ኢትዮጵያዊያኑ በበርሊን ማራቶን የአሸናፊነት ግምት አግኝተዋል

9

በየዓመቱ መስከረም ወር የመጨረሻው እሁድ በሚካሄደው የበርሊን ማራቶን አራት ስመጥር ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ተሳታፊ እንደሚሆኑ ታውቋል። በአለም አቀፉ የአትሌቲ ክስ ፌዴሬሽ ኖች ማህበር የወርቅ ደረጃ የተሰጠው ይህ ውድድር፤ ቀዳሚ ከሆኑት ውድድሮች መካከል አንዱ ሲሆን በማራቶን የዓለም ክብረወሰን የሆነ ሰዓት የተመዘገበበትም ነው።

በዘንድሮው ውድድር ላይም ኢትዮጵያዊያኑ ጉዬ አዶላ፣ ልዑል ገብረስላሴ፣ ሲሳይ ለማ እና ብርሃኑ ለገሰ አሸናፊ ይሆናሉ በሚል ባለሙያዎች ቅድመ ግምታቸውን አስቀምጠዋል። ምክንያታቸው ደግሞ የሁሉም አትሌቶች የግል ፈጣን ሰዓት ከ2 ሰዓት ከ04 ደቂቃ በታች በመሆኑ ነው።

የዚህ ውድድር ዳይሬክተር የሆኑት ማርክ ሚልዴ «በወንዶቹ በኩል የተሻለ ብቃት እንደሚመዘገብ ተስፋ እናደርጋለን። በዚህ ውድድር ላይ የዓለም ክብረወሰን ይሰበራል ብለን ባንጠብቅም ፈጣን ሰዓት እንደሚመዘገብ እንጠብቃለን» ብለዋል። የጀርመኑ ታላቅ የአትሌቲክስ ውድድር ለአስር ዓመታት ያህል በኢትዮጵያዊያን ክብር የደመቀ ነበር።

አንጋፋው አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ እአአ ከ2006-2009 ለተከታታይ ዓመታት አሸናፊ ሲሆን፤ ሁለት የዓለም ክብረወሰኖችንም መስበር ችሏል። ከሁለት ዓመታት በፊት የቦታው አሸናፊ የነበረው ቀነኒሳ በቀለም ሁለተኛውን ፈጣን ሰዓት የግሉ ያደረገበት ስፍራ ነው።

በዚህ ውድድር ላይ ከሁለት ዓመታት በፊት ተሳትፎ ሁለተኛ ደረጃ ያስመዘገበው ጉዬ አዶላ የአሸናፊነት ተራውን ከኬንያዊያን የሚነጥቅበት ጊዜ አሁን መሆኑን ማህበሩ በድረገጹ ያስነብባል። በወቅቱ ጉዬ የገባበት ሰዓትም 2:03:46 የግሉ ፈጣን ሰኣት በመሆን ተመዝግቦለታል።

ጠንካራ አትሌት መሆኑ ሲጠቀስ፤ በዚህ ውድድር የዓለምን ክብረወሰን ያስመዘገበው ኬንያዊው ኢሉድ ኪፕቾጌን የሚያሰጋ ጭምር መሆኑም ነው ድረገጹ ያስነበበው። እአአ የ2014 የዓለም ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮኑ ጉዬ ለረጅም ጊዜ በጉዳት ላይ ቢቆይም አገግሞ ወደ ውድድር ተመልሷል። በመሆኑም ጥንካሬውንና በቦታው ያለውን ልምድ ተጠቅሞ አሸናፊ እንደሚሆን አዘጋጆቹ ተስፋ አድርገዋል።

በውድድሩ ከፍተኛ የአሸናፊነት ቅድመ ግምት ያገኘው ልኡል ገብረስላሴ፤ 2:04:02 ከአንድ ዓመት በፊት በአረብ ኤሜሬትስ ያስመዘገበው ሰዓት ነው። የ25 ዓመቱ ወጣት አትሌት በቫሌንሺያ ማራቶንም 2:04:31 የሆነ ሰዓት በማስመዝገብ የቦታው የክብረወሰን ባለቤት ነው።

ሲሳይ ለማ የውድድሩ ብርቱ ተፎካካሪ እንደሚሆን የሚጠበቀው ሌላኛው አትሌት ነው። በዱባይ ማራቶን ተሳትፎው አምስተኛ ደረጃን ያስመዝግብ እንጂ፤ ውድድሩን ያጠናቀቀበት 2:04:08 የሆነ ሰዓት ግን የግሉ ምርጥ ነው። በቬና እና ፍራንክፈርት ማራቶኖች አሸናፊ የሆነው የ28 ዓመቱ ሲሳይ፤ በበርሊን ማራቶን ተሳትፎ 2:06:56 ሰዓት በማስመዝገብ አራተኛ ሆኖ ነበር የጨረሰው። በመሆኑም አትሌቱ ልምዱን ተጠቅሞ ለአሸናፊነት ይበቃል የሚል ግምት አግኝቷል።

በዚህ ዓመት በተካሄደው አቦት ማራቶን አሸናፊ የሆነው የ24 ዓመቱ ብርሃኑ ለገሰ፤ የቶኪዮ ማራቶንን የገባበት 2:04:48 የሆነ ሰዓት የግሉ ፈጣን ነው። በዱባይ ማራቶን ተሳትፎውም ፈጣን ሰዓቱን በማሻሻል 2:04:15 ገብቷል። አትሌቱ በቺካጎ ማራቶን የተካፈለ ሲሆን፤ እአአ በ2015 በበርሊን የግማሽ ማራቶን አሸናፊ ነበር። ይህም አትሌቱ የሌሎች ውድድሮችንና በቦታው ያለውን ልምድ ተጠቅሞ ጥሩ ውጤት ያስመዘግባል በሚል እንዲጠበቅ አድርጎታል።

አዲስ ዘመን ነሃሴ 6/2011

ብርሃን ፈይሳ