መቋጫ ያጣው የፓርቲዎች ውልደት

55

በመጪው ዓመት የሚካሄደው ስድስተኛ ዙር አገር አቀፍ ምርጫ ፍትሀዊና ነፃ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ራሱን እንደገና በማደራጀት እየሰራ መሆኑን እየገለፀ ነው። በሌላ በኩል ጠንካራ ፓርቲ ሆኖ ለመውጣት ተመሳሳይ ፕሮግራም ያላቸው ፓርቲዎች ውህደት እየፈጠሩ ቢሆንም አሁንም የፓርቲዎች ቁጥር እየቀነሰ ከመምጣት ይልቅ እየጨመረ ይገኛል። በ2011 ዓ.ም በግንቦት ወር 107 የነበሩ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ቁጥር አሁን ላይ 137 እንደደረሰ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ አድርጓል።

ቀደም ሲል የፓርቲዎች ቁጥር በየጊዜው መጨመር ያሳሰባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድም የፖለቲካ ፓርቲዎች የቃል ኪዳን ሰነድ የፊርማ ሥነ ሥርዓት ላይ ተመሳሳይ ፕሮግራም ያላቸው ፓርቲዎች ወደ አንድ ሰብሰብ እንዲሉ ጥሪ ማቅረባቸው የሚታወስ ነው። ፓርቲዎቹ ከአምስት ያልበለጡ ቢሆኑ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ምቹ እንደሚሆን ገልጸው ነበር።

ይህንን ጥሪ ተከትሎ አብሮ ለመሥራት ያስችለናል ካሉት የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት አድርገው ራሳቸውን አክስመው አንድ ፓርቲ የፈጠሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ። ለምሳሌ ሰማያዊ፣ ኢዴፓና አርበኞች ግንቦት ሰባትን ጨምሮ ስድስት ፓርቲዎች ራስን በማክሰም ተዋህደዋል። ሆኖም የምርጫ ጊዜው እየተቃረበ በሄደ ቁጥር የተወሰኑት ፓርቲዎች ቢሰባሰቡም አሁንም የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥር ከመቀነስ ይልቅ እየጨመረ መጥቷል።

በአሁኑ ጊዜ ያሉት ብዛት ያላቸው ፓርቲዎች ተሰባስበው አልያም ከስመው አራት ወይም አምስት ጠንካራ ፓርቲዎች እንዲሆኑ ሶስት ችግሮች መፈታት አለባቸው የሚሉት ደግሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ናቸው። አንደኛው ገዥው ፓርቲ ህገ ወጥ በሆነ መልኩ ፓርቲዎችን የመቀለቡ ስራ ሲያቆም ነው ይላሉ።

ለምሳሌ በአገር ውስጥ ያሉት አብዛኛዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገዥው ፓርቲ በተለያየ መንገድ የሚቀልባቸው፣ የፈጠራቸው፣ ያሳደጋቸውና ከእናት ፓርቲያቸው የነጠላቸው ናቸው። በመሆኑም ገዥው ፓርቲ ህገ ወጥ በሆነ መንገድ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲከፋፈሉ የሚሰራውን ድርጊት ሲያቆም እየተሰፈረላቸው የነበሩና የህዝብ ተቀባይነት የሌላቸው ፓርቲዎች ህልውናቸው አብሮ ያከትማል ባይ ናቸው። ምክንያቱም የኢህአዴግ ድጋፍ ከቆመ፣ የህዝብ ድጋፍና በቂ ፋይናንስ ከሌላቸው በፖለቲካው መድረክ የሚቆዩበት ምክንያት አይኖርም። ስለዚህ እነዚህ ፓርቲዎች ወደ ገዥው ፓርቲ ይጠቃለላሉ ወይም ከጨዋታ ውጭ ይሆናሉ።

