በፓርቲዎቹ እምነት፤ በአገሪቱ ያለው ሁኔታ ምርጫ ከማካሄድ አያግድም

106

በቅርቡ ኢህአዴግ ባካሄደው ስብሰባ ምርጫ 2012 በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት እንዲካሄድ ስለመፈለጉ በራሱ በኩል ያለውን አቋም አሳውቋል፡፡ ገዥው ፓርቲ ምርጫ እንደሚካሄድ መግለጹን በመደገፍ ለምርጫ አስፈላጊ የሆኑ ዝግጅቶችን በማድረግ የምርጫ መዋቅሩን እስከ ታች ድረስ በማወረዱ በኩል መስራት እንዳለበት ደግሞ የተለያዩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ተናግረዋል፡፡

ያነጋገርናቸው የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ/ ኦፌኮ/ ሊቀመንበር፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አብን/ ፕሬዚዳንትና የኦሮሞ ነፃነት ግንባር /ኦነግ/ ቃል አቀባይ እንደገለጹት፤ምርጫ 2012 በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት እንዲካሄድ ይፈልጋሉ፡፡ ኢህአዴግም ምርጫ 2012ን ለማካሄድ ያለውን ቁርጠኝነት ማሳየቱ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ ምርጫውን ለሌላ ጊዜ ማስተላለፉ ተገቢ አይደለም፤ ከዚህ የተሻለ ጊዜ ይመጣል ብሎ መጠበቅም አያስፈልግም፡፡

የኦፌኮ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፣ «ገዥው ፓርቲ በቁርጠኝነት ከሰራ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሂደት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አቅጣጫ ሊያስይዝ የሚችል ታሪካዊ ሥራ ልንሰራ እንችላል፡፡» ሲሉ ተናግረው፤ ተፎካካሪዎችም ቢሆኑ ሌላ ሌላውን ነገር ትተው የራሳቸውን የቤት ሥራ ለመስራት መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ያመለክታሉ፡፡ «ከኢህአዴግ መና መጠበቅ የለባቸውም፡፡» ሲሉም ነው ያስገነዘቡት፡፡

ፕሮፌሰር መረራ እስካሁንም ቢሆን ችግሮች ሲፈጥር የነበረው ኢህአዴግ እንደሆነ ጠቅሰው፣ የሰላሙም ጉዳይ ከዚያ በላይ ያሻሽላል ብሎ መጠበቅ አስቸጋሪ ነው ይላሉ፡፡ ከሕዝብ ጋር ሆኖ ለተፈጠሩ ችግሮች መፍትሄ መፈለግ እንደሚሻል ተናግረው፣ ሕዝቡ የራሱን ዕድል በራሱ ለመወሰን ከዚህ የተሻለ መንገድ እንደማይኖረው ነው ያብራሩት፡፡

«ኢህአዴግ ምርጫ እንዲካሄድ መወሰኑ መልካም ሆኖ ሳለ መንግሥታዊ ኃላፊነቱን መወጣት ግን አለበት» ሲሉ ገልጸው፣ ምርጫ ቦርድ መዋቅሩን ሲያወርድ እንደቀድሞው ከመንግሥት ጋር ንክኪ ያላቸውና የመንግሥትን አሞሌ ሲልሱ የነበሩ ሰዎችን እንዳያስቀምጥ አስገንዝበው፣ ገለልተኛ ሰዎች ሊሆኑ እንደሚገባ ያመለክታሉ፡፡

በእነሱ በኩል ዝግጅት እያደረጉ ሲሆን፣ እየሰሩ ያለውም ለመመረጥ እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡ ፡ ምርጫው ነፃ፣ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ እስከሆነ ድረስ ማንም ቢመረጥ ግድ እንደሌላቸው አመልክተው፤ ምርጫው ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሁም ነፃ የማይሆን ከሆነ ግጭት ውስጥ ሊከት እንደሚችል ስጋታቸውን ይናገራሉ፡፡

የአብን ፕሬዚዳንት ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ በበኩላቸው፤ምርጫው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት መካሄድ እንዳለበት ይጠቅሳሉ፡፡ ይህን ሲሉም ምርጫውን ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ለማካሄድ የሚያስፈለጉ ሁሉም ዝግጅቶችና መደላድሎች አሉ ብለው ስለሚያስቡ እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡ ይሁንና ከነችግሩም ቢሆን መካሄድ አለበት የሚል እምነት እንዳላቸው ይጠቁማሉ፡፡

«በእኛ በኩል የተለያዩ ዝግጅቶችን ስናካሂድ ቆይተናል፡፡ አማራጭ ፖሊሲዎችን የማዘጋጀት፣ የምርጫ ስትራቴጂ የመቅረፅና የምርጫ 2012 ማንፌስቶ የማዘጋጀት ሥራ እየሰራን ነው፡፡ »ያሉት ዶክተር ደሳለኝ፣«በፓርቲዎች በኩል ሊደረግ የሚገባው ነገር መጠናከርና ኢህአዴግን ለመገዳደር የሚያስችል ቁመና ላይ ለመገኘት በርትቶ መስራት ነው፡፡» ሲሉ ያስገነዝባሉ፡፡

ዶክተር ደሳለኝ እንደሚሉት፤ ፓርቲዎች በአመለካከት ሊቀራረቡ ከሚችሉ ፓርቲዎች ጋር በውህደትም ሆነ በአጋርነት ቅንጅቶችንና የጋራ ትብብሮችን መፍጠር ያስፈልጋቸዋል፡፡ በዚህም ኢህአዴግን ከተቻለ ከሥልጣን ማስወገድ አሊያም በመገዳደር ትርጉም ያለው የምክር ቤቶችን መቀመጫ ለማግኘት መስራት አለባቸው፡፡

