፤ በሰዎች ላይ ያደሩ ቃላትም ጭምር እንጂ። ጉዳዩን ችላ ብለው ካዩት ለክርክር የሚበቃ አይመስልም። ግን በየመድረኩ፣ ጋዜጣና መፅሄቱ፤ አሁን አሁን ደግሞ በመፃህፍት ሲያምስና ሲያተራምስ ነው ውሎ የሚያድረው። “አርቲስት”፣ “ምሁር”፣ “አዋቂ”፣ “ታዋቂ” እና የመሳሰሉ ማንነት ገላጭ ቃላት የትርምሱና ጭቅጭቁ ሰለባዎች ከሆኑ ሰነባብቷል።

የአንዱ “ስመ-ጥር” ለዛኛው “ዲያብሎስ”፤ ላንዱ “ምሁር” የሆነው ሌላው ጋር ሲደርስ “ፊደላዊ” ሆኖ ቁጭ ይላል። አንዱ “አዋቂ” ሲል ያነገሰውን ያኛው ይነሳና “አለቅላቂ” ብሎት እንደ ቲማቲም አውርዶ ያፈርጠዋል። ያኛው “አርቲስት” ሲል ያንቆለጳጰሰውን ጓደኛው ይመጣና “አዝማሪ” መሆኑን ያብራራለታል። (እንዲህ እንዲህ እያለ ነው እንግዲህ በመዲናችን ያለው ውሎና አዳር። የ“ስመ-ጥር ማህበር” ቢኖረን ይህንንም ሊፈታው ይችል ይሆናል እኮ።)

ከሁሉም የሚያስደነግጠው ግለሰባዊ መሿሿምና መሻሻሩ አይደለም። ከሁሉም የሚያስፈራው የጅምላው ነው። ምን ምሁር አለና፤ ምን ሰው አለና፤ ምን አዋቂ አለና . . . (ይህ እውነት ከሆነ ከሰፈር አልፎ አገር ይረብሻል።) ግን አለ? ግን የለም? የብዙዎችም ጥያቄ ይሄ ነው። ከሚጢጢየው ድምፅ፤ “አሉ” ከሚሉት እንጀምር።

ኢትዮጵያ የጀግኖች አገር ነች፣ ስንትና ስንት ላገር የሰራ፣ ስንትና ስንት መፃህፍት የደረሰ፣ ለህዝቡ መብትና ነፃነት የሚታገል፣ ስንት ያደባባይ ምሁር፤ ስንትና ስንት ለደሀ የሚያዝኑ፣ ለተራበ የሚያበሉ፣ ለተጠማ የሚያጠጡ እያለ ይቀጥላል።

“የሉም” ባዮች በበኩላቸው፤ ዘንድሮ ምን ምሁር አለ ሁሉ ጓዙን ጠቅሎ የዘር ከረጢት ውስጥ ተወሽቆ፤ ድንቄም አዋቂ – ምን አዋቂ አለ ሁሉ በሆዱ ተሰንጎ፣ ምን ሰው አለ ያለው በሙሉ የፌስቡክ መንጋ ብቻ ነው፤ አሁን ምን ሰው አለ? ቢዘፍኑ የነ ጥላሁንን፣ ሰው ቢኖር መች አገር እንዲህ ይታመስ ነበር፣ ከ“እኔ” ውጪ “እኛ” የሚል በሌለበት አገር ደሞ የምን “ሥመ- ጥር”? እዚህ አገር ሰው ቢኖር ነው 137 ፓርቲ የተቀፈቀፈው? ኧረ በባንዲራው ተውኝ ያሉም እንዳሉ ይሰማል።

ተወደደም ተጠላ፤ አገር ሁሉንም አቅፋ መያዟ እርግጥ ነው። ይሁን እንጂ ቅኖችን፣ ደጎችን፣ አስተዋዮችን፣ ሀይ ባይ ያገር ሽማግሌዎችን፣ ዋሽተው የሚያጣሉትን ሳይሆን ዋሽተው የሚያስታርቁትን፣ ጀግኖችን አጥብቃ ትሻለች። ወግ ጠባቂ፣ ባህል አክባሪ ትውልድን ከልቧ ትሻለች። ያኔ፤ ሥመ-ጥር ሰው ብቻ አይደለም ስመ-ጥር ትውልድም ይፈጠራል። የባለ ቅኔው ዮፍታሄ ንጉሴ የተራበ አይንም ይጠግባል።

ኧረ የሰው ያለህ፣ ኧረ የሰው የሰው፤

አይኔን ሰው እራበው አይኔን ሰው ሰው።

አዲስ ዘመን ነሃሴ 6/2011

ግርማ መንግስቴ