ቀደም ሲል የነበረው የምርጫ ቦርድ የኢህአዴግ መጫዎቻ በመሆኑ የ1997 ምርጫ ተከትሎ ቅንጅትና ኦፌኮ የሚባሉ ተቀጥያ ፓርቲዎችን ፈጥሮና ቀለባቸውንም ይሰፍርላቸው እንደነበር አውስተዋል። እናም ገዥው ፓርቲ ብዙ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ለማዳከም ብሎ የሚፈጥራቸው ፓርቲዎች የፖለቲካ ፓርቲዎችን ቁጥር እንዲበራከት ማድረጉን ነው የተናገሩት። አሁን ግን ኢህአዴግ የቀደመ አሰራሩንና ለፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያደርገውን ድጋፍ አቆማለሁ ስላለ የኢህአዴግን ቀለብ ካላገኙ መኖር የማይችሉ ፓርቲዎች እንዳሉ አንስተዋል። ይህም የፓርቲዎችን ቁጥር ይቀንሳል የሚል እምነት አላቸው።

ሁለተኛ አንዳንድ ግለሰቦች ለራሳቸው ዝና ሲሉ የፈጠሯቸው ፓርቲዎች መኖራቸውን ዶክተር መረራ ያነሳሉ። እነዚህ ደግሞ የዲሞክራሲ ሜዳው ከሰፋ ይጠፋሉ ይላሉ። ለምሳሌ በአሜሪካን አገር ፓርቲዎች ነን ብለው የሰየሙ ብዙዎች ቢሆኑም በአሜሪካ ምርጫ ግን ሁሌም የሚፎካከሩት ዲሞክራቶችና ሪፐብሊካኖች መሆናቸውን በአብነት ይጠቅሳሉ። በኢትዮጵያ የመድብለ ፖርቲ ስርዓቱ ስር ሲሰድ ቢያንስ ሁለት፤ ቢበዛ ከአምስት ያልበለጡ ጠንካራ ፓርቲዎች እንደሚፈጠሩ ነው የገለፁት።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ረቂቅ- ህግ ላይ አንድ አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ ለመመስረት ቢያንስ አስር ሺህ እንዲሁም አንድ የክልል ፓርቲ ለመመስረት ደግሞ ቢያንስ አራት ሺህ አባላት እንደሚያስፈልጉ ሰፍሯል። ይህ አንቀፅ በራሱ የግለሰቦች ፓርቲዎችን ህልውና እንዳይኖራቸው በማድረግ የፓርቲዎች ቁጥር ሊቀንስ ይችላል የሚል ሀሳብ አላቸው።

‹‹ብዙም የፖሊሲ ልዩነት ሳይኖራቸው ተለያይተው ያሉ ፓርቲዎችም በጊዜ ከሚመስላቸው ጋር ይደባለቃሉ፤ አለበለዚያ በሂደት ራሳቸው ከፖለቲካው ሜዳ እየከሰሙ ይሄዳሉ፤ አልያም ህዝቡ ያስወጣቸዋል። በአንጻሩ አቅምና የተሻለ የህዝብ ድጋፍ ያላቸው ፓርቲዎች ተጠናክረው ይወጣሉ።

በየትኛውም አገር ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተፈጠሩት ሰፊ የህዝብ ድጋፍና የተሻለ ፖሊሲ ያላቸው ናቸው፤ እነዚህ ፓርቲዎች ምርጫው እየተቃረበ ሲሄድ በግንባርም ሆነ በሁደት የተወሰኑ ጠንካራ ፓርቲዎችን ይፈጥራሉ›› የሚል ሀሳብ አላቸው ፕሮፌሰር መረራ።

በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ብዛት ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ለብቻቸው መሮጡ የትም እንደማያደርሳቸው ሲረዱት አንድ መሆናቸው እንደማይቀር ፕሮፌሰር መረራ ይገልፃሉ። ምክንያቱም ገዥው ፓርቲ የዲሞክራሲ ሜዳውን ካሰፋና የህዝብ መሰረት የሌላቸው ፓርቲዎች መቀለቡን ካቆመ፤ ህዝቡም አላስፈላጊ የሆኑትን ፓርቲዎች ጡረታ እያስወጣ፣ አስፈላጊ የሚላቸውን ያጠናክራል። እናም በመጪው የምርጫ ዘመን የህዝብ ድጋፍ የሌላቸው ፓርቲዎች ከፖለቲካ ሜዳው ሲገለሉ በአንጻሩ የተወሰነ ቁጥር ያላቸው ጠንካራ ፓርቲዎች ይፈጠራሉ የሚል እምነት አላቸው።

ፕሮፌሰር መረራ እንደገለፁት፤ ሶስተኛ የብሄር ፖለቲካ ለፓርቲዎች ቁጥር መበራከት አስተዋፅኦ የለውም ባይባልም ችግሩ የመጣው ከታሪካችን ነው። በኢትዮጵያ የብሄር ጥያቄ ካልተመለሰ በስተቀር በአዋጅ አይፈታም። አሁንም ቢሆን የህዝብ ድጋፍ ያላቸው ፓርቲዎች ይህን ጥያቄ አንግበው ታግለዋል። ሆኖም የብሄር ጥያቄው እየተፈታ ሲሄድና የዜግነት መብት ደረጃ ሲደርስ የብሄር ፓርቲዎች እየከሰሙ የሚሄዱ ይሆናል።

አሁን ባለሁ ሁኔታ ግን የማንነት ፖለቲካ ከሌለ አገር ትናወጣለች የሚሉ ወገኖች ሲኖሩ በሌላ በኩል ደግሞ የዜግነት ፖለቲካ ብቻ ስራ ላይ ካልዋለ ኢትዮጵያ ትጠፋለች የሚሉ አሉ። የዜግነትና የብሄር መብቶች እንዲከበሩ ተባብረን ስራዎችን እየሰራን ከሄድን፤ ጨዋታውም ዲሞክራሲያዊ ከሆነ ብዙ ነገሮች መልክ እየያዙ ይሄዳሉ የሚል አስተያየት እንዳላቸው ገልጸውልናል።

ስለዚህ መንግስት የፖለቲካ ሜዳውን ካስተካከለው ፓርቲዎቹ ወደዱም ጠሉም በውይይት ወደ አንድ ይመጣሉ። ህዝቡ የተሻለ ፖሊሲ አላቸው፣ በእውነተኛ መንገድ ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ይታገላሉ፣ በተሻለ መልኩ ያስተዳድሩኛል የሚላቸውን አንጥሮ ያወጣል።

በአስራኤል ከ30 በላይ ፓርቲዎች ቢኖሩም የሚመረጡትና ጠንካራ የሚባሉት ከሶስት የማይበልጡና ፓርቲዎቹም ዓላማ ያላቸውና የሚሰሩትን የሚያውቁ መሆናቸውን በአብነት ጠቅሰዋል። በአንጻሩ በኢትዮጵያ ግን የተወሰኑ ፓርቲዎች የሚመሰረቱት የግለሰቦችን ዝና ለማግዘፍና ከገዥው ፓርቲ የሚገኘውን ድጎማ ለመጠቀም ተብሎ መሆኑን ነው የሚናገሩት።

በኢትዮጵያ ህይወት ካላቸው ፓርቲዎች ይልቅ ህይወት የሌላቸው ፓርቲዎች ብዙ ናቸው፤ እናም ፓርቲዎች የቤት ስራዎቻቸውን ከወዲሁ መስራት ካልቻሉ ከሜዳው እየወጡ ይሄዳሉ። ዋናው ጉዳይ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያድጉበት፣ የሚያብቡበት፣ በነጻ ሜዳ የሚወዳደሩበት፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ይሁንታ ሲሰጣቸው ስልጣን ላይ የሚወጡበት፣ ድጋፉን ሲነሳቸው ደግሞ ከስልጣን የሚወርዱበትን ምህዳር መፍጠር ነው።

