የፋይናንስ እጥረት የፈተነው የደን ልማት ዘርፍ

23

አርሶ አደር ሙክታር ያሲን በጅማ ዞን ጎማ ወረዳ የኮኤ ሴቻ ቀበሌ ማህበር ነዋሪ ናቸው። የደን ባለሙያዎች በሰጧቸው ምክር አማካኝነት ከአንድ ዓመት በፊት ደን ማልማት እንደጀመሩ ያስታውሳሉ። ከወንድሞቻቸው ጋር በመሆንም በዘጠኝ ሄክታር መሬት ላይ ሸውሸዌና ግራቪሊያ የተሰኙ የዛፍ ዝርያዎችን በመትከል ለገበያ ለማቅረብ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ይገልፃሉ። ከዛፍ ገበያው የተሻለ ገቢ ለማግኘት ተስፋ መሰነቃቸውንም ይናገራሉ።

በደን ባለሙያዎች የሚደረጉ መጠነኛ ድጋፎች ቢኖሩም አንዳንድ ችግሮች ግን መኖራቸው አልቀረም የሚሉት አርሶ አደሩ፣ በተለይም በቂ የችግኝ አቅርቦት ባለመኖሩ ዛፎችን በብዛት በመትከል ከደን ልማት ተጠቃሚ መሆን እንዳልተቻለ ይገልፃሉ። አነስተኛ የእርሻ መሳሪያዎች ድጋፍም ዝቅተኛ መሆኑ ዛፎችን በተሻለ ሁኔታ አምርቶ በቶሎ ለገበያ ለማቅረብ እንቅፋት እንደሆነም ይጠቁማሉ።

እንደ አርሶ አደሩ ገለፃ፤ በደን ልማት ዋነኛው ችግር የገንዘብ እጥረት በመሆኑ በመንግስት በኩል የረጅም ጊዜ ብድር መመቻቸት ይኖርበታል። ችግኞችን እንደ ልብ ማቅረብና አነስተኛ የእርሻ መሳሪያዎች ድጋፍ ማድረግም ያስፈልጋል። ለአርሶ አደሩ የደን ጥበቃ ድጋፍም ሊደረግለት ይገባል።

አርሶ አደር ቡልቻ መሃመድም በጅማ ዞን ጎማ ወረዳ ኮዬ ሴቻ ቀበሌ ማህበር በደን ልማት ዘርፍ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ ተሰማርተው ቆይተዋል። መንግስት በጥቂቱ ችግኞችን ሲያቀርብላቸው ቀስ በቀስ ደን ወደማልማቱ ስራ እንደገቡም ያስረዳሉ። በሁለት ሄክታር መሬት ላይ የግራቪሊያ፣ ፅድና ባህር ዛፍ ችግኞችን በመትከል የደን ልማቱን እንደጀመሩም ያስታውሳሉ።

በወቅቱ የደን ልማቱን ሲጀምሩ በባለሙያዎች በኩል ድጋፍ ሲደረግላቸው የቆየ ቢሆንም ከጊዜ በኋላ ግን በመንግስት በኩል የሚደረገው ድጋፍ እየተቀዛቀዘ መምጣቱን አርሶ አደሩ ያመለክታሉ።

በመሬታቸው ላይ ያለሙትን ባህርዛፍ በመሸጥ በአራት ዓመታት ውስጥ ከሃያ እስከ ሰላሳ ሺ ብር ማግኘታቸውን የሚገልፁት አርሶ አደሩ፤ ግራቪሊያ የተሰኘውና ለጣውላ አገልግሎት የሚውለው የዛፍ አይነት ለሽያጭ የደረሰላቸው ቢሆንም የዛፉ ዋጋ ወረድ በማለቱና የማሽን አቅርቦት ባለመኖሩ ምርቱን ለገበያ ለማቅረብ ስጋት እንዳደረባቸው ያስረዳሉ።

ለእርሳቸውም ሆነ በዚሁ ዘርፍ ለተሰማሩ አርሶ አደሮች የሚያዋጣው ቦታው ድረስ ማሽን በማምጣትና ዛፉን ቆርጦ በመሰነጣጠቅ ለገበያ ማቅረብ መሆኑን ጠቅሰው፣በረጅም ጊዜ ብድር ወይም በሌላ አማራጭ መንግስት የመሰንጠቂያ ማሽን ማቅረብ እንደሚኖርበት ያመለክታሉ። በተመሳሳይም የምርት መሸጫ ቦታዎች መመቻቸት እንደሚኖባቸውም ይጠቁማሉ። ገበያ ላይ የሚፈለጉና ምርጥ ዝርያ ያላቸው የችግኝ አይነቶችን በብዛት ለአርሶ አደሩ መቅረብ እንደሚኖርበትም ያሳስባሉ።

የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ምክትል ዋና ፀሃፊ አቶ ውቤ መንግስቱ እንደሚሉት፤ በኢትዮጵያ በደን ልማትና የእንጨት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ዙሪያ ያሉ ችግሮችና መልካም እድሎች በፕሮጀክት ድጋፍ የተሰሩ ናቸው። ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያ መንግስት ከዓለም ባንክ ጋር በመሆን እ.ኤ.አ በ2013 የተጀመረ ሲሆን በዚህም መሰረት በደን ልማትና እንጨት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ያሉ ችግሮችና መልካም አድሎችን ለማወቅ ጥናት ተሰርቷል።

ጥናቱ አጠቃላይ የሀገሪቱ የደንና እንጨት የማቀነባበሪያ ዘርፉ ያለበትን ደረጃና አቅርቦቱና ፍላጎቱ ምን እንደሚመስል አሳይቷል። ይህንንም መሰረት በማድረግ የግሉ ዘርፍ በዚህ ኢንዱስትሪ ተሳታፊ እንዲሆን በጥናቱ ላይ ምክክር ተደርጎበታል። ጥናቱንና የምክክር መድረኩን ለማከናወንና አስተዳደራዊ ስራዎችን ለመስራትም በዓለም ባንክ በኩል የ2 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ተደርጓል።

እንደ ምክትል ዋና ፀሃፊው ገለፃ ፤በጥናቱ ላይ የመጀመሪያው ምክክር በንግድ ሚኒስቴር እየተመራ በኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ተዘጋጅቶ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተካሂዷል። ይህም መድረክ የደን ልማቱና የእንጨት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ሥርዓቱና አገልግሎቱ በተሻለ ሁኔታ ሊሰራና ውጤታማ ሊሆን የሚችለው ወደታች ሲወርድ መሆኑን አመላክቷል። ይህንኑ መነሻ በማድረግ ምክክሩ በአራት ክልሎች ማለትም በአማራ፣ትግራይ፣ ኦሮሚያና የደቡብ ብሄር ብህረሰቦችና ህዝቦች ክልሎች ላይ እንዲካሄድ ተደርጓል።

የደን ልማቱንና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪውን በተሻለ ሁኔታ ለማሳደግና ያሉበትን ችግሮች ለመፍታት ጥናቱን መነሻ በማድረግ ውይይቶች በነዚሁ ክልልች ሲካሄዱ ቆይተዋል። በውይይቶቹ ውስጥም በርካታ ጉዳዮች ተነስተዋል። ከነዚህ ውስጥም በተለይ ፖሊሲ ነክ የሆኑና የደን ልማቱንና የእንጨት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪውን እየጎዱ ያሉ ችግሮች ይገኙበታል። የገንዘብ አቅርቦት ክፍተቶችና የመሬት አቅርቦት ችግሮችም እንዳሉ ለማወቅ ተችሏል።

ምክትል ዋና ፀሃፊው እንደሚሉት፤ በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ጥናቱን መነሻ አድርገው የተካሄዱ ውይይቶችንና የቀረቡ ሃሳቦችን በግብአትነት በመጠቀም ወደ ተግባር መቀየር ያስፈልጋል። በመንግስት በኩልም የደን ዘርፍን የመሳሰሉና የካፒታል እጥረት ያለባቸው ዘርፎችን በማበረታታት ለማሳደግ የህዝብና መንግስት አጋርነት ፕሮግራም ተዘጋጅቷል።

ጥናቱን መነሻ አድርጎ ዘርፉን ለማሻሻልና ለማሳደግ የሚደረጉ ውይይቶችን በክልሎች ነባራዊ ሁኔታ እንዲቃኙ ማድረግ ይገባል። የግሉ ዘርፍ በምን መልኩ ቢገባ የዘርፉን ችግር ሊፈታ እንደሚችልም ጥናቱ የጠቆመ በመሆኑ ይህንን በግብአትነት በመጠቀምና በጥናቱ መሰረት የሚከናወኑ ስራዎችን የሚከታተል ኮሚቴ በማዋቀር ክትትል ለማድረግ ያስችላል።

በኢትዮጵያ የአካባቢና የደን ምርምር ኢንስቲትዩት የማህበራዊ፣ፖሊሲ ሥርዓትና ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶክተር አለማየሁ ነጋሳ እንደሚሉት፤ በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ያለው የደን ሽፋንና ፍጆታ የሚመጣጠን አይደለም። በአሁኑ ወቅት ካለው የደን ሽፋን ውስጥ ውስጥ 72 ሺ ሄክታር የሚሆነው ያለአግባብ ጥቅም ላይ ይውላል። በየአመቱም 92 ሺ ሄክታር የሚሆን ደን ይጠፋል። ይህም የደን ሽፋኑና ፍጆታው ተመጣጣኝ ባለመሆኑ በቀጣይ ይህን አጣጥሞ መቀጠል እንደሚገባ ያመላክታል።

