አፍሪካዊያን ተጫዋቾች በዘንድሮው ፕሪምየር ሊግ

11

ከአውሮፓ እና ከደቡብ አሜሪካ አህጉራት ቀጥሎ የተሻለ የእግር ኳስ ክህሎት ያላቸው ተጫዋቾች እንዳሏት ይነገራል፤ አፍሪካ። በአህጉሪቷ ከተንሰራፋው ድህነት ለማምለጥ በሚደረገው ጥረትም ታዳጊዎች እግር ኳስን እንደ አማራጭ ይይዙታል። የተሻለ ብቃት ያላቸው በርካታ ተጫዋቾችም ባህር አቋርጠው ከዘመነው ዓለም ክለቦች ተቀላቅለዋል።

ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ በአዲስ የውድድር ዓመት በተመለሰው ተወዳጁ የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግም በርካታ አፍሪካዊያን ተጫዋቾች ይገኛሉ። ፉታ የተሰኘ አንድ ድረገጽ እንደሚያስነብበው ከሆነም ባለፈው የፕሪምየር ሊግ ዓመት (እአአ 2018/19) ከ12 ሃገራት የተወጣጡ 42 አፍሪካዊያን በፕሪምየር ሊጉ ክለቦች ተጫውተዋል። ከአፍሪካዊያኑ ሃገራት መካከልም ሴኔጋል ስድስት፣ ናይጄሪያና ኮትዲቯር አምስት አምስት ተጫዋቾችን በመያዝ ቀዳሚውን ስፍራ ይቆናጠጣሉ።

የእንግሊዝን ጨምሮ በተለያዩ ሃገራት ሊጎች ውስጥም ምርጥ ብቃት በማሳየት ችሎታቸውን አስመስክረዋል። ባለፈው የፕሪምየር ሊግ ዓመትም አፍሪካዊያን ተጫዋቾች የተሻሉ እንደነበሩ፤ ለወርቃማ ጫማ ክብር የታጩትን ሶስት ተጫዋቾችን (ፔሪ ኤምሪክ ኡባሚያንግ፣ ሳዲዮ ማኔ እና ሞሃመድ ሳላህ) በማሳያነት ማንሳት ይቻላል። ከዚሁ በተጓዳኝ የሻምፒዮንስ ሊጉ ባለቤት የሆነው ሊቨርፑልም የሁለቱ አፍሪካዊያን ተጫዋቾቹ ጥምረት ከስኬት እንዳበቃው ይታወቃል።

ግብጻዊው ሞሃመድ ሳላህ እና ሴኔጋላዊው ሳዲዮ ማኔ አሁን ያሉበት ሁኔታም ከአስር ዓመታት በላይ የቆየውን የአንጋፋዎቹን ዲዲየር ድሮግባ እና ሳሙኤል ኤቶን ዘመን የሚያስታውስ ሆኗል። ሁለቱ አንጋፋ ተጨዋቾች የአፍሪካ መለያ ቀለም እስከ መሆን ከመድረሳቸውም ባሻገር ለአህጉሪቷ የእግር ኳስ ከዋኝ ታዳጊዎች ተምሳሌትም ሆነው ቆይተዋል።

በዚህ ወቅት ደግሞ የሊቨርፑሎቹ ተጫዋቾች ጥምረት የሚጠቀስ ይሁን እንጂ «እንደ ድሮግባ እና ኤቶ በወጥ ብቃት ዓመታትን ይዘልቁ ይሆን?» የሚለው አጠያያቂና አጠራጣሪም ነው። ምክንያቱ ደግሞ እነዚህን ተጫዋቾች በብርቱ ሊፈትኑ የሚችሉና በእነርሱ ምትክ መድመቅ የሚችሉ አፍሪካዊያን ተጫዋቾች በሊጉ መኖራቸው መሆኑን አፍሪካን ፉትቦል ዶት ኮም ያትታል በዘገባው። ድረ-ገጹ የሁለቱ ተጫዋቾች ተቀናቃኝ ይሆናሉ ያላቸውን ተጫዋቾችም እንደሚከተለው ጠቁሟል።