ይህ ከሆነ ጠንካራ ፓርቲዎች የማይፈጠሩበት ምክንያት አለመኖሩን ነው ፕሮፌሰር መረራ የሚያብራሩት። የፓርቲዎች ቁጥር መበራከት ጊዜያዊ ችግር ነው ያሉት ፕሮፌሰር መረራ መንግስት እንደጀመረው የፖለቲካ ምህዳሩን የማስፋት ስራ ከተጠናከረና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ከተገነባ ህዝባዊ ድጋፍና ተቀባይነት የሌላቸው ፓርቲዎች ከመጪው ምርጫ በኋላ አይቆዩም ይላሉ። ለምሳሌ በአሜሪካን አገር ብዙ ፓርቲዎች ቢኖሩም በምርጫ ጠንካራ ፉክክር የሚያደርጉትና የሚያሸንፉት ሁለቱ ፓርቲዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ፕሮፌሰር መረራ እንዳሉት በአገሪቱ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለመፍጠር፣ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲካሄድና ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር በኃላፊነት መንፈስ ከሰሩ ከጊዜያዊ ችግራቸው በራሳቸው ወይም በህዝብ ግፊት እየተስተካከሉ ይመጣሉ።

የቀድሞው የግንቦት ሰባት የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ኤፍሬም ማዲቦ በበኩላቸው እንደገለጹት በኢትዮጵያ ሰዎች በፓርቲ ውስጥ መደራጀትን የሚያገናኙት ከኢኮኖሚ ጥቅም ጋር ነው። ይህ ደግሞ ባለፉት 27 ዓመታት ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ ተለጣፊ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በመደራጀታቸው የገንዘብ ጥቅም ሲያገኙ የነበሩ ናቸው።

ይህንን ያዩ ሰዎች የፖለቲካ ፓርቲ ሲያደራጁ የሚገኘውን ጥቅም በማሰብ እንደሆነ መገመት አይከብድም። አሁንም የፓርቲዎች ቁጥር መብዛት ከዚህ ጥቅም ጋር የሚያያዝ ነው። ለምሳሌ በቅርቡ እንኳ ከምርጫ ቦርድ ጋር የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚያደርጉት ድርድር ላይ የውሎ አበል ስጡን ብለው መንግስትን የጠየቁ የፖለቲካ ፓርቲዎች መኖራቸው ምን ያህል ለጥቅም የቆሙ እንደሆነ አንዱ ማሳያ ነው ።

የፖለቲካ ፓርቲ በየትኛውም አገር ውስጥ ሲመሰረት በህዝብ ድጋፍና በአባላት መዋጮ ነው የሚደራጀው። የፓርቲውን ወጪ የሚሸፍነው ፓርቲው ከህዝብ በሚያገኘው ድጋፍ እንጂ በመንግስት አይደለም። በተቃራኒው በኢትዮጵያ ውስጥ ግን መንግስት ሲሸፍንላቸው መቆየቱን ነው ያወሱት።

በዚህ ምክንያትም ለጥቅም ብለው ብቻ ብዙ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲደራጁ አድርጓል። በዚህ ምክንያት የፓርቲዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ መንግስት ለፖለቲካ ፓርቲዎች ጸህፈት ቤት ለመስጠት እንኳን አስቸጋሪ ሆኖበታል ሲሉ አቶ ኤፍሬም ገልጸዋል።

ሌላው ‹‹ለፓርቲዎች ቁጥር መጨመር የብሄር ፖለቲካ አስተዋፅኦ እንዳደረገም አቶ ኤፍሬም ያነሳሉ። እያንዳንዱ ብሄር የእኔን ጥቅም የሚያስጠብቀው በብሄር የተደራጀው ነው በሚል ሁሉም በየዘውጉ እንዲደራጅ ምክንያት ሁኗል። “እናም” አሉ አቶ ኤፍሬም “በኢትዮጵያ ውስጥ የፓርቲዎችን ያለ ልክ ቁጥር እንዲጨምር ያደረጉት ጥቅምና የዘውግ ፖለቲካ ናቸው”።