‹‹አርሶ አደሩ በደን ልማት ዙሪያ ከፍተኛ አቅም አለው›› የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ በተለይ አብዛኛው መሬት በአርሶ አደሩ እጅ ስር በመሆኑ ከደን ልማት ተጠቃሚ ሊሆን የሚችልበትን ግንዛቤ በስፋት መስጠት እንደሚያስፈልግ ይጠቁማሉ። ደን አምርተው ለገበያ በሚያቀርቡበት ጊዜ ሊያጋጥሟቸው የሚችሉ የህግ ክፍተቶችንም ማሻሻል እንደሚገባ፣ በመንግስት በኩል ገበያዎችን ማመቻቸት፣ የገበያ ትስስር መፍጠርና የማምረቻ መሳሪያዎችን ለአርሶ አደሩ በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብም እንደሚጠበቅ ያብራራሉ። የምክር፣ የግንዛቤ፣ የቁሳቁስና ሌሎችም ድጋፎች ሊያቀርብላቸው የሚችል መዋቅር መዘርጋትም ያስፈልጋል ይላሉ።

በምክትል ፕሬዚዳንት ማእረግ የኦሮሚያ የገጠር ልማት ሃላፊ ዶክተር ግርማ አመንቲ እንደሚሉት፤ የደን ልማት በመንግስት ጥረት ብቻ ሳይሆን የግሉን ዘርፍ ባካተተ መልኩ ሊሰራበት የሚገባ ዘርፍ መሆን ይኖርበታል። ከዚህ አንፃር የባለሀብቱ ተሳትፎ ውስን በመሆኑ ዘርፉ በብዙ መልኩ ወደ ኋላ ቀርቷል። ይህም የሆነው ደንን ጥቅም ላይ ለማዋል ብዙ ጊዜ የሚፈጅ በመሆኑና ባንኮችም ለአልሚዎች ብድር በአብዛኛው የመስጠት ልምድ ስለሌላቸው ነው። በረጅም ጊዜ ወለድ ባለሀብቶችን የሚደግፉ የፋይናንስ ተቋማት አለመኖርም የዘርፉ አንዱና ዋነኛ ማነቆ ሆኖ ቆይቷል።

እንደ ሃላፊው ገለፃ ፤የፋይናንስ አቅርቦቱን ችግር በዋናነት ለመፍታት የግሉ ባለሀብት በተናጥል ሳይሆን በጋራ ተደራጅቶ በደን ልማት ዘርፍ ተሳታፊ ሊሆን ይገባል። በተለይም በንግድና የዘርፍ ማህበራት ውስጥ የብረታብረት፣ የምግብ የመጠጥ፣ የደንና ሌሎችም የዘርፍ ማህበራት በፋይናንስ ረገድ እያጋጠማቸው ያሉ ችግሮችን ተሰባስበው የሚያቀርቡት መድረክም መመቻቸት ይኖርበታል።

በሌላ በኩል ደግሞ የደን ምርቶችን ሰብስቦና አቀነባብሮ ለፋብሪካዎች የሚያቀርብ አካል የሌለ በመሆኑና በአርሶ አደሩ ደጆች ላይ የሚገኙ ደኖችን የእንጨት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ላለው ባለሀብት ሰብስቦ በተናጠል ማቅረብ አዋጭ ባለመሆኑ ወጣቶችን በማደራጀትና ከታች ጀምሮ ምርቶችን በጋራ በማሰባሰብ ለኢንዱስተሪዎች ማቅረብ ያስፈልጋል። ይህም የዘርፉን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ከፍ ከማድረግም ባሻገር ሰዎች ደን የማልማት ዝንባሌያቸው እንዲያድግና ከዘርፉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይረዳል።

ሃላፊው እንደሚሉት ፤ለንግድ የሚሆኑ ደኖችም መልማት ስለሚኖርባቸው በመንግስት በኩል ምቹ መሬት፣ መሰረተ ልማትና ሌሎችንም አገልግሎቶችን ማሟላት ይገባል። ለኢንዱስትሪ ግብአት የሚውሉ ደኖችን ለማምረትም መሬት በአነስተኛ ሊዝ ለባለሀብቶች ሊሰጥ ይገባል።

የደን አስተዳደር እቅድ በማዘጋጀት ደኖች በዘላቂታዊነት ጥቅም ላይ እንዲውሉና ህብረተሰቡም ተጠቃሚ እንዲሆን በማድረግ ብሎም ለባለሀብቶች ማበረታቻ በመስጠት እንዲያለሙ ቢደረግ ከዘርፉ በተሻለ ተጠቃሚ መሆን ይቻላል። በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ የደን ውጤቶችንም ማስቀረት ያስችላል።

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ የኢትዮጵያ የደን ሽፋን በፊት ከነበረበት 40 በመቶ ወደ አራት በመቶ ዝቅ ያለ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፣ የደን ዘርፉ ለኢኮኖሚው እያበረከተ ያለው አስተዋፅኦም እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።

ይሁንና በአሁኑ ወቅት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አነሳሽነት የተጀመረው የደን ልማት ፕሮግራም የሀገሪቱን የደን ሽፋን በማሳደግ የአየር ንብረት ለውጡን ከማስተካከል በዘለለ ከዘርፉ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንደሚያጎላውም ታምኖበታል።

አዲስ ዘመን ነሀሴ 7/2011

አስናቀ ፀጋዬ