ለመላ አፍሪካ ጨዋታዎች ቡድኖቹ ዝግጅት እያደረጉ ነው

17

በሞሮኮ ራባት የሚካሄደው 12ኛው የመላ አፍሪካ ጨዋታዎች ሊጀመር የአንድ ሳምንት ዕድሜ ብቻ ይቀረዋል። በዚህ ውድድር ላይ ኢትዮጵያ በ13 የስፖርት ዓይነቶች የምትሳተፍ ሲሆን፤ ብሄራዊ ቡድኖቹም ዝግጅታቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል። ጠንካራ ዝግጅት በማድረግ ላይ ከሚገኙት መካከልም የሜዳ ቴኒስ እና ጂምናስቲክስ ይጠቀሳሉ።

በሜዳ ቴኒስ ስፖርት ኢትዮጵያ በሶስት ሴት እና አራት ወንድ ስፖርተኞች ትወከላለች። ቡድኑ ውጤታማ ለመሆን ከሚያደርገው ልምምድ በተጓዳኝ በስፖርቱ ባለሙያዎች ሙያዊ ድጋፍ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ተሞክሮ እንዲያገኙ መደረጉንም የኢፌዲሪ ስፖርት ኮሚሽን በድረገጹ አስነብቧል።

በምስራቅ አፍሪካ በተካሄዱ ውድድሮች ጥሩ ውጤት ያለው ቡድኑ፤ ውጤታማነቱን በመላ አፍሪካ ጨዋታዎች ለመድገምም ዝግጅት እያደረጉ ይገኛሉ። ብሄራዊ ቡድኑን የሚመሩት አሰልጣኝ ህሩይ አምሳሉም ለቡድኑ አባላት እየተደረገላቸው ያለው ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ቴኒስ ፌዴሬሽ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይልማ ከፈለኝ፤ በዚህ ስፖርት የሚወክሉ ስፖርተኞች ፍትሐዊ በሆነ መልኩ መመልመላቸውን እና ለስልጠናው የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን በማሟላት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ይገልጻሉ። ፌዴሬሽኑ የሚስተዋልበትን የውድድር ቁጥር ማነስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ክፍተቱን በመለየት፤ በሀገርና ዓለም አቀፍ ውድድሮች እንዲሁም ስልጠናዎች ላይ በስፋት ለመሳተፍ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራም ጠቁመዋል።

የጂምናስቲክስ ብሄራዊ ቡድንም በውድድሩ ለመሳተፍ በቂ ዝግጅት ማድረጉን አስታውቋል። በአርቲስቲክ ጅምናስቲክስ የምትሳተፈው ኢትዮጵያ በአምስት ሴት እና አምስት ወንድ ስፖርተኞች ትወከላለች።

ፍሎር ኤክሰርሳይስ፣ ቮልቲግ ቴብል እና ቢም ባላንስ ሴቶች የሚወዳደሩባቸው የውድድር ዓይነቶች ናቸው። ወንዶች በበኩላቸው በፓራራል ባር፣ ፍሎር ኤክሰርሳይስ እና ቮልቲግ ቴብል ይሳተፋሉ።

የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ቢንያም ዓለሙ ዝግጅቱን አስመልክተው፤ ቀደም ብለው እንደጀመሩ ጠቁመዋል። በዚህ ወቅትም በሳምንት ለስድት ቀናት ለሁለት ጊዜያት ልምምድ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል። ሠልጣኞችም የሚሰጣቸውን ስልጠና የመቀበል አቅማቸው ከፍተኛ በመሆኑ በውድድሩ ብርቱ ፉክክር በማድረግ ውጤት ለማስመዝገብ በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን ጠቁመዋል። ከዚህ ባሻገር የልምምድ መሳሪያዎች ጊዜ ያለፈባቸውና ያረጁ በመሆናቸው በቀጣይ ዘመናዊ መሳሪያ ወደ ሀገር የሚገባበት ሁኔታ እንዲመቻች አሰልጣኙ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ጅምናስቲክስ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ስንታየሁ ፍቅረዮሐንስ በበኩላቸው፤ ለውድድሩ እየተደረገ ያለው ዝግጅት እና ከመንግስት እየተደረገ ያለው ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል። ጅምናስቲክስ ስፖርት የዘመናዊ ስፖርት መሠረት ቢሆንም ለስፖርቱ አገልግሎት የሚውሉ መሳሪያዎች በጣም ኋላቀር በመሆናቸው ተጠግነው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ። መሳሪያዎቹን ገዝቶ ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባትም በፌዴሬሽኑ አቅም የሚቻል ባለመሆኑ ጥያቄው ለመንግስት ቀርቦ በጎ ምላሽ ማግኘቱን ኃላፊዋ ገልጸዋል።

በሁለቱም ስፖርቶች ሃገራቸውን ለመወከል ዝግጅት በማድረግ ላይ የሚገኙት የብሄራዊ ቡድን አባላትም በሚካፈሉበት ውድድር የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እየተዘጋጁ መሆኑን ገልፀዋል።

አዲስ ዘመን ነሃሴ 6/2011

ብርሃን ፈይሳ