በመጪው ዓመት ምርጫ የኢትዮጵያ ህዝብ ወደሚፈልገው አድማስ የሚወስደውን መሪ ነጻና ፍትሀዊ ሆኖ መምረጥ ቢኖርበትም የፓርቲዎች መብዛት ለድምፅ ሰጪው ማነው የሚሻለኝ የሚለውን ለመምረጥ ውዥንብር ውስጥ እንዲገባ ያደርገዋል የሚሉት አቶ ኤፍሬም ለምሳሌ 100 ፓርቲ በመጪው ምርጫ ቢወዳደሩ ፓርቲዎች በመከፋፈላቸውና ድምጻቸው በመበታተኑ ምክንያት ብቻ ኢህአዴግ ተመልሶ ስልጣን ላይ እንዲመጣ ሊያደርግ ይችላል የሚል እምነት አላቸው።

የፖለቲካ ፓርቲዎችን አትደራጁ ብሎ በህግ መከልከል ባይቻልም አንድ ፓርቲ ተደራጅቶ የፖለቲካ ስልጣን እፈልጋለሁ ሲል ማሟላት ያለባቸውን መስፈርቶች በእርግጥ መሟላቱን ማረጋገጥ ግን ተገቢ እንደሆነ አቶ ኤፍሬም ይገልፃሉ። ለምሳሌ በቅርቡ አገር አቀፍ ፓርቲዎች ከ10 ሺ በላይ ፊርማ ማሰባሰብ አለባቸው የሚለውን አዲሱ የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ረቂቅ ህግ ተቃውመው የወጡ ሰዎች እንዳሉ ሰምተናል።

ከ100 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ባላት አገር ይህ በጣም አነስተኛ ቁጥር ነው። ይህ ሲጸድቅ የምርጫ ቦርድ ፖለቲካ ፓርቲዎች የድጋፍ ፊርማ ማስፈረማቸውንና ፊርማው ከሁሉም አገሪቱ አካባቢ መሰብሰቡና ትክክለኛ መሆኑ መጣራት አለበት የሚል እምነት አላቸው።

ሌላው ምርጫውን ተከትሎ ከአውሮፓ፣ ከአሜሪካና ከሌሎች ዓለም አቀፍ የሚሰጥ የገንዘብ ድጋፍ ወደ መንግስት ካዝና ከገባ በኋላ የህዝብ ፋይናንስ ነው። ነገር ግን የህዝብን ገንዘብ አንድ ፓርቲ አገኛለሁ ብሎ ለምርጫ መወዳዳር ከፈለገ 540 ወረዳዎች ውስጥ በአንድ ሶስተኛው መወዳዳር መቻሉ መረጋገጥ አለበት።

ይህን ካላደረገ የህዝብ ገንዘብ ሊሰጠው አይገባም የሚል እምነት አላቸው። በክልልም የሚወዳደሩ ፓርቲዎች በተመሳሳይ በክልሉ ባሉ ወረዳዎች ተሰልቶ በአንድ ሶስተኛ መወዳደራቸው ተረጋግጦ መሆን ይኖርበታል። እነዚህ አይነት ተቋማዊ አሰራሮች የፓርቲዎችን ቁጥር ዕድገት ውስን የሚያደርገው መሆኑን አስተያየታቸው ሰጥተውናል።

“ለምሳሌ” አሉ አቶ ኤፍሬም “አሜሪካ ውስጥ አንድ ፓርቲ በፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እወዳደራለው ሲል ስሙ የምርጫ ወረቀት ላይ እንዲጻፍ በእያንዳንዱ ግዛት ይህን ያህል ፈርማ ማሰባሰብ አለብህ ይባላል፣ ይህን ቁጥር ካላሰባሰበ እንኳን የህዝብ ገንዘብ ሊሰጠው ቀርቶ ስሙ የምርጫ ወረቀት ላይ ሊጻፍለት አይችልም” ሲሉ በአብነት ጠቅሰዋል።