«ይሁንና መንግሥትም ሲያዘናጋ ነበርና ብዙዎቹ ፓርቲዎች የተዘጋጁ እንዳልሆነ ግልፅ ነው፡፡ ምክንያቱም በባከነ ሰዓት አዲስ ሕግ መውጣቱም ጫና ለመፍጠር በመታሰቡ ነው፡፡ »ያሉት ዶክተር ደሳለኝ፣የሕዝብ ድጋፍና መሠረት ያላቸው ፓርቲዎች አሁንም ቢሆን መድረስ እንደሚችሉ ይጠቁማሉ፡፡

በምርጫ 97 ቅንጅት ስድስት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ተፈጥሮ ነው ኢህአዴግን በዝረራ ማሸነፍ የቻለው ሲሉ ገልጸው፣ ባለው የጠበበ ምህዳር ውስጥም ቢሆን ተወዳድሮ ማሸነፍ የሚቻልበት ዕድል ዝግ አለመሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡

«እኛ በጋራ ስለመስራትና ስለውህደት ስናስብ ሁለት አቅጣጫዎች አሉን፤አንደኛ ከምርጫ በፊት ተቀራራቢ መርሃግብር ካላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ለመስራት እንሞክራለን፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች አሁን ላይ እነማን እንደሆኑ መጥቀስ ባይቻልም ከኦሮሞ፣ከትግራይ እንዲሁም ከሶማሌ ፓርቲዎች ጋር ተነጋግረናል፡፡ይህም ቢሆን ንግግሩን ከምርጫ በፊት አሊያም ከምርጫ በኋላ ሊሆን ይችላል፡፡»ብለዋል፡፡

የኦነግ ቃል አቀባይ አቶ ቶሌራ አደባ፤የፓርቲያቸው ፍላጎት ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ተካሂዶ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት እንዲቋቋም መሆኑን ጠቅሰው፣በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ውስጥ ያለውን ሁኔታ ሲያስተውሉት ምርጫውን ለማካሄድ እንቅፋት አይሆንም ይላሉ፡፡ አቶ ቶሌራ ችግሮች ቢኖሩም እንኳ ከምርጫው በፊት ሊፈቱ ይችላሉ የሚል እምነት አላቸው፡፡

ለዚህ ምክንያታቸው ደግሞ ገዢው ፓርቲ ችግሮቹን መፍታት የሚያስችል አቅም እንዳለው በማመናቸው ነው፡፡ የትም ቦታ ያሉትን ችግሮች ገዥው ፓርቲ ለመፍታት ፍላጎቱና ቁርጠኝነቱ ካለው አሁን ሊፈቱ ይችላሉ፤ማሸጋገሩ እንደማይጠቅም እና መፍትሄም ሊሆን እንደማይችል ያብራራሉ፡፡

እንደ ቃል አቀባዩ ገለፃ፤ምርጫ ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ ሊያስደርጉ የሚችሉ ብዙ ምክንያቶች ቢኖሩም፣ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ይህን ሊያስደርግ የሚችል ምክንያት ግን የለም፤በእዚህም ላይ መንግሥትም ምርጫ ቦርዱም እያመኑበት ነውና መካሄድ አለበት፡፡ ስለዚህ ኃላፊነት የተሰጠው ተቋም በራሱ ይካሄድ እያለ ችግር አለ በሚል ይራዘም ማለቱ ተገቢ አይሆንም፡፡

«ለምርጫው የተቻለንን ሁሉ ለማድረግ እየሞከርን ነው፤ነፃ፣ተዓማኒና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲካሄድ በተለይ ተፎካካሪዎች እንደልባቸው እንዲንቀሳቀሱና ሐሳባቸውን ለሕዝቡ እንዲያካፍሉ የማድረጉ ሁኔታ በበለጠ ሰፋ ተደርጎ መታየት አለበት፡፡»ሲሉ ያብራራሉ፡፡

ተፎካካሪ ፓርቲዎች በአንዳንድ ሁኔታ እንደልባቸው እንዳይንቀሳቀሱ የማድረግ ሁኔታ እንደሚታይም ጠቅሰው፣ ይህ ችግር ተፈትቶ ምቹ ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚገባም ይጠቁማሉ፡፡ «ቃል የተገባለት ሕዝብ በራሱ ውሳኔ የሚፈልገውን ለመምረጥ እንዲችል ምቹ ሁኔታ ሊፈጠርለት ይገባል፡፡» ብለዋል፡፡

አቶ ቶሌራ እንደገለፁት፤ተመሳሳይ አቋም ያላቸው ተፎካካሪዎች ተዋህደው ለውድድር ቢቀርቡ ጠቀሜታ አለው፡፡ በተበታተነ ሁኔታ መፎካከሩ ውጤታማ አያደርግም፡፡ በእሳቸው ፓርቲ በኩል ተመሳሳይ አቋም ካላቸው ፓርቲዎች ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፣ አሁን የተፈጠረ ውህደት ባይኖርም በጊዜ ሂደት ለመፍጠር ታስቧል፡፡ በመሆኑም ውህደትን በተመለከተ ከሁሉም የኦሮሞ ፓርቲዎች ጋር በመነጋገር ላይ ይገኛሉ፡፡

እንደ ተፎካካሪ ፓርቲዎቹ ገለፃ፤ምርጫው በተያዘለት ጊዜ የማይካሄድ ከሆነ ሌላ ቀውስ ሊፈጠር ይችላል፡፡ አገሪቱንም ወደባሰ አለመረጋጋት ሊወስዳት ይችላልና ማካሄዱና በጉዳዩ ላይ መነጋገር ይገባል፡፡

አዲስ ዘመን ነሀሴ 7/2011

 አስቴር ኤልያስ