የተሻለ የውድድር ዓመት በማሳለፍ የሁለቱን ተጫዋቾች ክብር ይገዳደራል በሚል የተጠቀሰው የመጀመሪያው ተጫዋች የሰማያዊዎቹ ሪያድ ማህሬዝ ነው። አልጄሪያዊው ማህሬዝ የተጠናቀቀውን የውድድር ዓመት ከክለቡ ማንቺስተር ሲቲ ጋር የሊጉን ዋንጫ በማንሳት ስኬት ያስመዘገበ ሲሆን፤ በቅርቡ በተካሄደው የአፍሪካ ዋንጫም ሃገሩን ለድል ማብቃቱ የሚታወስ ነው።

ተጫዋቹ እአአ በ2015/2016 የውድድር ዓመት ሳይጠበቅ ዋንጫውን ባነሳው ሌስተር ሲቲ ያሳየው ብቃት አይዘነጋም። በወቅቱ በርካታ ክብሮችን የግሉ እንዳደረገም የሚታወቅ ነው። በዚህ ዓመት ከክለቡ እና ከብሄራዊ ቡድኑ ጋር ያነሳቸው ሁለት ዋንጫዎችም በውድድር ዓመቱ በተሻለ ብቃት እንዲገኝ የሚያግዘው እንዲሁም ወደ ቀድሞ ብቃቱ የሚመለስበት እንደሚሆን ተስፋ ተጥሎበታል።

ሌላኛው ተጫዋች ደግሞ የመድፈኞቹ ፔሪ ኤምሪክ ኡባሚያንግ ነው። ትውልደ ፈረንሳዊውና የጋቦን ብሄራዊ ቡድን አባል በቡንደስሊጋ የነበረውን ጎል አምራችነት በሊጉ ክለብ አርሰናልም እንደሚደግመው ይጠበቃል። በመጀመሪያው ዓመት የክለብ ቆይታው በሊጉ 22 ግቦችን፤ በዩሮፓ ሊግ ደግሞ ስምንት ግቦችን አስቆጥሯል።

 የፕሪምየር ሊጉ የወርቃማ ጫማ አሸናፊው የ30 ዓመቱ ተጫዋች በዚህ የውድድር ዓመትም ወደ ግብ አዝናቢነቱ እንደሚመለስ ድረገጹ ቅድመ ግምቱን አስቀምጧል።

የመድፈኞቹ ሌላኛው ተጫዋች ኒኮላስ ፔፔም በሊጉ የተሻለ ብቃት ያሳያሉ በሚል ከሚጠበቁት አፍሪካዊያን ተጫዋቾች መካከል ተገኝቷል። በውድድር ዓመቱ የፈረንሳዩን ክለብ ሊልን ለቆ አርሰናልን የተቀላቀለው ወጣቱ ተጫዋች በመጀመሪያው ዓመት የፕሪምየር ሊግ ቆይታው ጥሩ ብቃት እንደሚያሳይ ይጠበቃል።

ኮትዲቯራዊው ፔፔ የእንግሊዙን ክለብ የተቀላቀለው የክለቡ ክብረወሰን በሆነ ዋጋ ሲሆን፤ በኡባሚያንግ የተያዘውን 62 ሚሊዮን ዩሮ ወደ 72 ሚሊዮን ዩሮ አሳድጎታል። ያለፈውን የውድድር ዓመት በሊግ ዋን ምርጥ አፍሪካዊ ተጫዋች ቢሰኝም፤ በግብጹ የዓለም ዋንጫ ግን ብሄራዊ ቡድኑ እንደተጠበቀው ውጤት ማስመዝገብ አልቻልም። ይሁን እንጂ ጥሩ ተስፋ ያለው ወጣት በመሆኑ በውድድር ዓመቱ ስመ ጥር አፍሪካዊ የፕሪምየር ሊግ ተጫዋች እንደሚሆን ይጠበቃል።

የክሪስታል ፓላሶቹ ዌልፍሬድ ዛሃ እና ጆርዳን አየውም በተያዘው የሊግ ዓመት ጥሩ አቋም እንደሚያሳዩ ዕምነት የተጣለባቸው ተጫዋቾች ሆነዋል። ቀድሞ ለእንግሊዝ ይጫወት የነበረው ዛሃ ዝሆኖቹን መቀላቀሉን ተከትሎ ከስመ ጥር አፍሪካዊያን የፕሪምየር ሊግ ተጫዋቾች ተርታ ተገኝቷል። ጋናዊው አየውም በተመሳሳይ በሊጉ ጎልተው ሊጠቀሱ ከሚችሉ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ይሆናል በሚል ድረገጹ ቅድመ ግምት ሰጥቶታል።

አዲስ ዘመን ነሃሴ 6/2011

ብርሃን ፈይሳ