‹‹እኛም አገር እንደዚህ መሆን አለበት እንጂ የቤተሰብ ፓርቲ ማለትም አባት ፕሬዚዳንት እናት ገንዘብ ያዥ፣ ወንድም የህዝብ ግኙነት ሀላፊ የሆነበት ፓርቲ ይዘን የትም አንደርስም። የፓርቲ ስርዓታችንን ስንገነባ የሚኖሩትና የሚፈጠሩት ፓርቲዎች ትርጉም ያላቸውና ሰፊ የህዝብ መሰረት ያላቸው ይሆናሉ።

ስለዚህ ባለፉት 27 ዓመታት የነበሩት በመንግስት መኪና የሚቀሰቅሱ፣ ገንዘብ የሚሰጣቸው፣ አበል የሚያገኙ ፓርቲዎች መቅረት አለባቸው። ምክንያቱም ሌላ አገር ህዝብ ለፓርቲዎች ያዋጣውን ገንዘብ ለግል ጉዳዩ የተጠቀመ የፓርቲ አመራርና የምርጫ ተወዳዳሪ የሚከሰስበትና እስር ቤት የሚወሰድበት ዓለም ውስጥ ነው ያለነው። እነዚህ ህጋዊ ስርዓቶች ቀስ በቀስ ኢትዮጵያ ውስጥ መተግበር አላባቸው ሲሉ ምክረ ሀሳባቸውን ሰጥተውናል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ አሸን መብዛት ጥቅም የለውም የሚሉት በወለጋ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር የሆኑት ዶክተር አለሙ ዋቅጋሪ የአገሪቱን የፖለቲካ ሁኔታ ውስብስብ ከማድረግ ባለፈ ህዝብም ወደየትኛው ጎራ እንደሚሄድ ያደናግራል ባይ ናቸው።

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥር እየተበራከተ የመጣው በአመራር ጥማት፣ በሴራ ፖለቲካና ያለመተማመን ምክንያት ሊሆን ይችላል የሚሉት ዶክተር አለሙ በጥርጣሬ፣ ዓላማችን ላይሳካ ይችላልና የስልጣን ቦታችንን ልናጣ እንችላለን በሚል አስተሳሰብ ለፓርቲዎች መሰነጣጠቅም ሆነ ቁጥር መበራከት መንስኤ ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል።

እንደ ዶክተር ዓለሙ ገለፃ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለይ ደግሞ ተመሳሳይ ፕሮግራምና ርዕዮተ ዓለም ያላቸው ፓርቲዎች ጥምረት በመመስረት የፓርቲዎችን ቁጥር ውስን ማድረግ ያስፈልጋል። ጥምረት ሲያደርጉም ውሎችና መግባባቶች ሊኖሩ ይገባል። ለምሳሌ በኦሮሚያ ክልል ወደ 15 የሚጠጉ ፓርቲዎች አሉ።

እነዚህ ፓርቲዎች ውይይት አድርገው በመተማመን የጋራ ዓላማቸውን በተጠናከረ መልኩ ለማሳካት እየተጣመሩ ወደ ሁለት ቢመጡ የተሻለ ይሆናል። በሎሎችም ክልሎች ያሉ ፓርቲዎች እንደዚሁ ጥምረት እያደረጉ በአገር ደረጃ የፓርቲዎችን ቁጥር ውስን ማድረግ ይቻላል።

ሌላው የምርጫ ቦርድ ከፓርቲዎች ጋር ምክክር አድርጎ ህዝባዊ መሰረት የሌላቸውን የይስሙላ ፓርቲዎች እንዳይፈጠሩ የሚያደርግ ማዕቀፍ በማዘጋጀት ተገቢውን ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ ይኖርበታል። የብሄር ተኮር የፖለቲካ ፓርቲዎችን ማስቀረት አሁን ባለው የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ የሚከብድ ነው የሚሉት ዶክተር አለሙ ምክንያቱም በህገ መንግስቱ የተቀመጠ መብት ነው።

ብሄር ብሄረሰቦች የራሳቸውን መብት መወሰን እንዳለባቸው ህገ- መንግስቱ ያስቀምጣል። ሆኖም እንደ መድረክ ከስሩ በብሄር የተደራጁና ህብረ ብሄራዊ የሆኑ አራት የፖለቲካ ፓርቲዎች በስሩ እንዳጣመረው ሁሉ ሌሎች ፓርቲዎችም የዚህን ፈለግ መከተል ይቻላል የሚል እምነት አላቸው።

በመነታረክ፣ በመጠላላት፣ አገር አይገነባም። እናም የፖለቲካ ፓርቲዎችን እንዲበራከቱ ያደረገው የፌደራል ስርዓቱና ህገ መንግስቱ ነው እያሉ ከማራገብና ቃላት ከመወራወር ይልቅ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን መብታቸው ሊከበር፣ በእኩልነት ሊጠቀሙና የትም አካባቢ ሄደው መስራት በሚችሉበት መልኩ በጠረጵዛ ዙሪያ ውይይት በማድረግና በመተማመን ነገሮችን ማስተካከል ይቻላል የሚል ምክረ ሀሳብ አላቸው።

‹‹እንኳን ኢትዮጵያዊያን የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው ሰዎች በኢትዮጵያ ይኖራል። በአንጻሩ ኢትዮጵያዊያንም በተለያዩ የውጭ አገራት ሄደው እየኖሩ ናቸው። ስለዚህ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የሚጠቀምበትን መንገድ ከተለምን፣ ከተወያየን፣ ከተሳሰብን፣ አንዱ ሌላውን መረዳት ከቻለ የፓርቲዎች ቁጥር መብዛት ችግርም ሆነ የአገሪቱ ችግሮች በቀላሉ ይፈታሉ የሚል እምነት አለኝ ብለዋል ዶክተር አለሙ።

በ1997 ዓ.ም አገር ዓቀፍ ምርጫ ለመወዳደር በህጋዊነት ከተመዘገቡ 84 የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ በምርጫው የተወዳደሩት 36ቱ ናቸው። ከእነዚህም ከፍተኛ የህዝብ ድጋፍ አግኝተው የነበሩት ኢህአዴግ፣ ቅንጅትና ህብረት መሆናቸውን መረጃዎች ያስረዳሉ።

ከእነዚህ ፓርቲዎች በተለይም ቅንጅት በምርጫው መቃረቢያ ወቅት መኢአድ፣ ኢዴፓ፣ ቀስተ ደመናንና ኢዴሊ የተሰኙ ፓርቲዎችን በማቀፍ ቅንጅት በመፍጠር በምርጫ በመወዳደር የተሻለ የህዝብ ድምፅ ለማግኘት ችሏል። ሂደቱም ጠንካራ ተፎካካሪ ፓርቲ ሆኖ ለመውጣትና የህዝቡን ይሁንታ ለማግኘት ወደ አንድ መሰባሰቡ ጠቃሚ መሆኑን አመላክቶ ያለፈ ምርጫም ተደርጎ ይወሰዳል።

ፓርቲዎቹ በራሳቸው ተነሳሽነትም ሆነ በህዝቡ አስገዳጅነት ወደ አንድ በመሰባሰብ የተወሰኑ ጠንካራ ፓርቲዎች ካልተፈጠሩ ለህዝቡ የተሻለ የሚለውን ፓርቲ ለመምረጥ ይቸገራል። ፓርቲዎቹም የተበጣጠሰ ድምፅ ከማግኘት ያለፈ ለአሸናፊነት አይበቁም። ጠንካራ ተፎካካሪ ፓርቲን ለማፍራት የሚደረገው ጥረት ፍሬ አያፈራም። ህዝቡም ጠንካራ አማራጭ ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎችን ለማየት አይታደልም።

አዲስ ዘመን ነሃሴ 6/2011

ጌትነት ምህረቴ